Pages

‹‹ወጣቱ ትውልድ ፖለቲካውን መነገጃ እንዳያደርገው ሥጋት አለኝ››------ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የመድረክ ምክትል ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ

March 22, 2015 | Ethiopian Reporter
ዶ/ር መረራ ጉዲና የመድረክ ምክትል ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ናቸው፡፡ ከመድረክ አራት አባል ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበርም ናቸው፡፡
ዶ/ር መረራ በፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያነታቸው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በርካታ የምርምር ሥራዎችን በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች-ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢሕአዴግ›› በሚል ርዕስ በአማርኛ ቋንቋ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ ከዚህ በፊት የሦስተኛ ዲግሪ (PhD) ማሟያ ጽሑፋቸው ‹‹Ethiopia-Competing Ethnic Nationalisms and the Quest for Democracy, 1960-2000›› በሚል የታተመ ሲሆን፣ ይህንኑ መጠነኛ ማሻሻያ አድርገውበት ‹‹Ethiopia-From Autocracy to Reveolutionary Democracy 1960s - 2011›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን አቅርበውታል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር፣ በፓርላማ ቆይታቸው (ከ1998-2002 ዓ.ም.) እና ከጋዜጠኞች ጋር በሚያደርጓቸው ቃለ ምልልሶች ቀልድና ጨዋታ ጣል እያደረጉ በማዝናናት የሚታወቁት ዶ/ር መረራ፣ ከ28 ዓመታት በላይ ካስተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ክፍል ጋር ለመለያየት የተቃረቡ ይመስላል፡፡ ሰለሞን ጎሹ በግል ሕይወታቸውና መድረክ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው ማኒፌስቶ ዙርያ ዶ/ር መረራን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ለረጅም ጊዜያት ከቆዩ ግለሰቦች አንዱ ነዎት፡፡ በመጪው ምርጫም ተሳታፊ ነዎት፡፡ እስካሁን ድረስ የሄዱበትን የፖለቲካ ውጣ ውረድ በአጭሩ እንዴት ያስቀምጡታል?  
ዶ/ር መረራ፡- መጽሐፎቼ ላይ አስቀምጨዋለሁ፡፡ እስካሁን የነበረውን የፖለቲካ ጨዋታ፣ ለወደፊቱ ማየት እስከሚቻል ድረስ ሊኖር የሚችለውን ጨዋታ በግልጽ አስቀምጫለሁ፡፡ ውጣ ውረዱ ባለፉት አርባ ዓመታት ቀላል አልነበረም፡፡ በተለይ የእኛ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ያደገው ሙከራ አልተሳካለትም፡፡ ከትውልዱ በወጡ ሰዎች ጭምር ሙከራው ተጨናግፏል፡፡ እየሄድን ባለንበት መንገድ የትም የምንደርስ አይመስለኝም፡፡ መሠረታዊ የሆኑ የአገሪቱን ችግሮች በጋራ ለመፍታት ስምምነት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም የራሱ ችግር ቢኖረውም ኳሱ ያለው በገዥው ፓርቲ ሜዳ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ከ24 ዓመታት ጉዞ በኋላም ከጫካ እንደመጣ ነው የሚመስለው፡፡ ሥልጣን ወይም ሞት ነው እንጂ ከሌሎች የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር የመደራደርና ብሔራዊ መግባባት ላይ የመድረስ ምልክት አይታይበትም፡፡ መጪው ምርጫም የሚካሄደው በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሳንስማማ ነው፡፡ ለምሳሌ ስለ የሕግ የበላይነት፣ ስለ ሚዲያ አጠቃቀምና ስለ ምርጫ ቦርድ ሚና አልተስማማንም፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው የትግራይ ልሂቃን ሥልጣን ወይም ሞት ብሎ እስከቀጠለ፣ የአማራ ልሂቃንም የበላይነትን መልሰን እናገኛለን ብለው እስከገፉበት ድረስ፣ የኦሮሞ ልሂቃን ብቻችንን እንወጣለን [እንገነጠላለን] ብለው እስከገፉ ድረስ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከአደጋ ቀጣና አይወጣም፡፡ ኢትዮጵያ ወደፊት ሰላም፣ መረጋጋትና እውነተኛ ልማት እንድታመጣ የግድ የሦስቱ ብሔሮች ልሂቃን የሆነ ነገር ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ አለበለዚያ የአገሪቱ ሀብትና ልማት አንዱ ሌላውን ለመጨቆንና ለማፈን፣ አንዱ ሌላውን ከሥልጣን ለማውረድ እየተጠቀመበት የሚባክንበት ዕድል ነው የሚፈጠረው፡፡  
ሪፖርተር፡- በፖለቲካ ትግሉ ውስጥ እኔ በግሌ አደረግኩት የሚሉት ትልቁ አስተዋጽኦ ምንድነው?  
ዶ/ር መረራ፡- ተስፋ ሳልቆርጥ ሦስት መንግሥታትን መታገል መቻሌ ትልቁ አስተዋጽኦዬ ነው፡፡ ከአምቦ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ የአፄውን መንግሥት በደረጃዬ ለመቃወም ሞክሬያለሁ፡፡ በመኢሶን ዘመንም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊ እስከመሆን ደርሼ ነበር፡፡ በዚያም ወንድሜን መስዋዕት ማድረግ ብቻም ሳይሆን ለሰባት ዓመታት ውድ ሕይወቴን እስር ቤት አሳልፌያለሁ፡፡ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የተሻለ ስላልሆነ እየታገልኩት ነው፡፡ ሁለተኛው አስተዋጽኦ ተሳካም አልተሳካም የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ወደ መሀል መንገድ እንዲመጡና ሁሉንም በእኩልነት ሊያስተናግድ የሚችል ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር መታገሌ ነው፡፡ ይኼ ትግል የአንድ ብሔረሰብ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ሰፋ አድርጎ ያካተተ ነበር፡፡   
ሪፖርተር፡- በግልዎ ከኦነግ ጋር ያለዎት የፖለቲካ ልዩነት ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ከድርጅቱ ዋነኛ አንቀሳቃሾች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሌንጮ ለታ የአቋም ለውጥ አምጥተው ከድርጅቱ መለየታቸውን እንዴት አዩት?  
ዶ/ር መረራ፡- በዚያም ሆነ በዚህ ከዚህ በፊትም ብዙ የተወዛገብንበት ስለሆነ አስተያየት ባልሰጥ ይሻለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ኦፌኮ ዋነኛ ትኩረቱ ኦሮሚያ ነው፡፡ ፓርቲው በኦሮሞ ጥያቄ ላይ ያለው አማራጭ ምንድነው?  
ዶ/ር መረራ፡- የእኛ ዋነኛ ዓላማ ሀቀኛ ፌዴራሊዝም መፍጠር ነው፡፡ ይህም ሁለት ነገሮችን ይይዛል፡፡ ፌዴራሊዝም በማዕከል የጋራ መንግሥትና የጋራ ሥልጣን፣ በአካባቢ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች መጎናፀፍን ይጠይቃል፡፡ የኦፌኮ ዋና ዓላማ ከሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠርና የጋራና አካባቢያዊ ሥልጣንን ለመከፋፈል ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በዚህ መብት ነው ራሱን በራሱ የማስተዳደር ነፃነት የሚጎናፀፈው፡፡ በእኛ እምነት አሁን የጋራ ሥልጣንም የለም፣ ራስን በራስ ማስተዳደርም የለም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በማዕከላዊ መንግሥት ተገቢ የሆነ የሥልጣን ቦታ የለውም፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ እወክላለሁ የሚለው የኦሕዴድ የቀድሞ መሪዎች የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ጨምሮ የኦሮሞ ሕዝብ ተገቢ ቦታ የለውም ብለው እየተከራከሩ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመፍጠሩ ሚና ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ተገቢውን ሚና እንዲጫወት እንፈልጋለን፡፡  
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል በተለያዩ ፅንፍ ላይ ባሉ የፖለቲካ ኃይሎች ጤናማ ያልሆነ ፉክክር እንደሚገለጽ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ የዚህ ዋነኛ መነሻ ምንድነው? ከገዥው ፓርቲ ውጪ እናንተስ ለችግሩ የተጠያቂነት ድርሻ የላችሁም?  
ዶ/ር መረራ፡- ገዥው ፓርቲ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ የገዥው ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሁሉም ችግሮች እናት ሆኖ እያስቸገረን ነው፡፡ ችግሮችን በመፍጠርም ሆነ በመፍታት ዋነኛው ተጠያቂ ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የፅንፈኝነት ባህል ከሁለት መሠረታዊ ነገሮች ነው የመነጨው፡፡ አንደኛ ከኢትዮጵያ ባህል ይነሳል፡፡ የኢትዮጵያ ነገሥታትና የሥልጣን አያያዝ ሥነ ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ አልነበሩም፡፡ አንድ ንጉሥ ወደ ሥልጣን የሚመጣው በጠብመንጃ ነበር፡፡ ነገሥታቱ ለልጆቻቸው እንኳን ሥልጣን በሰላም ለቀው አያውቁም፡፡ ላለፉት 150 ዓመታት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተደርጎ አያውቅም፡፡ ከዚያ የአገዛዝ ባህል አልወጣንም፡፡ እርግጥ የተራው ሕዝብ ባህልና የአንዳንድ ማኅበረሰቦች የአገዛዝ ባህል ከዚህ የተለየ ነበር፡፡ ለምሳሌ የቦረና ኦሮሞ የገዳ ዴሞክራሲ ከኢሕአዴግ ዴሞክራሲ በጣም ይሻላል፡፡ ቢያንስ ስምንት ዓመት ጠብቆ በምርጫ ከሥልጣን ይለቀቃል፡፡ ከዘመናዊ ሕግ የተሻለ ችግሮቻቸውን ይፈቱበታል፡፡ አሁን አሁን ግን መንግሥት ጣልቃ እየገባ አባ ገዳዎችንም ወደ ካድሬነት እየለወጠ እያበላሸው ነው፡፡ 
ሌላው የፅንፈኝነት ምንጭ ባለፉት 40 ዓመታት ንቁ የነበረው ለውጥ ፈላጊ ትውልድ ነው፡፡ ሶሻሊስት ሆነንም ሆነ አሁን ዴሞክራት ሆነን ፅንፈኝነት አልለቀቀንም፡፡ በሶሻሊስት ትግል ዘመን ከኢዲዩ በስተቀር ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የሶሻሊዝም ተከታዮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን በመካከላቸው ደግሞ ስምምነት አልነበረም፡፡ አሁን ሁላችንም የምዕራቡ ዓለምን ፍልስፍና እንከተላለን እያልን በተመሳሳይ ስምምነት የለንም፡፡ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው ልሂቅ ሥልጣን ላይ እንዴት ልቆይ ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያን እንዴት ልለውጣት የሚል አስተሳሰብ የለውም፡፡ ዴሞክራት ሳትሆን እንዴት ዴሞክራሲን ትመራለህ? ለምሳሌ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንዳንድ የምንቃወማቸው ነገሮች ቢኖሩም ሰብዓዊ መብትን በማጎናፀፍ ደረጃ ብዙ ችግር የለበትም፡፡ በተግባር ይህ የማይፈጸመው ገዥው ፓርቲ ፅንፈኛ ኃይል በመሆኑ ነው፡፡ የሕወሓት ዴሞክራሲ የተወለደበት ትግራይ እንኳን ሰዎች ይህን ፅንፈኝነት እየተቃወሙ ነው፡፡ በሕወሓት ቁመት የተሰፋው ጥብቆ አልበቃቸው ብሎ እነ ተወልደ፣ ገብሩ፣ ስዬ፣ አረጋሽ ከፓርቲው ለቀዋል፡፡ ኢሕአዴግ የተወሰኑ ነገሮችን ከሶሻሊዝም፣ ሌላውን ከካፒታሊዝም እየወሰደ የፈጠረው ዲቃላ ሥርዓት ሕይወት ያለው ነገር አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ገዥው ፓርቲም ሆነ አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እኔ ብቻ ለችግሩ መፍትሔ እሰጣለሁ በሚለው የግራ ፖለቲካ በመመራት ፅንፈኝነትን ባህል እንዳደረጋችሁ ይተቻሉ፡፡ ችግሩ ከእናንተ ትውልድ ይመነጫል በሚለው ይስማማሉ?  
ዶ/ር መረራ፡- የ60ዎቹ ትውልድ በመከፋፈልና በመጠፋፋት ፖለቲካ መሳተፉ ስህተት ነው፡፡ አሁንም ያ ጥፋት ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን ያን ትውልድ የሚተቹ ሰዎች የተሻለ ሥራ እየሠሩ አይደለም፡፡ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ አላይም፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ዕውቀቱና ብቃቱ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ያ ትውልድ ቢያንስ የታገለው ለትርፍና ለራሱ ጥቅም አልነበረም፡፡ ራሱን ሳይለውጥ ነበር ኢትዮጵያን ለመለወጥ የተንቀሳቀሰው፡፡ እርግጥ ለዴሞክራሲ በማደረገው ትግል ውስጥ አሁንም ወጣቱ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ ዋነኛው ነገር የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ የዕድሜ ፖለቲካውን ቀውሳችን ውስጥ ባንጨምር ጥሩ ነው፡፡ ሁሉም ትውልድ የራሱን ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡ ለምሳሌ በእኛ ፓርቲ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ ራሳቸውን ከሚያገሉ በሚችሉት መጠን እንዲያገለግሉ ከነፕሮፌሰር ተሰማ ተአ ጋር በመሆን የአማካሪ ምክር ቤትን እየመሩ ነው፡፡ በሌላ በኩል ወጣት ሊግም አለን፡፡ ትግሉ ውስጥ በማንም ላይ በር አልዘጋንም፡፡ በእኛ ፓርቲ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ ፖለቲካውን መነገጃ እንዳያደርገው ግን ሥጋት አለኝ፡፡  
ሪፖርተር፡- ከመጪው ምርጫ በግልዎ ምን ይጠብቃሉ? ኦፌኮስ በኦሮሚያ ምን ዓይነት ውጤት ይጠብቃል?  
ዶ/ር መረራ፡- ለምርጫው በቂ ተወዳዳሪዎችን አቅርበናል፡፡ ኢሕአዴግ እንደሚለው ምርጫውን ነፃ፣ ሰላማዊና ገለልተኛ ካደረገ ኦሮሚያ ላይ ያለምንም ጥርጥር እናሸንፋለን፡፡ እንድናሸንፍ ኢሕአዴግ እያገዘን ነው፡፡ በኦሕዴድ ላይ የሚያደርሰው ጫና አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ-ኦሮሚያ ማስተር ፕላን ላይ የተነሳውን ውዝግብ ማንሳት እንችላለን፡፡ የትኛውም ከተማ ተፈጥሮአዊ ዕድገት ያመጣል፡፡ እሱን ትቶ በማስተር ፕላኑ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አርሶ አደሮችን ለመግፋት ነው የተሞከረው፡፡ የመሬት ንግድ ነው እየተካሄደ ያለው፡፡ ድሮም ኦሕዴድ የኦሮሞ ሕዝብ ድጋፍ አልነበረውም፡፡ አሁን ግን ራሱም ውስጥ ቀላል ያልሆነ ውጥረት እየፈጠረ ይመስላል፡፡ በቀላሉ ተማሪውንና ወጣቱን መያዝ ሲቻል በአምቦና በተለያዩ ከተሞች የተፈጠረው ግጭት አሁንም የበረደ አይመስለኝም፡፡ ከአምቦ በደቡብ ምዕራብ የሚገኘው ጥቁር እንጭኒ በግጭቱ ከታሰሩ ልጆች አንዱ እስር ቤት በመሞቱ ተማሪዎችና ፖሊሶች እየተጋጩ ነው፡፡ የት እንደሚቆም አናውቅም፡፡ እንዴት ተሰርቆ እንደወጣ ባላውቅም በቅርቡ አቶ ዓባይ ፀሐዬ ኦሕዴዶች ወደዱም ጠሉም ማስተር ፕላኑ ሥራ ላይ ይውላል ብለው በኢሕአዴግ ስብሰባ ላይ ሲያስፈራሩና ዕርምጃ እንደሚወሰድ ሲያስጠነቅቁ ሰምተናል፡፡ [አቶ ዓባይ ፀሐዬ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው የተሠራጨው ድምፅ የእሳቸው እንዳልሆነና ንግግሩን አለማድረጋቸውን መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል]   
ሪፖርተር፡- ነገር ግን ማስተር ፕላኑ በአዲስ አበባና በልዩ ዞን ምክር ቤቶች በተናጠል የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ስለማቀናጀት እንጂ ስለመስፋፋት አያነሳም፡፡ መንግሥትም የአዲስ አበባ ድንበር በግልጽ እንደሚታወቅና በአካባቢው የፖለቲካ ግጭት እንዲፈጠር የሚፈልጉ ኃይሎች ያሠራጩት የተዛባ መረጃ በኅብረተሰቡ ላይ ችግር እንደፈጠረ ይገልጻል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?  
ዶ/ር መረራ፡- ግጭቱ ሲፈጠር አሜሪካ ነው የነበርኩት፡፡ የኦሕዴድ አባላት ሲናገሩ እንዳየሁት ስምምነት ተደርጎበት የወጣ ማስተር ፕላን አይደለም፡፡ ይመስለኛል ኢሕአዴግ ሕዝቡንም ሆነ ኦሕዴድን በፓርቲ ደረጃ ሳያማክር ለተወሰኑ የኦሕዴድ አባላት ይኼን ታስፈጽማለህ ብሎ የሰጠ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ነው በቅድሚያ ተቃውሞ ያሰሙት የኦሕዴድ አባላት የሆኑት፡፡ እንዲያውም ኦሮሞነታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣላቸው በዚያን ጊዜ ነው፡፡ ሌላ ኃይል ነው የተዛባ መረጃ ያሠራጨው የሚለው ውኃ የሚቋጥር ነገር አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ መድረክ ያወጣው ማኒፌስቶ የገዥውን ፓርቲ ጉድለትና አድሎአዊ አሠራር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ከገዥው ፓርቲ ፖሊሲና አፈጻጸም አንፃር በመገምገም አማራጭ ፖሊሲና ስትራቴጂ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ለምን አላቀረባችሁም?  
ዶ/ር መረራ፡- አቅርበናል፡፡ ለምሳሌ ኢሕአዴግ ሥልጣን ለብቻ ጨምድዶ ሰላምና መረጋጋት በአገሪቱ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ እኛ ሥልጣን ብንይዝ ሁሉን አቀፍ የሆነ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንፈጥራለን፡፡ ኢሕአዴግ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዳይካሄድ እያደረገ ነው፡፡ ሰብዓዊ መብትን አያከብርም፡፡ ነፃ ፍርድ ቤት እንዳይኖር እያደገ ነው፡፡ ነፃ የመንግሥት ተቋማት እንዳይኖሩ እያደረገ ነው፡፡ እኛ ብንመረጥ ነፃ የመንግሥት ተቋማት ይመሠረታሉ፡፡ ሰብዓዊ መብት እናከብራለን፡፡ ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤቶችና ምርጫ ቦርድ እናቋቁማለን፡፡ በመሬት ጥያቄ ላይ መፈናቀልን እናቆማለን፡፡ በገበሬው ላይ ያለ አቅሙ እየተጨመረ ያለውን ግብር እንቀንሳለን፡፡ በኢሕአዴግ ሀቀኛ ነጋዴዎች እየተገፉ ወደ መንግሥት የተጠጉት ነጋዴዎች እየተጠቀሙ ነው፡፡ እኛ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት ተገቢና ተመጣጣኝ ቀረጥ ተቀንሶለት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነግዶ እንዲኖር እናደርጋለን፡፡ 
ሪፖርተር፡- በማኒፌስቶው ኢሕአዴግ የአገሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት በመቆጣጠሩ የተከሰቱ ተፅዕኖዎችን ዘርዝራችኋል፡፡ ዋና የሚባሉ ተፅዕኖዎች የትኞቹ ናቸው?  
ዶ/ር መረራ፡- የሁሉም ችግሮች እናት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ይኼ ርዕዮተ ዓለም ወይ አብዮት አልፈጠረም ወይ ደግሞ ሕዝቦች በነፃነት መብታቸውን እንዲያስከብሩ አላደረገም፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የፓርቲና የመንግሥት ሥራን ይቀላቅላል፡፡ በዚህም የመንግሥት ተቋማት የአንድ ፓርቲ ጉዳይ አስፈጻሚዎችና አገልጋዮች ሆነዋል፡፡ የፓርቲና የመንግሥት ሥራ መቀላቀል የሥልጣን ክፍፍሉን ጎድቶታል፡፡ ሦስቱ የመንግሥት አካላት [ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ] አንዱ ሌላውን ሊቆጣጠረው ይገባ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ግን የሥልጣን ክፍፍል የለም፡፡ ሥራ አስፈጻሚ የሚባለው ዳኛም ነው፣ ሕግ አውጪም ነው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የሥልጣን ክፍፍሉ የተሻለ ነበር፡፡ የሥልጣን ክፍፍል አንዱ አካል የፈለገውን እንዳያደርግ ገደብ ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ የመንግሥት አካላት የተሰጣቸውን ሥልጣን በተሰጣቸው ክልል ውስጥ እንዲጫወቱ ለማድረግ ያገለግላል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት የሚባሉትን እንደ ሚዲያና ሲቪል ማኅበራትን ኢሕአዴግ አንቋቸው በነፃነት መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ ነፃ ተቋማት ከሌሉ የዴሞክራሲ ምሰሶ የለም ማለት ነው፡፡ ኢሕአዴግ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን እከተላለሁ ቢልም፣ እንደ ኮሙዩኒስት ፓርቲ ውሳኔ አሰጣጡ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሥጋ ሰጥቶ ቢላዋ እንደ መከልከል ነው፡፡ በክልሎች ፕሬዚዳንቶችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚወጡትና የሚወርዱት በሕዝብ ፍላጎት ሳይሆን በገዥው ፓርቲ ፍላጎት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ዴሞክራሲ አልባ የሞግዚት አስተዳደር ነው፡፡ መንግሥት ሀብት ሲቆጣጠር ትንሽም ቢሆን ሁላችንም ድርሻ ይኖረናል፡፡ ነገር ግን ፓርቲው ሀብቱን ከተቆጣጠረ ተጠቃሚው የፓርቲ አባል ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ሀብት እንዳይኖራቸው ሕጉ ያግዳል፡፡ ኢሕአዴግ ግን የራሱ የቢዝነስ ኢምፓየር አለው፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች ሚዲያ በተለይ የብሮድካስቲንግ ሚዲያ እንዳይኖራቸው ሕጉ ያግዳል፡፡ ኢሕአዴግ ግን የራሱን ሚዲያ ያንቀሳቅሳል፡፡  
ሪፖርተር፡- በአንድ በኩል በተግባር ከኢሕአዴግ ጋር ተያይዘው የሚጠቀሱ ችግሮች አሉ፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት የሚመራባቸው ሕገ መንግሥቱና ሌሎች ተቋማዊ አሠራሮች ያመጧቸው ለውጦች አሉ፡፡ መድረክ ሕገ መንግሥቱ የኢሕአዴግ አባላትንና መሪዎችን መብት ብቻ እንዳስከበረ ገልጿል፡፡ ከዚህ ቀደም ሕገ መንግሥቱ የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ ለመመለስ ያደረገውን ዕርምጃ ታመሰግኑ ነበር፡፡ አሁን ግን የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ አልተመለሰም ብላችኋል፡፡ ስለሥርዓቱ ይዘት ነው ወይስ ስለአፈጻጸሙ ነው እያነሳችሁ ያላችሁት?  
ዶ/ር መረራ፡- ኢሕአዴግ መጀመሪያ ሲመጣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገባውን ቃል እያጠፈ ነው የመጣው፡፡ በሁሉም ነገር ወደኋላ እየተንሸራተተ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የፌደራል ሥርዓቱ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ እንደ ኦነግ ያሉ አቅም የነበራቸው ኃይሎች የነበሩ ቢሆንም ተገፍተው ወጡ፡፡ ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ራሱን ከማስፋት ይልቅ ይበልጥ እያጠበበ ነው፡፡ ከአሳታፊ ፖለቲካ ይልቅ የአንድ ቡድን አመራርን ነው ያሰፈነው፡፡ በተለይ ከ97 በኋላ ብዙ ኃይሎች ተስፋ እየቆረጡ ወደ ውጭ ተገፍተዋል፡፡ 
ሪፖርተር፡- በማኒፌስቶው ላይ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲነት የሚንቀሳቀሱ ነገር ግን በኢሕአዴግ የሚደራጁና የሚደገፉ አካላት እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡ እነዚህ የትኞቹ ፓርቲዎች ናቸው? ይህንንስ ለማለት ምን ማስረጃ አላችሁ?  
ዶ/ር መረራ፡- ሌሎቹ በደንብ ስለሚታወቁ መጥቀስ አያስፈልግም፡፡ ለምሳሌ ግን የቀድሞው የእኛ ፓርቲ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) በኢሕአዴግ እንደሚረዳ ማስረጃ አለኝ፡፡ አቶ ገብሩ አሥራትም በቅርቡ በጻፉት መጽሐፍ ላይ በኢሕአዴግ የደኅንነት ባለሥልጣናት በኩል ኢሕአዴግ እየከፈለ የሚያሠራቸው የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡  
ሪፖርተር፡- በርካታ ተቋማት ከኢሕአዴግ ተፅዕኖ ነፃ እንዳልሆኑ ጠቅሳችኋል፡፡ ነገር ግን ከምርጫው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤት ነፃ እንዲሆኑ ከአደረጃጀት አንፃር መድረክ ሥልጣን ቢይዝ ምን ያደርጋል?  
ዶ/ር መረራ፡- ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ምርጫ ቦርድን ወይ ከባለሙያዎችና ስለምርጫ ከሚያውቁ፣ ገለልተኝነታቸውን ሕዝብ ከመሰከረላቸው ሰዎች ታዋቅራለህ፡፡ በሁሉም ተፎካካሪ ወገኖች የሚታመኑ ባለሙያዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማ ይሾማሉ ነው የሚለው፡፡ ኢሕአዴግ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲመርጥ ነው ያደረገው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ሁለቱም ወገኖች አባል ሆነው የሚቆጣጠሩበት ሥርዓት ነው፡፡ ከሁለቱ አንዱ ነው የዓለም ተሞክሮ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አንድ ፓርቲ ዳኛም ተጨዋችም ሆነ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የምትሸነፍበት ዕድል የለም፡፡ በሽግግሩ መንግሥት እነ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የቦርዱ አባል ነበሩ፡፡ የፍርድ ቤቶችን ነፃነት በተመለከተ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ዳኞች የተሻለ ነፃነት ነበራቸው፡፡ በከፍተኛ ባለሥልጣናትና ደሃን በሚገፉ ላይ መፍረድ እንደ ትልቅ ጀግንነት ይቆጠር ነበር፡፡ ዳኝነትን ነፃ ለማድረግ ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች በመሆናቸው ቋሚ ኮንትራት እንዲሰጣቸውና ከፍተኛ የሆነ ወንጀል ካልሠሩ በስተቀር ነፃ ሆነው እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሕግና ሕግን ብቻ ተከትለው እንዲሠሩ ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የዳኞች ሥርዓትና የአስተዳደር ሁኔታ ሻል ይል ነበር፡፡ ነፃ ነበር ማለቴ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በተጨባጭ የሕዝቦችን ኑሮ እንዳላሻሻለ ገልጻችኋል፡፡ በምን መሥፈርት ነው እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሳችሁት?  
ዶ/ር መረራ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ ሁለት ዓለም እየተፈጠረ ነው፡፡ ሸራተን አዲስ ስትሄድ ከ250,000 ብር በላይ የሚሸጥ ልዊስ ፎርቲንዝ የሚባል ኮኛክ አለ፡፡ ከሸራተን አዲስ ጥቂት ሜትሮች ስትሄድ ከቆሻሻ እየለቀሙ ምግብ የሚበሉ ኢትዮጵያዊያን አሉ፡፡ አስደንጋጭ የሆነ የኑሮ ውድነት አለ፡፡ የታደሉ ሚሊየነር የሆኑ የኢትዮጵያ ልጆች የሉም ማለቴ አይደለም፡፡ ነገር ግን ወደ ድህነት ወለል እየወረደ የሚበላውን አጥቶ የሚንከራተት ብዙ ሕዝብ አለ፡፡ መጽሐፌ ላይ ያነሳሁትን ‘የሚበላው ያጣ ሕዝብ አንድ ቀን መሪዎቹን ይበላል’ የሚለውን አባባል ኢሕአዴግ ባይረሳ ጥሩ ነው፡፡ በደሃና በሀብታም መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት አደገኛ በሆነ ሁኔታ እየሰፋ ነው፡፡  
ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ግን የኢሕአዴግ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ደሃ ተኮርና ደሃውን የኅብረተሰብ ክፍል ከድህነት ለማውጣት ወይም ለመቀነስ ያነጣጠሩ ናቸው በሚል በየዓመቱ በሚያወጡት ሪፖርት ይገልጻሉ፡፡ ይህ የእናንተ ግምገማ ከእነዚህ ሪፖርቶች ጋር አይጋጭም?  
ዶ/ር መረራ፡- የእነዚህ ተቋማት ግምገማ ላይ ብዙ ጊዜ ተከራክረናል፡፡ ማነው ይኼን ዳታ የሚያመጣው? ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ወቅት ፓርላማ እያለሁ ዳታውን ማነው የሚጋግረው በሚል ጠይቄአቸው ነበር፡፡ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ጋርም ተከራክረናል፡፡ ዳታው የሚዘጋጀው በወረዳ ነው፡፡ ነፃ በሆነ አካል ተረጋግጦና ታምኖበት የተዘጋጀ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያዘጋጀው ነው፡፡ ፈረንጆቹ ሰፊ ጥናት አድርገው ሳይሆን 20 ወይም 30 ወረዳ ናሙና ወስደው የሚሠሩት ዳታ ነው፡፡ ዳታው ደግሞ ጥቅል ነው፡፡ ማን ምን ዓይነት ኑሮ እንደሚኖር አይገልጽም፡፡ የገንዘብ የመግዛት አቅም በጣም ወርዷል፡፡ የሕዝብ ኑሮ ነው ወይስ የከተማ ገጽታ እየተለወጠ ያለው? ከተማን ለማልማት ተብሎ የተወሰደው ዕርምጃ የብዙ ሺዎችን ሕይወት እያመሰቃቀለ ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- ከአማርኛ በተጨማሪ ብዛት ያለው ሕዝብ የሚናገረው ቋንቋ ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንደሚሆን ገልጻችኋል፡፡ በዚህ የመድረክ የቋንቋ ፖሊሲ የሥራ ቋንቋ ለመሆን የትኞቹ ቋንቋዎች ዕድል ይኖራቸዋል?  
ዶ/ር መረራ፡- እንደ አገሪቱ አቅም የሚወሰን ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚኛ፣ ከዚያ ቀጥሎ ትግርኛ፣ ከዚያ ቀጥሎ ሶማሊኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ኦሮሚኛ ከአማርኛ ጋር መምጣቱ ለብዙ ነገሮች የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ ለአገሪቱ የተሻለ ሰላም፣ አንድነት፣ መረጋጋትና አንድ የጋራ የፖለቲካ ኅብረተሰብ ለመፍጠርም ጠቃሚ ነው፡፡ ሁለቱን ቋንቋዎች የሚናገረው የሕዝብ ብዛት ከ70 በመቶ በታች አይሆንም፡፡ 
ሪፖርተር፡- ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ እንዲመጣ ያደረጉ አገሮች የኢኮኖሚው ተፅዕኖው ከባድ ሆኖባቸው ውሳኔያቸውን ለመከለስ ተገደዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋን ለመሸከም ዝግጁ ነው?  
ዶ/ር መረራ፡- የተወሰነ የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ማምጣቱ ምንም የሚያከራክር አይደለም፡፡ የእኛ ትውልድ እኮ ከሞላ ጎደል በአንድ ቋንቋ ይነጋገራል፡፡ ይኼ ችግር ካልተፈታ የሚቀጥለው ትውልድ እርስ በርሱ መነጋገር የማይችል ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ብዙ አካባቢዎች ስትሄድ ‘እኔ የቁቤ ትውልድ ነኝ አማርኛህን እርሳው’ ይልሃል፡፡ የዚህ ችግር ዋጋ ከኢኮኖሚ ተፅዕኖው የበለጠ ነው፡፡ ዜጎች ፈልገውና ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ሌላ ቋንቋ መማር የሚፈልጉበት ጊዜ ይመጣል፡፡ 
ሪፖርተር፡- በማኒፌስቶው ላይ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላሉ የምትሏቸውን ዝርዝር ዕቅዶች አስፍራችኋል፡፡ ዝርዝሮቹ ባለው አሠራር ላይ ማሻሻያ የሚያደርጉና ብዙ ወጪ የሚጠይቁ እንደ አዳዲስ ተቋማት ግንባታና አገልግሎቶችን መጨመር ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ወጪዎቹን በምን መንገድ ለመሸፈን አስባችኋል?  
ዶ/ር መረራ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ትልቁ ችግር የአገሪቱን ሀብት ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ አለማዋሉ ነው፡፡ ዕርዳታ እያገኘ ነው፣ ከግብር ገቢ እያገኘ ነው፡፡ ኢንተርናሽናል ኢንተግሪቲ ፈንድ ከኢትዮጵያ በአሥር ዓመት ውስጥ 11.7 ቢሊዮን ዶላር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንደወጣ ሪፖርት አድርጓል፡፡ ይኼ ሦስት የህዳሴ ግድብ ይሠራል፡፡ ችግሮቹ ያልተፈቱት በገንዘብ እጦት አይደለም፡፡ ያለውን የአገሪቱን ሀብት በተገቢው መንገድ ብትቆጣጠር ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ሶማሊያ በመግባታችንና ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው ግጭት አላስፈላጊ ወጪዎችን አውጥተናል፡፡ ባለው ሀብት የተሻለ ነገር መሥራት ይቻላል፡፡ ሌላ ሀብት አንፈጥርም ማለት አይደለም፡፡ እዚህ አገር ለውጭ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከዜጎች አራት እጥፍ ደመወዝ ነው የሚከፈለው፡፡ ነገር ግን አውሮፓና አሜሪካ የሚሠሩ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን በስደት ይኖራሉ፡፡ እዚህ አገር የተሻለ እየተከፈላቸው ቢሠሩ ስደትን አይመርጡም ነበር፡፡ ፖለቲካው ከተስተካከለ ንግዱ፣ ትምህርቱ፣ ልማቱና ብልፅግናው አብሮ ይስተካከላል፡፡  
ሪፖርተር፡- ከፖለቲካውስ ራስዎን የሚያገሉት መቼ ነው?  
ዶ/ር መረራ፡- አሁንም ቢሆንም ከፖለቲካው ጡረታ ብወጣ አልጠላም፡፡ ነገር ግን እኔን አምነው እዚህ ትግል ውስጥ የገቡ ሰዎች በተለይ ወጣቶች አሉ፡፡ አንዳንዶቹም እስር ቤት ነው ያሉት፡፡ እኔ ኑሮ አልተመቸኝም ብዬ ጥያቸው አልሄድም፡፡  

No comments:

Post a Comment