Pages

ይኼ ሕዝብ ማለት

በወሰንሰገድ ገ/ኪዳን (ጋዜጠኛ)(September 3/2012)

 ይኼ ሕዝብ ማለት
…. ወንዝ ነው ይፈሳል
ቦይ ከቀደዱለት መውረዱን ይወርዳል- መቅናቱን ይቀናል፤
ይኼ ሕዝብ ማለት…. የሰው ጥርቃሞ
ላቆመው የሚቆም ባዘመመው ዘ’ሞ
ልውጥ ነው መልከኛ ለአምናና ለከርሞ፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
ልክ እንደወንዝ ውሃ ድንጋይ ‘ሚያላጋ - ድንጋይ ‘ሚያናግር
በድልቂያ ጭብጨባ ልብን የሚያሳውር- መንፈስ የሚሰብር
ተዓምረኛ ነው- በአንድ ወግ ‘ማይረጋ
ባሻው አሸብሻቢ አመድ ሲሉት ሥጋ- ባልጋ ሲሄድ መንጋ፤
በግ ሲሉት እረኛ
ከሳሽ ሲሉት ዳኛ
ሁሉንም የሚሆን እንደሁሉ አዳሪ
መጣ ሲሉት ነጓጅ ሄደ ሲሉት ቀሪ፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
እንደሁሉ አዳሪ
እንደሁሉ ኗሪ
ሁሉን ቻይ ፍጥረት ነው፣ ሁሉን ቻይ ኤልሻዳይ
የሚያይ መስሎ ‘ማያይ- ያላዩትን የሚያይ፡፡  
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
ለክስ ‘ማይመች ለፍርድ ‘ማይቀና ፍጥረቱ ልዩ ነው
እዚህ ሲሉት እዚያ የሚገኝ መንትያ
ልክ እንደሸማኔ ጥበብ መወርወሪያ
ውስጠቱ ነው ልቡ- የእምነቱ ማደሪያ፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
ልክ እንደወንዝ ውሃ ወራጅ ነው አቆልቋይ
ከላይ አለ ሲሉት ከታች ወርዶ ‘ሚታይ
ወርዷል ሲሉት ከታች የሚነግሥ ወደላይ፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
የምን ወንዝ ብቻ ባህርም ይሆናል
ሲያሻው ውቅያኖስ ማ‘በሉም ይንጣል፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
ሳይታሰብ ሰግሮ ሳይታለም ደርሶ
አለ ሲሉት የለም ይሄዳል መልሶ፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
ሲወርድ ያዋርዳል- ከፍ ሲል ያስቀናል
እንደደራሽ ውሃ አሳስቆ መውሰድ- ማስመጥ ያውቅበታል፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
ልክ እንደ ነቢይ ነው
በጊዜውም ቢሆን ባሻው ያለ ጊዜው፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
አንዳንዴ ግጥም ነው- አንዳንደ ቅኔ
አንዳንዴ ንስር ነው - አንዳንደ ዋ‘ኔ፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት መመዘኛም የለው
መለኪያው ጊዜ ነው እርቦና መስፈሪያው
ሞላ ሲሉት ሥፍሩ የልኩ ጢምታ
የለም አይገኝም በሚዛን ገበታ፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
በበረደው በርዶ በሞቀበት ሞቆ
ሲመርም ጉፍንን ነው ልክ እንደመቅመቆ፤
ይኼ ሕዝብ ማለት ፍቺ የለው አቻ
እንዲሉ ነገር ነው ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
ጡር ፈሪ ጦረኛ
ሲለው ሞገደኛ
ሳያሻው ምርኮኛ
የጊዜ ሥሪት ነው
ሲያደባም በጊዜ- ሲያሰላም በጊዜ- ሲሄድ ጊዜ አይቶ ነው፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
አንዳንዴ ሥምም ነው- አንዳንዴ መለያ
ሲያጠፋም ሲጠፋም የሌለው አምሳያ፡፡
በእርግጥ ሕዝብ ማለት ዝም ብሎ አይናቅም
በዝምታው ዘምቶ ሲያነሳም ሲጥልም
‘ሚያድን ‘ሚገልም፣ ቅንም ነው ቅን-ቅንም
የልቡ አይገኝም፡፡
ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
ይኼ ሕዝብ ማለት…. ብታውቅ እወቅበት
ባታውቅ እወቅለት
አንዳንዴ ረሀብ ነው - አንዳንደ ቁንጣን
አንዳንዴ መልዓክ ነው - አንዳንደ ሰይጣን
እውነት እውነት እውነት ይኼ ሕዝብ ማለት…. 
አንዳንዴ ውሸት ነው - አንዳንዴ እውነት፡፡

                                                                     

No comments:

Post a Comment