Pages

‹‹ለተቃዋሚዎች ውድቀት የሚታዩና የማይታዩ የኢሕአዴግ እጆች አሉበት›› ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የመድረክ አመራር አባል

Sunday, 18 November 2012 | By Yemane Nagish

ዶ/ር መረራ ጉዲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና የመድረክ አመራር አባል ናቸው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈትን ተከትሎ በመንግሥት ሚዲያ በስፋት እየተነገረ ስላለው የሥልጣን ሽግግር፣ በአገሪቱ ስላለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታና ተቃዋሚዎች በተለይ ደግሞ መድረክ አማራጭ ፖሊሲ ይዞ ስለመቅረቡ ይናገራሉ፡፡ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮችን አስመልክቶ የማነ ናግሽ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በተቃዋሚዎች የውስጥ ጉዳይ እንጀምርና አንዳንድ ቅርበት ያላቸው ታዛቢዎች የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች አገርን ለመምራት የሚያስችል የአመራር አቅም፣ ግልጽ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፕሮግራም የላቸውም ይላሉ፡፡ ከመድረክ አንፃር ምን ይላሉ?

ዶክተር መረራ
፡- የተሳሳተ ነው፡፡ ስለፕሮግራም ካወራን ችግር የለብንም፡፡ የሚዲያ ሽፋን በማጣታችን ነው እንጂ መድረክ ግልጽ የሆነ ፕሮግራም አስቀምጧል፡፡ ሌላ ቀርቶ መድረክ ውስጥ ያሉት እያንዳንዳቸው አባል ፓርቲዎች ግልጽ የፖለቲካ ፕሮግራም አላቸው፡፡ የእኛን [ኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ] ብትወስድ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት ከሆነው ኦሕዴድ በጣም የተሻለ ፕሮግራም ነው ያለው፡፡ የመምረጥና የመወሰን ጉዳይ ግን የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. አይተነዋል፡፡ ሕዝቡ እኛን መርጧል፡፡ በእርግጥ በበቂ ሁኔታ ፕሮግራማችን እየበተንን አይደለንም፤ በብዛት አልተተዋወቅንም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ገንዘብ ስለሌለን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን መድረክ 65 ገጽ ያለው የነጠረና ዝርዝር የፖለቲካ ፕሮግራም ቀርጿል፡፡ በውስጡ ሰብዓዊ መብቶችን፣ የሚዲያ አጠቃቀምን፣ የገጠርና ግብርና ልማትን፣ የኢንዱስትሪን፣ ብሔራዊ ደኅንነትንና ሌሎች ትላልቅ የሚባሉ አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከሞላ ጎደል አካቶ ይዟል፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮግራማችሁን ሕዝብ ያውቀዋል ብለው ያምናሉ? ሕዝብ መድረክን ከስሙ አልፎ ምን ዓይነት ፕሮግራም እንዳለው የሚያውቅ ይመስልዎታል?

ዶክተር መረራ
፡- ሁሉም ሰው የእኛን ፕሮግራም እንዲያውቀው አንጠብቅም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው ስለአገሪቱ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ያለው ግንዛቤ የተለያየ ስለሆነ፡፡ እያንዳንዱ ሰው ግን የራሴ ቢሆን የሚለው ፍላጎት ይኖረዋል፡፡ ቢያንስ ደግሞ የኢሕአዴግ ፖሊሲ በየቀኑ ምን እያስከተለበት እንደሆነ ያውቃል፡፡ አማራጭ ፖሊሲ ይዘን መጥተናል፤ እሱን መገንዘብ ሁለተኛ ደረጃ ይሆናል፡፡ ቢፈቀድልን ከኢሕአዴግም በላይ አባላት ልንመለምል እንችላለን፡፡ ኢሕአዴግም ይህን ያውቃል፡፡ ለዚህም ነው መንገዱን የሚዘጋብን፡፡ ለዚህም ነው በየቀኑ የመድረክን ስም እያነሳ የሕዝብ ቁጥር አንድ ጠላት አድርጎ የሚያቀርበን፡፡ አሁን ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማካሄድ ክልክል ነው፡፡ ሠልፍ መጥራት በጥብቅ የተከለከለና ሕገወጥ ነው፡፡ የአባሎቻችን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ የተገደበ ነው፡፡ በርካታ ወጣት አባሎቻችን ደግሞ በሽብርተኝነት ሰበብ በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ፡፡ፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ሆን ተብሎ የተቃዋሚዎችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመገደብ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለመሆኑ መድረክ ወቅታዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጉዳዮችን የሚያጠና ራሱን የቻለ ክፍል አለው?

ዶክተር መረራ
፡- አዎ! በተለያዩ ደረጃዎች ምሁራንን ጨምሮ የቢዝነስ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች አሉን፡፡ ሌላ ቀርቶ እጅግ የላቀ ዕውቀት ያላቸው የግብርና ባለሙያዎች አሉን፤ የሚያማክሩን፡፡ ኢሕአዴግ ይህንን ያውቃል፤ ከኢሕአዴግ የተሻሉ እንጂ ያነሱ ባለሙያዎች የሉንም፡፡

ሪፖርተር፡- የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ሕልፈት ተከትሎ የተደረገ ሽግግር አለ፡፡ ስለአዲሱ አመራር ምን ይላሉ?

ዶ/ር መረራ
፡- ለእኔ ሽግግር የሚባለው ነገር አልተደረገም፤ ተደርጎም ከሆነ ከኢሕአዴግ ወደ ኢሕአዴግ ነው፡፡ እየተባለ ያለው ለእኔ ስሜት አይሰጠኝም፡፡ አስቂኙ ነገር እዚህ አገር የተደረገውን በሙሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እየሰጡ ነው፡፡ ነገሮች ከእውነት ርቀው እየተወሰዱ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሱዳን ብሔራዊ ቡድንን ያሸነፈው በጠቅላይ ሚኒስትር ሌጋሲ ነው ብሎ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡ እኔ ሌጋሲ የሆነውና ያልሆነውን እንኳን መለየት አቅቷቸዋል ልበል? የኢትዮጵያ መንግሥት ዴሞክራት ሳይሆን አምባገነናዊ ባህሪ የሚያጠቃው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አባባል የአምባገነኖች ባህል መሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የምርጫ ሥነ ምግባሩን ሰነድ ባለመፈረማችሁ ከኢሕአዴግ ከፍተኛ ወቀሳ ሲያቀርብባችሁ ቆይቷል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ግን ከመድረክም ጋር መነጋገር እንደሚቻል ተናግረው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቃዋሚዎቸ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ከበፊቱ የተለየ ይሆናል ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር መረራ
፡- ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት እኮ እንዲህ ነበር የሚሉት፡፡ መድረክ ለመነጋገር አልፈልግም ያለበት አንድም ቀን የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ እንነጋገር በማለት በተለያዩ ጊዜያቶች ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ የምርጫ ሥነ ምግባሩን ሰነድ ካልፈረማችሁ ይላሉ፡፡ በነገራችን ላይ ይኼ ሰነድ ሙሉ ለሙሉ ከአይዲያ ኢንተርናሽናል የተኮረጀ ነው፡፡ ድርጅቱ ሦስቱ መሠረታዊ ሰነዶች ነበር ያዘጋጀው፡፡ የመጀመሪያው ስለምርጫ አስተዳደር ነው የሚደነግገው፡፡ ሁለተኛው ስለምርጫ ታዛቢዎች የሚያስረዳ ነው፡፡ ሦስተኛው የምርጫ ክንውንን የሚመለከት ነው፡፡ ሁለቱ ዋነኛ ሰነዶች እጅግ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ግን እነዚህን ሰነዶች ቆርጦ በመጣል ሦስተኛውን ብቻ ነጥሎ እንፈራረም ይላል፡፡ በሁለቱ ቀዳሚ ዋና ሰነዶች ላይ ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች መስማማት ከቻሉ፣ መድረክ በሦስተኛው ሰነድ ላይ የማይፈርምበት አንዳች ምክንያት አይኖረውም፡፡

ኢሕአዴግ ግን በሥነ ምግባር ሰነዱ ላይ ብቻ ያተኮረበት ምክንያት አለው፡፡ መድረክ ደግሞ የተሟላ ሰነድ አይደለም በሚል ለመፈረም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡  ኢሕአዴግ ልጓሙን የበቅሎ ግንባር ላይ አድርጎ ነው እየተጫነው ያለው፡፡ ያም ሆኖ ግን ያለውን ጠባብ የፖለቲካ ከፍተት ተጠቅመንም ቢሆን ሕዝቡን ማስተባበር እንቀጥላለን፡፡ በየጊዜው በእያንዳንዳቸው አገራዊ ጉዳዮችና ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ አቋማችን ለሕዝብ በግልጽ እናሳውቃለን፡፡ ለአገሪቱ ሁለተናዊ ለውጥና ብልፅግና ስንልም በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር የኢሕአዴግን በር ማንኳኳታችንን አናቆምም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርነትዎና እንደ ፖለቲከኛነትዎ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዴት ያዩዋቸዋል?

ዶክተር መረራ
፡- ዋናው ትልቁ ችግር የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ የማያፈናፍን መሆኑ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች የሚያንቀሳቅስ የፖለቲካ አካባቢ አግኝተው አባላትንና ደጋፊዎችን በነፃነት ማፍራት እስካልቻሉ ድረስ ደካማ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ አሁን እያደረግን ያለነው ወይም ማድረግ የምንችለው ባለው አስቸጋሪ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ህልውናችንን ማረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ እያደረገ ያለው ይኼንን የፖለቲካ ምኅዳር አጥብቦ ማቆየት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአጋጣሚ የሆነ አይደለም፡፡ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም (አብዮታዊ ዲሞክራሲ) ራሱ ከዚህ በላይ ሊያስኬደው አይችልም፡፡ በአገሪቱ ለምታየቸው የፖለቲካ ችግሮች በሙሉ ወላጁ እሱ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በነጭ ወረቀት ያስቀመጠው በአገሪቱ የሚያሠራ ነፃ የፖለቲካ ምኅዳር እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ማለት ነው? በዝርዝር ሊያስረዱን ይችላሉ?

ዶክተር መረራ
፡- በመጀመርያ በገዢው ፓርቲና በመንግሥት መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡ ሁለቱንም በሚመሩ ግለሰቦች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡ በድርጅት ደረጃ የሚያስቡትን ነው በመንግሥት ደረጃ የሚያስፈጽሙት፡፡ እንደ ገዢ ፓርቲነቱ ለምን ፕሮግራሙን በመንግሥት ደረጃ ያስፈጽማል አይደለም ጥያቄው፡፡ ግልጽ የሆነ ልዩነት ግን መኖር አለበት፡፡ ሌላው ኢሕአዴግ በየትኛውም የመንግሥት አካል፣ በሕግ አውጪው፣ በፍትሕ ሥርዓቱም ሆነ በአስፈጻሚው አካል በፈለገው ጊዜ ጣልቃ ይገባል፡፡ በሦስቱ የመንግሥት አካላት መካከልም ምንም ዓይነት የሥልጣን መመጣጠን (Balance of Power) ሆነ ነፃነት የለም፡፡

የፓርላማውን 99.6 በመቶ መቀመጫ ገዥው ፓርቲ ነው የተቆጣጠረው፡፡ በዚህ ሁኔታ አሁን ያለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ሳይሆን የሶቪየት ዘመን ውስጥ ያለን ነው የሚመስለው፡፡ ትልቁ ችግር የአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት ነፃነት የለውም፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ጥቅምት ወር ውስጥ በሽብርተኝነት የተጠረጠሩ አባሎቻችን ተከሰው ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡ እኔም የፍርድ ቤቱን አሠራር ለማየት ተገኝቼ ነበር፡፡ የፍርድ ቤቱ አካሄድ የተሳሳተ ነው ብቻ ሳይሆን፣ ነፃነት የሚባል የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደዚህ ድምዳሜ እንዲደርሱ ያስገደደዎት ትዝብት ምንድን ነው?

ዶክተር መረራ
፡- ለምሳሌ በዓቃቤ ሕግ ስለቀረበው አንድ ምስክር ልንገርህ፡፡ መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ በአምቦ አባላችን ሆኖ ሠርቷል፡፡ አሁን ግን ስሙ ተቀይሮ ከወለጋ እንደመጣ ተደርጎ አድራሻው ተቀይሮ ምስክር ሆኖ ቀርቧል፡፡ ይኼ የፍትሕ ሥርዓቱ ምን ያህል እንደዘቀጠ የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ተቃዋሚዎች በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው ነው እየሠሩ ያሉት፡፡ ይኼ የሚደረገው በተለይ ወጣቱ ምሁር በምንም መንገድ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ተሳትፎ እንዳይኖረው ነው፡፡ በዚሁ አስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ነው እየኖርን ያለነው፡፡ ምክንያቱም ኢሕአዴግ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዲፈጠር አይፈልግም፡፡ ደካሞች ሆነው እንዲኖሩ እንጂ ጨርሰው እንዲጠፉ ደግሞ አይፈልግም፡፡ ለዕርዳታ ሰጪዎች ማሳያ እንዲሆኑ ይፈልጋል፡፡

አንዳንዴም ራሱ ተቃዋሚዎችን ይፈጥራል፡፡ በአገሪቱ እንደ አሸን የፈሉ ተቃዋሚዎች አሉ፡፡ አብዛኞቹ ግን ራሱ ኢሕአዴግ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ ከራሱ ገንዘብ እየተከፈላቸው እንደሚኖሩ እናውቃለን፡፡ እኛን ተቃዋሚዎች እንዲቃወሙ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ በ97 ምርጫ የነበረውን ሁኔታ ተመልከት፡፡ በርካታ ምሁራን በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚዎችም ተፈጥረው ነበር፡፡ አገሪቱ አንድ ደረጃ ወደፊት አንቀሳቅሰናታል፡፡ በረከት ስምኦን [የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ጸሐፊ] ስለሚያወራው ናዳ ማለት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ያመለጠበት ናዳ፡፡ ወቅቱ በነፃነት መንቀሳቀስ፣ አባላትና ደጋፊዎችን ማፍራትና ሠልፍና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን መጥራት የቻልንበት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ከእኛ ጋር ወግኗል፡፡ አሁን ይኼ ሁሉ የውኃ ሽታ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ሐሳብ በመጪው ሚያዚያ ወር ከሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ ጋር አያይዘው ሊነግሩን ይችላሉ?

ዶክተር መረራ
፡- ከ97 ምርጫ በኋላ የተወሰዱ ዕርምጃዎች ታውቃቸዋለህ፡፡ በርካታ አፋኝ ሕጎች ፀደቁ፡፡ ኢሕአዴግ አባላቱን ከ760 ሺሕ (በ1997) ወደ አምስት ሚሊዮን (በ2002) ከፍ አድርጓል፡፡ ሴቶች፣ ወጣቶችና ነዋሪዎች እያሉ ሁሉንም ዓይነት የኅብረተሰብ ክፍል የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችና አደረጃጀቶች ተጠቅመው ለአባልነት መልምለዋል፡፡ የቀበሌ ተመራጮችን ቁጥር ከ600 ሺሕ ወደ 3.6 ሚሊዮን ከፍ አድርገውታል፡፡ ስለሆነም በመጪው የአካባቢ ምርጫ ከተሳተፍን 3.6 ሚሊዮን ተመራጮች ያስፈልጉናል ማለት ነው፡፡ ይኼ ቁጥር በርካታ የአፍሪካ አገሮች ካላቸው አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር የሚበልጥ ነው፡፡ ይኼ ስትራቴጂ የወጣው ተቃዋሚዎችን አቅም ለማሳጣት ሆን ተብሎ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ዲሞክራሲን አርስቶትል ወደ ነበረበት ዘመን ወስዶታል ማለት ትችላለህ፡፡ ከውክልና ዲሞክራሲ ቀድሞ ወደነበረው ቀጥተኛ ዲሞክራሲ መልሶታል፡፡ በዚያን ጊዜ የአንድ አካባቢ ሰዎች በአንድ ላይ ይሰበሰቡና የተለያዩ ውሳኔዎችን ያስተላልፉ ነበር፤ መሪያቸውን በቀጥታ ይመርጣሉ፡፡ የውክልና ዴሞክራሲ (Representative Democracy) ፅንሰ ሐሳብ በኢሕአዴግ ትርጉሙ ተቀይሯል፡፡ ሰውን በሙሉ አባል አድርገህ ውሳኔ ስጥ ማለት አትችልም፡፡ ኢሕአዴግ ግን እያደረገ ያለው ይኼንን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚዎች ግን ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ መሥራት ያቃታቸው ወይም ከጨዋታ ውጪ የሆኑት በዚህ ተፅዕኖ ምክንያት ብቻ ነው ብለው ያምናሉ?

ዶክተር መረራ
፡- ሁልጊዜም ለተቃዋሚዎች ውድቀት በግልጽ የሚታዩና የማይታዩ የኢሕአዴግ እጆች አሉበት፡፡ ለምሳሌ በምርጫ 97 ማግስት ሁለት የድርጅታችን አባላት ከኢሕአዴግ ጋር እጅና ጓንት ሆነው በምስጢር ይሠሩ ነበር፡፡ ስማቸውን መጥቀስ አልፈልግም፡፡ አንደኛው አሁንም በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሙስና ተከሷል፡፡ በደርግና በኢሕአዴግ መካከል ያለውን ልዩነት ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ደርግ በግልጽ “እንዲህ እንዲህ አትሥራ” ይልሃል፤ ያንን ትዕዛዝ አልፈህ ከሠራህ ግን ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደሚገጥምህ ታውቃለህ፡፡ ኢሕአዴግ ግን እንድትሠራ የማይፈልገውን እንድትሠራው ይፈቅድልሃል፡፡ ስትሠራው ደግሞ ተከታትሎ ውድቀትህን ያመቻችልሃል፡፡ ለዚህም ነው ወጣት ምሁራን በጣም የሚጠነቀቁትና የሚፈሩት፡፡

በተለይ ደግሞ የተቃዋሚዎች አባል ወይም ደጋፊ መሆንን በነፃነት የምትመርጠው አይደለም፡፡ ሁለቴና ሦስቴ ማሰብ ይጠይቃል፡፡ በመጀመርያ መስዋዕትነት ለመክፈል መወሰንን ይጠይቃል፡፡ ቃሊቲ ብትሄድ ኦሮሚኛ የእስር ቤቱ መግባቢያ ቋንቋ እስኪመስል ድረስ ብዙ የኦሮሞ ወጣቶችን ታያለህ፡፡ የሌሎችን ብሔር ተወላጆች እንዲሁ በብዛት ታገኛለህ፡፡ አንድ ጊዜ የመከላከያ ምስክር ሆኜ ወደ ችሎት ሄጄ ነበር፡፡ በአንድ በኩል በመቶዎች የሚቆጠሩ የእኛ አባላት አየሁኝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በዓቃቤ ሕግ የመጡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ምስክሮች ስመለከት ደነገጥኩኝ፡፡ ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለንም አሳሰበኝ፡፡ በአንድ ትልቅ አዳራሽ ለስብሰባ የተጠራ ሕዝብ ነው የሚመስለው እንጂ ፍርድ ቤት አይመስልም፡፡ ይኼ ሁሉ የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ያስከተለው ጣጣ ነው፡፡  Ethiopian reporter news paper

No comments:

Post a Comment