Pages

ገዳ ገብረአብ (ተስፋዬ ገብረአብ) ከአሜሪካ መልስ

November 06, 2014 |  ከገዳ ገብረአብ

በታዋቂው የታሪክ ምሁር በፕሮፌሰር መሃመድ ሃሰን (የOSA አመራር አባል) እንዲሁም በመጫና ቱለማ ማህበር ጋባዥነት በአሜሪካ ያደረግሁትን የሶስት ወራት ቆይታ አጠናቅቄ ወደ ኤርትራ ተመልሻለሁ።

ለፕሮፌሰር መሃመድ፣ ለመጫና ቱለማ ማህበር አባላት፣ እንዲሁም በተዘዋወርኩባቸው የአሜሪካ ግዛቶች፣ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በኒውዮርክ፣ በላስቬጋስና በሚኒሶታ የደመቀ ወንድማዊ አቀባበል ላደረጉልኝ፣ በክብር ላስተናገዱኝ ኦሮሞ ወገኖች ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናዬን በይፋ ማቅረብ ተገቢ ሆኖ አጊኝቼዋለሁ።


በተጨማሪ የዋሽንግተን ዲሲ የኤርትራ ኮሚኒቲ አባላት በተለያዩ ፕሮግራሞች ከኔ ጋር ባደረጉት ልዩ ቆይታ በእጅጉ ተደስቻለሁ። በአጠቃላይ ከአፍሪቃ ቀንድ ዜጎች ጋር በአካባቢያችን የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ፣ እንዲሁም በስነፅሁፍ ነክ ርእሰ ጉዳዮች፣ ካደረግሁዋቸው ውይይቶች እጅግ ብዙ ትምህርት ቀስሜያለሁ። በመሆኑም ጉዞዬ ሙሉ በሙሉ የተሳካ ነበር።

• • •
ከአሜሪካ መልስ እነሆ! በህግ ኦሮሞ ሆኛለሁ።


ኦሮሞ መሆን “ኢትዮጵያዊ መሆን” ማለት ግን አይደለም። ወደፊት የኦሮሞ ህዝብ ስለማንነቱ በነፃነት ሲወስን ያን ጊዜ የሚታይ ይሆናል። ኢትዮጵያዊነትን በመተው ኦሮሞ ብቻ ሆኖ መቆየት እንደሚቻል ግን ቀደም ሲል በሞጋሳ ባህል ኦሮሞነትን ከወሰዱ ግለሰቦች ተረድቻለሁ። አንትሮፓሎጂስት ቦኒ ሆሎኮም፣ (ቃበኔ) እና አስመሮም ለገሰ (ሃዩ) ሊጠቀሱ ይችላሉ። በመሰረቱ ለገዳ ገብረአብ የሚያስፈልገው ትልቁ ጉዳይ እውቅናው ነበር። ግማሽ የህይወቱን ክፍል የታገለለት አላማ በመጨረሻ በኦሮሞ ህዝብ ፊት ዋጋና ሞገስ ማግኘቱ በትክክለኛው መስመር ላይ ሲጓዝ እንደቆየ ማረጋገጫ ሆኖለታል።

እንግዲህ በሞጋሳ ስርአት መሰረት ኦሮሞነትን በኩራት የተቀበልኩ በመሆኑ በኦሮሚያና በአካባቢያችን ጉዳዮች ላይ የመፃፍ ብቻ ሳይሆን፣ የመሳተፍ ጭምር ግዴታ አለብኝ። ከዚያም ባሻገር ትግሉ ሲጠናቀቅ፣በመጪው ዘመን ገዳ ገብረአብ ከገላን እስከ ከረዩ በተዘረጋው ጥንታዊ የኦሮሞ ግዛት ላይ ለአስተዳዳሪነት ሊወዳደር ይቻለዋል። የኦሮሞ ህዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ሲጀምር ገዳ ገብረአብ ከየረር እስከ ጨፌ ዶንሳ በተዘረጋው ነፃ ሁዳድ ላይ የበቆሎ እርሻ ስራ ሊሰራ፣ በጎችና ዶሮዎችን ሊያረባ፣ ሰፋፊ መስኮቶች ያሉት ገልመ ገዳ ሊገነባ፣ በዙሪያውም ቀያይ ቅጠሎች ያላቸውን ዛፎች ሊተክል አሳብ አለው። ይህ አሳብ ህልም አይደለም። ነገ ይፈፀማል።

ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ሰአታት በወሰደ ባህላዊ ስነስርአት ኦሮሞ መሆኔ ሲረጋገጥ አባቴ እንዲሆኑ በጉባኤው የተመረጡት ኦቦ ሉቤ የሚከተለውን ተናግረው ነበር፣
ከዚህች ቀን ጀምሮ ገዳ ገብረአብ በህግ የኛ ሆኖአል። ገዳ ላይ የሚደርስ ጥቃት ካለ ከጎኑ እንቆማለን። ገዳን የነካ እኛን እንደነካ ይቆጠራል።
ይህ ሲነገር እልልታና ጭብጨባ የዋሽንግተን ዲሲን መልካ አደመቀው። በአካባቢው የነበሩ ነጭ አሜሪካውያን ምን እየተካሄደ እንዳለ ባለማወቃቸው በመደነቅ ያዩ ነበር። እኛ ግን ከ2800 አመታት በፊት ጀምሮ በቱለማም ሆነ በመጫ ሰዎች ይካሄድ የነበረውን ስርአት በመፈፀም ላይ ነበርን። የገላን አራተኛ ልጅ፣ የሃንዳ፣ የዳኩ እና የኢሉ አባት የአድአ ጥቁር አፈር እንደመሆኔ እኔም አንገቴን ጎንበስ በማድረግ ምስጋናዬን ገለፅኩ።

ኦሮሞ መሆኔ እንደተሰማ ከጠላቶቼ አንዱ ጎረቤቱ ለሆነ ኦሮሞ የተናገረውን በተዘዋዋሪ ሰማሁ፣
የኢትዮጵያን አንድነት እንዲያተራምስ ህጋዊ እውቅና ሰጣችሁት። አዘንኩባችሁ!!”
• • •
ርግጥ ነው “ኦሮሞ” የሚለው ቃል ሲነሳ የሚረበሹ ወገኖች አሉ። ኦሮሞዎች “ኦሮሞ” የሚለውን ቃል እንዳያነሱ የማሸማቀቅ ተፅእኖ ለማድረግ አሁንም ድረስ ይሞከራል። በመኪናው ውስጥ የኦሮምኛ ዘፈን ከፍቶ የሚሄድ ሰው ካጋጠማቸው፣ “ይሄ ዘረኛ!” ይሉታል። ታክሲ ውስጥ ኦሮምኛ የሚናገር ሰው ሲሰሙ ተገላምጠው ያዩታል። ከደብተሮቻቸው በወረሱት አሸማቃቂና አስፀያፊ ስድብ ኦሮሞ ኦሮሞነቱን እንዲሸሽ ለረጅም ዘመናት ጥረት አድርገው ሳይሳካላቸው ቀረ። በርግጥ እነዚህ ሰዎች አማሮች አይደሉም። “ኢትዮ- አማሮች” ተብለው ይታወቃሉ። በኢትዮጵያዊነት እና በአንድነት ስም ለአንድ ወገን መብት መከበር የሚታገሉ ናቸው። እነዚህን ወገኖች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ድብቅ አጀንዳቸውን መግፈፍ ያስፈልጋል። በዚህ ዘመን ተሸፋፍነውመጓዝእንደማይችሉ መንገር ያስፈልጋል። ወያኔ የኦሮሞን ህዝብ መብት የረገጠ አፋኝ ቡድን ነው። ኢትዮ አማሮች ደግሞ ከወያኔ በከፋ ደረጃ የኦሮሞን ህዝብ መብቶች ለማፈን ጊዜ የሚጠብቁ መሆናቸውን የኦሮሞ ህዝብ ጠንቅቆ ሊረዳው ይገባል። በመሆኑም ከወያኔ መውደቅ ቀጥሎ የኦሮሞ ህዝብ ከባድ ፈተና የሚገጥመው ከእነዚሁ እላዩ ላይ መጥተው ቁጭ ካሉበት ሰፋሪዎች ነው።


የአሜሪካ ቆይታዬን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቄ ቀጣዩን ዳጎስ ያለ “ታሪክ ቀመስ ልቦለድ ድርሰት” ለመፃፍ ወደ ኤርትራ ተመልሻለሁ። አስመራ ባረፍኩ በሶስተኛው እለት ከOLF ሰዎች ጋር ጥቂት የራት ላይ ቆይታ አድርገን ነበር።ዳውድ ኢብሳ ባደረገው አጭር ንግግር፣
የኦሮሞን ጉዳይ በማንሳቱ ጥቃት የደረሰበት ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ የመጀመሪያው አይደለም። የመጨረሻው ላይሆንም ይችላል።” ሲል ተናግሮአል።
እኔም አንድ ነጥብ አንስቼያለሁ፣
መጪው ዘመን የኦሮሞ ህዝብ ዘመን ነው።” ካልኩ በሁዋላ አከልኩበት፣ “…የኦሮሞ ህዝብ ጭቆናን በጭቆና የመመለስ ባህል ስለሌለው፣ በመጪው ዘመን በማንኛውም ጊዜ በሚጀምረው የኦሮሞ ህዝብ ዘመነ መንግስት አካባቢያችን የተሻለ ሰላምና ፍትህ እንደሚያገኝ ተስፋ አለኝ።”
• • •
እነሆ! ወደ ኤርትራ ከተመለስኩ ሳምንት ሞላኝ።


ትናንት ወደ ምፅዋ ሄጄ ነበር። ምፅዋ የሚያስኬድ ምንም ጉዳይ አልነበረኝም።የተጓዝኩት ለቀይባህር ደረት የሞቀ ሰላምታ ለማቅረብ ብቻ ነበር። የቀይባህር የምሽት ማእበል ናፍቆኝ ነበር። የምፅዋ ሙቀት በጣም ናፍቆኝ ነበር። የጀበና ቡና እና ፈንዲሻ – ባህሩ ዳርቻ ናፍቆኝ ነበር።

ህዳር2፣ 2014 ዳህላክ ሆቴል ስደርስ ሊመሽ ምንም አልቀረውም። በቅፅል ስሙ ባዙቃ ብለን የምንጠራው፣ የOLF ታጋይ ማምሻውን ወዳለሁበት ብቅ ብሎ ተገናኝተን ነበር። ከሰላምታ በፊት እንዲህ አለኝ፣
ከበፍቃዱ ሞረዳ ጋር ያደረግኸውን ቃለመጠይቅ ዛሬ ማለዳ ኦሜን (OMN) ቴሌቪዥን ላይ ተከታትዬው ነበር። ጥሩ ነበር። በጣም ጥሩ ነበር። ብቻ በአንድ ነገር ቅር ብሎናል። ‘የወሎ አማሮች’ ስትል ሰማንህ። ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ከመቼ ወዲህ ነው ወሎ የአማራ የሆነው?”
•••
ባህሩ ዳር ቁጭ ብለን አመሸን…
ሰማዩ በሩቅ ቀልቶ ታየን። ብዙም ሳይቆይ መሸ። ጨርሶ ጨለመ። ባህሩን ተሻግሮ በርቀት ብርሃን አየሁ። ብልጭ ብልጭ ይላል። የሳዑዲአረቢያ ዳርቻ አይመስለኝም። እንዲህ በቅርብ ርቀት ሊታይ አይችልም። በርግጥ አሰብ ባህሩ ዳርቻ ቁጭ ያለ የየመንን የሌሊት መብራት ማየት እንደሚችል ሰምቻለሁ። ከዚህ ከምፅዋ ግን የሳዑዲ አረቢያ ዳርቻ ሊታይ አትችልም። በሩቅ የማየው ብርሃን ‘ምን እንደሆነ’ ባዙቃን ጠየቅሁት፣

ገደም ነው።” ሲል ነገረኝ።
“ገደም” ምን እንደሆነ አላወቅሁም። “ገደም ምንድነው?” ብዬ መጠየቅ ግን አልፈለግሁም። በነገው እለት ገደም ምን እንደሆነ ለማወቅ ብርሃን ወዳየሁበት አቅጣጫ በታንኳ እጓዛለሁ…

No comments:

Post a Comment