Pages

አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ በሙስና ክስ ላይ ምስክርነት ሰጡ

May 08, 2013 | Ethiopian Reporter (Government's allay news paper)

የኦሮሚያ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ፣ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሬት ሙስና ክስ በመሠረተባቸው ከ80 በላይ ተከሳሾች በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ማክሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው ምስክርነት ሰጡ፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላ የመከላከያነት ምስክርነታቸውን የሰጡት፣ በኦሮሚያ ክልል የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት አቶ ኃይሉ ደቻሳና ሌሎች ተጠርጣሪ ተከሳሾች በምስክርነት ስለቆጠሯቸው ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ከሕገወጥ የመሬት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉት እነ ኃይሉ ደቻሳ ላይ፣ የክልሉ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ሰኔ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ያለውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ለኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስና ያቀረበውን ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድን፣ የልዩ ዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ቱሉን፣ የኦሮሚያ ከተማ ልማት ኃላፊን፣ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን አቶ ደዋኔ ከድርንና ሌሎችንም በመከላከያ ምስክርነት ቆጥረዋቸው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ባለፈው ቀጠሮው የተጠርጣሪዎችን መከላከያ ምስክሮች ለማድመጥ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ በሥራ ምክንያት ያልቀረቡት አፈ ጉባዔ አባዱላ፣ ማክሰኞ ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከተከሰሱበት ከመሬት አሠጣጥ ጋር በተያያዘ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ እሳቸው የክልሉ ባለሥልጣን በነበሩበት ወቅት መሬትን በሚመለከት የወጣው መመርያ፣ የተከለለንና የአርሶ አደሮችን ይዞታ ጭምር እንዲሰጥ መፍቀድ አለመፍቀዱን እንዲያስረዱ አፈ ጉባዔውን ጠይቋል፡፡

እሳቸውም በሰጡት ምላሽ የሕዝቡ ኑሮ እንዲሻሻል፣ ውኃና ኤሌክትሪክን ጨምሮ ሁሉንም ነገር እንዲያገኝ የሚፈቅደውን መመርያ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ከእሳቸው ጋር በወቅቱ የነበሩና እስካሁንም በክልሉ በተለያየ ሥልጣን ላይ ያሉ አብረው ያወጡት መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ሌሎች መከላከያ ምስክሮች ቀርበው መስክረዋል፡፡ በመከላከያ ምስክርነት ተቆጥረው የነበሩት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድን ጨምሮ ያልቀረቡ ኃላፊዎች መኖራቸው ታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment