Pages

የአቶ በቀለ ነዲ ኢደኣ አጭር የህይወት ታሪክ

February 17, 2014 Gadaa.com
Obituary of the Honorable Mr. Bekele Nadhi, an eminent leader, entrepreneur, community organizer and attorney.
———————–
Gadaa.com
ክቡር አቶ በቀለ ነዲ ከአባታቸው ከአቶ ነዲ ኢደኣ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ደስታ ብሩ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ጥር 21 ቀን 1927 ዓ. ም. ተወለዱ፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሽመልስ ሃብቴ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል፡፡
ከዚያም ከፍተኛ ትምህርታቸውን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው በ1950 ዓ.ም. በሕግ የኤል. ኤል. ቢ. ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ በዚሁ ሙያ የበለጠ ለመካን በነበራቸው ፍላጎትና ባሳዩትም ታታሪነት የነፃ ትምህርት እድል በማግኘታቸው ወደ ካናዳ ሄደው በታዋቂው ማጊል ዩኒቨርሲቲ በ1953 ዓ. ም. በሕግ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡
በሥራዉም መስክ በተለያዩ የመንግስት፣ የግልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዉስጥ በከፍተኛ ሃላፊነት ደረጃ ጭምር በርካታ አገልግሎቶችን ያበረከቱ ሰው ነበሩ፡፡ ከነዚህም ጥቂቱን ለማዉሳት፡-
ለአምስት ዓመታት ያህል የእርሻና ኢንዱስትሪ ልማት ባንክ የህግ አማካሪ በመሆን ባንኩ በዘመናዊ ሥርዓት እንዲደራጅ፣ የልማት ስራዉን ለማካሄድ በሚያስፈልገው የፖሊሲ፣ የብድርና የቴክኒክ አቋሙ የተሟላ እንዲሆን ረድተዋል፡፡ በተለይም እንደ ዓለም ባንክ ካሉ የውጭ አበዳሪዎችና ተባባሪዎች ጋር ባንኩ የነበረው ግንኙነት በብቃት እንዲመራ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ረገድ ጠቃሚ ምክሮችን በመስጠትና መሰረታዊ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ እንዲሁም በድርድር መድረኮች ላይም በመሳተፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
ቀጥሎም የግል ድርጅታቸውን ከሙያ ባልደረባቸው ከአቶ ተፈሪ ብርሃኔ ጋር በማቋቋምና ስራዉንም በመምራት ለብዙ የመንግሥት፣ የግልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የህግ ምክርና የጥብቅና አገልግሎት ሲያበረክቱ ቆይተዋል፡፡
ክቡር አቶ በቀለ ነዲ በቤተሰብ ሥነ ስርዓት የታነፁ፣ በጓደኞቻቸውም ዘንድ የተወደዱና አቻዎቻቸዉን ለበጎ ስራ የሚያስተባበሩ ነበሩ፡፡ በአገር ዉስጥና በዉጭ ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያና የዓለም አቀፍ ተማሪዎች ማህበራትን በማቋቋምና በፕሬዝዳንትነት ጭምር በመምራት ለለውጥ በተደረጉ ጥረቶች ገንቢ ሚና ተጫውተዋል፡፡
ክቡር አቶ በቀለ ነዲ ከወጣትነት ዘመናቸው አንስቶ ለአገርና ወገን የሚበጁ የጋራ ጥረቶች እንዲጎለብቱ ንቁ ተሳትፎ ያደረጉ ሰው ናቸው፡፡ በዚሁ መንፈስ የሜጫና ቱለማን ማህበር ከመሰረቱት አንዱ ሲሆኑ ከማህበሩ ምስረታ ጀምሮ እስከ 1994 ዓ. ም. ድረስ በምክትል ፕሬዝዳንትነት፣ በኋላም በክብር ፕሬዝዳንትነት መርተዋል፡፡ በዚህና በቀጣይም የማህበሩ ዉጣ ዉረድ ወቅቶች ሁሉ አቶ በቀለ ሙያቸውንና አመራራቸውን በመቸር ብቻ ሳይሆን ያልተቆጠበ የገንዝብ እርዳታም እያደረጉ ማህበረሰቡን በማስተባበር ከፍተኛ እገዛ ያደረጉ ባለውለታ ናቸው፡፡
በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ ገጠር አካባቢዎች በጣም ተፈላጊ በሆነው የውሃ አቅርቦት ሥራ መስክ ላይ ያተኮረ የኦሮሞ ራስ አገዝ ማህበር (“OSRA”) የሚባል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በማቋቋም ከፍተኛ ሚና ከመጫወታቸውም በላይ በቦርድ ሰብሳቢነትም በመምራት የህዝብ አለኝታነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡
በተጨማሪም የገጠሩ የኦሮሞ ሕዝብ ኑሮ እንዲሻሻል ካለዋስትና ብድር በማቅረብ አገልግሎት የሚሰጥ ወሳሳ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በማቋቋም ብዙ ሺህ ገበሬዎች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረጋቸውም በላይ በሞት እስከተለዩን ድረስ በቦርድ አባልነት አገልግለዋል፡፡ እንዲሁም ለረዥም ዓመታት በአዲስ አበባ የሮተሪ ኢንተርናሽናል ክለብ አባል ነበሩ፡፡
ክቡር አቶ በቀለ ነዲ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አ. ማ. ሲቋቋም በጥናቱ ከመሳተፋቸውም በላይ፣ በባንኩ አመሰራረትም ጉልህ ሚና ተጫውተው፣ ባንኩ ከተመሰረተም በኋላ በቦርድ አባልነትና ሰብሳቢነት ለረዥም ዓመታት በማገልገል፣ ባንኩ ላስመዘገባቸው አመርቂ ውጤቶችና አሁን ባንኩ ለደረሰበት ከፍተኛ የእድገት ደረጃ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
ክቡር አቶ በቀለ ነዲ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ዘነበች ነጋሽና ከመላ ቤተሰባቸው ጋር በመልካም አኗኗራቸው የተመሰገኑ ነበሩ፡፡
የካቲት 3 ቀን 2006 አቶ በቀለ በሞት ስለተለዩን የምንሰናበታቸው በመሪር ሃዘን ቢሆንም፣ የምንሸኛቸው ከልጅነት እስከ አንጋፋ ህይወታቸው ባሳዩት የቅንነት፣ የሙያ ብቃት፣ የአገር ወዳድነትና የህዝብ ወገንነት በጎ ቅርሳቸውን በማስታወስ እና ከመልካም ሥራዎቻቸው ጋር፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎችና በህመማቸው ወቅት ባሳዩት የመንፈስ ፅናትና የሞራል ጥንካሬም አርአያነታቸውን በመዘከር ነው፡፡
የሚወዱትን የትዳር ጓደኛ፣ አባት፣ ወንድም፣ አለኝታ የሆነን ጓደኛና ወዳጅ ማጣት አጅጉን የሚያሳዝን እንደመሆኑ፣ በዚህ መልክ ለተጎዱት ሁሉ መፅናናትንና ብርታትን እንመኛለን፡፡
የካቲት 6 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment