Pages

እንዳንተማ ቢሆን! – ይህ ግጥም ለአቤ ቶክቻዉ, ለዶክተች ፍቅሬ ቶለሳ እና ለመሰሎቻቸዉ ማስታወሻ ይሁን

July 10, 2013 | በበሪሶ ገዳ*
እንዳንተማ ቢሆን!!

እንዳንተማ፡ ቢሆን፡ እንደ፡ አስተሳሰብህ
ሆነን፡ እንቀር፡ ነበር፡ አሽከር፡ ለጌቶችህ!
በስመ፡ ኢትዮጵያ፡ ብሄረ፡ ኢትዮጵያዊነት
የማይጨበጥ፡ ተረት፡ የቀን፡ ህልም፡ ቅዥት
አንድ፡ ላይ፡ ሊወቀጡን፡ ሁሉንም፡ ጨፍልቀዉ
በራሳቸዉ፡ ምስል፡ ሊሰሩን፡ ጠፍጥፈዉ
ያልሆንነዉን፡ እንድንሆን፡ ማንነት፡ ቀይረዉ
በአንድነት፡ መዶሻ፡ ብሄርን፡ ደፍጥጠዉ
የኦሮሞ፡ ልጅ፡ ኩራት፡ ወግ፡ ባህል፡ አጥፍተዉሳር፡ መሬት፡ ቅጠሉን፡ ወንዝ፡ ሸንተረሩን
ሁሉን፡ ቀያይረዉ፡ አፍርሰው፡ ሊገጥሙን
እንድንኖር፡ ተጭነን፡ እንደጋሪ፡ ፈረስ
ክረምትና፡ በጋ፡ ጌቶች፡ ስናመላልስ
ጭሰኛና፡ ገባር፡ የነፍጠኞች፡ አሽከር
መወለድ፡ ከኦሮሞ፡ መሆን፡ ከአንዱ፡ ብሄር
አንገት፡ የሚያስደፋ፡ ሆኖ፡ የሚያሳፊር
ከሰዉ፡ በታች፡ ታይቶ፡ ተሸማቆ፡ እንዲኖር
የጨለማ፡ እስር-ቤት፡ ተፈርዶበት፡ ነበር
ገመዳ፡ ገመቹ
ጫልቱና፡ ግንብቹ
መባል፡ ያስቆጥራል፡ ከሀጥያኖቹ
አዎን! …
እንዳንተማ፡ ቢሆን፡ እንደ፡ አስተሳሰብህ
ሆነን፡ እንቀር፡ ነበር፡ አሽከር፡ ለጌቶችህ!
እንጣጥ፡ እንጣጥ፡ አትበል፡ ተዉ! ወጥ፡ አትርገጥ
በማያገባህ፡ ገብተህ፡ አታዉቀዉን፡ አትበጥብጥ
በነገር፡ በሽሙጥ፡ አሽሙር፡ ማንጓጠጥ
የሰዉ፡ ቁስል፡ ወግተህ፡ አትነካካ፡ በእንጨት
መጠቀሚያ፡ ሆነህ፡ ስትል፡ ቀደም፡ ቀደም
ጎርፍ፡ ሆኖ፡ እንዳይበላህ፡ የሚሊዮኖች፡ ደም
ከብር፡ ለጀግኖቹ፡ የቁርጥ፡ ቀን፡ ልጆች
የደም፡ እንባ፡ አንብተዉ
በደም፡ ላብ፡ ጨቅይተዉ
መተኪያ፡ የሌላት፡ የህይወት፡ ዋጋ፡ ከፍለዉ
አቀጣጠሉ፡ ችቦ፡ የብርሃን፡ ጮራ
ከቶ፡ የማይጠፋ፡ እሳተ፡ ጎመራ
እየጋመ፡ ከታች፡ ከሩቅ፡ የሚያበራ
ሊደርስ፡ ያንዣበበ፡ የነፃነት፡ አዝመራ
*በሪሶ ገዳ: ገጣሚዉን ለማግኘት በዚህ ኢሜይል ይጠቀሙ ear_tuf12@hotmail.com

No comments:

Post a Comment