Pages

"ጄል-ኦጋዴን”

January 26, 2015 | From Anoole Wako

ጄል ኦጋዴን በሱማሌ ክልል ርዕሰ-መዲና የሚገኝ፤ ለ800 እስረኞች ታቅዶ በ1992 ዓ.ም የተገነባ እስር ቤት ነው፡፡ የግቢውን ዙሪያ ከከበበው አጥር በግምት 15 ሜትር ፈንጠር ብሎ ሌላ ተደራቢ የድንጋይ አጥር ተበጅቶለታል፡፡ እስከ ሚያዝያ 24 1999 ዓ.ም ድረስ እስር ቤቱ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ካሉ መሰል ማጎሪያዎች ብዙም የተለየ አልነበረም፡፡ በዚህ በተጠቀሰው ቀን የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ታጣቂዎች፣ አቦሌ እና ሰንደሬ ወታደራዊ ካምፖችን ጨምሮ፣ በነዳጅ ዘይት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ቻይናውያን ባለሙያዎች መኖሪያ ሰፈር ላይ የሰነዘሩትን ከባድ ጥቃት ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞች ብቻ የሚታጎሩበት እስር ቤት ከሆነ ወዲህ ግን በዋይታ የሚናወፅና በደም ጅረት የሚጥለቀለቅ ምድራዊ ሲኦል ለመሆን በቅቷል፡፡ መንግስት በጥቃቱ ከዘጠኙ ቻይናውያን ጋር 74 ሲቪል ዜጎችና ወታደሮች መገደላቸውን ቢያምንም፤ የአካባቢው የአይን እማኞች ከሰራዊቱ ብቻ እስከ 300 እንደተሰዉ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኦብነግ እንደ አል-ቃይዳ እና አል-ሸባብ የአባላቱን አስከሬን ትቶ የመሸሽ ልምድ ስለሌለው በቡድኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት በትክክል ለማወቅ አዳጋች እንደሆነ ቀጥሏል፡፡

የሆነው ሆኖ ከዚህ ጥቃት በኋላ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የሚመራ አምስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያካተተ የደህንነትና (ጄነራል ሳሞራ የኑስ እና ጌታቸው አሰፋ ያሉበት) የፀጥታ ኮሚቴ ተቋቁሞ የሚከተሉትን (ዛሬም ድረስ እየተተገበሩ ያሉ) አስቸኳይ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ ‹‹ከጅጅጋ ውጭ ባሉ በክልሉ ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ተሽከርካሪ እንዳይንቀሳቀስ፣ ትዕዛዙን ጥሶ የተገኘ ከነጭነቱም ሆነ ተሳፋሪዎቹ በከባድ መሳሪያ እንዲመታ፤ አብዛኛውን ህዝብ በፍጥነት ከመኖሪያ ቀዬው በማፈናቀል ለቁጥጥር ወደሚያመቹ ከተሞች ማስፈር (በ2006 ዓ.ም መጀመሪያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ካሳ ተክለብርሃን 2300 መንደሮችን ወደ ተመረጠ ቦታ ማስፈሩ እንደተሳካ መናገሩን ልብ ይሏል)፤ ወታደራዊ መኪና ላይ ምንም አይነት የደፈጣ ጥቃት ከደረሰ በአቅራቢያው የሚገኝ መንደርን ያለርህራሄ ማውደም (ለማሳያ ያህልም ፍልቼ፣ ቃሙዳ፣ ሳስባኒ፣ ሁለሌ፣ ለንካይርተ፣ ቻለሌን… የመሳሰሉ ከተሞች ወደ ፍርስራሽነት መቀየራቸውን መጥቀስ ይቻላል) እና ከአንድ ሻምበል ያነሰ ኃይል ለአስቸኳይ ጉዳይም ቢሆን ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ›› የሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚህ በኋላም ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ሳሞራ የኑስ በክልሉ የሚገኘውን የደቡብ ምስራቅ ዕዝ ወታደራዊ አዛዦችን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ሰብስቦ ማብራሪያ ሰጥቶ ሲያበቃ ውሳኔውን ያለምንም ማቅማማት ተግባራዊ እንዲያደርጉት በጥብቅ አሳስቧል፡፡

ደቡብ ምስራቅ ዕዝ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት (ከ1993 ዓ.ም) በኋላ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሰፈረ ሲሆን እስከ ታህሳስ 1999 ዓ.ም ድረስ በሜ/ጀነራል ባጫ ደበሌ ሲመራ ቆይቷል፡፡ ከታህሳስ 1999 እስከ 2000 ዓ.ም ደግሞ ብርጋዴር ጄነራል ስዩም አስተዳድሮታል፤ በዚሁ ዓመት ከጥቅምት እስከ ሚያዚያ ድረስ ባሉት ጊዜያትም በብ/ጄነራል ሙሉጌታ በርሄ ስር የቆየ ሲሆን፤ ከሚያዚያ 2000 ዓ.ም አንስቶ አሁን ድረስ እየተመራ የሚገኘው በሌ/ጄነራል አብርሃም ወ/ማርያም (ቅፅል ስሙ ‹‹ኳርተር››) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ 

ከዚህ ዕዝ ውስጥ በዋናነት ሶስት ክፍለ ጦሮች (12ኛ፣ 13ኛ እና 32ኛ) ክልሉን ሶማሊያ ድንበር ድረስ እንዲቆጣጠሩት ተመድበዋል፡፡ ሰፈራቸውን ነገሌ ቦረና ያደረጉት 43ኛ እና 44ኛ ክፍለ ጦሮችም፣ ኦጋዴን ድረስ እንዲንቀሳቀሱ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአናቱም የአግአዚ ኃይል በቀድሞ ምክትል አዛዡ ብ/ጄኔራል ገ/መድህን ፈቀደ (‹‹ወዲ ነጮ››) ስር ሆኖ አልፎ አልፎ በተደራቢነት እየተላከ በነዋሪዎቹ ላይ በደረሰው ጅምላ ጭፍጨፋ እና ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፈ ስለመሆኑ ከወታደራዊ መረጃ ምንጮቼ ሰምቻለሁ፡፡ ይህም ሆኖ ለደረሱ እልቂቶችና ጭፍለቃዎች በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ ተደርገው የሚጠቀሱት ከጄነራል ሳሞራ፣ ከጀኔራል ‹‹ኳርተር›› እና ከክልሉ ፕሬዝዳንት በተጨማሪ በብ/ጄነራል በየነ ገ/እግዚአብሔር (‹‹ወዲ አንጥር››) የተመራው 12ኛ ክ/ጦር እና በብ/ጄነራል ፀጋዬ ገ/ጨርቆስ (‹‹ጀብጀብ››) ዕዝ ስር የነበረው 13ኛ ክ/ጦር እንደሆነ ይነገራል፡፡ ኦብነግ በስፋት ይንቀሳቀስባቸዋል ተብለው የሚታሰቡት፡- ደገሃቡር፣ ቀብሪደሃር፣ ዋርደር፣ ጎዴ እና ቪቅ ከተሞች መደበኛ የጦር ቀጠናዎች ከሆኑ 15 አመት ያለፋቸው በመሆኑ፣ ከሌሎች የክልሉ አውራጃዎች በተለየ ሁኔታ የችግሩ ቀጥተኛ ተጠቂ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም የሚፈፅማቸውን ኢ-ህገ መንግስታዊ ድርጊቶች ለመሸፈን እንደ ቀይ መስቀል፣ ዓለም-አቀፍ ሚዲያዎች፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና መሰል ተቋማት ከጅጅጋ ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ በኃይል አግዷል፡፡ ይህ ኩነትም በ ዙ-23 እና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ተደብድበው ከምድረ-ገፅ የጠፉ መንደር ነዋሪዎች፣ የቤት እንስሳት እና ቁሳዊ ንብረቶች በአንድነት ተቃጥለው መውደማቸውን ዛሬም ድረስ በምስጢርነት ሸሽጎ ለማቆየት አስችሎታል፡፡

የሆነው ሆኖ የመከላከያ ሰራዊቱ እና በክልሉ ከ70-80 በመቶ በሚሆኑ አካባቢዎች ላይ መንቀሳቀስ የቻለው ኦብነግ፣ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ከባድ ውጊያ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ግጭቱ አሁንም ሳያበራ የመቀጠሉ ምክንያት አማፂው ቡድን ያን ያህል ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ አይደለም፤ ይልቁንም የጄነራሎቹ እጅ በዘወርዋራ ስላለበት መሆኑን ወታደራዊ ምንጮቼ ያስረግጣሉ፡፡ ‹‹የኦብነግ ህልውና በተለይም ለከፍተኛ መኮንኖች ዋነኛ ንግድ (ቢዝነስ) ነው›› ይላሉ፡፡ የክልሉ መንግስት ‹‹የመረጃ እና ፀጥታ ባጀት›› በሚል ሽፋን በዓመት የሚመድበውን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብ ሀብት እንዲያወራርዱ አዛዦቹ አይገደዱም፡፡ መከላከያ ራሱም ‹‹የመረጃ እና የበረሃ ፍሳሽ›› በሚል የሚበጅተው አመታዊ ወጪ በብዙ ሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ በጀት እስከ ኃይል አመራሮች ድረስ ወርዶ እንደየድርሻቸው መጠን የሚመዘበርበት አሰራርም ተዘርግቶለታል፡፡ እናም ጀነራሎቹ ኦብነግ ሙሉ በሙሉ ተወግዶ የገቢ ምንጫቸው እንዳይደርቅም ሆነ፤ ከአቅም በላይ ተጠናክሮ በብቃት ማነስ እንዳያሳጣቸው (እንዳያስወቅሳቸው) ተቆጣጥረው ለመዝለቅ የቻሉበትን ቀመር እንዲከተሉ ይህ የገቢ ምንጭነት ገፊ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከመከላከያ ሠራዊቱ እና ከፌዴራል ፖሊስ በተጨማሪ በቀጥታ የክልሉ አስተዳደር የሚያዝዘውና ‹‹ልዩ ኃይል›› ተብሎ የተቋቋመው ታጣቂ ቡድን ዛሬም ድረስ የሎጅስቲክ አቅርቦቱን ያለጨረታ ጠቅላላ የያዘችው የሜ/ጀነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ (በአሁኑ ወቅት ጀነራል አበባውን ተክቶ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ነው) ባለቤት ሃዋ መሆኗ በራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ (በነገራችን ላይ ክልሉን የሚያስተዳድሩት በህዝብ የተመረጡት ሳይሆኑ ‹‹የፀጥታ አማካሪ›› በሚል በየወረዳው የተመደቡ የሻለቃ ወይም የሻምበል አዛዦች ከጀርባ ሆነው ነው፡፡ ለነርሱ ያልተመቸ ኃላፊን በሌላ እስከመቀየር ድረስ የሚንጠራራ ስልጣን አላቸው፡፡ የፕሬዚዳንት አብዲና እና የጄነራል ‹‹ኳርተር››ን የ‹‹ሥራ ግንኙነት›› መመልከቱ ጉዳዩን ፍንትው አድርጎ ለመረዳት ያስችላል፡፡ በርግጥም አስራ ሦስት ፕሬዚዳንቶች የተፈራረቁበት ክልል ዛሬ እንዲህ በጨካኙ አብዲ መርጋት መቻሉ እንቆቅልሽ ሊሆን አይችልም)፡፡

‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ከደረቅ ወንጀለኞች ማረሚያነት፣ በኦብነግ አባልነት የሚጠረጠሩ ንፁሃንን ወደማሰቃያ እስር ቤት እንዲቀየር የተደረገበት መግፍኤ ከላይ የጠቀስኩትን (የ1999 ዓ.ም የኃይል ጥቃትን) ተከትሎ ሟቹ አምባ-ገነን ጠ/ሚኒስቴር በደህንነት ኮሚቴው ስም የሰጠው ትዕዛዝ ነው፡፡ መቼም ዕድል ፊቷን አዙራበት ወደዚህ ግቢ የተላከ ምስኪን፣ በቀን አንድ መናኛ እንጀራ እየተወረወረለት፣ በ‹‹ምርመራ›› ስም የተወለደበትን ቀን ከመርገም አልፎ ዘላለማዊ ዕረፍት የሚያጎናፅፈው መልአከ-ሞት ቶሎ መጥቶ እንዲገላግለው እስከመናፈቅ ለሚያደርስ ስቀየት (ቶርቸር) ይዳረጋል፡፡ እስር ቤቱ የተገነባው 800 ታሳሪዎችን ታሳቢ ተደርጎ ቢሆንም፣ ወደምድራዊ ገሃነም ከተቀየረ ወዲህ ግን ከ5000 በላይ ሰዎች የሚታጎሩበት የሰቆቃ ግቢ ሆኗል፡፡ ሁሉም ታሳሪዎች ከጠዋት 2፡30 እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ አንድ ቦታ ተሰብስበው ክብርን፣ ሞራልን እና ሰብዕናን የሚያጎድፍ ግፍ ይፈፀምባቸዋል፡፡ 

በተለይም ሴት እስረኞች በየተራ እንዲቆሙ ይደረግና ወንዱ አንድ በአንድ እየተነሳ ሴተኛ አዳሪ መሆኗን፣ እሱ እና ጓደኞቹ ከእርስዋ ጋር ግብረ-ስጋ ግንኙነት መፈፀማቸውን፣ ወዘተ እንዲናገር ይገደዳል፡፡ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኖ ካልተገኘም በጨካኝ ታጣቂዎቹ ፍዳውን ይበላል፡፡ ሁኔታውን መራር የሚያደርገው ደግሞ ‹‹ስብሰባው›› ሲጠናቀቅ፣ ሰብሳቢው እስረኞቹ ወደየክፍላቸው እንዲገቡ ትዕዛዝ የማይሰጥ መሆኑ ነው፤ ይልቁንም ወፋፍራም ዱላ ጨብጠው ዙሪያውን ለከበቡት ፖሊሶች በአይኑ ምልክት ያስተላልፋል፤ ይሄኔ በያዙት ቆመጥ ከአቅራቢያቸው ያገኙትን ሁሉ መቀጠቀጥ ይጀምራሉ፤ እስረኛውም ከዱላው ውርጅብኙ ለማምለጥ ባገኘው አቅጣጫ ይተራመሳል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በየቀኑ የተለመደ በመሆኑ የዕለቱ ፕሮግራም ሊገባደድ በተቃረበ ቁጥር፣ ሁሉም ለመሸሽ ዝግጁ ሆኖ ይጠባበቃል፤ ከድብደባው ማምለጡ ግን ብዙም የሚሳካ አይሆንም፡፡

በ‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ሴት እስረኞችን አስገድዶ መድፈር፣ ሙዝ ልጦ እንደመብላት ቀላል ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በዚህም በርካቶች በየጊዜው ለውርጃ ወደሆስፒታል ሲላኩ ይስተዋላል፡፡ አልፎ አልፎ እዚያው ለመውለድ የሚገደዱ እህቶችም አሉ፡፡ አብዛኞቹ ሴት እስረኞች ፀጉራቸውን ከማሳደግ ይልቅ መላጨትን ይመርጣሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ የሚፈፀምባቸው ስቅየት የበሰበሱ ቆሻሻዎችንና ፈሳሽ-ሰገራዎችን ፀጉራቸው ላይ መደፋትን ስለሚያካትት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እዚህ ቦታ ሴቶች አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ እና ልብሶቻቸውን እንዲያወልቁ ከተደረገ በኋላ እርቃናቸውን የሚገረፉበት ጊዜም እንዳለ ከአይን እማኞች ሰምቻለሁ፡፡ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ንፅህናን ካለመጠበቅና በምግብ እጥረት የሚነዛው ወረርሽኝ ነው፡፡ በ2004ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ በሽታው ተከስቶ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ 700 ያህል ሰዎች በሞት መቀጠፋቸው ይነገራል፡፡ በወቅቱ አስከሬን ቶሎ ስለማይነሳ እስረኞቹ ከአስከሬኑ ጋር እስከ 3 ቀን ድረስ ጋር ለመቆየት ይገደዱ ነበር፡፡

በ‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ግቢ ከሚገኙ ማጎሪያዎች መካከል 3ኛ፣ 4ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ክፍሎች ‹‹የቅጣት ቤት›› ሲሆኑ፤ አሰራራቸውም ሶስት በሶስት ሜትር የሆነ እጅግ በጣም ጠባብ፤ ውስጣቸውም ሃምሳ ሳንቲ-ሜትር ጥልቀት ባለው ውሃ የተሞላ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክፍልም የግድ ከ25 እና ከዚያ በላይ እስረኞች እንዲይዝ ስለሚደረግ ለቅጣት ወደግቢው የተላከ እስረኛ ለሳምንት ያህል እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር ለመሰንበት ይገደዳል፡፡ በአናቱም የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደዚህ ግቢ እየተላኩ ስቅየትም ሆነ ግድያ እንደሚፈፀምባቸው ሰምቻለሁ፡፡ በግቢው ለአራት ወራት ገደማ ያሳለፈው ሀሰን፣ በውል በማያስታውሰው በአንድ የተረገመ ቀን 3 ወታደሮች ሲረሸኑ ማየቱንና ከመካከላቸው አንዱም ‹‹እባካችሁ አትግደሉኝ! የ3 ልጆች አባት ነኝ!›› እያለ ሲማፀን መስማቱን ያስታውሳል፡፡ እስረኞቹ ላይ የጭካኔ ተግባር የሚፈፅሙት ደግሞ ከዚህ ቀደም ‹‹አል-ኢትሀድ አል-ኢስላሚያ›› በሚል ስም ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ፤ በኦብነግ ተሸንፎ ከኦጋዴን የተባረረው አማፂ ቡድን አባላት የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መንግስት ምህረት አድርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ህይወት ከተመለሱ በኋላ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዛኛውን አሰባስቦ ‹‹ልዩ ኃይል›› ብሎ አደራጅቷቸው ሲያበቃ፤ ከኦብነግ ጋር ተያይዞ የሚጠረጠሩ እስረኞች ላይ ያሻቸውን እንዲፈፅሙ ባልተፃፈ ሕግ ስልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም የቀድሞ ሽንፈታቸውን ለመበቀል እንደ መልካም አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ዛሬ በክልሉ ከተሞች በሚገኙ የተለያዩ የእስር ቤት ግቢዎች ውስጥ የጅምላ መቃብር መመልከት አስገራሚነቱም አስደንጋጭነቱም እየቀረ የመጣው ከዚህ አኳያ ይመስለኛል፡

No comments:

Post a Comment