Pages

የስኮትላንድ ሪፈረንደም ለኦሮሞና ለሌሎችም የነጻነት ታጋይ ህዝቦች ኣንድ የድል ምእራፍ ነው

September 19, 2014 | በቦሩ በራቃ*

ባለፈው ሳምንት Essence of the Scottish Referendum in the Eyes of an Oromo Nationalist በሚል ርእስ በእንግሊዝኛ ባቃረብኩት መጣጥፍ ላይ የዩኬዋን ስኮትላንድና የኢትዮጵያዋን ኦሮምያ የፖለቲካ ህይወት ለማነጻጸር ሞክሬ ነበር። ስኮትላንድ ከ300 ኣመት በፊት በ1707 Act of Union በተባለው ውል መሰረት ከብሪታኒያ ጋር ኣንድነት መመስረታቸውን፣ በኣንጻሩ ኦሮምያ ግን ከኣንድ ክፍለ ዘመን በፊት በኣቢሲኒያዊያን ወራሪ ሰራዊት በሃይል ወደ ሃበሾች ግዛት መቀላቀሏን ጠቅሼ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ስኮትላንድ ለ300 ኣመታት የእንግሊዝ ኣካል ሆና ስትቆይ የራሷ የህግ ስርኣት፣ የራሷ ቤተክርስቲያን፣ የራሷ የትምህርት ስርኣት እና የራሷ የሆነ ገንዘብ የማሳተም መብት እንዳላት፣ በኣንጻሩ ግን ኦሮምያ መሰል መብቶች ከቶ የራቁዋት መሆኑን ለማገናዘብ ሞክሬያለሁ።


እነሆ ስኮትላንድ የራሷን እድል በራሷ ወስና ሁሉም ወገን ውጤቱን በፀጋ ተቀብሏል። የዴሞክራሲ ውቤቱ፣ ጉልበቱና ብስለቱም በዚህ የሪፈረንደም ሂደት በገሃድ ታይቷል። እኛን ጨምሮ የሶስተኛው ኣለም ኣገሮች ከዚህ የስኮትላንድ ሪፈረንደም ብዙ ይማራሉ ተብሎ ይጠበቃል። መብት ኣፋኞቹም ሆነ መብት ጠያቂዎች ከሎንዶንና ከኤድንበርግ ብዙ ልምድ ቢቀስሙ ጠቃሚ ይሆናል። መብት ኣፋኞች ከዴቪድ ካሜሩን ኣስተዳደር፣ መብት ጠያቂዎች ደግሞ ከኣሌክስ ሳይሞንድ ፓርቲ ብዙ የሚማሩት ቁምነገሮች ኣሉ። የመብት ጠያቂ ህዝብን ኣንገብጋቢ የፖለቲካ ጥያቄ ሳያናንቁ በሰላማዊ መንገድ ህዝቡን በማወያየት በሃይል ወይም በማስፈራራት ሳይሆን በማግባባትና በፍቅር ወደ ኣንድነት መስበክ የኣለማችን ጨቁዋኝ ስርኣቶች ከዌስት ሚንስቴር ኣስተዳደር መቅሰም የሚገባቸው ገንቢ ልምድ ይሆናል። እንደ ኣገር ነጻ ሆነው ለመቆም ያላቸውን ፍላጎት ያለምንም ነውጥ ወይም ሁከት በህዝብ ድምጽ ብቻ ተመርተው ኣብላጫ ወንበር በመያዝ የፓርቲያቸውን ፍላጎት ኣንሸራሽረው በህጋዊ መንገድ የራስን እድል በራስ የመወስን መብታቸውን መጠየቅ፣ ለዚህም ህዝባቸውን በሚገባ ማንቃትና ማደራጀት ደግሞ ታጋይ ድርጅቶች ከስኮትላንድ ብሄራዊ ፓርቲ (SNP) የሚቀስሙት ልምድ ይሆናል። ይህም እውን ሊሆን የሚችለው ዴሞክራሲ ያለምንም ኣምባገነናዊ ተፅእኖ በሚገባ ሲሰርፅ ብቻ ነው።
እነሆ የስኮትላንድ ሪፈረንደም ውጤት SNP እንደተመኘው ሳይሆን ቀርቶ ከዌስትሚኒስቴር መንግስት ጋር መቀጠል ሆኗል። ይህ ማለት ደግሞ ለኣፍቃሬ-ነጻነት ስኮቶችና ለመሪ ድርጅታቸው ለSNP ሽንፈት ሊባል ኣይችልም። ትልቁ ኣላማቸው ሪፈረንደሙን ማካሄድ ነበር። እናም በስኬት ኣካህደዋል። ውጤቱ ደግሞ የህዝባቸውን ፍላጎት ያንጸባረቀ ነውና ያከብሩታል። ኣብዛኛው ህዝባቸው ነጻ መንግስት ኣያስፈልገንም በእንሊዝ ኣካልነት መቀጠልን እንፈልጋለን ካለ ያንን ሊያስቀሩት እንደማይችሉ ያውቃሉ። ቢገነጠሉም ነጻነት ነበር። ባለመገንጠላቸውም ከነጻ ሃገርነት የማይተናነስ የተጨማሪ ዲቮሉሽን እድል ተጠቃሚ ሆነዋል። በዚህ ሪፈረንደም ስኮቶች የተጎናጸፉት ትልቁ ድል በሪፈረንደሙ ውጤት መሰረት ለዌስትሚንስቴር መንግስት ጠንካራ መልእክት ማስተላለፋቸው ነው። በመጠነኛ ቁጥር ተበልጦ የተሸነፈው የነጻነት ደጋፊ ህዝብ ብሄርተኝነት በጠባይ ካልተያዘ በቀር ነገም በታላቁዋ ብሪታንያ ኣንድነት ላይ ስጋት ማስከተሉ ኣይቀሬ መሆኑን የሪፈረንደሙ ውጤት ጠቁሞ ኣልፏል። እናም ውጤቱ ግራም ሆነ ቀኝ ያው ድል ነው። ከምንም በላይ ሪፈረንደሙ በስኬት ተፈጽሞ የህዝቡ ውሳኔ ተረጋግጧልና።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ኣንድ ለቆመለት ህዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የሚታገል ድርጅት ኣብላጫ ወንበር ኣግኝቶ የክልሉን መንግስት ቢቆጣጠርና የሪፈረንደም መብት ቢጠይቅ ጦርነት ነው የሚነሳው። ገና ሲጀመር እንዲህ ኣይነት ኣቅምና በህዝቡ መሃል ተሰሚነት ያለው ድርጅት በህጋዊ መንገድ ተንቀሳቅሶ የ SNP ኣይነት ሚና እንዲጫወት ኣይፈቀድለትም። በሰበብ ኣስባቡ ይጠለፍና ከጨዋታ ውጭ ይሆናል። ሰላማዊ መንገድ ይዘጋበትና ተገድዶ ብረት እንዲያነሳ ይደረጋል። ብረት ሲያነሳ ደግሞ ‘እሸባሪ’ እየተባለ ድራማ ይቀነባበርበትና በጭራቅነት ተፈርጆ በህዝቡ መሃል የመንቀሳቀስ መብቱ ጨርሶ ይዘጋበታል።
የስኮትላንድን ሪፈረንደም ሂደት ስንቃኝ እንዲህ ያለው የዴሞክራሲ እድገትና ስልጣኔ በኣገራችን ገቢራዊ ይሆናል ተብሎ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ኣይጠበቅም። ለዚህ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ቢቻልም ኣንኩዋር ኣንክዋሮቹን ብቻ እናያለን። ኣንዱና የመጀመሪያው ምክንያት በሁለቱ ማለትም በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መንግስታት ታሪካዊ ኣመሰራረትና ኣደረጃጀት መካከል የሚታየው የገዘፈ ልዩነት ነው። ስኮትላንድ ከእንግሊዝ ጋር የተሳሰረችው በስላማዊ ውል እንጂ ኣንደ ኢትዮጵያዋ ኦሮምያ በጦርነት ወረራ ተንበርክካ ኣልነበረም። ሁለተኛውና ኣሁንም ትልቁ ምክንያት እንግሊዝ በኣለም ኣቀፍ ደረጃ ያላት የበላይነትና የስልጣኔ ምጥቀት የስኮትላንዶች ልብ በእንግሊዝ ኣካልነታቸው ኣንገታቸውን እንዳይደፉ ሲያስችል ኢትዮጵያ በኣለም ላይ በሁሉም ዘርፍ ያላት ኣስቀያሚ የጭራነት ስፍራ በኢትዮጵያዊነት መጠራትን የሚያስጸይፍ ነው።
ሶስተኛውና እጅግ ትልቁን ምክንያት ኣንጥቀስ። ስኮትላንድ በእንግሊዝ ህግ መሰረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲሻሻልላቸው በቆየው Devolution በተባለውና የማእከላዊውን መንግስት ስልጣን ወደ ክልላቸው የማውረድ መብት ከሞላ ጎደል የረኩ ሲሆን በኣንጻሩ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት የዘለቀው የማእከላዊ መንግስት ፈላጭ ቆራጭነት እንደ ኦሮምያ ያሉትን ግዙፍና ከፍተኛ ኢኮኖሚ ያላቸውን ክልሎች ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። ምንም እንኩዋን ዩኬ ኣለም ላይ እንደ ኣንድ ኣገር የምትታይ ቢሆንም በውስጧ የያዘቻቸው ኢንግላንድ፣ ስኮትላንድ፣ ዌልስ እና ሰሜን ኣየርላንድ በብዙ ኣስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ራስገዝ ኣገሮች ናቸው። ኣሁን በኢትዮጵያ ተዘርግቷል በሚባለው የፌደራል ስርኣት መሰረት ‘ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳደራሉ’ ተብሏል። ነገር ግን ከቁዋንቁዋና ባህላዊ መብቶች ባለፈ እጅግ ወሳኝ የሆኑት የፖለቲካና የኢኮኖሚ መብቶች በብረት ሃይል እንደታፈኑ ናቸው። ይህ ደግሞ ከስኮትላንድ በበለጠ የኦሮሞና የሌሎች መስል ህዝቦች ልብ እንደ ኣገር ነጻ የመውጣትና ሙሉ መብታቸውን የመጎናጸፍ ፍላጎት በእጅጉ እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ነው።
የስኮትላንድን ሪፈረንደም ውጤት በመመልከት ሰሜነኞቹ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ራሳቸውን በሎንዶን መንግስት ተርታ መድበው በነጻነት መብት ጠያቂ ህዝቦች ላይ ሊሳለቁ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ ወገኖች መረዳት የነበረባቸው ሃቅ ኣለ። ስኮትላንድን ከመገንጠል ያዳነው የዳበረ ዲቮሉሽን መብት ነው። ስኮትላንዶች ቢገነጠሉም ባይገነጠሉም ሪፈረንደም በማካሄዳቸው ኣሸናፊዎች ናቸው። የእንግሊዝ መንግስትም ቢሆን ሪፈረንደሙን በጸጋ ተቀብሎ በሰለጠነ መልኩ በህገ መንግስቱ መሰረት የስኮት ህዝብ ፍላጎቱን እንዲወስን እድል በመስጠቱ ኣሸናፊ ነው። እናም በእንሊዙ የስኮትላንድ ሪፈረንደም ኣሸናፊና ተሸናፊ የሚባል ወገን የለም። እኔ የኦሮሞ ህዝብ ሪፈረንደም ተፈቅዶለት የራሱን እድል በራሱ ወስኖ ከኢትዮጵያ ጋር መኖርን ከመረጠ ለኔም ሆነ ለኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ድል ኣርጌ ነው የማየው። ድሉ ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ስልጣን ላይ ሆኖ ያን እድል ለኦሮሞ ለሚፈቅደው የፖለቲካ ሃይል ጭምርም ነው ብዬ ኣምናለሁ። ዋናው ነገር የህዝቡ ውሳኔ መለየቱ ነውና።
ሌላው እነዚህ ተሳላቂ ወገኖች መገንዝብ ያለባቸው ትልቁ ሃቅ እንግሊዝና ኢትዮጵያ ከቶ የማይገናኙ የተለያዩ ኣለም ኣገሮች መሆናቸውን ነው። ኦሮምያና ስኮትላንድም እንዲሁ። ስኮትላንዶች ሪፈረንደሙ ቀንቶኣቸው የራሳቸውን ኣገር ቢመሰርቱም ባይመሰርቱም በኦሮምያ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ እምብዛም ኣይታየኝም። ስኮትላንዶች ነጻ ኣገር ባለመመስረታቸው የኦሮሞ ህዝብ ፍትሃዊ የመብት ጥያቄ ከጀመረው ጉዞ ኣይደናቀፍም። ስኮትላንዶች ነጻ ኣገር ቢመስርቱም ለኦሮሞ ህዝብ ትግል ማበረታቻ የሚፈጠር ተኣምር ከባህር ማዶ ኣይታየኝም። ለኦሮሞና ለሌሎችም ነጻነት ጠያቂ ህዝቦች ትልቁ ድል ራሱ ሪፈረንደሙ መካሄዱ ነው። ዛሬም እነሆ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ትልቅ የፖለቲካ ችግር መፍቻ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ መሆኑ በኣለም መድረክ ላይ እየተረጋገጠ መሆኑ ነው ትልቁ ድል። ኣንዳንዶች እንደሚሳለቁት የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ጥያቄ ‘ከሶሻሊዝም ጋር ያረጀ ያፈጀ የስታሊን ፍልስፍና’ ሳይሆን ሊበራል ዴሞክራሲዎችም እየተገበሩት የሚገኝ ድንበርና ዘመን የማይገድበው በተባበሩት መንግስታት ቻርተር ውስጥም ግልፅ እውቅና የተሰጠው የፖለቲካ ችግር መፍቻ ቁልፍ መሆኑ ነው።
ተሳላቂዎችን ኣንድ ተጨማሪ ነገር ማስታወስ እሻለሁ። ገና ሲጀመር ኦሮምያ በህዝብ ብዛቷና በኢኮኖሚ ኣቅሟ የምትፎካከረው ከኢንግላንድ ጋር እንጂ ከስኮትላንድ ጋር ኣይደለም። በታላቁዋ ብሪታኒያ ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት፣ የቆዳ ስፋትና የኢኮኖሚ ኣቅም ባለቤት የሆነችው ኢንግላንድ እንደመሆኗ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥም በህዝብ ብዛት፣ በቆዳ ስፋትና በኢኮኖሚ ኣቅም የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘችው ኦሮምያ ነች። ኦሮምያና ኢንግላንድን የማያመሳስል ነገር ቢኖር ኢንግላንድ ከጥንት ጀምሮ የኢምፓየሮች ኣውራ ስትሆን ኦሮምያ ግን የኢምፓየሮች ወረራ ሰለባ መሆኗ ነው። በተጨማሪም ኢንግላንድ ዛሬም የብሪታንያ የስልጣን ኣውራ ከመሆን ኣልፋ ኣለም ኣቀፍ ጫና የማሳረፍ ኣቅም ያላት ገናናና ሃያል ግዛት ስትሆን ኦሮምያ ግን ምንም እንኩዋ ሃያል የመሆን እምቅ ኣቅም ያላት ቢሆንም ዛሬ መብቷ ተረግጦ እንደ ኣናሳ ወገን ተንቃና ኮስማና መስላ የምትታይ መሆኗ ነው።
እንዲህ ስል መሳለቅ ከሚዳዳቸው ወገኖች ኣንድ ጥያቄ ይወረወር ይሆናል። ኦሮምያ በህዝብ ብዛቷ፣ በቆዳ ስፋቷና በኢኮኖሚ ብልጽግናዋ የበላይ ከሆነች ታድያ ብዙሃን እንዴት ከኣናሳ ይገነጠላል የሚል። መልሱ ቀላል ነው። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የመገንጠል ጥያቄ ኣይደለም። ‘መገንጠል’ የሚለው ቃል በርግጥ ለኣናሳዎች እንጂ እንደ ኦሮሞ ላሉት ብዙሃኖች ኣይሰራም። የስኮትላንዶችን መሄድ መገንጠል ልንለው እንችላለን። ምክንያቱም እነሱ ትተው የሚሄዱት ኣካል ከነሱ የገዘፈ ነውና። ኦሮምያ ነጻ ብትወጣ ግን ኦሮምያን በሃይል ይዞት የነበረው ኣካል ከሷ ያነሰ በመሆኑ ኦሮምያን ‘ተገነጠለች’ ማለት የቁዋንቁዋ ኣላዋቂነትን ያመላክታል። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ትክክለኛ ትርጉም የራስን እድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ነው። ሪፈረንደም ተካህዶ ከኢትዮጵያ ጋር የመኖር ወይም ያለመኖር ምርጫን የማስተካከል ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ኦሮምያ ኣሁን ‘ኢትዮጵያ’ ከተባለችው የ130 ኣመት ኣድሜ ካላት ኢምፓየር ስር የተጠቃለለችው በህዝብ ውክልና በኢፋ ውል ተፈራርማ ኣልነበረም። በስምምነት ሳይሆን በጠመንጃ ሃይል የተመስረተ ኣገዛዝ ደግሞ ፈርሶ እንደ ኣዲስ በሰለጠነ መልኩ ውል በመዋዋል ኣብሮ የመቀጠል ወይም የመለያየት እድል መወሰን የግድ ይሆናል።
ለዚህ ስኬት ትልቁ ቁልፍ ምንድነው? የኦሮሞ ተወላጆች ባሉበት ሁሉ በሳል የፖለቲካ ንቃት መጎናጸፍ ኣንዱ ቁልፍ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ኣሁን ያለው ሁኔታ ኣጅግ ተስፋ ሰጭ ነው። ህዝባችን በፖለቲካ ጥያቄው ላይ የሚያዋጣውን ስልት ጠንቅቆ መረዳት ይገባዋል። በኢትዮጵያ ገዢዎችና በኦሮሞ ህዝብ መሃል ያለውን የእገዛሃለሁ ኣልገዛም የታሪክ ህይወት ለማጥናት የገድ የታሪክ ተማሪ መሆንን ኣይጠይቅም። ይሄ የሁላችንም ኦሮሞ ተወላጆች መሰረታዊ እውቀት ነው። መሰረታዊ እውቀታችን የሚጀምረው ከታሪክ ትምህርት መሆን ኣለበት። ታሪክ ለመላው የኦሮሞ ተማሪዎች ልክ እንደ እንግሊዝኛና ሂሳብ ኮምፓልሰሪ ሳብጀክት ሆኖ መታየት ይገባዋል። ዛሬ ስለ እስራኤል ታሪክና ማንነት የማያውቅ እስራኤላዊ የለም። ማንም ኣረብ ወይም ኣውሮፓዊ ኣንድን እስራኤላዊ ዜጋ ማታለልና ከህዝቡ ፍላጎት በተቃራኒ ማስቆም ኣይችልም። እያንዳንዱ የኦሮሞ ዜጋም የራሱን ህዝብ ታሪክና የፖለቲካ ህይወት ጠንቅቆ በመረዳት በጠላት ፕሮፓጋንዳ በቀላሉ ከመታለል መዳን ይኖርበታል።
ከዚህ በተቃራኒ የቆሙት የመብት ጥያቄያችን ጠላቶች ካሁን በሁዋላ የኦሮሞን ህዝብ ብሄርተኝነት ወደ ሁዋላ ማስመለስ ከቶ እንደማይቻል ተረድተው በጊዜ ቢደራደሩ ይጠቅማቸዋል። ዛሬም በነቀዘው የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኣስተሳሰብ ታውረው መቀጠል ካማራቸውም ይቀጥሉት። የማታ ማታ ድሉ የፍትሃዊ ትግል ባለቤቶች መሆኑ ኣሙን ነው። ግመሎች ይሄዳሉ ውሾቹም ይጮሃሉ እንደሚሉት የኣረቦች ብሂል እኛ ጉዞኣችንን ቀጥለናል። እነሱም ይጩሁ።
ቦሩ በራቃ: Gulummaa75@gmail.com

No comments:

Post a Comment