Pages

ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማሪያም እና የሀይሌ ፊዳ ሞት -

December 11, 2014 | አፈንዲ ሙተቂ

ዶ/ር ሃይሌ ፊዳ በፎቶግራፉ ላይ የምትመለከቱት ነው፡፡ ፎቶውን የሰጡን አንጋፋው ደራሲ አበራ ለማ ናቸው፡፡ ጋሼ አበራን እያመሰገንን በሃይሌ ፊዳ አሟሟት ዙሪያ የተጠናቀረውን ይህንን ጽሑፍ ጀባ ብለናችኋል፡፡

***** ኮ/ል መንግሥቱ ሀይለማሪያም “ሀይሌ ፊዳ የተገደለው በገበሬዎች ነው” ባይ ናቸው፡፡ ከጋዜጠኛና ደራሲ ገነት አየለ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ የሀይሌ ፊዳን ሞት እንዲህ በማለት አስረድተዋል፡፡

ገነት፡ ሀይሌ ፊዳስ? በነሐሴ 1970 ተይዞ ከአንድ ዓመት በኋላ ነገር ከበረደ፤ ሁሉ ነገር ከተረጋጋ በኋላ ነው የተገደለው፡፡ በዚያን ጊዜ የኃይሌ ፊዳ በህይወት መኖር መንግሥትን ያሰጋ ነበር?


መንግሥቱ፡ መቼ ነው የሞተው ሀይሌ ፊዳ?

ገነት፡ በሀምሌ 1971 ነው::

መንግሥቱ፡ ማን ነው የገደለው?
ገነት፡ እኔ ምን አውቃለሁ? አስከሬኑ ከቀድሞው የራስ አስራተ ካሣ ግቢ ነው ተቆፍሮ የወጣው፡፡ እዚያ ነው የተገኘው፡፡

መንግሥቱ፡ ሀይሌ?

ገነት፡ አዎን! ሀይሌ ፊዳ፡

መንግሥቱ፡ እዚያ ምን ሲሰራ?

ገነት፡ እዚያ ነው አስከሬኑ የተገኘው፡፡

መንግሥቱ፡ እኔ አላውቅም፡፡

ገነት፡ መሞቱንም አያውቁም? እርሱንም እዚህ ከመጡ በኋላ ነው የሰሙት?

መንግሥቱ፡ መኢሶኖች እኮ ጥለውን ሄደዋል፡፡ የሶማሊያ ጥቃት አይሎ ሲመጣ የሻዕቢያዎች ጎራ ስለጠነከረ ከዚህ ከደከመ መንግሥት ጋር ምን እንሰራለን ብለው አይደል እንዴ ጥለውን የነጎዱት? በነሱ ሃሳብ እኛ በመዳከማችን ወደፊት ከኛ ጋር በመቀጠል የስልጣን ጥማታቸውን የሚያረኩበት መንገድ ስለማይኖር ልዩ ልዩ ምክንያት ሲያቀርቡ ቆይተው በመጨረሻ ፈርጥጠዋል፡፡ በዚህን ጊዜ እነ መስፍን ካሱ ወደ ሲዳሞ፡ እነ ሀይሌ ፊዳ ወደ ወለጋ ሲሄዱ አግኝቶ ገበሬ ነው የከሰከሳቸው፡፡

ገነት፡ እዚያ ነው የተገደሉት?

መንግሥቱ፡ በሙሉ!

(ገነት አየለ አንበሴ፡ የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች፡ 1984፣ ገጽ 207-208)
*****
ሊቀመንበር መንግሥቱ “የሀይሌ ፊዳን መሞት ሰው ነው የነገረኝ” ነው የሚሉት፡፡ ነገር ግን ሀይሌ በነሐሴ 1969 ከተያዘ በኋላ በደርግ ምርመራ ክፍል ሲሰቃይ ቆይቶ እንደተገደለ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሆነውንና ሀይሌ ከመሞቱ በፊት የሰጠውን ባለ 36 ገጽ የምርመራ ቃል በልዩ ልዩ መንገዶች ታትሞ አንብበነዋል፡፡ ከሀይሌ ጋር በአንድ ክፍል ታስረው የነበሩ ጓዶችም ሀይሌ በዚያ ወር እንደተገደለ ተናግረዋል፡፡ የደርግ የቅርብ ሰው የነበሩት አቶ ገስጥ ተጫኔ (ዘነበ ፈለቀ) “ነበር” በሚል ርዕስ በጻፉት ባለሁለት ቅጽ መጽሐፍ የምርመራ ቃሉን ከማተማቸውም በላይ ሀይሌ ከሱሉልታ ኬላ ተይዞ ወደ ደርግ ጽ/ቤት በመጣበት ወቅት በብሄራዊ ቤተመንግሥት እንዳዩት መስክረዋል፡፡

በዚህም መሰረት “ሊቀመንበር መንግሥቱ ሀይሌን በእርግጥ ገድለውታል ወይ?” የሚለው ጥያቄ ለአሁኑ ዘመን አይሰራም፡፡ “መንግሥቱ ሀይሌን ለምን ገደሉት?” የሚለው ግን አሁንም ያከራክራል፡፡ ገነት አየለ እንደገለጸችው ሀይሌ በተገደለበት ወቅት ነገሮች ሁሉ በጣም በርደዋል፡፡ የሶማሊያ ወራሪዎች ከምስራቅ ኢትዮጵያ ከተባረሩ አንድ ዓመት አልፎአቸዋል፡፡ ሻዕቢያና ጀብሃ በሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ክፉኛ ተደቁሰው ወደ ሱዳንና ወደ ሳሕል በረሃ ገብተዋል፡፡ ከነዚህ ሁለት ክስተቶች ቀደም ብሎም ሀገር ያተራመሰውና ሺዎችን የቀሰፈው የቀይ ሽብር ዘመቻ ደርግ በሚፈልገው መልኩ ተጠናቋል፡፡ አብዮታዊው መንግሥት ከዚያ በፊት ያላየው ሰላምና እርጋታ በሀገሪቱና በሁሉም የስራ መስኮች ሰፍኗል፡፡ ታዲያ በዚህ ሰላማዊ ወቅት ሀይሌ ፊዳን ማስገደሉ ለምን አስፈለገ?

በርካታ ተመልካቾች የየራሳቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡ አንዳንዶች ነገሩን ከቂም በቀል ጋር ያያይዙታል፡፡ “መንግሥቱ አንድ ቀን የገላመጠውን እንኳ የማይምር ቂመኛ ነው” -ይላሉ እነዚህ ወገኖች፡፡ የተወሰኑት ደግሞ መንግሥቱ በችሎታና በእውቀት ከርሱ የሚበልጥ ሰው ከታየው ወደፊት ስልጣኔን ይነጥቀኛል በሚል እንደሚያስገድለው ያወሳሉ፡፡ እነዚህኛዎቹ ክርክራቸውን ሲቀጥሉ “መንግሥቱ ሀይለማሪያም ሀይሌ ከእስር ቢለቀቅ ወይም ቢያመልጥ የራሱን ቡድን አደራጅቶ ወይ አንዱን ጄኔራል ተጠግቶ ከስልጣኔ ሊያሽቀነጥረኝ ይችላል” የሚል ፍራቻ ነበረው” ባይ ናቸው፡፡

ከሁለቱ ወገኖች የሚለይ አስተያየት የሚሰጡ ጸሐፊያንና የታሪክ ሰዎችም አሉ፡፡ እነዚህኛዎቹ እንደሚሉት ኮሎኔል መንግሥቱ ሃይለማሪያም በሀይሌ ጉዳይ ላይ የሞት ውሳኔ ያሳለፉት እርሳቸውን ያስደነገጠ አንድ አደገኛ ክስተት ስለተፈጠረ ነው፡፡ እስቲ ታሪኩን አብረን እንየው፡፡
*****

ሊ/ር መንግሥቱ ለጉብኝት ወደ ኩባ ይጋበዛል፡፡ ከጓድ ፊደል ካስትሮ ጋር ጉብኝትና ስብሰባውን ማካሄድ ይጀምራል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ለስራ ጉዳይ ወደ ውጪ ሀገር በመሄዱ ህይወቱ ለጥቂት የተረፈችው የመኢሶኑ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ አዲስ አበባ መግባቱ ይነገረዋል፡፡ “እንዴት መጣ?” ብሎ ቢጠይቅ “የደቡብ የመንን ፓስፖርት ይዞ፤ ከደቡብ የመን ልዑካን ጋር ተቀላቅሎ” ሆነ መልሱ! (ደቡብ የመን አሁን ከሰሜን ጋር ተዋህዳለች)፡፡ “ዶ/ር ነገደ ተይዟል ወይ?” ብሎ ሲጠይቅ አለመያዙ ተነገረው፡፡ ያለበትን ቦታ ጠይቆ የተሰጠውን መልስ ሲሰማ ደግሞ ሊ/ር መንግሥቱ በድንጋጤ ፈዝዞ ቀረ!
*****
በርግጥ ዶ/ር ነገደ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ ነገር ግን መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ ድሮ ከሚያውቀው የኤርፖርት ደህንነት ሃላፊ ጋር አይን ለአይን ተገጣጠመ፡፡ ደህንነቱ ነገሩን ወዲያኑ ለደርጎች አስታወቀ፡፡ ደርጎችም ነገደ ጎበዜን ለመያዝ ተንቀሳቀሱ፡፡ ሆኖም ዶ/ሩ ኩባ ኤምባሲ ገብቶ ተደበቀ፡፡ ሁኔታው ለጓድ ፊደል ካስትሮ ሲነገራቸው ካስትሮ አማላጅ ሆኑና በነገሩ ውስጥ ገቡ፡፡ በርሳቸው ተማጽኖም ዶ/ር ነገደ ከኤምባሲው ወጥቶ ወደ አውሮጳ ተመለሰ፡፡

ይህ ድርጊት የተከሰተው የሶማሊያ ወረራ ካበቃ ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር፡፡ ደርጎች ነገሩን እንደ ኩዴታ ነው የወሰዱት፡፡ ለዚህም ነው በውስጣቸው ከፍተኛ መሸበር የተፈጠረው፡፡ እርግጥ ሀገራቱ ኩዴታ እናድርግ ቢሉ የማስፈጸም አቅሙ ነበራቸው፡፡ በወቅቱ የ"ሶማሊያን ወረራ ለመቀልበስ በተደረገው ዘመቻ አብዮታዊ አጋር ሆኖ የመጣው የኩባ ሀያ ሺ ሜካናይዝድ ጦርና የየመን ሁለት ሺህ መድፈኛ ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበሩ እነርሱን ይዘው አንድ ነገር ማድረግ ይችሉ ነበር ተብሎ ይገመታል፡፡ የዘመኑ ሀያል ሶሻሊስት ሀገር የሆነችውን ሶቪየት ህብረትንም ለእርዳታ ቢጠሯት “በጄ” ከማለት የምትመለስ አይሆንም-ከመንግሥቱ ይልቅ ኩባና ደቡብ የመን ይበልጡባታልና፡፡ ሆኖም የዶ/ር ነገደን መምጣት ብቻ በማየት “ኩዴታ” ተጠንስሷል ለማለት ይከብዳል፡፡

ሊ/ር መንግሥቱ በዚህ መረጃ ላይ በመመርኮዝ “ኩዴታ” እንደታቀደባቸው አሰመሩበት፡፡ ሀገራቱ ፈጸሙብኝ ላሉት በደል ደግሞ ቀጥተኛ ምላሽ መስጠት ከበዳቸው -ምክንያቱም የክፉ ቀን ወዳጆች ናቸውና፡፡ በሌላ በኩል ግን ሊቀመንበሩ ቁጭታቸውን መዋጥ አቃታቸው፡፡ ለምን ቢባል እንኳንስ እንዲህ ዓይነቱን ምልክት አግኝተው ይቅርና በጥርጣሬ ብቻ ብዙዎችን ቀስፈዋልና፡፡ የቀይ ሽብሩ ትርዒት ሳይደመር የተፈጁትን ሰዎች ቤት ይቁጠረው፡፡ ሌ/ኮ/ አጥናፉ አባተን “ለሀገራችን ሶሻሊዝም አይጠቅማትም፤ እንደ ዩጎዝላቪያ የቅይጥ ኢኮኖሚ መርህ መከተል አለብን” በማለታቸው ብቻ አስገድለዋቸዋል፡፡ “ለኤርትራ ጥያቄ ሰላማዊ መፍትሔ ያስፈልጋል” ያሉ በርካታ ጓዶቻቸውን አስረሽነዋል፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ቄስ ጉዲና ቱምሳ እና ሼኽ ሰይድ ቡደላ (የአብሬት ሼኽ) የመሳሰሉ የሀይማኖት አባቶች ያለ አንዳች ምክንያት ተገድለዋል፡፡ ከዚህ አንጻርም ለዶ/ር ነገደ ጎበዜ ድፍረት የሚሰጡት ቅጣት ከፍተኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ግን ዶ/ር ነገደ አልተያዘም፡፡ ስለዚህ ቁጭቱ በምን ይውጣላቸው?

እንግዲህ በአንዳንዶች እምነት ዶ/ር ሀይሌ ፊዳ የተገደለው በዚህ እርግጠኛነቱ ባልታወቀ የዶ/ር ነገደ ጎበዜ “ኩዴታ” ጦስ ነው፡፡ ኩባና የመንን መበቀል ሲያቅታቸው ቁጭታቸውን በግቢአቸው ባጎሩት እስረኛ ላይ ተወጡት፡፡ ሀይሌን በአንድ ቀዝቃዛ ምሽት አሰናበቱት፡፡
*****
በቅርብ ጊዜ የተገኙ መረጃዎች ግን ከላይ የቀረበውን ታሪክ ዋጋ ቢስ አድርገውታል፡፡ እነዚህ መረጃዎች እንደሚሉት ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የመጡት በሊቀመንበር መንግሥቱ እውቅና ነው፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር መረራ ጉዲና በቅርቡ ባሳተሙት መጽሓፋቸው “ነገደ ጎበዜ በመንግሥቱና በኩባዊያን እውቅና መምጣቱን ነግሮኛል” በማለት ጽፈዋል፡፡ ከአሜሪካ የስለላ ምንጮች የተገኘው መረጃም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ ደርጎች “መፈንቅለ መንግሥት ሊካሄድ ነበር” እያሉ ወከባ ይፈጥሩ የነበረው ህዝቡንና የተቃዋሚውን ክፍል ለማደናገርና የበለጠ ጸጥ ለማድረግ ነው ማለት ነው፡፡ የሀይሌ ፊዳ ግድያም ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጋር አንዳች ግንኙነት አልነበረውም፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ሀይሌ ፊዳ የተገደለበት ሀምሌ 1971 በውል ሊመረመር የሚገባው የታሪክ ወቅት ሆኖ ሳለ ምሁራን በጥልቀት ሳያስሱት መቅረታቸው ይገርማል፡፡ ይህ ወር መንግሥቱ ከቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር የተረፉ በርካታ ተቃዋሚዎቹን፣ አማካሪዎቹንና ታዋቂ ግለሰቦችን በድብቅ የገደለበት ጊዜ ነበር፡፡ እነ አቡነ ቴዎፍሎስን ጨምሮ የኢህአፓው ብርሀነ መስቀል ረዳ፣ የመኢሶኖቹ ከበደ መንገሻ፣ ንግሥት አዳነ፣ ደስታ ታደሰ፣ መስፍን ካሱ ወዘተ… በዚሁ ጊዜ ነበር የተገደሉት፡፡ “የማዕከል” ጥያቄ ደርጎችን ያናቆረው በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ኢማሌድህ የሚባለውን የማርክሲስቶች ህብረት ከመሰረቱት አምስት ድርጅቶች (አብዮታዊ ሰደድ፣ መኢሶን፣ ወዝሊግ፣ ኢጭአት እና ማሌሪድ) መካከል መንግሥቱ ከሚመሩት “ሰደድ” ጋር በመድረኩ ላይ የቀረው የማሌሪድ መሪ ተስፋዬ መኮንን የታሰረውና የማሌሪድ ግብአተ ሞት የተፈጸመውም በዚህ ወር ነበር፡፡ ስለዚህ ያ ታሪካዊ ወቅት የምሁራን እይታ ሊያርፍበት ይገባል፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 21/2006

ሸገር- አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment