Pages

ከኦነግ ኢንፎ ዴስክ የተሰጠ መግለጫ: ወቅቱ የኦሮሞ ህዝብ በይበልጥ ታጥቆ ራሱን የሚከላከልበት እንጂ ባህላዊ ትጥቁ ሳይቀር በጠላት የሚፈታበት ወቅት ሊሆን ኣይገባም !


የወያኔ መንግስት የኦሮሞን ህዝብ ዋነኛ የጥቃት ኢላማው በማድረግ ካለፉት ስርኣቶች ሁሉ የከፋ ስለመሆኑ ኣያጠያይቅም። በተቻለለት መንገድ ሁሉ ይህን ህዝብ በማዋረድና በማዳከም ላይ ሲተጋ ይታያል። ወያኔ ለሁለት ኣበይት ጥቅሞች ሲል ከኦሮሞ ህዝብ ጫንቃ ላይ ኣለመውረድን ኣሻፈረኝ ብሏል። የመጀመሪያው የኢኮኖሚ ጥቅም ነው። የኦሮምያን ሃብት ዘርፎ ጡንቻውን እያፈረጠመበት የኣገዛዝ እድሜውን ያራዝምበታል። የወደፊት ኣገሩንም ይገነባበታል። ሁለተኛው የፖለቲካ ጥቅም ነው። ኣለምን በሚያታልልበት የውሸት ዴሞክራሲያዊው ስርኣት ውስጥ የዚህን ብዙሃን ህዝብ ድምጽ በሃይል እየነጠቀ በኣገሪቷ መሰረተ-ሰፊ ድጋፍ ያለው መንግስት ራሱን ኣስመስሎ ኣውጇል። በይስሙላ ፓርላማው ውስጥ በኢህኣዴግ ኣባልነት ብዙሃኑን ወንበር ይዞ ሁሌም ስርኣቱን ከሽንፈት ኣደጋ ሲታደግ የምናየው የኦሮሞን ህዝብ ድምጽ ያላንዳች ጠንካራ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ተሳትፎ ራሱ ጠቅልሎት የያዘው ኦፒዲኦ ነው።
የወያኔ መንግስት እነዚህን ሁለት ኣበይት ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ ሲል ኦሮሞን ኣስፈራርቶ በኣገዛዙ ስር ለማስቀጠል ደፋ ቀና ይላል። ከህዝቡ መሃል የታጠቁ ወገኖችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ከጎሮቤቶቹ ህዝቦች ጋር ማጋጨት፣ ኦነግን ትደግፋለህ እያለው መዝረፍና ማሰር፣ ከዚህም ኣልፎ መግደል ላለፉት 22 ኣመታት ዋነኞቹ የስርኣቱ ተግባሮች ነበሩ። በማንኛውም መልኩ የኦሮሞ ህዝብ ክንድ ጠንክሮ ስጋት ላይ እንዳይጥለው ከመግታት ቦዝኖ ኣያውቅም። በቅርቡ ከምስራቅ ኦሮምያ የሚወጡ መረጃዎች የሚጠቁሙትም ይህንኑ ኣውነታ የሚመሰክር ነው። በነዚህ መረጃዎች መሰረት የወያኔ መንግስት ምእራብ ሃረርጌ ውስጥ የኦሮሞ ተወላጆችን ትጥቅ በማስፈታት ዘመቻ ተጠምዷል። የሚገርመው ደግሞ ከህዝቡ ላይ የሚፈቱት ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ሳይሆኑ ባህላዊ የልማትና የጦር መሳሪያዎች መሆኑ ነው። ኦሮሞ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ መታጠቅ ይቅርና ባህላዊ መሳሪያውን ሳይቀር እንዲፈታ እየተገደደ ነው። በተለይም ጉባ ቆሪቻ እና ገመቺስ ወረዳዎች ውስጥ የስርኣቱ ተላላኪዎች መንጫ በመባል የሚታወቀውን ባህላዊ መሳሪያ ከህዝቡ ላይ የመቀማት ዘመቻ ላይ ተሰማርተዋል። በምስራቅ ኦሮምያው ህዝባችን ዘንድ መንጫ ከበርካታ ክፍለ ዘመናት በፊት ጀምሮ የልማትና የመከላከያ መሳሪያ በመሆን የሚታወቅ ነው። ይህ ብቻም ሳይሆን መንጫ የኦሮሞ ህዝብ የባህል ቅርስም ነው። በዚህ የኦሮምያ ክፍል መንጫ የማንነት መገለጫ ባህል ኣካል በመሆን በዘፈንና በጭፈራ ወቅት ጥቅም ላይ ይውላል። በባህል ኣልባሳት ተውቦ መንጫ በመያዝ ሸጎዬ መጨፈር ከጥንት ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብ ባህል ኣካል ነው። በተጨማሪም ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰው መንጫ የልማት መሳሪያም እንደመሆኑ መጠን ገጀራ፣ መጥረቢያና ማጭድ ከመሳሰሉት ቁሳቁሶች ጋር ተመሳሳይ ኣገልግሎት ይሰጣል።
ይህን ባህላዊ መሳሪያ ከህዝቡ ላይ ለመቀማቱ ዘመቻ የተሰጠው መሰረተ ቢስ ምክንያት ደግሞ ‘ህዝቡ በመንጫ እየተጨፋጨፈ ነውና መሳሪያውን ከህዝቡ ኣሰባስበን ወደ ብረት ፋብሪካ በመላክ ወደ ምርት መሳሪያነት እንቀይራለን’ የሚል ነው። ይህ ነጭ ውሸት መሆኑን ህዝባችን በውል መገንዘብ ይኖርበታል። ማንኛውም ዜጋ በዚህ ተራ የወያኔ ቅጥፈት መታለል ኣይገባውም። ከጥንት ጀምሮ በዚህ መሳሪያ በኣግባቡ ሲጠቀም የኖረ ህዝብ ዛሬ ላይ ምን ኣግኝቶት በመንጫ ይጨፋጨፋል? በሃይለ ስላሴና በደርግ መንግስታት ዘመን ኣንድም ጊዜ ኣደገኛነቱ ተነግሮ የማያውቀው መንጫ ዛሬ በወያኔው ዘመን ለምን ለውግዘት በቃ? ይህ ስርኣት ከማናቸውም የኢትዮጵያ ክልሎች በተለየ ሁኔታ ኦሮምያ ላይ በማነጣጠር በተለይም የኦሮሞ ህዝብ መሬት ተቆርሶ ሆን ተብሎ ወደ ሶማሊ ክልል እየተካለለ ባለበት ምስራቅ ኦሮምያ ላይ ይህን መሰል ባህላዊ መሳሪያ የማስፈታት ዘመቻ ለምን ኣስፈለገው? ህዝቡ እነዚህንና የመሳሰሉትን ኣበይት ጥያቄዎችን ማንሳት ኣለበት። የጥያቄዎቹ መልስም እንደሚከተለው ነው።
የዚህ ስርኣት ትልቁ ኣላማ የኦሮሞን ህዝብ ባህላዊ ትጥቁ ሳይቀር ኣስፈትቶት ባዶ እጁን በማስቀረት እንደፈለገው ረግጦ መግዛት ነው። ወያኔ ምስራቅ ኦሮምያ ውስጥ ሁለት ተያያዥ ጸረ ኦሮሞ ዘመቻዎችን ኣንድ ላይ እያከናወነ ይገኛል። ባንድ ወገን የኦሮሞን ህዝብ ኣንጡራ መሬት ቆርሶ ወደ ሶማሊ ክልል በማካለል በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ኣደገኛ ግጭት እንዲፈጠር ኣያሰሬ ነው። ‘ልዩ ሃይል’ በተሰኘው ሰራዊቱ ኣማካኝነት ኦሮሞውን ከቀዬው ሲያፈናቅል በተቃራኒው ደግሞ ሶማሊዎችን እስከ ኣፍንጫቸው እያስታጠቀ በኦሮሞ ቀዬ ላይ ያሰፍራል። ከዚሁ ጎን ለጎን በሁለተኛ ተግባርነት የተያያዘው ኦሮሞን ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ ነው። ኦሮሞ ባህላዊ ትጥቁን ሳይቀር ፈትቶ ባዶ እጁን ቀርቶ በቀላሉ እንዲመታ ለማመቻቸት የተያዘ ዘመቻ መሆኑ ነው። ኦሮሞው ቀዬው ላይ ጠመንጃ ቀርቶ ባህላዊ የመከላከያ መሳሪያ እንኩዋን እንዲፈታ በሚገደድበት በዚህ ወቅት ሌላ ሃይል ደግሞ ዘመናዊ ጠመንጃዎችን እስከ ኣፍንጫው ታጥቆ ኦሮምያ መሬት ላይ እንዲሰፍር እገዛ ይደረግለታል። ከዚህ እርምጃ በላይ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተቃጣ ጠላታዊ ጥቃት ታይቶ ኣይታወቅም። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደርግም ሆነ ከሱ በፊት የነበሩ የፊውዳል ስርኣቶች ኦሮሞ ላይ ብቻ ባነጣጠረ መልኩ ባህላዊ የጦር መሳሪያ ሲያስፈቱ ተሰምቶ ኣያውቅም። ወያኔ ከቀደሙት ስርኣቶች በከፋ መልኩ የኦሮሞ ህዝብ ደመኛ ጠላት መሆኑን ለማረጋገጥ ከዚህ የበለጠ መረጃ ኣያስፈልግም።
ኣሁን በምስራቅ ኦሮምያ የተያዘው ዘመቻ ወደተቀሩት የኦሮምያ ክፍሎችም እንደሚዛመት ከስርኣቱ እኩይ ልምድ መረዳት ይቻላል። የወያኔ ኣላማ ኦሮሞን እንደ ኦሮሞነቱ ባዶ እጅ በማስቀረት በቀላል ጥቃት ማንበርከክ ነውና። ስለሆነም ይህ የከፋ መንግስት ያሰናዳለትን ጥቃት መክቶ ለመመለስ ህዝቡ ካለበት ሁሉ ማመጽ ይጠበቅበታል። የምስራቁም ሆነ የማንኛውም የኦሮምያ ክፍል ህዝባችን የወያኔን ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ ከማክሸፍ ኣልፎ በስርኣቱ ላይ የመልሶ ማጥቃት ክንዱን ማንሳት ኣስፈላጊ ሆኗል። የኦሮሞ ህዝብ በማንኛውም የስርኣቱ ማታለያ መደናገር የለበትም። ‘የጦር መሳሪያን ወደ ልማት መሳሪያ ለመቀየር የተያዘ ዘመቻ ነው’ የሚለው የጠላት ማታለያ ከቶ ህዝባችንን ማሳሳት የለበትም። በኣለማችን ላይ ማንኛውም ህዝብ ለልማት ከሚገለገልባቸው መሳሪያዎች በተጨማሪ ባህላዊ ወይም ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችም ይኖሩታል። የሰው ልጅ እንደ ማጭድ፣ ገጀራና ኣካፋ ባሉት መሳሪያዎች የልማት ስራውን እንደሚያከናውነው ሁሉ ጦር፣ ጎራዴና መንጫ በመሳሰሉት መሳሪያዎች ደግሞ ከጠላት ጥቃት ራሱን ይከላከላልባቸዋል። ከኣደገኛ የዱር ኣራዊቶችም ራሱን ይጠብቅባቸዋል። ይህ የሰው ልጅ ራሱን የመከላከል ተፈጥሮኣዊ መብት ነው። ይህንን ሰብኣዊ መብት ለመግፈፍ የሚደረግ ሙከራ ሲያጋጥም ደግሞ በጋራ ክንድ መቀልበስ የግድ ይሆናል። መንጫም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ባህላዊ የጦር መሳሪያ ከህዝቡ ለመቀማት መንደር ለመንደር የሚንከላወሱ የጠላት ተላላኪዎች የህዝቡ የተባበረ ክንድ መቅመስ ይገባቸዋል። ህዝባችን ማንኛውንም ኣይነት ትጥቁን ፍታ ሲባል መፍታት፣ ተንበርከክ ሲባል መንበርከክ ካሁን በሁዋላ ኣስነዋሪና መቆም ያለበት ነው።
በጥቅሉ የወያኔ መንግስት የኦሮሞን ህዝብ ፈርቶ ባህላዊ መሳሪያው ሳይቀር ለማስፈታት የተነሳበት ምክንያት ግልጽ ነው። በመላው ኦሮምያ ህዝቡ በተለያዩ መንገዶች በስርኣቱ ላይ ያፋፋመው የኣልገዛም ባይነት ንቅናቄ ከቁጥጥሩ ውጭ ከሚወጣበት ደረጃ መቃረቡ ነው። በትጥቅ ትግል ላይ ከተሰማሩት ቆራጥ የኦሮሞ ልጆች በተጨማሪ እዚያው የስርኣቱ ጉያ ስር ሆነው በወያኔ ኣደገኛ ካድሬዎች ላይ ኣስደማሚ የጥቃት እርምጃ የሚወስዱ ጀግኖች መበራከታቸው ስርኣቱን ክፉኛ ኣስበርግጎታል። በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ኦሮምያ ከኣጭር ጊዜ በሁዋላ ከእጁ ልታመልጥ መሆኑ ለስርኣቱ የገባው ይመስላል። ለዚህ ደግሞ እንደ መፍትሄ መውሰድ የመረጠው እርምጃ ኦሮሞን ማንኛውም ትጥቅ ኣልባ ማድረግ፣ እርስ በራሱና ከጎሮቤቶቹ ጋር ማጋጨት፣ ባጠቃላይ ከውስጥና ከውጭ ህዝቡን ሰላም ነስቶት የትግል ክንዱን ማላሸቅ ሆኗል። ህዝባችን ግን ይህ የጠላት ምኞት እንዳይሳካ በተባበረ ክንድ መፋለም ብቸኛ ምርጫው ሆኗል። ህሊና ያላቸው የኦፒዲኦ ኣባላት ሳይቀሩ ነገ ከማይቀርላቸው የታሪክ ተጠያቂነት ለመዳን ከፈለጉ ኣንዲህ ባለው ወቅት ህዝባቸው ላይ የሚፈጸመውን ግፍ በግልጽ መቃወም ይጠበቅባቸዋል።
ወቅቱ ለኦሮሞ ህዝብ ተጨማሪ ዘመናዊ መሳሪያዎችን በሚገባ በመታጠቅ ራስን የሚከላከሉበት እንጂ ባህላዊ መሳሪያም ሳይቀር የሚፈቱበት ወቅት ሊሆን ኣይገባም። በተለይም ወጣቱ ትውልድ ቄሮው ኣንደ ቄሮነቱ ባለበት ሁሉ ተደራጅቶ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ከጠላት እጅ እየነጠቀ በመታጠቅ እየተዋረደ ያለውን ህዝቡን ከውርደት ማዳን የወቅቱ ጥያቄ ነው።
ድል ለኦሮሞ ህዝብ!
የኦነግ ኢንፎ ዴስክ

No comments:

Post a Comment