Pages

ኃላፊነቱን የማይወጣ ባለሥልጣን እንዲወገድ ፓርላማው ግፊት አደርጋለሁ አለ

Sunday, 11 November 2012 By Wudineh Zenebe

-    መንግሥት ተግባራዊ ዕርምጃ እንዲወስድ እየተጠየቀ ነው


የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሚመለከት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በቅርቡ በተካሄደው ስብሰባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ችግሮቹን እንዲያርም ተነግሮት ማስተካከል ያልቻለ ኃላፊ ከሥልጣኑ እንዲነሳ ፓርላማው ግፊት እንደሚያደርግ አስታወቁ፡፡

“አስተካክል ተብሎ ማስተካከል ያልቻለ ኃላፊ በመጀመርያ የሥራው ስህተት ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል፤ቀጥሎም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ከሥልጣኑ እንዲነሳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግፊት ያደርጋል፤” ብለዋል አፈ ጉባዔው፡፡ አክለውም “ከዚህ በኋላ ይህንን አሠራር ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ እናደርጋለን፤” ሲሉ አቶ አባዱላ አስታውቀዋል፡፡

“የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናና የአስፈጻሚ ተቋማት ኃላፊነት” በሚል ርዕስ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን፣ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፎዚያ አሚን፣ ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታውና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 16ቱም ቋሚ ኮሚቴዎች ተገኝተዋል፡፡

ስብሰባው ከወትሮው በተለየ ግልጽነት የታየበት ሲሆን፣ ሥራቸውን በአግባብ መሥራት ያልቻሉ መሥርያ ቤቶችም ያሉባቸውን ችግሮች ገልጸዋል፡፡

ባልተለመደ ሁኔታ ስብሰባው ጠንከር ያለና ግልጽ መሆኑ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል እያነጋገረ ይገኛል፡፡ “በግልጽ እንደተናገሩት ሁሉ በተግባር ቢያሳዩን መልካም ነበር፤” ሲሉ ስብሰባውን በቴሌቪዥን መስኮት የተከታተሉ ለሪፖርተር ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ስብሰባ ላይ በተጠቀሱት ተቋማት መካከል የፀረ ሙስና ኮሚሽን አንዱ ነው፡፡ የሕወሓት ነባር ታጋይና በአሁኑ ወቅት በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይ ፀሐዬ እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት በሙስና ግንድ ላይ ሳይሆን በቅርንጫፎች ላይ ነው ብለዋል፡፡

“እየታዩ ያሉት መለስተኛና መካከለኛ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ትላልቁ ጉዳይ በጣም ውስን ነው፡፡ አጥርቶ ለማምጣት ትላልቅ ጉዳዮችን ማናወጥና ከሥር መናድ ያስፈልጋል፤” በማለት ኮሚሽኑ በትላልቅ ጉዳዮች ላይ እንዲሠራ አስገንዝበዋል፡፡ የኮሚሽኑ ወይም የዲሞክራሲ ተቋማት የመጋፈጥ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚገባና የሚያደናቅፋቸውን አካልም መቅጣት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት ፀረ ሙስና ኮሚሽን ትናንሽ ጉዳዮች ላይ መጠመድ እንጂ ትላልቅ ጉዳዮችን እንደማይደፍር ሲነገር ቆይቷል፡፡

ኮሚሽኑ ባገኘው አጋጣሚ ይህንን አባባል ቢያስተባብልም፣ ከወራት በፊት የኢትዮጵያ የሰላምና የዴሞክራሲ ልማት ተቋም ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ነባሩ የሕወሓት አቶ ስብሃት ነጋ (አቦይ) አሁን ደግሞ አቶ ዓባይ የኮሚሽኑን ደካማ እንቅስቃሴ ይፋ አውጥተዋል፡፡

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ በበኩላቸው፣ መሥርያ ቤታቸው ያለበትን ችግር በስብሰባው ተናግረዋል፡፡ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን የሚያጋልጡ ሰዎችን ከአደጋ መከላከል የመሥርያ ቤታቸው ድርሻ መሆኑን አቶ ዓሊ ገልጸው፣ ነገር ግን ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን የሚያጋልጡ ሰዎች የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ሰዎች ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በማጋለጣቸው መኩራት ሲገባቸው እየተሸማቀቁ ነው ያሉት አቶ ዓሊ፣ ኮሚሽኑ ከለላ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ሲመጡ ኮሚሽኑ ከለላ ለመስጠት ሙከራ በሚያደርግበት ወቅት በተወሳሰበ የአስተዳደር ችግር ውጤታማ ያለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

“በማጋለጣቸው የሚፀፀቱ ሰዎች አሉ” በማለት አቶ ዓሊ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከለላ በመስጠት በኩል ያለበትን ችግር ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ዓሊ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፎዚያም መሥርያ ቤታቸው ያለበትን ችግር አንፀባርቀዋል፡፡ወደ ተቋሙ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች መልስ የሚሰጠው በድሏል የተባለው አስፈጻሚ መሥርያ ቤት ተጠይቆ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ዕንባ ጠባቂ ምላሽ እንዲሰጠው ለአስፈጻሚ መሥርያ ቤቶች ሲልክ በቅን ልቦና አለማየትና ከዚህም ብሶ ዛቻና ማስፈራርያ እንደሚደርሳቸው ወይዘሮዋ ገልጸዋል፡፡

“ከዚህ አንፃር በተለይ አዲስ አበባ ቁጥር አንድ ቅሬታ የሚቀርብባት ከተማ ናት፡፡ ለምንጠይቀው ጥያቄ መልስ መስጠት አንድ ነገር ሲሆን፣ ዜጎችን በአግባቡ ማስተናገድ ብሎም ለመልካም አስተዳደር መታገል ሌላ ነገር ሆኖ እያለ፣ ዕንባ ጠባቂ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አገባው? ዕንባ ጠባቂ ሲያስፈጽምላችሁ እናያለን፤” የሚል ምላሽ ይሰጣል ሲሉ ወይዘሮ ፎዚያ ተናግረዋል፡፡ ወደ ክፍለ ከተማና ወረዳ ሲወረድ ደግሞ ከዚህ እንደሚብስም አስረድተዋል፡፡

የወይዘሮ ፎዚያን ቅሬታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስመላሽ ደግፈው ይናገራሉ፡፡ አቶ አስመላሽ እንዳሉት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12 ማንኛውም ተሿሚ ወይም የሕዝብ ተመራጭ ግልጽነትና ተጠያቂነት አለበት፡፡ ነገር ግን እያጋጠመ ያለው ለምሳሌ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር በደል የደረሰበትን ሰው ቅሬታ ይዞ ወደ አስፈጻሚ ሲሄድ፣ ከዚህ ዞር በል እየተባለ ነው ሲሉ አቶ አስመላሽ የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በአስተዳደሩ መሥርያ ቤቶች ቅሬታዎች የሚነሱ መሆኑ ባይካድም፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ሁሉንም ቅሬታ እያግበሰበሰ እንደሚልክ አስታውቀዋል፡፡

“ዝም ብሎ ቅሬታ የመሰብሰብ ነገር አለ፤ ለግለሰቦችም ያደላል፤” ያሉት አቶ አባተ፣በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል፡፡

አቶ አባዱላ ግን የአቶ አባተን ቅሬታ ወዲያውኑ ውድቅ አድርገውታል፡፡ አቶ አባዱላ እንዳሉት፣ ቅሬታ ማቅረብ የዜግነት መብት ነው፡፡ ቅሬታ ተቀብሎ መርምሮ የሚሆነው ይሆናል፡፡ የማይሆነው አይሆንም ማለት የአስፈጻሚው አካል ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወቅታዊ አቅምና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በግልጽ ውይይት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የያዙት አቋም መነጋገርያነቱ ቀጥሏል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስብሰባውን የተከታተሉ አስተያየት ሰጪዎች መንግሥት በሙሰኞችና መልካም አስተዳደር እንዳይኖር በሚያደርጉ ኃይሎች ላይ መነጋገሩ መልካም መሆኑን ጠቁመው፣ ተገቢውን ዕርምጃ ካልወሰደ ግን ያስተዛዝባል እያሉ ነው፡፡ በተግባር ያልተደገፈ ውይይት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይብሳል በማለት አስረድተዋል፡፡
Ethiopian reporter amharic newspaper

No comments:

Post a Comment