Pages

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በቱኒሲያ

Deutsche Welle | 14 November 2012

የሊቢያው ጦርነት ከመካሄዱ በፊትና በጦርነቱ ወቅት ፤ ከዚያም በኋላ ፣ ወደ ሌሎች ሀገራት ፤ በተለይም ወደ አውሮፓ ለመግባት የሜድትራንያንን ባህር በጀልባዎች ለማቋረጥ ሲሞክሩ ፤ ዘግናኝ ሁኔታ እያጋጠማቸው በመስመጥ ህይወታቸውን ስላጡ ኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች ኤርትራውያንና ሌሎችም የአፍሪቃ ሃገራት ዜጎች ባለፉት 2 ዓመታት ገደማ በተደጋጋሚ ዘገባዎችን አዳምጠናል። የከፊሉ ስደተኞቹ እንጂ የብዙዎቹ ችግር እስከዛሬ እልባት እንዳላገኘ ይሰማል። ከሊቢያው ጦርነት ሸሽተው ቱኒሲያ የገቡ ኢትዮጵያውያን እስካሁን በዚያው ድንበር አካባቢ የሚገኙ ሲሆን፤ ትናንት አደባባይ በመውጣት ለ UNHCR ስለወደፊቱ ዕጣቸው አቤት ብለው ነበር። ተክሌ የኋላ ስልክ በመደወል ስደተኞቹን አነጋግሮ ነበር።


ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት AI ሊቢያ ውስጥ፤ በጥቁር አፍሪቃውያን ላይ የሚካሄደው ቁም ስቅል ማሳያ የግፍ እርምጃና አፈሳ ተባብሶ መቀጠሉን አጋልጧል። ካለፈው ዓመት ግንቦት እስካለፈው መስከረም፤ በሊቢያ 9 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን የጎበኙት የ AI ሰዎች፤ 2,700 ያህል የውጭ ተወላጆች፤ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ነው የገባችሁ ተብለው በእሥር በመማቀቅ ላይ መሆናቸውን ተገንዝበዋል። ከፊሉ የሊቢያ ህዝብ ፣ የሌሎች አገሮች ተወላጆች የሆኑ ጥቁር አፍሪቃውያንን የጋዳፊ ቅጥረኛ ወታደሮች ነበራችሁ እያሉ እንደሚያጥላሏቸው ነው AI ያስታወቀው።




ስለሚያጋጥም ስንትና ስንት አሰቃቂ ፈተና ፤ መከራ እየሰሙም ቢሆን፤ ወደ ደቡብ ፣ ሰሜንና ምሥራቅ የሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን መጠን ሊገታ አልቻለም። የስደታቸው ምክንያት ዘርፈ ብዙ ነው። ሊቢያ ከገቡ በኋላ በጦርነቱ ሳቢያ ሊቢያና ቱኒሲያ ድንበር አካባቢ ፣ ቱኒሲያ ግዛት ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ይገኛሉ።  ችግሩን መገናኛ ብዙኀን አውቀው ለሚመለከታቸው ጭምር በማሳሰብ መፍትኄ እንዲያፈላልጉላቸዉ ይፈልጋሉ።

በዚያው በቲኒሲያ የሚገኙትን፤ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቅርንጫፍ መ/ቤት ባለሥልጣናት አግኝተን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ አልተሣካልንም።

ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሰደዱ የሚያጋጥማቸው አሰቃቂ አደጋ ብቻ ሳይሆን ፣ የመሰደዳቸው ምክንያትና ፤ መፍትኄው፣ በሀገር ውስጥም በውጭም ያለውን ኢትዮጵያዊውን ማኅበረሰብ በጥሞና ሊያነጋግር የሚገባ ጉዳይ ነው።
Deutsche Welle
 

No comments:

Post a Comment