Pages

ክፍት ደብዳቤ ለኣሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ኣማርኛ ፕሮግራም ማኔጂንግ ኤዲተር ወ/ሮ ትዝታ በላቸው

ያ 09, 2014 | ከያህያ ጀማል

በቅድሚያ ይድረስ የተከበረ ሰላምታዬ ለወ/ሮ ትዝታ በላቸው። ከሰላምታዬ በማስከተል ይህን ክፍት ደብዳቤ ለመጻፍ ወዳነሳሳኝ ፍሬ ጉዳይ ልዝለቅ። ወ/ሮ ትዝታ ቢያንስ ከ20 ኣመታት በላይ በኣሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ኣማርኛው ፕሮግራም ላይ የማውቅሽ ሚዛናዊ የሆኑ ዝግጅቶችን ስታቀርቢ ነው። በተለይም በፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ዙሪያ እንግዶችን ጋብዘሽ በምታዋይያቸው ወቅቶች ሁሉ ተገቢና ፍትሃዊ ጥያቂዎችን እየፈለፈልሽ በመሰንዘር የኣድማጮችሽን የልብ ትርታ ማዳመጥ የምትችይ የቱባ ጋዜጠኝነት ልምድ ባለቤት መሆንሽን ነበር የማውቀው። በዚህም የቪኦኤን ኣማርኛ ፕሮግራም ማድመጥ ከጀመርኩበት ወቅት ኣንስቶ ከሞላ ጎደል ኣድናቂሽ ሆኜ ቆይቻለሁ።

ዛሬ ግን ይህን ክፍት ደብዳቤ እንድጽፍልሽ ያነሳሳኝ ጉዳይ በቅርቡ በተከታታይ ክፍሎች የቀረበውንና ሶስት ምሁራንን በማሳተፍ ኣንቺው ራስሽ ባወያየሽው በኢትዮጵያ የታሪክ ጭብጦች ላይ ያተኮረ ወይይት ይዘት ነው። በዚህ ውይይት ውስጥ ለረጅም ጊዜ የማውቅሽ የወ/ሮ ትዝታ በላቸው ሚዛናዊ ኣወያይነትና ጠለቅ ያለው የጋዜጠኝነት ጥያቄ ኣጠያየቅ ልምድሽ የት እንደገባ ኣልተረዳሁም። ውይይቱ ኣንድን ወገን ኣስደስቶ ሌላውን ያሳዘነ ሆኖ ሳለ ይባስ ተብሎ እየተደጋገመ ኣየር ላይ ሲውል ታዝቤያለሁ። በዚህ ክፍት ደብዳቤዬ ቢያንስ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች እንዳዘንኩብሽ ለመግለጽ እገደዳለሁ።
ገና ሲጀመር በኢትዮጵያ የታሪክ ጭብጦች ዙሪያ ከተጋበዙት ሶስቱ ምሁራን መካከል ኣንዱ የተመረጡበት መስፈርት ምን እንደሆነ ለኔ ግልጽ ኣይደለም። የታሪክ ምሁር በመባል የሚታወቁት ዶክተር ጌታቸው ሃይሌ በታሪክ ጉዳይ ላይ የራሳቸውን ኣቅዋም እንዲያንጸርባርቁ መመረጣቸው ለኣንድም ሁለት ወይም ሶስት ምክንያቶች ተገቢ ሆኖ ይታየኛል። እሳቸው በሞያ የታሪክና የቁዋንቁዋ ተመራማሪ ከመሆናቸው በተጨማሪ በራሳቸው ስም ኣልፎ ኣልፎ በድረ-ገጾች ላይ በሚያሰራጯቸው ታሪክ ነክ መጣጥፎች ይዘት ዙሪያ ለበርካታ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚጠበቅባቸው ‘ተጠያቂ’ ምሁር ናቸው። በግጭት ኣስወጋጅነት ምርምር ስራ ላይ የተሰማሩት ዶክተር ብርሃኑ መንግስቱም ቢሆኑ በታሪክ ሂደት ውስጥ ስለተከሰቱ ግጭቶች የምናወጋ እስከሆነ ድረስ ውይይቱ ሊመለከታቸው ይችላል። ለነገሩ ዶክተር ብርሃኑ በዚህ ውይይት ውስጥ እንዲጫወቱ የተፈለገው ሚና ኣስታራቂ ሃሳቦችን በማንሸራሸር ሁለት ጽንፈኛ ኣመለካከቶችን ለማቀራረብ ታስቦ ቢሆንም እሳቸው ግን በዚህኛው ውይይት ውስጥ ስልታዊ በሆኑ ቃላት የዶክተር ጌታቸውን ኣቁዋም በመደገፍና በማዳበር ሶስተኛውን ተወያይ እያጠቁ ማንበርከካቸውን ነው ለመረዳት የቻልኩት።
በዚህ ታሪክ ነክ ውይይት ላይ የተጋበዙት ሶስተኛው ሰው ዶክተር በያን ኣሶባ ግን በምን መስፈርት ለዚህ ውይይት ብቁ ተደርገው እንደተመረጡ ነው ያልገባኝ። ውይይቱ የታሰበው (ከመንደርደሪያ ሃሳቡም ኣንዳደመጥነው) ሁለቱን ተጻራሪ የታሪክ ጭብጦች (የኣማራ ልህቃንና የኦሮሞ ልህቃንን በመወከል) ኣገናኝቶ ለማወያየት እስከሆነ ድረስ ኦሮሞን ወክለው የሚቀርቡት ምሁር ልክ እንደ ኣማራው ዶክተር ጌታቸው ሁሉ በታሪክ እውቀት የተካኑና ውሃ መቁዋጠር የሚችል የክርክር ነጥብ የማንሳት ኣቅም ያካበቱ መሆን ይጠበቅባቸው ነበር። ዶክተር ጌታቸው የወዲያኛውን ጽንፈኛ ኣቁዋም ወክለው እንዲቀርቡ ከተመረጡ ዘንዳ የወዲህኛውን ‘ጽንፈኛ’ ኣቁዋም መንስኤ ማስረዳትና መከራከር የሚችል ተመጣጣኝ የታሪክ ምሁር መመረጥ ነበረበት። ዶክተር በያንን እስከማውቃቸው ድረስ ግን እሳቸው የኣንድ ፖለቲካ ድርጅት ኣመራር ኣባል እንጂ በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ከተቀሩት ሁለቱ ምሁራን ጋራ የሚመጣጠን የታሪክ ትምህርት እውቀት ያካበቱ ኣይመስሉኝም። ባልሳሳት እሳቸው በሞያ የህግ ምሁር እንጂ እንደ ተቀሩት ሁለቱ ሰዎች የታሪክ ወይም የታሪክ ወለድ ግጭቶች ኣወጋገድ ሊቅ ኣይደሉም። በዚህ ረገድ ሲታይ ታሪክና ፖለቲካ ለየቅል መሆናቸውን ልብ እንላለን። ፖለቲካ ሳይንስም ኣርትም ነው። ኣርቱ ካለው ማንኛውም ሰው ብድግ ብሎ ፖለቲከኛ ሊሆን ይችላል። ከዚህም የተነሳ ብዙ የማህበራዊ ሳይንስ ያላጠኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ምሁራን ሃይለኛ ፖለቲከኛ (technocrats) በመሆን ኣገር ሲመሩ በኣለም ዙሪያ እናያለን። ነገር ግን ታሪክ ለታሪክ ኣጥኚዎች (historians) ብቻ የሚተው ጉዳይ ነው። የዚህኛው ውይይት ጭብጥም ታዲያ ህግ ነክ ወይም ወቅታዊ ፖለቲካ ሳይሆን ታሪክና ታሪክ ነክ ጉዳይ ነው።
ዶክተር በያን በውይይቱ ላይ ሲጋበዙ የኦሮሞ ልህቃንን በመወከል በኢትዮጵያ ታሪክ ጭብጥ ላይ እንዲወያዩ ታሳቢ ተደርጎ ይመስለኛል። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ከዶክተር በያን ይልቅ ልክ እንደ ዶክተር ጌታቸው ሃይሌ ሁሉ በታሪክ ወይም በቁዋንቁዋ ጥናት Ph.Dያቸውን ከሰሩ የኦሮሞ ተወላጅ ምሁራን መካከል ተፈልጎ መጋበዝ ነበረበት። ከተቃራኒው ጫፍ ለሚነሱ ታሪክ ነክ ማብራሪያዎች ተመጣጣኝ የሆነ ታሪክ ነክ የመከራከሪያ ምላሽ መስጠት የሚችል የኦሮሞውን የፖለቲካ ጎራ የሚወክል የታሪክ ምሁር መጋበዝ ፍትሃዊነት ይኖረው ነበር። ወ/ሮ ትዝታ ይህን ማድረግ እየቻልሽ ሳታደርጊ በመቅረት ኣድሎኣዊነት የሚንጸባረቅበትን ውይይት/ክርክር ማቅረብ በመምረጥሽ በጣም ካዘኑብሽና ከታዘቡሽ የኦሮሞ ተወላጆች መካከል ኣንዱ መሆኔን እገልጽልሻለሁ።  (በነገራችን ላይ ኣብዛኞቹ የኦሮሞ ብሄረተኞች የቪኦኤ ኣማርኛ ፕሮግራም የመከታተል ፍላጎት የላቸውም። ምክንያቱ ደግሞ ኣብዛኛውን ጊዜ በሚቀርቡት እንዲህ ባሉት ኣድሎኣዊነት በሚያጠቃቸው ዝግጅቶች በመሰላቸትና በማዘን ነው። ኣሁን ስለምናወራው ውይይትም በተመለከተ ብዙ የማውቃቸውን ሰዎች ጠይቄ ኣብዛኞቹ እንዳልተከታተሉት ነግረውኛል።)  ከኦሮሞው ወገን በዚህ ዘርፍ ምሁር ተፈልጎ የታጣ ይመስል የታሪክ ጉዳይ የማይመለከታቸውን ዶክተር በያን ላይ የሙጥኝ በማለት እሳቸውን ኣግባብቶ ለማቅረብ የሳምንታት ጊዜ እንደወሰደ ሳስታውስ የውይይቱ ኣዝማሚያ ወዴት እንደሆነ ኣስቀድሞ የሚጠቁም ነበረ። የውይይቱ ኣላማም የሁለቱን ጫፍ ኣመለካከቶች በቅንነት ለማስታረቅ ሳይሆን የኦሮሞውን የፖለቲካ ማህበረሰብ የታሪክ ግንዛቤን በስህተትነት ለመፈረጅና በተለይም ባሁኑ ወቅት በወጣቱ ትውልድ መካከል የሚታየውን የኣባቶችን ታሪክ መሰረት ባደረገ የፖለቲካ ኣመለካከት ውስጥ የኦሮሞውን ወገን ኣፍ ለማስያዝ ታስቦ መሆኑን ከውይይቱ ኣጀማመርና ኣጨራረስ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ለዚህም ነው ከውይይቱ ፍጻሜ በሁዋላ በቀረቡት የኣድማጮች ኣስተያየት የኣንዱ ፖለቲካ ማህበረሰብ (የኣማራው ወገን) ኣባላት ብቻ በውይይቱ መደሰታቸውን ሲገልጹ ከሁለተኛው (ከኦሮሞው) ወገን ግን ዝምታ የተመረጠው።
ወ/ሮ ትዝታ ሌላው ያዘንኩብሽ ምክንያት ደግሞ ከላይ እንደጠቀስኩት በሳልና ፍትሃዊ የሆነው የኣወያይነት ልምድሽ በዚህኛው የውይይት ሂደት ከቶ ስላልታየኝ ነው። ይሄን ሳነሳልሽ የግድ ስለ ዶክተር ጌታቸው ሃይሌ ጽንፈኛ ኣቁዋም ከዶክተር በያን ኣሶባ ውሱን የሆነ የታሪክ እውቀት ጋር እያነጻጻርኩ መናገሬ የግድ ይሆናል። እንደምትረጂው (ኣንቺም እንዳነበብሽው በውይይቱ ወቅት ጠቅሰሻልና) ዶክተር ጌታቸው ሃይሌ ለዚህ ውይይት ከመቅረባቸው ጥቂት ቀናት ኣስቀድሞ ‘እርቅና ሰላም፣ የህይወት ቅመም’ በሚል ርእስ ያዘጋጁትን ኣንድ ጽሁፍ በተለያዩ ድረ-ገጾች ላይ ለንባብ ኣውለውት ነበር። ዶክተር ጌታቸው በዚህ ኣርእስቱ እንደ ቂቤ በለሰለሰና ይዘቱ ግን ኣንደ ጩቤ በሰላ ግጭት ሰባኪ ጽሁፋቸው ኦሮሞና እስልምናን በኢትዮጵያ ጠላትነት በመፈረጅ እስከሚበቃቸው ድረስ ዘልፈዋል፣ ረግመዋል። ኦሮሞን በሚመለከት በጽሁፉ ውስጥ ኣንዲህ ብለዋል። ‘ኦሮምኛ የሚናገሩ ጎሳዎች የእስላሞቹ ኣመጽ በተገታ ማግስት ፈልሰው ከእስላሞቹ የተረፈውን የስልጣኔ ምልክት ጠራረጉት…ጋዳ በሚሉት (ገዳ ማለታቸው ነው) ሁሉን ለጦርነት በሚያሰልፍ የማፊያ ስርኣት በውትድርና ተደራጅተው፣ በግብርና፣ በንግድ፣ በድብትርና የሚተዳደረውን ሰላማዊ ህዝብ ኣረዱት፣ ንብረቱን ኣወደሙት።…’ እያሉ ጠብ ጫሪ የተረት ተረት ትረካቸውን ይቀጥላሉ። ዶክተር ጌታቸው እንዲህ ያለውን በኣደገኛ ጽንፈኝነት የተጠናወተ ወገንተኛ ኣቁዋም ይዘው ሲጽፉ ኣቁዋማቸውን በሚደግፉት ወገኖች ዘንድ ኣንቱ የሚባሉ ምሁር እንደመሆናቸው መጠን ‘የኢትዮጵያ ስልጣኔ ባልቤት ነኝ’ ብሎ ራሱን የሚጠራው የፖለቲካ ማህበረሰብ በኦሮሞ ላይ ምን ያክል በዘረኝነት የተሞላ ጥላቻ እንዲያድርበትና ብሎም የሩዋንዳውን ኣይነት ጭፍጨፋ ሊጋብዝ የሚችል ቡራኬ እያሰሙ ስለመሆናቸው ግልጽ ነው።
‘ፕሮፈሰሩ’ እዚህ ላይ ቢያቆሙ ደግ ነበር። ግን ቀጠሉ። ‘እስላሞቹ የክርስቲያኖቹን ስልጣኔ ኣጥፍተው በራሳቸው ስነ ፅሁፍ ሊተኩት ኣስበው ነበር። ኦሮምኛ ተናጋሪዎቹ ግን እረኞች ስለነበሩ ስልጣኔን በስነ ጽሁፋዊ ስልጣኔ የመተካት ግዴታ ኣልነበራቸውም…’ ኣያሉ ከኣንድ ፕሮፌሰር የማይጠበቁ ትምክህተኝነትን የሚያቀነቅኑና በንቀት የተሞሉ ቃላትን እየተጠቀሙ ኦሮሞን ተሳድበዋል። የወቅቱን የኦሮሞን ህዝብ እንስሳት ኣርቢነት ህይወት ለመግለጽ ፈልገው ባልጠፋ ቃል ‘እረኞች’ የሚለውን የዘለፋ ቃል መርጠው መጠቀማቸው የነፍጠኝነት ትምክህታቸው እብጠት ዛሬም ገና ኣለመተንፈሱን ያስረዳናል። ከዚሁ ጋርም ኣያይዞ እሳቸው የሚወለዱበት ብሄር ወይም የፖለቲካ ማህብረሰብ በስልጣኔ የመጠቀና ኦሮሞው ግን ስልጣኔ ኣልባ ወይም በሳቸው ቃል ‘እረኛ’ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል። ይህ ብቻም ኣይደለም። ኦሮሞን እንደ ኣንድ ብሄር ‘ኦሮሞ’ እያሉ መጥራትን ተጠይፈው ‘ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች’ የሚል ኣገላለጽ ሆን ብለው ሁሉም ቦታ ላይ ተጠቅመዋል። ዶክተሩ በታሪክ ምርምር ሃቅ ላይ ተመስርተው የጻፉ ቢሆኑ ኖሮ ገዳን የመሰለ ኣገር በቀል የኣፍሪቃ የደሞክራሲ ባህል ቅርስን ኣንደ ኣንድ የኦሮሞ ህዝብ የስልጣኔ እሻራ ኣንጂ ‘የማፊያ ስርኣት’ እያሉ በመጥራት ባልተሳደቡ ነበር።
ግለሰቡ በዚህ ጽሁፋቸው ማሳረጊያ ላይ ‘ለእርቅና ሰላም’ (ድንቄም እርቅና ሰላም) ያሉትን ሶስት ትምክህታዊ ውሳኔዎች ኣሳልፈዋል። ኣንደኛው ‘…የመጀመሪያው እርምጃ ኣባቶቻችንን እንወክላለን የሚሉ እስላሞችና ኦሮሞዎች… በኢትዮጵያ ላይ ላደረሱት…ጥፋት የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ይጠይቁ…’ የሚል ነው። (ኦሮሞዎችና እስላሞች ዛሬም ‘የኢትዮጵያ ህዝብ’ ኣካል ሳይሆኑ ‘የኢትዮጵያን ህዝብ’ ይቅርታ መጠየቅ የሚጠበቅባቸው መጤዎች መሆናቸውን እየነገሩን ነው።) ሁለተኛው መፍትሄያቸውም‘ኣጼ ምኒልክና ራስ ጎበና ዳጬ የተበታተኑትንና እርስ በራሳቸው የሚባሉትን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ኣንድ ያደረጉበትን ቀን…ኦሮምኛ ተናጋሪዎች…በጨፌኣቸው ወስነው በያመቱ ማክበር ኣለባቸው’ የሚል ነው። ሶስተኛው እርምጃ ያሉት በግልጽ ማንን እንደሚመለከት ባይቀመጥም (ነገር ግን ከግለሰቡ ትምክህታዊ ኣቁዋም ኣንጻር ለኦሮሞው ወይም ለህዝበ ሙስሊሙ ሊሆን ኣንደሚችል ይገመታል) ‘ኣስተሳሰባቸውን ከሰብኣ-ትካት (primitive) ወደ ሰብኣ-ዘመን (modern) ኣስተሳሰብ መቀየር ኣለባቸው’ የሚል ቀጭን ትእዛዝ ኣስተላልፈዋል። ዶክተር ጌታቸው ሃይሌ ስለሚባሉት ግለሰብ ማንነት ከላይ የተጠቀሱት ሶስቱ ትምክህታዊ ‘የመፍትሄ’ ሃሳባቸው በቂ ምስል ያሳያሉና ሶስቱን ነጥቦች እየተነተንኩ ኣንድ ባንድ መተቸት የሚያስፈልገኝ ኣይመስለኝም።
ክብርት ወ/ሮ ትዝታ ሆይ!
ይህን የመሰለ ጠብ ኣጫሪ ጽሁፍ ያቀረቡትን ግለሰብ በራዲዮው የውይይት መድረክ ላይ ስትጋብዢ ዶክተሩ በጽሁፋቸው ውስጥ ስለተጠቀሟቸው ጠብና ቁርሾን የሚቀሰቅሱ፣ ባለፉት የታሪክ ቁስሎቻችን ላይ እንጨት እየሰደዱ የሚያደሙንን ተንኩዋሽ ቃላታቸውን እየጠቃቀስሽ በተለመደው ሞያዊ ብቃትሽ ተፈታታኝ ጥያቄዎችን ትሰነዝሪላቸዋለሽ የሚል ግምት በተወሰነ ደረጃ ኣድሮብኝ ነበር። በውይይቱ ወቅት የታዘብኩት ግን ተቃራኒውን ነበር። ዶክተሩ በጽሁፋቸው ውስጥ ከእባብ በከፋ መልኩ የተፉትን መርዝ ለማለባበስ ኣፋቸውን ቂቤ ቅብተው በውይይቱ ላይ ሊያሞኙን ሲታትሩ ሰማሁኣቸው። በጽሁፋቸው ውስጥ ኦሮሞውን ‘እረኛ’ ኣያሉት ድንቅ የስልጣኔ ኣሻራው የሆነውን የገዳ ስርኣቱንም ‘የማፊያ ስርኣት’ እያሉ እንዳልተሳደቡ ሁሉ በራድዮው ውይይት ላይ ደግሞ መርዛቸውን ምላሳቸው ስር ቀብረው ኦሮሞን ጭራሽ የኣቢሲኒያ ገዢዎች ኣካል ኣድርገው ለማቅረብ ሲሞክሩ ሳቅሁባቸው። በ’ዶክተርነታቸውም’ ኣፈርኩባቸው። በጽሁፋቸው የተናገሩትንና ራድዮ ላይ በሚያቀርቡት ሃሳብ መከከል የሚታየውን እንደ ተራራ የገዘፈ የምሁራዊ ስነ ምግባርና የኣቅዋም ልዩነት ኣጋልጦ ግለሰቡን ማፋጠጥ ያንቺ የጋዜጠኛዋ ስራ ኣልነበረምን? ዶክተሩ በጽሁፋቸውን ውስጥ ስላስቀመጧቸው ሶስቱ መፍትሄ ተብዬ ‘ትእዛዞች’ በራድዮው ወቅት ቢደግሙት መልካም ነበር። እሳቸው ለመድገም ፍላጎት ከሌላቸው ደግሞ የመፍትሄኣቸውን ኣነጋጋሪነት ማጋለጥና ማስተቸት የማን ድርሻ ነበር? የዶ/ር ጌታቸውን ኣቅዋም በተመለከተ ኣድማጭ ግለሰቡ ኣስቀድመው የጻፉትን ይመን ወይስ ራድዮ ላይ የተናገሩትን?
በመሰረቱ ይህንን የዶ/ር ጌታቸውን መንታ ምላስነትና ጠብ ኣጫሪ ኣቁዋም በዋናነት ማጋለጥ የነበረበት በውይይቱ (ውይይት ሳይሆን ክርክር መባል ነበረበት) ውስጥ በባላንጣነት የቀረቡት ዶ/ር በያን ኣሶባ ናቸው። ዶክተር በያን ግን ይህንን መዘዘኛ ጽሁፍ ኣስቀድመው ኣግኝተው ያነበቡትም ኣይመስለኝም። ዶክተር በያን በዚህ ውይይት/ክርክር ላይ ፈቃደኛ ሆነው ለመቅረብ እስከወሰኑ ድረስ ደግሞ የባላንጣቸው ጠንካራና ደካማ ጎኖች ምን ምን እንደሆኑና የተፈታታኝነት ልካቸውስ ምን ያህል እንደሆነ ኣስቀድመው ተረድተው የመከራከሪያ ኣቅማቸውን ማጎልበት ነበረባቸው። የዶክተር ጌታቸውን መርዘኛ ቃላት ከጽሁፋቸው እየጠቀሱ በራድዮው ውይይት ላይ ከተናገሩት ጋር በማገናዘብ ማፋጠጥ ከማንም በላይ የርሳቸው ድርሻ ነበረ። እሳቸው ግን በሚያሳፍር መልኩ ጭራሽ ወረዱና የዶክተር ጌታቸው ‘የታሪክ ተማሪ’ እስከመሆን ድረስ የዘቀጠ ተረቺነታቸውን ኣስመስክረው ዶክተር ጌታቸውን ‘ለታሪክ ትምህርታቸው’ ኣመስግነው ኣረፉት። የኦሮሞ ኣብራክ ኣገር ቤትም ሆነ በዳያስፖራው ኣያሌ የታሪክ ምሁራንን እንዳላፈራ ዛሬ በዶክተር ጌታቸው ‘ሌክቸር’ ኣማካኝነት የታሪክ ሀሁን እየቆጠሩ መሆናቸውን በነገሩን በዶክተር በያን ኣሶባ ኣንዲያፍር ተፈረደበት። ዶክተር በያን ለዚህ ትችት ላለመዳረግ ሲባል ኣስቀድመው እንዲህ ባለው የታሪክ ጉዳይ ላይ ኣለመቅረብን መምረጥ ነበረባቸው።
ኣንደዚህ ኣይነቱ የኣንዱ ተወያይ ብቃት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ሲገባ ኣወያዩ ጋዜጠኛ የራሱን ኣስተዋጽኦ ማድረግ ይችል ነበር። በተለይም ወ/ሮ ትዝታን ከጥንት ጀምሮ ስናውቅሽ በዚህ ኣይነቱ የጋዜጠኝነት ችሎታ የተካንሽ መሆንሽን እናስታውሳለን። በዚህኛው ውይይት ላይ ግን ሞያሽን በፍትሃዊ መልኩ ገቢራዊ ያደረግሽው ኣልመሰለኝም። የዶክተር ጌታቸውን ጠብ ኣጫሪ ጽሁፍ ኣስቀድመሽ ኣንብበሽ ኣያለ በተጠቀሟቸው ቃላት ላይ የጥያቄ ናዳ ልታወርጂባቸው ሲገባ ኣለባብሶ ማለፍን መረጥሽ። ኣለባብሶ በማለፍ ደግሞ ኣለመግባባቶች ጭራሽ ይብሳሉ እንጂ በሃሳብ መቀራረብ ወይም እርቅ ሊመጣ ኣይችልም።
በዚህ ክፍት ደብዳቤዬም ይህንን ትዝብቴን እንድትረጂልኝና ይህ ትዝብት ደግሞ የኔ ያንድ ተራ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ትቂቶች ቢሆኑም ውይይቱን የተከታተሉት የሌሎች ወገኖቼ ትዝብትም መሆኑን ላስገነዝብሽ እፈልጋለሁ። ቢያንስ ለወደፊቱ ራስሽ በምታዘጋጂኣቸው ወይም ባንቺ ማኔጂንግ ኤዲተርነት ሌሎች የስራ ባልደረቦችሽ በሚያቀርቧቸው መሰል ውይይቶች ላይ የኦሮሞ ህዝብ የምሁር መካን ኣለመሆኑን ተረድታችሁ ለሚዛናዊ ውይይት ተገቢ ምሁር መርጣችሁ በመጋበዝ እንድታወያዩ በቀረችኝ የተስፋ እንጥፍጣፊ ለማስታወስ እወዳለሁ። ካልሆነ ግን የኣሜሪካ ድምጽ ራድዮ ኣማርኛው ፕሮግራም ዛሬም በትምክህተኛ ኣቁዋም ደጋፊነቱ እንደሚታማው ሁሉ ይህንን ኣይነት ኢፍትሃዊና በኣድልኦ የተሞላ የውይይት ፕሮግራምም ሆን ብሎ የሚያሰናዳው መሆኑን እንገነዘባለን።
ወ/ሮ ትዝታ ስለጊዜሽ በጣም ኣመሰግናለሁ!
ቸር እንሰንብት!
ያህያ ጀማል

No comments:

Post a Comment