Pages

[የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘገባ]- በአዲስ አበባ ዙሪያ ገበሬዎች የሚፈናቀሉት ያለ በቂ ዝግጅት ነው ተባለ

February 23, 2015 | የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘገባ | ናፍቆት ዮሴፍ እና አለማየሁ አንበሴ

ከግማሽ ሚሊዮን እስከ 2 ሚሊዮን ብር ካሣ የተከፈላቸው ገበሬዎች አሉ በተከፈላቸው ካሣ ንድግ ጀምረው የተሳካላቸው ጥቂቶች ናቸው
“ቦታው ለሪል እስቴትና ለልማት ይፈለጋል ተብለን የእርሻ መሬታችንና የመኖሪያ ቦታችን በመንግስት ከተወሰደብን አራት አመታት ሞላን” ይላሉ - በሰበታ አዋስ ወረዳ እያረሱ ይኖሩ እንደነበር የገለፁ አርሶአደሮች፡፡ ለእርሻ መሬት እንደየስፋቱ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ የተከፈላቸው ገበሬዎች መኖራቸው አይካድም፡፡ ለመኖሪያ ቤትም 24 ሺ ብር ድረስ ካሳ እንደተከፈላቸውና ቤት መስሪያ ቦታ እንደሚሰጥም ቃል ተገብቶላቸው እንደነበር የተፈናቀሉ ገበሬዎች ያስታውሳሉ፡፡ “ከዛሬ ነገ ቦታ ተሰጥቶን ባለችን ብር ጭቃ ቤት እንሰራለን ብለን ብንጠብቅም ቄሱም ዝም መፅሀፉም ዝም ሆነ” ብለዋል - ገበሬዎቹ፡፡ 
የአራት ልጆች አባት የሆኑት የሰበታ አካባቢ ገበሬ፤ መሬታቸው ከተወሰደባቸው በኋላ ስለገጠማቸው ህይወት ሲናገሩ፤ “ስድስት ቤተሰብ ይዤ ሰበታ ከተማ ሁለት ጠባብ ክፍሎችን ተከራይቼ በጭንቀት መኖር ጀመርኩ፡፡ ገንዘቡ ለቤት ኪራይ፣ ለቀለብ፣ ለልጆች ት/ቤት፣ ለትራንስፖርት ሲወጣ፣ በአጭር ጊዜ ተሟጦ ለችግር ተጋለጥኩ” ብለዋል፡፡ ከአካባቢው በርካታ አርሶ አደሮች አብረዋቸው እንደተፈናቀሉ የሚናገሩት አርሶአደሩ፤ አቅመ ደካማው ለረሀብና ለእርዛት ተጋልጦ፣ ለልመና እጁን ሲዘረጋ፣ ጉልበት ያለው የቀን ስራ እየሰራ ኑሮውን ሲገፋ፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እያቋረጡ ወደ ሰው ቤት ሰራተኝነትና ሴተኛ አዳሪነት ሲገቡ መመልከት ክፉኛ እንደሚያሳምም ተናግረዋል፡፡ ከአካባቢው በዚህ መልኩ የእርሻ መሬታቸውን ካጡ አርሶአደሮች መካከል ወደ ንግድ ገብተው የተሳካላቸው ሶስት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ የጠቆሙት ተፈናቃዩ፤ የቀረው ግን በካሳ መልክ ያገኘውን ገንዘብ ለቤት ኪራይና ለቀለብ አውጥቶ በአካባቢው ብዙ ማህበራዊ ቀውስ መከሰቱንና እስካሁንም እልባት እንዳልተገኘለት በቁጭት ይናገራሉ፡፡ 
ሱሉልታ አካባቢ በግብርና ይተዳደሩ የነበሩ አንድ ሌላ አርሶአደር ደግሞ መሬታቸው ለልማት ሲወሰድ 19 ሺ 200 ብር ካሳ ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡ ገንዘቡን ይዘው ወደ ከተማ በመምጣት፣ ቤት ተከራይተው ከሶስት ልጆቻቸውና ከሚስታቸው ጋር ለጥቂት ወራት ቢኖሩም፣ ኑሮው በዚያው መልክ መቀጠል አልቻለም ይላሉ፡፡ “ብሩ እየመነመነ ሲሄድ ትልቋን ልጄን ወንድሜ እንዲያስተምርልኝ ጫንቾ ልኬ፣ ሁለተኛዋ ልጄ ሰርታ ራሷን እንድትችል አዲስ አበባ ዘመድ ጋር አስጠግቼ፣ ቀን ቀን ዘመዶቼን እያገለገለች ማታ ማታ ትማራለች” ያሉት የቀድሞው አርሶ አደር፤ ትንሹን ወንድ ልጄንና ባለቤቴን ይዤ የቀን ስራ እየሰራሁ፣ ባለቤቴ ሰው ቤት እንጀራ እየጋገረችና ልብስ እያጠበች፣ በምናገኛት ገቢ ኑሮን እየገፋን ነው ብለዋል፡፡ “እህል ከጎተራ ዝቆ እንደልቡ ልጆቹን መግቦ መኖር የለመደ አርሶ አደር፤ ከለመደው ባህልና ወግ ውጭ ሲሆን ብስጭቱና ቁጭቱ ጤና ያሳጣዋል፤እኔም የዚህ ችግር ሰለባ ሆኜ ያለ እድሜዬ አርጅቻለሁ፤ ባለቤቴም ሁለት ሴት ልጆቿ ከጉያዋ እርቀው ሲበተኑ፣ ቀን ማታ እያለቀሰች ሌላ ራስ ምታት ሆናብኛለች” ያሉት አባወራው፤በአካባቢያችን የእኛ አይነት ችግር የደረሰባቸው በርካታ አርሶ አደሮችን ብታነጋግሩ፣ ከእኛ የበለጠ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ትረዳላችሁ ሲሉ ሁኔታው የከፋ መሆኑን ጠቁመውናል፡፡
ከኦሮሚያ ልዩ ዞን አስተዳደር ወረዳዎች አንዷ በሆነችው ዱከም አካባቢ አርሶ አደር የነበሩት አቶ ደሜ ፈዬራ (ስማቸው ተለውጧል) ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞንን ጨምሮ ለሌሎች የኢንዱስትሪ ልማቶች ከተወሰደባቸው የእርሻ መሬት ዳጎስ ያለ ካሳ ማግኘታቸውን ይገልፃሉ - የገንዘብ መጠኑን መጥቀስ ባይፈልጉም፡፡ ከ4 ዓመት በፊት ባገኙት በዚህ የካሳ ክፍያ፣ በዱከም ከተማ አንድ የሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ መደብር እንዲሁም ባለ 5 ክፍሎች መኖሪያ ቤት እና ያገለገለ አይሱዙ መኪና ወደ 1 ሚሊዮን ብር ገደማ አውጥተው እንደገዙ ይናገራሉ፡፡ መኪናዋ የተገመተውን ያህል አገልግሎት መስጠት ባትችልም የንግድ ሱቁና የከተማ መኖሪያ ቤቱ ግን ለቤተሰቡ ሁነኛ የኑሮ ዋስትና ሆኗቸዋል፡፡ አቶ ደሜ፤ የእርሻ መሬታቸው ለልማት እንደሚፈለግ ከባለስልጣናት በሰሙ ጊዜ፣ ከሚወዱት የግብርና ሙያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊቆራረጡ እንደሆነ በማሰብ ከመጨነቅ ውጭ ቤተሰባቸውን በምን እንደሚያስተዳድሩ ግራ ገብቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ልጆቼ ፊደል የቆጠሩ መሆናቸው በጀኝ የሚሉት አባወራው፤ በልጆቻቸው ብርታት የተሰጣቸውን የካሣ ገንዘብ፣ ለቤተሰቡ ዋስትና በሚሆን ነገር ላይ ለማዋል እንደቻሉ ይናገራሉ፡፡ ከምወደው የግብርና ሙያ ብለያይም ፈጣሪ ይመስገን ሳልቸገር እኖራለሁ ብለዋል፡፡ እሳቸው የገንዘብ አጠቃቀሙን በማወቃቸው ለችግር ባይጋለጡም ከቅርብ ወዳጆቻቸው መካከል የተሰጣቸውን ገንዘብ ቁም ነገር ላይ ሳያውሉ በመቅረታቸው፣ ዛሬ ለከፋ ችግር የተጋለጡ እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ አንድ ወዳጃቸው፣ መኖሪያ ቤት ገላን ከተማ ውስጥ ከገዙ በኋላ በቀሪው ሚኒባስ ታክሲ ቢገዙም፣ ኑሮን ማሸነፍ አቅቷቸው በችግር እየተንገላቱ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ የተሰጣቸውን ገንዘብ በየመጠጥ ቤቱ አራግፈው፣ የቀን ሰራተኛና በረንዳ አዳሪ የሆኑ በቅርብ የሚያውቋቸው ገበሬዎች እንዳሉም አቶ ደሜ ይናገራሉ፡፡ 
ሀገር ባደገና በዘመነ ቁጥር ከከተሜነት ጋር መተዋወቅና መለማመድ የግድ ነው የሚሉት ገበሬው፤ ነገር ግን መንግስት የእርሻ መሬትን ለኢንቨስትመንት ሲፈልገው፣ አስቀድሞ የገበሬውን መውደቂያ ሊያጤን ይገባል ይላሉ፡፡ ዝም ብሎ መሬቱ ለልማት ይፈለጋልና የካሳ ክፍያህን ተቀብለህ ተነስ ማለት ለገበሬው ከብርሃን ወደ ጨለማ የመጓዝ ያህል ነው የሚሉት አባወራው፤ መንግስት አስቀድሞ የስራ ፈጠራና የኑሮ ዘይቤዎችን የሚያመላክቱ ስልጠናዎችን መስጠትና ሁኔታውንም እስከመጨረሻው መከታተል አለበት ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ገበሬውን ከይዞታው አያፈናቅልም፣ የእርሻ መሬቱንም አይነጠቅም የሚለው የመንግስት መከራከሪያ ተቀባይነት የለውም ያሉት አንድ የህግ ባለሙያ፤ ቤተሰቦቻቸው በኢንዱስትሪ መስፋፋት ምክንያት የእርሻ መሬታቸው ሙሉ ለሙሉ ተወስዶባቸው፣ወደ ከተማ መፍለሳቸውን ይናገራሉ - በርካታ የአካባቢው አርሶአደሮች በዚህ መልኩ ከምርት አቅራቢነት ወደ ሸማችነት መሸጋገራቸውን በመጠቆም፡፡ 
በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ የሚገኙት ገላን እና ዱከም በተለይ በጤፍ አብቃይነታቸው የሚታወቁ ሲሆን ስንዴ፣ ሽምብራ፣ ጓያና ምስር የአካባቢው ገበሬዎች የሚታወቁባቸው ምርቶች እንደሆኑ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት የህግ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ አዲስ አበባና የዙሪያዋ ፊንፊኔ ልዩ ዞን ማስተር ፕላንን አስመልክቶ ለውይይት በቀረበው ሰነድ ላይም፣ በአጠቃላይ በልዩ ዞን ከ1.3 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች እንዳሉ መጠቀሱን አውስተዋል፡፡ የእነዚህ አርሶ አደሮች ምርት ዋነኛ የገበያ መዳረሻ ደግሞ አዲስ አበባ ነች፡፡ የገላን፣ የዱከም እንዲሁም በአዲስ አበባ አስተዳደር ስር የሚገኙት ገላን ጉራ፣ ቂሊንጦ፣ ኮዬና ፈጨ የሚባሉ የአርሶ አደር አካባቢዎች፣ ቀደም ሲል ለአዲስ አበባ ህዝብ እህል አቅራቢዎች እንደነበሩም ነጋዴዎች ይመሰክራሉ፡፡ በአቃቂና ሳሪስ ገበያ በእህል ነጋዴነታቸው የሚታወቁት አቶ ቶሎሳ ሁንዴ፤ በአቃቂና ገላን ከተሞች መካከል ባለው መንገድ ላይ በሳምንት ሁለት ቀን ማክሰኞ እና ቅዳሜ ሚዛናቸውን ሸክፈው እህል ለመገብየት የሚወጡ ሲሆን ማታ ላይ የሸመቱትን በአይሱዙ ጭነው አቃቂ ወደሚገኘው የእህል መጋዘናቸው ይሄዳሉ፡፡ ማክሰኞ በጅምላ የሸመቱትን ረቡዕ ለሳሪስ ገበያ ሲያቀርቡ፣ ቅዳሜ የሸመቱትን ማክሰኞ ለአቃቂ ገበያ እንደሚያቀርቡም ነጋዴው ይናገራሉ፡፡ አንዳንዴም በተለይ የደሞዝ ወቅት ሆኖ፣ የችርቻሮ ሸማች በርከት ሲል በሰራተኞቻቸው አማካኝነት እንደተፈላጊነቱ እያመላለሱ ይሸጣሉ፡፡ በአሁን ሰአት ግን እንደድሮው ከገበሬው ጤፍ እና ስንዴ እንደልብ ማግኘት አልተቻለም የሚሉት ነጋዴው፤በተለይ በክረምት ወቅት ገበሬዎቹ ራሳቸው ሸማቾች እንደሚሆኑ ይገልፃሉ፡፡ እህል ትሸምታላችሁ ሲባሉም “መሬታችን ተወስዶ በማለቁ ነው” የሚል መልስ እንደሚሰጡ ነጋዴው ተናግረዋል፡፡ 
የአካባቢው አርሶ አደር እንደ ነጋዴ እህል ቸርችሮ መሸጥን እምብዛም አለመደውም የሚሉት አቶ ቶሎሳ፤ አንዳንዶች ለእርሻ መሬታቸው ግምት ተሰጥቷቸው የግብርና ስራቸውን ካቆሙ በኋላ፣ ነጋዴ ለመሆን ይሞክሩና የስራውን ፀባይ ባለማወቅ ለኪሳራ ተዳርገው፣ ራሳቸውንም ቤተሰባቸውንም ለችግር ያጋልጣሉ ብለዋል፡፡ በርካታ ወዳጆቼን መጥቀስ እችላለሁ የሚሉት ነጋዴው፤ አንዳንድ አርሶ አደር አንዱ ያደረገው ለኔም አይቅርብኝ በሚል ገንዘቡን ዘላቂ ባልሆነ ጉዳይ ላይ አውሎ ባዶ እጁን ይቀራል በማለትም የአንድ ወዳጃቸውን ተመክሮ ይጠቅሳሉ፡፡ “የእርሻ መሬቱ ለልማት ተፈልጎ በመንግስት ሲወሰድ ወደ 750 ሺህ ብር ገደማ ካሳ ተከፈለው፤ ግማሹን መኖሪያ ቤት ሰራበትና ግማሹን ሚኒባስ ታክሲ ገዛበት፡፡ ለቤተሰቡ መተዳደርያ ተብላ የተገዛችው አሮጌ ሚኒባስ ግን የተገዛችበትን ዋጋ ሩብ ያህል እንኳ ሳትመልስ በዘጠኝ ወሯ ከአገልግሎት ውጪ ሆነች፡፡ ወዳጄ በመጦርያ እድሜው አካባቢው በሚገኝ አንድ የጠጠር ማምረቻ ድርጅት ውስጥ በጥበቃነት ተቀጥሮ በሚያገኛት 650 ብር ወርሃዊ ደሞዝ ቤተሰቡን ለማስተዳደር ቢታትርም የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አልቻለም፡፡ ይሄኔ የቀረችውን ጥቂት ጥሪት አሟጦ፣ ሁለት ሴት ልጆቹን ከትምህርት ገበታቸው ላይ በማፈናቀል፣ ወደ አረብ ሃገር ሰደዳቸው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በአርሶ አደር አካባቢነታቸው የሚታወቁት ገላን ጉራ፣ ኮዬ፣ ፈጨ እና ቂሊንጦ የተባሉ አካባቢዎች ለጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ለዩኒቨርሲቲና ለቢራ ፋብሪካ ግንባታዎች እንዲሁም ለተለያዩ የኢንዱስትሪ ልማቶች ይፈለጋሉ በሚል በርካታ አርሶ አደሮች ከእርሻ መሬታቸውና ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ሪፖርተሮቻችን በአካባቢው ተገኝተው እንደታዘቡት፣ በተለይ ለኮንዶሚኒየም እና ለቢራ ፋብሪካ ግንባታ ቁጥራቸው ከ50 የሚልቅ አርሶ አደሮች ከቀዬአቸው ተነስተው እዚያው አካባቢ በተሰጣቸው ተለዋጭ መሬት ሰፈረዋል፡፡ አብዛኞቹ ቦታዎችም የቤት እና የዩኒቨርሲቲ ግንባታ እየተከናወኑባቸው ነው፡፡ በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችም እየተካሄዱ ነው፡፡ በቅርቡ ከንቲባ ኩማ ድሪባ፤ ለ3 መቶ ሺህ ነዋሪዎች የሚሆን የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ በአካባቢው ላይ መጀመሩን መግለፃቸው የሚታወስ ሲሆን የአርሶ አደር አካባቢ የነበረው ሥፍራንም ወደፊት ዘመናዊ ከተማ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ 
ካነጋገርናቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ስሜ አይጠቀስ ያሉን የ65 ዓመቱ አዛውንት፤ ከሁለት ዓመት በፊት ወደ 8 ሄክታር የእርሻ መሬታቸው ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በሚል መወሰዱን ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ ከወረዳው እና ከከተማ አስተዳደሩ የመጡ አመራሮች፤ የእርሻ መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ሊሰጣቸው መሆኑን በመግለፅ በካሬ ሜትር መለካት እንደጀመሩ፣ ገበሬውም የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ይሰጠኛል በሚል ተስፋ ተባባሪ እንደሆነ አስታውሰው፤ ኋላ ላይ ግን ቦታው ለልማት ስለሚፈለግ ለመኖሪያ ቤታችሁ ምትክ ቦታና ግምት ይሰጣችኋል፤ ለእርሻ መሬታችሁም ከመሬቱ ላይ የሚገኘው የ10 ዓመት አላባ (ትርፍ) ተሰልቶ ካሳ ይከፈላችኋል እንደተባሉ ይገልፃሉ፡፡ ገበሬው ምንም አይነት ስነልቦናዊ ዝግጅት ሳያደርግ መተዳደሪያ መሬቱ እንደተወሰደበት የሚጠቅሱት አዛውንቱ ገበሬ፤ ለእርሻ መሬት በካ.ሜ 18ብር ከ50 ሳንቲም ተሰልቶ ክፍያ ሲፈፀም የመኖሪያ ቦታ ግምት 9 ብር ከ25 ሣንቲም ተሠልቶ ክፍያ መፈፀሙን ያስታውሣሉ፡፡ “ለእርሻ መሬቱ የ10 አመት አላባ ተሠልቶ ይከፈላችኋል የተባለው ግን እንዴት እንደተሰላ አላውቅም” የሚሉት ገበሬው፤ የእርሻ መሬት ካሣ፣ የመኖሪያ ቦታና ቤት ግምት እንዲሁም፣ የመፈናቀያ ካሣን ጨምሮ ከግማሽ ሚሊዮን እስከ 2 ሚሊዮን ብር ለእያንዳንዱ አርሶ አደር እንደተከፈለ ይጠቁማሉ፡፡ አብዛኛው አርሶ አደር በተሰጠው ምትክ ቦታ ላይ በተለምዶ አሞራ ክንፍ የሚባለውን የጭቃ ቤት እንደገነባና በተረፈው ገንዘብ ለወደፊት የኑሮ ዋስትና ይሆነኛል ያለውን ንብረት እንደገዛበት የጠቆሙት አዛውንቱ፤ ነቃ ያለው በከተማ የመኖሪያ ቤት ገዝቶ በማከራየት ኑሮውን ሲደጉም፣ ግንዛቤ የሌለው ደግሞ ስለተሽከርካሪ ምንነት በሚገባ ሳይረዳ ተሽከርካሪ በመግዛት፣ አጠቃቀሙን ባለማወቅ ለኪሣራ እየተዳረገ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ አንድም ገበሬ ከመኖሪያው የተፈናቀለ የለም የሚለው የመንግስት ባለስልጣናትን መግለጫ እንደማይቀበሉት የተናገሩት አዛውንቱ፤ ሩቅ ሳይሄዱ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የገበሬ አካባቢዎች ተዘዋውረው ቢመለከቱ፣ እውነታውን ይረዳሉ ብለዋል፡፡ አሁን በተሰጠን የመኖሪያ ቦታም ቢሆን ተረጋግተን ለመኖራችን ዋስትና የለንም የሚሉት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፤ “ዙሪያውን ባለ ፎቅ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው፣ እኛ የጭቃ ቤታችንን ይዘን ማንም የሚያስቀምጠን የለም፤ ወደፊት ተነሺ ናችሁ የሚባሉ ወሬም እየተናፈሰ ነው” ይላሉ፡፡ 
አቶ ኤርሚያስ ሙሉጌታ በሙያቸው የማህበረሰብ ሰራተኛ (Social Worker) ናቸው፡፡ ላለፉት ሰባት ዓመታት በሙያው ማገልገላቸውን ይናገራሉ፡፡ አንድ ሰው ወይም ማህበረሰብ ከነበረበት አካባቢ ባህልና የአኗኗር ዘይቤ ሲፈናቀል ሊደርስበት ስለሚችለው ችግር ሲያስረዱ፡፡ “አንድ ማህበረሰብ ወይም ግለሰብ በምንም መልኩ ከኖረበት ባህል ወግና አካባቢ ባይለይ ጥሩ ነው፤ ግድ ሆኖ መልቀቅ ካለበት ግን ሊሟሉ የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው” ብለዋል፡፡ አንዱና የመጀመሪያው ጉዳይ የስነ-ልቦና ዝግጅት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሁለተኛ ደግሞ በጉዳዩ ዙሪያ ወደፊት ስለሚያጋጥሙ ሁኔታዎች እና መሰል ጉዳዮች በቂ ግንዛቤ መፍጠር እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ ከትውልድ ቀዬ፣ ከለመዱት ሙያና የአኗኗር ዘይቤ መፈናቀልም ለከፍተኛ ምስቅልቅል እንደሚዳርግ የተናገሩት ባለሙያው፤ አንድ አርሶ አደርን ገንዘብ ሰጥተነው “ሂድ ነግድ” ብንለው አሊያም በንግድ ሥራ ጥርሱን የነቀለ አንድን ነጋዴ፣ ጥሩ ጥሩ በሬዎች አዘጋጅተን ሞፈርና ቀንበር አቀናጅተን “ሂድ እረስ” ብንለው የማይሆን ነገር ነው ይላሉ፤ አቶ ኤርሚያስ፡፡ “ይህ ማለት ግን ነጋዴውም ገበሬ፣ ገበሬውም ነጋዴ መሆን አይችሉም ማለት አይደለም” የሚሉት ባለሙያው፣ ነጋዴውን ጥሬ ገበሬ ለማድረግ የስነ ልቦና ዝግጅት፣ የሙያ ስልጠናና ምክር እንዲሁም በዘርፉ የሰለጠነ አማካሪና በቂ ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልፀው፤ ገበሬውንም ጥሩ ነጋዴ ለማድረግ ተመሳሳይ ጉዳዮችን ማሟላት እንደሚስፈልግ ይናገራሉ፡፡ 
በዚህ በኩል የሚመለከተው አካል በተለይ መንግስት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለተፈናቃዮች የስነ-ልቦና ዝግጅት ስልጠናና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ካላደረገ፣ መዘዙ ለራሱ ለመንግስት በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላንን የተቃወመው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ፓርቲ አመራር አቶ ገብሩ ገብረማርያም፤ ኦሮሚያ ውስጥ ገበሬዎች እየተፈናቀሉ፣ በአጠቃላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ሄክታር መሬት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች እንደተሰጠ እናውቃለን ብለዋል፡፡ አብዛኛውም ለአበባ እርሻ ልማትና ለኢንዱስትሪ ዞን እየዋለ ነው ያሉት አመራሩ፤ በተለይ በዱከምና ቢሾፍቱ አካባቢ መንግስት ቁጥሩ በውል የማይታወቅ ገበሬ አፈናቅሎ፣ መሬት ለባለሀብት ሠጥቷል ብለዋል፡፡ 
ገበሬው ብዙ ቤተሰብ የማፍራት ልማድ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ገብሩ፤ በመፈናቀሉ ራሱን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡም ተጐጂ ነው ይላሉ፡፡ ገበሬው ከመሬቱ እንዲለቅ ሲደረግም ተገቢው ካሣ ተሰጥቶት እንዳልሆነም ከተለያዩ አካባቢዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን መነሻ አድርገው አቶ ገብሩ ይናገራሉ፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ህዝብ በሚገባ ሳይመከርበት በድንገት አዲስ ፕላን አውጥቶ ለመተግበር መሯሯጡ ቀውስ ማስከተሉ አይቀርም ብለዋል፡፡ በኦሮሚያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አዲሱን ማስተር ፕላን አስመልክቶ የተነሣውን ተቃውሞ ተከትሎ በማረጋጋት ስራ ላይ ከተጠመዱ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት መካከል አንዱ የሆኑት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፤ የጋራ ማስተር ፕላኑ አርሶ አደሩን ያፈናቅላል የተባለው አሉባልታ እንደሆነ ገልፀው፤ እቅዱ የአንድም አርሶ አደር መሬት እንደማይነካ ተናግረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment