Pages

በ2007 በኢትዮጵያ የተካሄደውን ምርጫ በሚመለከት ከመድረክ የተሰጠ መግለጫ:- ሕገ-መንግሥታዊና ሕጋዊ የምርጫ ሥርዓት በተጣሰበት ሂደት የተከናወነው ሕገ ወጥ የምርጫ ድራማ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም!

June 29, 2015

ሕገ-መንግሥታዊና ሕጋዊ የምርጫ ሥርዓት በተጣሰበት ሂደት የተከናወነው ሕገ ወጥ የምርጫ ድራማ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም!

በሀገራችን ኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እውን ሆኖ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አማካይነት የሕዝባችን የሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥበት ሁኔታ በሕገ-መንግስቱ እውቅና ተሰጥቶት በይፋ ተደንግጎአል፡፡ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ሕገመንግሥቱንና የምርጫ ሕጎችን የጣሰ የምርጫ ድራማ በየ5 ዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሀገር ገንዘብ እያባከነ ያካሂዳል፡፡ ኢህአዴግ ይህንን የምርጫ ድራማ የሚያከሂደው፣ ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ ማካሄድ በዓለም አቀፍ ለጋሽ ዴሞክራሲያዊ ሀገሮች ዘንድ እውቅና የስገኝልኛል በሚል ተስፋ ነው፡፡ ተጨባጩ እውነታ የሚያሳየው ግን ኢህአዴግ በሥልጣን ላይ በቆየባቸው 24 ዓመታት ራሱ ያጸደቃቸውን ሕጋዊና ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በመርገጥ የራሱን አምባገነናዊ ገዥነት ለማስቀጠል እንዲያስችለው የሕዝብ ድምፅ መንጠቂያና ማፈኛ ሕገወጥ የምርጫ ስትራቴጂዎችን እያወጣና ሥራ ላይ እያዋለ መሆኑን ነው፡፡ የሕዝባችንን ድምፅ መቀማቱንና ማፈኑን በየምርጫ ዙሮቹ እያባባሰ መሄዱን ቀጥሎበት አሁን ለደረስንበት የ100 ፐርሰንት ቅሚያም ደርሶአል፡፡ በተለይም በ2007 ዓም በተካሄደው የ5ኛ ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ሕጋዊና ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በማንአለብኝነት በመጣስ በአጋርነት የፈረጃቸውን ፓርቲዎች አስከትሎና ሕዝቡንና ሐቀኛ ሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በኃይል አፍኖ ምርጫውን በሕገወጥ መንገድ መቶ በመቶ ለመቆጣጠርና ጠቅልሎ ለመውሰድ የፈጸማቸው አስነዋሪ ተግባራት ከአንድ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ከሚገኝ ፓርቲ የማይጠበቁ ናቸው፡፡ አገዛዙ በዚሁ ምርጫ ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ ከፈጸማቸው ሕገወጥ ተግባራት ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

1ኛ፡- የኢህአዴግ ካድሬዎች ከምርጫ ቦርድ በሚደረግላቸው ትብብር ብዛት ያላቸው የመራጮች ምዝገባ ካርደ እየተሰጣቸው አህአዴግን ይመርጣሉ ለሚሏቸው ቤት ለቤት በመዞር ለአንድ ሰው ከአስር ካርዶች በላይ ከተለያዩ ማስፈራሪያዎችና መደለያዎች ጋር ጭምር የምርጫው ዕለት ድረስ በማደል አንድ ሰው አንድ ድምጽ የሚለውን ሕግ በመጣስ ወንጀል ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ ተቃዋሚዎችን ይመርጣሉ ብለው የጠረጠሩዋቸውን በርካታ ዜጎችንም የምርጫ ምዝገባው ጊዜ ከማለቁ በፊት በምርጫ አስፈጻሚዎች #መዝገቡ ሞልቷል$ ወይም #ካርዱ አልቋል$ እየተባለ ሳይመዘገቡ እንዲቀሩ ተደርጓል፡፡ እንደዚሁም መድረክ በመረጃ የደረሰባቸውን ለሰው የታደሉ ትርፍ የመራጭ ካርዶችን ከመራጮች ምዝገባ ላይ ለማመሳከር ባደረገው ጥረት ካርዶቹ ተመዝግበው ያለመገኘታቸውን ማረጋገጡ፣ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ከፍተኛ ወንጀል እንደተፈጸመ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ አዋጅ 532/1999፣አንቀጽ 65 3ለ ላይ የሰፈረውን #እያንዳንዱ መራጭ በመራጮች መዝገብ ላይ ስሙ ሰፍሮ መገኘት አለበት$ የሚለውን ድንጋጌ መጣሱም ምርጫውን ሕገወጥ የሚያደርግ ነው፡፡

2ኛ፡- በየምርጫ ጣቢያዎቹ የሕዝብ ታዛቢዎች ተብለው የተሰየሙት ሰዎችም የምርጫ ደንብ በሚያዘው መሠረት፣ በምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች በደብዳቤ ተገልጾላቸው ተወካዮቻቸው በተገኙበት መመረጥ ሲገባቸው ያለተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፎ በአህአዴግ ደጋፊነታቸው የተመለመሉ መሆኑ ምርጫው ነፃና ታአማኒ እንዳይሆን ከመነሻው የተወጠነ ሕገወጥ አካሄድ ነበር፡፡

3ኛ፡- ገዥው ፓርቲ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ያለአግባብ በመጠቀም በየክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር ሕግ የተፈቀደውን የቅስቀሳ ጊዜ ፈቃድ ለመድረክ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ከልክሎ የኢህአዴግ አባላት የሆኑ ከፌዴራል እሰከ ወረዳ ደረጃ ያሉት እጅግ በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች ዕጩ ተወዳዳሪ ያልሆኑት ጭምር ከሙሉ ክፍያ ጋር ከመደበኛ ሥራቸው ነፃ ሆነው በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት በየተወለዱበት ወረዳዎችና ቀበሌዎች ተሠማርተዋል፡፡ ለምርጫ የተመዘገበውን ሕዝብም ቤት ለቤት እየዞሩ በማስፈራራትና በመደልል የንብ ምልክት ብቻ እንዲመርጡና መምረጣቸውንም ለኢህአዴግ ተወካዮች በግልጽ እያሳዩ ኮሮጆ ውስጥ እንዲጥሉ፣ ይህንን ካላደረጉ ግን ተቃዋሚዎችን እንደመረጡ እንደሚቆጠርና ተለይተውም እንደሚታወቁ በማስጠንቀቅና በማስፈራራት ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡ ለዚሁ ሕገወጥ ሥራ የተሰማሩት የኢህአዴግ አባላት የሆኑት የመንግሥት ሠራተኞች በብዙ አከባቢዎች የመንግሥት ተሸከርካሪዎችን ለምርጫ ቅስቀሳ በማንአለብኝነት ሲገለገሉበት ቆይተዋል፡፡

4ኛ፡- በምርጫው ሂደት በብዙ ምርጫ ክልሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የመድረክ ዕጩዎችና ቀስቃሾች ሲደበደቡና ከባድ ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ሲታሰሩና ለቅስቀሳ የሚጠቀሙባቸውን መሳረያዎች በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ሲነጠቁና ሲቀሙ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በደቡብ ክልል በጋሞጎፋ ዞን በዳራሞሎ ወረዳ 26፣ በዛለ ወረዳ 19፣ በካምባ ወረዳ 4፣በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ 2፣ በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን ዶሎ መና ወረዳ 40፣ በቦረና ዞን ቡሌ ሆራ ወረዳ 40፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦና ጀልዱ ወረዳዎች 27፣ በትግራይ ክክል በመቀሌ ከተማ 17 ፣ እስከአሁን በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩት በዋስ ተፈትው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

5ኛ፡- የዜጎችን ነፃና ምስጢራዊ የድምፅ አሰጣጥ መርሕ በመጣስ አንድ አባል 11 መራጮችን መልምሎ እንዲከታተልና ሕዝቡ በ1ለ5 ተጠርንፎ እስከ ምርጫ ጣቢያዎች ድረስ ተያይዞ በመሄድ ድምፅ እንዲሰጥ በገዥው ፓርቲ በተቀየሰው ስተራቴጂ ምርጫው እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ በአከባቢው በሌሉና በማይታወቁ ሰዎች ስምም የተመዘገቡ ካርዶችን በመጠቀም ምርጫው እንዲካሄድ አድርገዋል፡፡ ለምሳሌም በደቡብ ክልል በቀድዳ ጋሜላ ወረዳ ይህ ተፈጽሟል፡፡

6ኛ፡- በምርጫው ዕለት በአብዘኛው ምርጫ ጣቢያዎች የመድረክ ተወካዮች እንዳይገኙ በማባረር፣ በመደብደብና በማሰር ምርጫውን ታዛቢዎቻችን በሌሉበትና የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የሆኑት የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራር አባላት የምርጫ ጣቢያዎችን ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠሩበትና አዋጅ ቁጥር 532/1999 አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 3 በመተላለፍ ልዩ ኃይል ፣የፌዴራል ፖሊስና ታጣቂዎችን በሕዝቡ መካከል በብዛት በማሰማራት በህዝቡ ላይ የሥነ ልቦና ሽብር በፈጠሩበት ሁኔታ ምርጫው ሊካሄድ ችሎአል፡፡ ብዙ የምርጫ ጣቢያዎችንም በርካታ ታጣቂዎች ልዩ ትጥቅ አንግበው እንዲቆጣጠሩት ተደርጓል፡፡ ከበርካታ ምርጫ ጣቢያዎችም በየጣቢያዎቹ ተገኝተው የነበሩት ወኪሎቻችን እየተፈጸሙ ያዩትን የምርጫ ሕግ ጥሰቶች ለማሳረም ሲሞክሩ ተደብድበው ተባረዋል፡፡

7ኛ፡- በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሰነዶች፣ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች የምርጫ ጣቢያ የኮድ ማሕተሞችና የኮሮጆ ቁልፎች በሥርዓት ባልተያዙበትና ኮሮጆዎቹ ቀድመው ሞልተው ባደሩበት እንደዚሁም አዲስ የመራጭ ካርድም በአዲስ መልክ ሲታደል በነበረበትና የንብ ምልክት የተደረገባቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ከውጭ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየገቡ ጥቅም ላይ ሲውሉ በነበረበት ሁኔታ የድምፅ አሰጣጡ ተከናውኖአል፡፡

8ኛ፡- ለመድረክ ድምፅ የተሰጠባቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በብዛት ሽንት ቤት የተጣሉበትና የተቃጠሉበት ሁኔታ በብዙ አከባቢዎች ተከስቶአል፡፡ ለዚሁም ማስረጃ የሚሆኑ በርካታ ከሽንት ቤት የተሰበሰቡ ድምጾች ለአብነት በእጃችን ይገኛሉ፡፡

9ኛ፡- የመራጭ ምዝገባ አፈጻጸም መመሪያ 2/2000፣ አንቀጽ 13/7 # በአንድ ድምፅ መስጫ ጣቢያ ከ1000 በላይ ድምፅ አይሰጥም$ የሚለውን ድንጋጌ በመተላለፍ የኢህአዴግ ተወዳዳሪዎች ከ1000 በላይ ድምጽ እንዳገኙ ተደርጎ ይፋ መደረጉና ይህ እየታወቀ በምርጫ ቦርድም የእርምት እርምጃ አልተወሰደም፡፡

10ኛ፡- በቅድመ ምርጫም ሆነ በምርጫው ዕለት የተከሰቱ የሕግ ጥሰቶችና የኃይል እርምጃዎችን በሚመለከት መድረክ ከምርጫ ጣቢያዎች አንስቶ እስከ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድረስ ላሉት አካላት ያቀረባቸው ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ተገቢው መፍትሔ ሳይሰጣቸው ቀርቶ ችግሩ እየተባባሰ ገዥው ፓርቲ በወታደራዊ ኮማንድ ፖስት በመመራት የታጠቀ ኃይል በሰላማዊ ሕዝብ ላይ በማዝመት ጭምር ያከናወነው ምርጫ ሊሆን ችሎአል፡፡

11ኛ፡- በምርጫው ዕለት በኦሮሚያ ክልል በምራብ ሸዋ ዞን ሚዳ ቀኝ ወረዳ በአቶ ጊዲሳ ጨመዳ እና በምዕራብ አርሲ ዞን በቆራ ወረዳ በአቶ ገቢ ጥሴቦ ላይ ግድያዎች የተፈጸሙ ሲሆን፣ ከምርጫው በኋላም በምራብ ትግራይ ዞን በማይካድራ ከተማ በአቶ ታደሰ አብርሃና በደ/ብ/ብ/ሕ ክልል በሀዲያ ዞን በሶሮ ወረዳ በአቶ ብርሃኑ ኤረቦ በሚባሉ በምርጫው ሂደት ንቁ ተሳትፎ ባደረጉት የመድረክ ሰላማዊ ታጋዮች ላይ አሰቃቂ ግዲያዎች ተፈጽመዋል፡፡ በጋሞጎፋ ዞን በአርባ ምንጭ ምርጫ ክልልም በምርጫው እንቅስቃሴ ጠንካራ ተሳትፎ ባደረገውና በላካ ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ የመድረክ ወኪል/ታዛቢ በነበሩት በአቶ ዳንኤል ጉዴ ላይ በተደረገው የመግደል ሙከራ ከቤተሰባቸው ጋር እቤት ውስጥ ተኝተው እያሉ ቤታቸውን ከውጭ በገመድ አስረው በእሳት በማቃጠል ከነቤተሰባቸው ለመጨረስ ሙከራ የተደረገ ሲሆን የመድረክ አባሉና ቤተሰቡ በጎረቤት እርዳታ ሕይወታቸው ሲተርፍ ቤት ንብረታቸው በሙሉ ተቃጥሎ በአሰቃቂ ሁኔታ ሜዳ ላይ ቀርተው ይገኛሉ፡፡ የሰላም ታጋዩ በአሁኑ ወቅት ከቀበሌአቸው በኢህአዴግ ካድሬዎች የተባረሩ ሲሆን ከአቅመደካማና ቤቱ ከመቃጠሉ በፊት በካድሬዎቹ ክፉኛ ከተደበደቡት አሮጊት እናታቸው ጋር ወደ ቀበሌአቸውም እንዳይመጡ በካድሬዎች ተከልክለው እየተንከራተቱ ይገኛሉ፡፡

12ኛ፡- ከዚህ በላይ በአጭሩ ለመግለጽ በተሞከረበት ሁኔታ በምርጫው የሕዝቡን ድምፅ ጠቅልለው የወሰዱት የኢህአዴግ ካድሬዎች ይህ አስነዋሪ ተግባራቸው አልበቃ ብሎ ከምርጫው ማግስት ጀምረው በብዙ አከባቢዎች #ለመድረክ በታዛቢነት አገልግላችኋል፣ሕዝቡ መድረክን እንዲመርጥ ቅስቀሳ አድርጋችኋል፣ መድረክን መርጣችኋል$ ወዘተ ባሉዋቸው በርካታ ዜጎች ላይ የበቀል እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚሁም መሠረት በተለያዩ አከባቢዎች በርካታ አባሎቻችንን በማሰር፣ በመደብደብ፣ ቤታቸውን በማፍረስና በሐሰት ወንጅሎ በማስቀጣት፣ ከሥራቸውና ከትምህርት ገበታቸው በማባረር፣ የሥልጠና ዕድል በመንፈግና በመንግሥት ሥራ እንዳይቀጠሩም በመከልከል እንደዚሁም በገጠር በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ አባሎቻችን የሰፍትኔት ዕርዳታና ሌሎች መንግሥታዊ እርዳታዎችንና አገልግሎቶችን እንዳያገኙ በማድረግ ወዘተ የዜግነት መብታቸውን ነፍገው እያሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቻችንንም በግድ ዝጉ በማለት እያስፈራሩ በማዘጋት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌም በምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ሮቢ ወረዳ በ16/10/07 በወረዳው አስተዳዳሪና በወረዳው ፖሊስ አዛዥ በተሰጠ ትዕዛዝ የኦፌኮ/መድረክ ቅ/ጽ/ቤት ተዘግቷል፡፡

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትና በገዥው ፓርቲ የተፈጸሙት ተግባራት በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ 1 #የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በምስጢር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት አመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ&$ ተብሎ የተደነገገውን የጣሰ ነው፡፡ እንደዚሁም የየክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫን በሚመለከትም በየክልላዊ መንግሥታቱ ሕገመንግሥታት በተመሳሳይ የተደነገጉትን፣ በተሻሻለው የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 አንቀፅ 26 በሰፈሩት የምርጫ መርሖዎችም #ማንኛውም ምርጫ ሁሉአቀፍ፣ ቀጥተኛ፣በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነፃነት የሚገለጽበት እና ያለምንም ልዩነት በእኩል ሕዝባዊ ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ ይሆናል& የመምረጥ መመረጥ መብቱ በሕግ ያልተገደበ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብት አለው& እያንዳንዱ መራጭ የሚሰጠው ድምፅ እኩል ነው& ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ አይገደድም&$ ተብሎ የተደነገገውንም የጣሰ ነው፡፡ በተጨማሪም በሀገራችን የምርጫ ሥነምግባር ሕግ አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ 1 ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀምን አስመልክቶ #ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፡- ያለውን የሥልጣን ኃላፊነትና የተለየ ዕድል ወይም ተፅዕኖ የማሳደር ችሎታ ለፖለቲካ ፍላጎቱ ለመጠቀም መደለያ ማቅረብን፣ ቅጣትንና ማንኛውንም የማስፈራሪያ መንገድ መጠቀምና የፈዴራል መንግሥትን፣ የክልል መንግሥታትን፣ የከተማ ማዘጋጃ ቤትን ወይም ሌላ የሕዝብ ሀብትን በምርጫ ሕጉ ከተፈቀደው አኳኋን ውጭ ለምርጫ ቅስቀሳ ዓላማ መጠቀም የለበትም&$የሚለውንም ድንጋጌ ያላከበረ ነው፡፡ የመንግሥት ሠራተኞችና ንብረት በሚመለከትም የመንግሥት ሠራተኛና ኃላፊ ሆኖ በራሱ የግል ጊዜ ካልሆነ በስተቀር በመንግሥት የሥራ ሰዓትና ኃላፊነት ተቋሙን በመጠቀም እጩዎችን ያስተዋወቀ ወይም ሌሎች እጩዎች ራሳቸውን በሕጋዊ መንገድ ለማስተዋወቅ ያላቸውን እድል ያደናቀፈ፣ በመንግሥት ንብረት ለምርጫ ቅስቀሳ የተጠቀመ፣ እንደሆነ የሥነምግባር ጥሰት እንደፈጸመ ይቆጠራል& ተብሎ በአንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 7 እና 8 የተደነገገውን በመጣስ የተፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት ናቸው፡፡

በአጠቃላይም በ2007 ዓ ም በሀገራችን ተካሄደ የተባለው ምርጫ በሕግና ሥርዓት ያልተመራና በሕገ-መንግሥቱና በምርጫ ሕጎች የተደነገጉትን የነፃ፣ፍትሐዊና ታአማኒነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መርሖዎች በኃይል በተጣሱበት ሁኔታ የተፈጸመ በመሆኑ መድረክ የምርጫውን ሂደትም ሆነ ውጤት የማይቀበለው መሆኑን እየገለጸ፣ ለዚህ አሁን ሀገራችን ለገባችበት አስቸጋሪ ሁኔታ መፍትሔ ለማስገኘት የሚከተሉት እርምጃዎች እንዲወሰዱ በጥብቅ ይጠይቃል፡፡

1ኛ፡– በ2007 ዓ ም የተካሄደው 5ኛ ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ሂደትና ክንዋኔ በአጠቃላይ የሀገሪቱን ሕገመንግሥትና የምርጫ ሕጎች በጣሰ ሁኔታ የተከናወነ ስለሆነ፣ ይህንን ግዙፍ የሕግ ጥሰት አንድ ወገንተኛ ያልሆነ አካል ተቋቁሞ እንዲያጣራው፣

2ኛ፡- ከዚህ በላይ በተጠቀሱት አራት አባሎቻችን ላይ ግዲያ የፈጸሙ ወንጀለኞች ተገቢው ክትትል ተደርጎ ለሕግ እንዲቀርቡና ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው፣

3ኛ፡- ከምርጫው ቅስቀሳ ወቅት ጀምሮ በየምርጫ ክልሎቹ የታሰሩት አባሎቻችን ካለአንዳች ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱና የድብደባና የማሰቃየት ተግባራትን የፈጸሙባቸው የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣

4ኛ፡- ከምርጫው እንቅስቃሴ ወዲህ ቤታቸው የተቃጠለባቸው፣ የፈረሰባቸውና ንብረታቸው የተዘረፈባቸው አባሎቻችን ሀብትና ንብረት በአስቸኳይ እንዲመለስላቸውና እንዲከፈላቸው፣ በንብረታቸው ላይ ጉዳት ያደረሱ ካድሬዎችና የጸጥታ ኃይሎች አባላትም በሕግ እንዲጠየቁ፣

5ኛ፡- በአሁኑ ወቅት በኢህአዴግ ካድሬዎች በማንአለብኝነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየፈጸሙ የሚገኙት የማሸበር ተግባራት ማለትም በሰላማዊ ታጋዮቻችን ላይ በቀጣይነት እየተፈጸሙ ያሉት ግዲያዎች፣ ማስፈራራት፣ ወከባዎች፣ ዛቻዎችና የመሥራትና የመማር እንዲሁም እርዳታና አገልግሎት የማግኘት መብት በመንፈግ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት በአስቸኳይ እንዲቆሙ እንዲደረግና በዚህ አፍራሽና ፀረ ሰላም ተግባራቸው ምክንያት የሀገራችንና የሕዝባችን ሰላምና ደህንነት እንዳይናጋ ወቅታዊ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ፣

6ኛ፡- በ2007 ዓ ም በሀገራችን የተካሄደው ምርጫ ከሀገራችን ሕገ-መንግሥትና የምርጫ ሕጎች ውጭ መንግሥታዊ ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ሕዝብን በማስፈራራት፣ በኃይልና በአፈና ገለልተኛ ታዛቢዎች በሌሉበት ገዥው ፓርቲ ራሱ ተወዳዳሪ፣ ዳኛና ታዛቢ ሆኖ ያካሄደውና በምንም መልኩ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ያልሆነና ታአማኒነት የሌለው ሕገወጥ ምርጫ ስለሆነ፣ገዥው ፓርቲ በገለልተኛ የምርጫ አስተዳዳር አማካይነት ገለልተኛ ታዛቢዎች በተገኙበት ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነና ታአማኒነት ያለው ምርጫ ሊካሄድ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከመድረክና ሌሎች ሐቀኛ ሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአስቸኳይ በመደራደር ለነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክርሲያዊና ታዓማኒነት ላለው ምርጫ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

7ኛ፡- በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲረጋገጥ ሕጋዊ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ፣ እንደዚሁም ነፃ ፍትሐዊ ተዓማኒ ምርጫዎች ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይሳተፉ እንቅፋት የሆኑ ሕጋዊና ተቋማዊ ሁኔታዎችን ለማስወገድ ከኢህአዴግ ጋር የሚካሄድ ድርድርና የሌሎች ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎች ውጤት በቀጣዩ ለመድረክ በምርጫዎች መሳተፍ ወሳኝ ይሆናል፡፡ ይህ የሰላማዊ መፍትሔ እርምጃ ከዚህ በፊት በኢህአዴግ አሻፈረኝ ባይነት ተቀባይነት አጥቶ ችግራችን እየተባባሰ እንዲሄድ ሲደረግ እንደቆየው ሁሉ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጥሎ የሀገራችን ችግሮች እየተወሳሰቡና ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ ከሄዱ ኃላፊነቱ የኢህአዴግ ብቻ እንደሚሆን በቅድሚያ መግለጽ እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም ነፃ፣ ፍትሐዊና ታአማኒ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለዘመናት ሲትናፍቅና ስትታገልለት የኖርከው ሰላም ወዳዱ መላው የሀገራችን ሕዝብ መድረክም ሆነ አባል ድርጅቶቹ በኢህአዴግ የ24 ዓመታት አገዛዝ በሀገራችን በተካሄዱት ምርጫዎች በመሳተፍና የሀገራችንን ችግሮች በሰላማዊ ውይይት ለመፍታትና የሕዝባችንን የሥልጣን ባለቤትነት በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለማረጋገጥ ባካሄድናቸው ጥረቶች የኢህአዴግን በርካታ የግፍ ተግባራት በከፍተኛ ትዕግሥትና አርቆ አስተዋይነት ተቋቁመህ ከጎናችን በመሰለፍ ላበረከትከው አስተዋዖና ለከፈልከው መስዋዕትነት መድረክ ያለውን ታላቅ አክብሮትና ልባዊ ምስጋናውን ይገልጻል፡፡ የኢህአዴግ አገዛዝ ኃላፊነት በጎደለውና ሕግንና ሕገ-መንግሥትን በጣሰው እርምጃው የነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫን መንገድ ሙሉ በሙሉ በኃይል የዘጋብን ቢሆንም፣ በሀገራችን ሕገመንግሥት የተረጋገጡትና ገና ያልተጠቀምንባቸው የሰላማዊ የትግል ፈርጆች በርካታ ስለሆኑ በሰላማዊ የትግል አማራጫችን ጸንታችሁ አምባገነኑ የኢህአዴግ አገዘዝ ለሕግ የበላይነት እስኪገዛና ሰላማዊ የመፍትሔ ሐሳቦችን ተቀብሎ ሕገመንግሥታዊ መብቶች በተግባር እስኪረጋገጡ ድረስ ሰላማዊ ትግላችሁን ይበልጥ በተደራጃና በተጠናከረ መልኩ እንዲትቀጥሉ መድረክ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ድል ለሕዝባዊ ትግላችን!!

መድረክ
 

ሰኔ 19 ቀን 2007 ዓ.ም.
Finfinnee/አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment