Pages

ንገሪኝ ኦሮሚያ አቦ ምንድነዉ ጉድሽ ?!

ከበሪሶ ገዳ ቀን 11/01/2012

ንገሪኝ ኦሮሚያ አቦ ምንድነዉ ጉድሽ
ከቶ ምን ገጠመሽ አወይ ይሄ እድልሽ
የተዘረጋብሽ የተንኮል አስተዳደር
በጠርናፊ ተጠርናፊ የስለላ ቀመር
የሴረኞች መዐት የክፋት መዋቅር
የመሰሪዎች እቅድ የጥፋት መረሀግብር
ባልባሌ ፈሊጥ አጓጉል ተረት
ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል
እንብላ እንጠቀም ይሄ ጊዜ ያልፋል

እየተጠራሩ እያሰሙ ፉጨት
ይሄዉ ወና አስቀሩሽ ዘርፈዉ ያንችን ንብረት
ለሆዱ ያደረ ሰርቆ የከበረ
ዘራፊ አስዘራፊ አስመስሎ የኖረ
የበላበትን ድስት እወጪት ሰባሪ
አቁማዳ ጎርጓሪ ጎተራ ሰርሳሪ
የእናት ጡት ነካሽ ያባት ቤት ቆፋሪ
ሌባዉ ተወድሶ ሲባል ያራዳ ልጅ
ቀልጣፋና ፈጣን ለወገን የሚበጅ
ለእዉነት የሚቆም ፍትህ የሚናገር
ለህዝብ የሚያስብ ከልብ የሚቆረቆር
ተብሎ ይሰደባል ነገር የማይገባዉ ኋላቀር ገለጀጅ
ለእስር ይዳረጋል ይገደላል በአዋጅ
ከሀገር ይባረራል ይሰደዳል በግዳጅ


ልጆችሽ ተገርፈዉ በረሀብ አለንጋ
በእርዛት በሽታ ተዛምደዉ ከአልጋ
ሁሉ ዞሮባቸዉ ገብተዉ በቀለበት
ይሽከረከራሉ በድንቁሪና አዙሪት

አረ አንቺ ንገሪኝ እናት ኦሮሚያ
እንዴት ልትሆኝ ቻልሽ የግፈኞች መናሃሪያ
አይ አንቺ ሀገሬ ሁሉ እያለሽ ያጣሽ የሀብታሞች ደሀ
ተፈጥሮ ያደለሽ ሆንሽ ለምለም በረሀ
ታሪክ እያለሽ ሆነሽ ታሪክ አልባ
ሙሰኞች እርኩሳን ተሸክመሽ በአንቀልባ
እስክ መቼ ትኖሪ ሀቅ እየተዛባ
እኔስ እስከ መቼ ልኑር ሆዴ እንደ ባባ?!!


ንገሪኝ ኦሮሚያ አቦ ምንድነዉ ጉድሽ
ከቶ ምን ገጠመሽ አወይ ይሄ እድልሽ?!


በሪሶ ገዳ  E-mail: ear_tuf12@hotmail.com
Gadaa.com 

No comments:

Post a Comment