Pages

ቴዲ አፍሮ ለምን ከሙት ገናዥነት አይወጣም?

October 01, 2014 | በብርቱካን ወለቃ*

አብዛኛዎቻችን ቴዲ አፍሮን (ቴዎድሮስ ካሳሁን) የምናውቀው በመረዋ ድምፁና በሚያዜማቸው ‹መሳጭ መሳይ› ግጥሞቹ ነው፡፡
አንድ ግለሰብ ስለሚያስበውም ሆነ በተለያየ መንገዶች ስለሚሰነዝራቸው አስተያየቶች ማንንም የማማከር ግዴታ የለበትም፡፡ ነገር ግን በዘፈንም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶችና አስተሳሰቦች ዕውነትን መሠረት ያደረጉና በሌሎች ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት ይኖራቸዋል ብሎ ደጋግሞ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ 
እርግጥ ነው ቴዲ የሚለቃቸው ዘፈኖች ሊያስገኙ የሚችሉትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን በደንብ አስልቶ እንደሚያቀነቀንና የት ቦታ በምን ጊዜ ቢቀነቀኑ የበለጠ ገንዘብና ተቀባይነት ሊያመጡ ይችላሉ በሚል ስሜት እንደሚሠሩ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን በሆላንድ (አምስተርዳም) ባዘጋጀው የዘፈን ኮንሰርት ያቀነቀነው ዘፈን ግጥሞች ይዘት ነው፡፡ ግጥሞቹን እንመልከት፡፡

ቀስተ-ደመናው ላይ አንበሳው ከሌለ፣
የኢትዮጵያ ባንዲራ ትርጉሙ የታለ? ይለናል አርቲስቱ፡፡ 
ቁም ነገሩ ግጥም መግጠም ወይም የተሰጠውን ግጥም ማቀንቀን አይደለም፡፡ የግጥሙ መልዕክትና ትርጉም ምን ማለት ነው? የሚለው ነው በአፅንኦት መታየት ያለበት፡፡  የኢትዮጵያን ታሪክ በቅጡ የማያውቁና ተረት ተረትን እውነተኛ የሕዝብና የአገር ታሪክ አድርገው ከሚዘክሩ ግለሰቦች በመቀበል ያን እውነት አድርጎ መውሰድ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ዘፋኙ ወደ አቀነቀነው ግጥም ስንኝ እንመለስና በውስጡ የያዘውን መልዕክት እንመልከት፡፡
አንበሳው የተጫነበት የኢትዮጵያ ባንዲራ ትርጉሙ ምንድነው?
ለቴዲ አፍሮና ለመሰሎቹ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የዘር ሐረጋቸው ራሳቸውን ‹የዓለም ምርጥ› አድርገው ከሚጠሩ የእስራኤል ወገን አድርገው የሚቆጥሩ፣ ከዚህ የዘር ሐረግ ያልተገኘ ሰው በንጉሡ ምሕረት በኢትዮጵያ ምድር መኖር ቢችልም ቅሉ ኢትዮጰያን የማስተዳደር (የመምራት) መብት እንደሌለው በግልጽ በሕገ መንግሥቱ (በአፄ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት) ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም ራሱን ከአፈ ታሪኩ ሰሎሞናዊ የዘር ሀረግ መምዘዝ ያልቻለ ሰው ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ ይቆጠራል፡፡ የአንበሳው መልዕክት ባጭሩ (ሞዓ አንበሳ ዘዕምነ ነገደ ይሁዳ) ማለት ነው፡፡ ይህ አባባል ባጭሩ የሚነግረን ኢትዮጵዊነትና ሥልጣን በኢትዮጵያ የሚገኘው የሰሎሞናዊ ሥረወ መንግሥት ዘር በመሆን ሲሆን፣ ይህም ዘር እግዚአብሔርን ወክሎ ያለምንም ሃይ ባይነት ፍፁማዊ በሆነ መንገድ የተቀረውን ሕዝብ የመግዛት (የማስተዳደር) ሥልጣን ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ሕዝቡም መሬቱም  የንጉሡ ማለት ነው፡፡ ሌሎች ሕዝቦች ይህን አምነው መገዛቱንም ያለምንም ማንገራገር ሲቀበሉ በኢትዮጵያ ምድር የመኖር መብት ይኖራቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን በተወለዱበትና እትብታቸው በተቀበረበት ምድር ተገደው እንዲፈልሱ ይደረጋል፡፡ ይህን በተጨባጭ ለማስረገጥ ያህል ‹‹በአማካይ ለ300 ዓመታት ያህል በአገዎች ተይዞ የነበረው ሥልጣን በ1270ዎቹ ወደ ትክክለኛ የሥልጣን ባለቤት ወደሆነው ወደ ሰሎሞናዊው ዘር በሰላማዊ መንገድ ተሸጋገረ፤›› ይላሉ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ የታሪክ መጻሕፍት፡፡ 
ሌላው ቴዲ አፍሮ ያንጎራጎረለትና እንዲሆን የተመኘው ባንዲራ አንበሳው በኩራት የጨበጠውን መስቀል ዘሎታል እንጂ የመስቀሉ ትርጉም በአጭሩ ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት፡፡ የተለየ ዕምነት የሚከተሉ ማለትም እስልምናም ኦሪትም ፕሮቴስታንትም ወይም የባህላዊ ዕምነት ተከታዮች ኢትዮጵያዊ አይደሉም›› እንደማለት ነው፡፡ ቢኖሩ እንኳ የሚጠሩት ኢትዮጵያዊ ተብለው ሳይሆን በበኢትዮጵያ የሚገኙ ሞስሊሞች፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኦሪት ወይም ደግሞ የሌላ ዕምነት ተከታዮች በመባል ነበር፡፡
ታዲያ ቴዲ አፍሮ በሆላንድ ምድር ያዘጋጀው ሙዚቃ ኮንሰርት ግጥም
ቀስተ-ደመናው ላይ አንበሳው ከሌለ፣
የኢትዮጵያ ባንዲራ ትርጉሙ የታለ? ይላል፡፡
ያን ያለፈ የግፍ ሥርዓት ለመመለስ የተቀነቀነ ላለመሆኑ በምን ማረጋገጥ ይቻል ይሆን? እርግጥ ነው ይህ ኮንሰርት አምስተርዳም (ውጭ አገር) ያደረገበት ዋና ምክንያት የተሻለ ገንዘብ ለመቃረም ይሁን እንጂ፣ አሁን በኢትዮጵያ በመተግበር ላይ ያለው የፌደራል ሥርዓት የግል ጥቅማቸውን ያጎደለባቸው መስሎ የሚሰማቸው የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች የተሰባሰቡበት፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል መብት መረጋገጥ የሚያቅለሸልሻቸው መጠራቀሚያ ቦታ መሆኑን ማወቁ አቀንቃኙ ጥሩ የገበያ ባለሙያ አማካሪ እንዳለው ያሳያል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ‹አንበሳው› ላይመለስ ሞቶ ተቀብሯል፡፡ ሙትን መገነዝና ጊዜ እየጠበቁ በተለያየ መንገድ መዘከር ይቻል እንደሆን እንጂ፣ ሕይወት መዝራትና ማዳን ፍፁም አይቻልም፡፡ በዚህ የሞተ አንበሳ ስም ኢትዮጵያዊያን መከራና ሥቃይ አሳልፈዋል፡፡ በአገራቸው የባዕዳነት ስሜት እየተሰማቸው ኖረዋል፡፡ 
ቴዲ አፍሮ በመቀጠል በኢትዮጵያ ለዘመናት በውሸት ተረት ተረት ሲነገር የነበረን ‹‹የሰሎሞናዊ›› የዘር ሐረግን እውነት አድርጎ በመቀበል ዛሬም ኢትዮጵያዊያን የነሉሲ (ድንቅነሽ) የደምና የአጥንት ክፋይ መሆናቸውን በመካድ፣ ራሳቸውን ‹ምርጥ ዘር› ከሚሉት የእስራኤል ወገን ናቸው ብሎ ለማምታት እንዲህ ብሎ አቅንቅኗል፤
‹‹ሳባና ሰሎሞን እናትና አባቴ፣
አትማልዷትም ወይ ለኢትዮጵያ እናቴ፡፡››
እርግጥ ነው የዘፋኙ መሳሳት መነሻው ከእርሱ የሚጀምር ሳይሆን ያለፉት ገዥዎቻችን ‹‹እኛ ጥቁር ሳንሆን ከሰሎሞን ዘር ሲወርድ ሲዋረድ የተገኘን የ‹ሴም› ዝርያ ያለን ነን ብለው ራሳቸውንና ኢትዮጵያዊያንን በማንነት ቀውስ ከዘፈቁበት ጊዜ ይጀምራል፡፡ ምናልባት ቴዲ ልብ ያላለው ጉዳይ የዚያ ዘመንና የአሁኑ ዘመን ትውልድ የአስተሳሰብና የዕውቀት ደረጃ   ተመሳሳይ አለመሆኑን ነው፡፡ የዚያ ዘመን የታሪክ ምንጭ ብቸኛው መጽሐፍ ክብረ-ነገሥት የሚሉት በአራት የተለያዩ ቋንቋዎች ከአንደኛው ወደ ሌላኛው በቅብብሎሽ እየተተረጎመ የግለሰቦችን የግል ስሜት አጭቆ ወደ አገራችን የገባ ተረት ተረት ነው፡፡
 ልብ በሉ ይህ ክብረ መንግሥት የተባለው ተረት ተረት መጽሐፍ ከኢትዮጵያዊያን ይልቅ የእስራኤልን ሕዝብ ታላቅነት የሚያደንቅ፣ ኢትዮጵያ አገራችንን ሳይሆን በመካከለኛው ምሥራቅ የምትገኘውን እስራኤል ‹የተስፋይቱ ምድር› እንድንል፣ ንፁሁን ኢትዮጵያዊ (ኩሽ ሕዝብ) የሴም ወገን አድርጎ የሚያቀርብና ከቀደምት ገዥዎቻችን እስከ ተራው ሕዝብ ድረስ በማንነት ቀውስ ውስጥ እንዲዘፈቅ ያደረገ የክህደት ዲሪቶ ነው፡፡ ይህ በሰሎሞንና በሳባ መካከል ተደረገ የሚባለው ተረት ተረት ግንኙነት እውነት ቢሆን እንኳ፣ በአገራችን ባህል በሕጋዊ ጋብቻ ያልተወለደ ልጅ ‹ዲቃላ› እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ ይቅርታ! ለቃሉ አጠቃቀም፡፡ የእኛ ገዢዎችና የእነሱ አቀንቃኝ ሕዝቦች ግን ዲቃልነታቸውን በኩራት ተቀብለው ይተርኩታል፣ ያዜሙታልም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጭምር አሁንም ይሰበካል፡፡ ለማንኛውም እኔ የኩሽ ኢትዮጵያዊ ዘር በመሆኔ አንድም ቀን ‹‹የሰሎሞን ዲቃላ ነኝ›› ብዬ ስለማላውቅ በእነዚህ ሰዎች አፍርባቸዋለሁ፡፡ ግን እኮ ሰሎሞን የተባለው የእስራኤል ንጉሥ ግንኙነት ፈጸመ የሚባለው ከንግሥቷ ብቻ ጋር ሳይሆን ‹የንግሥቲቱን› ደንገጡርም ደፍሮ (Rape)  ወንድ ልጅ አስወልዷል ነው የሚባለው፡፡  ክብርና ንግሥና በእስራኤሉ ንጉሥ በኩል የሚገኝ ከሆነ ከደንገጡሯ ተወለደ ተብሎ የሚተርክለትና የእሱ የዘር ሐረግ የሆኑት ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ‹‹የቀዳማዊ ምንሊክን›› ያህል ክብር ያልተቸራቸው ለምን ይሆን? እንዲያውም የሁለቱ ዘሮች የተለያዩ ባላንጣ ሕዝቦች ተደርገው ለዘመናት በጦርነትና በጥላቻ አዙሪት ውስጥ እንደኖሩ ይተረካል፡፡ እባካችሁ የምታውቁ አስረዱኝ! ቀዳማዊ ምንሊክ በየትኛው ዘመን፣ የት ቦታ የነገሠና የገዛ ንጉሥ ነው? ይቅርታ! ከዋናው ነገረ ሐሳቤ ወጣሁ፡፡
የቴዲ አፍሮ ‹አትማልዷትም ወይ› መሠረታዊ ምክንያቱ ኢትዮጵያ ከተረት ተረቱ የሰሎሞን ወገን ያልሆነ ሕዝብ በኢትዮጵያ ምድር እኩል በዚህ ሥርዓት መታየት መጀመሩ ‹ኢትዮጵያን አፈራረሳት› ከሚል አጉል ማላዘንና ያን ሙት ሥርዓት ለመመለስ ከማሰብ  የመነጨ  ለመሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ ቴዲ አፍሮ በነካ አፉ ማቀንቀን የነበረበት ‹‹እኛ የምርጦች ዘር ስለሆን ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ምድር መኖር አትችሉም›› ተብሎ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊያነሳ ይገባው ነበር፡፡ የአገው ሕዝቦቸ አካል የሆኑት ገዥዎች ባወጡላቸው አጠራር ‹ፈላሻዎች› ዓለም ያልሰማው የዘር ማጥፋት ወንጀል ‹በሰለሞናዊ› ተብየው መንግሥት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ አቀንቃኙ ማወቅና ማሳወቅ የነበረበት ዓለም የማያውቀውን ይህን የዘር ማጥፋት ወንጀል ነበር፡፡ 
ኢትዮጵያ በዘረኝነት ስትታመስ የነበረችው በሰሎሞናዊ ሥርዓት እንጂ ዛሬ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እኩል መብት በተሰጣቸው በአሁኒቱ ኢትዮጵያ አይደለም፡፡ ምናልባት እነዚህ ራሳቸውን ‹የምርጦች ወገን› ነን ብለው የመደቡ በአገር ቤትና በውጭ አገር የሚኖሩ ሰዎች የሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል መብት መጎናፀፍ ለቴዲ አፍሮና ደጋፊዎቹ ኢትዮጵያን በዘር ማተራመስ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ አለ እንኳ ብለን ብንነሳ ምንጩ  ራሳቸውና ራሳቸው ብቻ ለመሆናቸው መገመት አያዳግትም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በዘር ተከፋፈለች፣ በጎጥ ተዋቀረች›› የሚሉት እነዚህ ራሳቸውን የውሸት ስም ሰጥተው እኛ ከዳር እስከ ዳር ያልገዛናት ኢትዮጵያ እንደተከፋፈለችና እንደተቆራረጠች ይቆጠራል ከሚል አጉል ቅዠት የሚመነጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ያለስማቸው ስም፣ ያለ ምግባራቸው አጉል ምግባር፣ ያለዕምነታቸው አጉል ዕምነት የተለጠፈባቸው በማን ሥርዓት እንደሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቴዲ አፍሮንና መሰሎቹን ጨምሮ በግልጽ ያውቁታል፡፡
ቴዲ አፍሮን የተጣባው ሌላው ተውሳክ ዘፈን መዝፈን ከጀመረ አንስቶ እስካሁን የሚያቀነቅው ራሱን ብቸኛ ‹የሐሳዊው ሰሎሞን› ወራሽ ብሎ ለሰየመው አንድ መንደር ብቻ ለተገኙ መሪዎች መሆኑ፣ ይህ ግለሰብ በዘረኝነትና በጠባብነት ልክፍት የተለከፈ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ጥቁር ሰው፣ ኃይሌ ኃይሌና ሌሎቹን ዘፈኖች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሰዎች በፊት እንደ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ፣ አሉላ አባ ነጋንና ሌሎች  ጀግኖች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሲታገሉ መስዋዕት ሆነዋል፡፡ የእነዚህን ታላቅ መሪዎች ተጋድሎና ምግባር የሚያወድስ አንዲትም ስንኝ አልተቃኘም፡፡ በእርግጥ የፈለገውን ማወደስ የማይፈልገውን መተው ግላዊ መብቱ ነው፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ መሪዎች ብቻ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት የታገሉ አስመስሎ መደስኮር ምክንያቱ በጣም ግልጽ ነው፡፡ ስለቴዎድሮስ፣ ስለዮሐንስ ወይም ስለሌሎች ጀግኖች ግጥም ተደረደረ አልተደረደረ ስለጀግንነታቸው ከኢትዮጵያ አልፎ  በዓለም ሕዝብ ዘንድ ሲመሰከር ይኖራል፡፡
 ሰሞኑም አምስተርዳም ላይ ዘረኝነትን አወገዝኩ ብሎ ባዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት ሌላ ዘረኝነትን እንዲህ በማለት አቅንቅኗል፡፡
‹‹ምን ይላል ምኒልክ ምን ይላል ቴዎድሮስ፣
የአንድነቱ ጎጆ በዘር ሲታመስ፣
ምን ይላል ምኒሊክ ካሳ ቴዎድሮስ፣ 
ምን ይላል ዮሐንስ ተፈሪ ቴዎድሮስ፣
የተዋለደ ሰው በዘር ሲታመስ፤››
ይህ ግጥም በእውነቱ ምን መልዕክት ለማስተላለፍ የተደረደረ ነው? በኢትዮጵያ ያሉ ሕዝቦችን በሙሉ ዕውቅና ሰጥቶ በእኩል መብት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር እንዲኖሩ ማድረግ ዘረኝነቱ ምን ላይ ይሆን? ዘርኝነት ማለት የተለያየ ቋንቋ፣ ባህልና ወግ ያላቸውን ሕዝቦች በአንድ የዘር ከረጢት ቋጥሮ ማንነታቸውንና የግል መጠረያ የሆነውን ስማቸውን መቀየር? ወይስ ተፈጥሯዊ መብታቸውን ማረጋገጥ? በእውኑ ይህ የፌደራል ሥርዓት ኢትዮጵያዊያን በዘር ተቧድነው እርስ በርስ እንዲፋጁና እንዲታመሱ በአዋጅ ደንግጓል? የሁሉም ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት መኖርና የውስጥ የራስ አስተዳደር መመሥረት መከፋፈል የሚሆነው በቴዲ አፍሮና መሰሎቹ ጭንቅላት ካልሆነ በስተቀር በግልጽ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ የመከፋፈል አንቀጽ አለ? የግል ስሜት የተጫጫናቸው ቡድኖችና ግለሰቦች ሥርዓቱን አዛብቶ በመተርጎምና የግል ጥቅማቸውን ለማራመድ ሥርዓቱን የጥላቻ ምንጭ አድርገው ተጠቅመውበት ሊሆን ይችላል፡፡ ሕዝቦች በሌሎች ክልል ተዘዋውረው የመኖርና ሀብት የማፍራት መብታቸውን ነፍገውና ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ካስቀመጠው በተቃራኒ እየሄዱ ሊሆን ይችላል፡፡ 
የፌደራል ሥርዓቱ ግን ኦሮሞው ወደ አማራ፣ አማራው ወደ ትግሬው፣ አፋሩ ወደ ሶማሌ፣ ሶማሌው ወደ ደቡብ ወይም ወደ ሌላ አካባቢ አንዳይዛወር አልደነገገም፡፡ ይህ የሚያሳየው ችግሩ ያለው ከሥርዓቱ ሳይሆን ከተወሰኑ ግለሰቦች የተንሸዋረረ የጠባብነትና የትምህክት አስተሳሰብ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ የግድ ይላል፡፡ አንድ ብሔር ከሚኖርበት ክልል ወደ ሌላው ክልል ስፖርት ለወዳጅነት የሚል መርህ አንግቦ ለመጫወት በሄደበት ከተማ በዘሩ ተሰድቦ የሚመለስ ከሆነና ሌላውም አፀፋውን ‹ዓይን ላጠፋ ዓይን› የሚል የኦሪት ዘመን ሕግን የሚከተልና በዚያ መንገድ የሚያስተናግድ ከሆነ፣ ችግሩ ከሥርዓቱ ሳይሆን ከአንዳንድ ጽንፈኛና ዘረኛ ግለሰቦች የሚመነጭ ነው፡፡ መቼም መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ‹‹ወደ ክልላችሁ የሚመጡ የሌላ ብሔረሰቦችን በዘራቸው ስደቧቸው ወይም ድንጋይ ወርውሩባቸው›› የሚል ሕግ ያስቀመጠ አይመስለኝም፡፡ 
ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ሥርዓቱ ለምን በጭፍን ጥላቻ ይወገዛል? ወይስ ደግሞ ‹‹እኛ ያልጋገርነው እንጀራ እኛ ያልወጠወጥነው ወጥ ይበላሻል›› ከሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ የሚመነጭ? ኢሕአዴግ እየተከሰሰ ያለው በሕዝቦች መካከል ለዘመናት ሰፍኖ የነበረው የተዛባ ግንኙነት አለማስቀጠሉ ከሆነ፣ ከብሔራዊ ጭቆና ለመውጣት የተካሄደው ረዥምና መራራ ትግል ያን ለማስቀጠል አልነበረምና ተሳስቶ እንኳ ይህን ላድርግ ቢል፣ በሕዝባዊ ማዕበል ከመንበረ ሥልጣኑ በአንድ ቀን ጀንበር እንደሚወገድ ጥርጥር የለውም፡፡ ሊታወቅ የሚገባው ዓብይ ጉዳይ ኢሕአዴግ እንደ መንግሥት ቀጠለም አልቀጠለም የፌደራሉን ሥርዓት ሊቀለብስ የሚችል አንድም ኃይል ከአሁን በኋላ ሊመጣ አይችልም፡፡ ይህ ሥርዓት የኢሕአዴግ ሳይሆን የሕዝቡ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ይህን ሥርዓት ለሕዝቦች ልዕልና የሚጨነቁ ዜጎች ሁሉ የፖለቲካ አባልነት  ካርድ ተሸከሙ አልተሸከሙ ይቆረቆሩለታል፡፡
እርግጠኛ ነኝ ቴዲ አፍሮ የተገኘበትን ብሔረሰብ ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ኢሕአዴግ ወደ መንበረ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የተፈበረኩ የኢንዱስትሪ ምርቶች ሳይሆኑ፣ ድሮም በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ይኖሩ የነበሩና ዛሬም የሚኖሩ ለወደፊትም የሚኖሩ ሕዝቦች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ኖረም አልኖረም የሕዝቦች የአኗኗርና የመብት ጉዳይ  ይለያይ ካልሆነ በስተቀር ከመኖር የሚገታቸው አንድም ነገር የለም፡፡ ልዩነቱ በሰሎሞናዊ ዘመን እነዚህ ሕዝቦች በእኩል መብት የሚኖሩ ሳይሆኑ በንጉሡ ምሕረት ብቻ የሚገዙ ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን ሁሉም አንድ ዓይነት መብት አግኝተዋል፡፡ ይህ ከሆነ የቴዲ አፍሮ ችግር የሚያጠነጥነው ሙትን አሳምሮ ከመገነዝ ያለፈ ኢትዮጵያዊያንን አብሮ በሰላም የሚያስቀጥል አይመስለኝም፡፡ የአንበሳ ምሥል የተጫነበት ባንዲራም ከሥርዓቱ ጋር አብሮ ተቀብሯል፡፡ 
ሙት ገናዦች ሙትን ያሸሞነሙኑትና ያሳምሩት ካልሆነ በስተቀር ነፍስ ሊዘሩለት ከቶም አይችሉም፡፡ ቴዲ አፍሮና መሰሎቹ ከሙት ገናዥነታችሁ ወጥታችሁ አዲሲቷን ኢትዮጵያ እንዴት በጋራ መገንባት እንዳለብን በጋራ ብንሠራ፣ ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ ይህ ቴዲ አፍሮ  ሁሉም ሰው ለህሊና መገዛት እንዳለበት ሲመክረን፣
‹አስገምቼ ራሴን፣ አልሞላውም ኪሴን› የሚል የዘፈን ስንኝ በአንድ ወቅት አቀንቅኖ  ነበር፡፡ እውን ዘፋኙና ድርጊቱ ምን ያህል የተጣጣሙ ናቸው? ሁላችንንም ከሙት ገናዥነት አውጥቶ የራሳችን ታሪክ ሠሪ እንድንሆን ፈጣሪ ይርዳን! አሜን፡፡ 
* ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው birtukanwoleka@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡

No comments:

Post a Comment