Pages

ባለፈረጀ ብዙውን የኢትዮጵያ መንግሥት የስለላ ተግባር መከላከል፤ እራስን ከስለላ የመከላከያ ብልሃቶች መመሪያ በአማርኛ ተዘጋጅቷል

October 04, 2015 | BY ENDALKACHEW CHALA

ከቴሌኮሙኒኬሽን እስከ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ስርጭት ያሉ የሕዝብ መገናኛዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ናቸው። ይህም መንግሥት በአጠቃላይ የመገናኛ የልማት አውታሮች ላይ ሙሉ የበላይነቱን መያዙ፤ ግላዊነት እና ሌሎች ግንኙነቶች በግልጽ ለስለላ ምቹ ኾነዋል ማለት ነው። በአንዳንድ አጋጣሚዎች የመንግሥትን የተጠናከረ እና ውስብስብ የስለላ መረብ አልፈው የሚደረጉ ግንኙነቶች ቢኖሩ እንኳ በየመንደሩ ያሉ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ጆሮ ጠቢዎች በኢትዮጵያን ላይ የሚዘሩት ፍርሃት ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ያህል አጠቃላይ አገራዊ ስምምነት የተደረሰ በሚመስል መልኩ፤ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩ ግለሰቦች ድምጻቸውን የሹክሹክታ ያህል አሳንሰው ሲያወሩ ማየት ያልተለመደ አይደለም። በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ የራስ ትከሻን እየተጠራጠሩ ማውራት ወይም በታክሲ እንዲሁም በሻይ ቤቶች ቁጭ ብለው የሚወያዩ ሰዎች አፋቸውን ከልለው ማውራታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። በዚህም አስፈሪ እና ዝግ በኾነ ምህዳር ምክንያት ዜጎች ዝምታን መርጠዋል። ዝምታውም ከቁጥጥራቸው በላይ የኾነውን ስለላ በተቃውሞ መግለጻቸውን ዋነኛ ማሳያ ነው። “ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባም” መሠል አባባሎች አሁን የሚታየውን የፍርሃት ጥግ የሚገልጹ ናቸው። 

አጠቃላይ አፈናው ፈርጀ ብዙ ነው፤ መንግሥት ላይ ያላቸው ልዩነት በሰላ ብዕር የሚከትቡትን ጦማሮች እና ድረ ገፆች ያግዳል፣ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የስለላ ሶፍትዌሮችን በመግዛት በአገር ውስጥም ኾነ ባህር ማዶ ያሉ ዜጎቹን ይሰልላል እንዲሁም ምስጠራን የሚያግዙ መመሪያዎችን ተጠቅማችኋልም ብሎ ጦማሪያንን ያስራል። በአሁኑ ጊዜ የሃሰት ስሞችን ወይም የብዕር ስሞችን መጠቀም ልክ በአደባባይ ሲያወሩ ኋላ እና ፊትን ገልመጥ እያሉ ወይም አፍን ከለል አድርጎ ማውራት ዓይነት በመስመር ላይ ግንኙነት የሚስተዋል ጠባይ ኾኗል። ብዙዎች ማንነታቸውን ለአደጋ የማያጋልጡ የሃሰት ስሞችን ካልተጠቀሙ በስተቀር የማህበራዊ ገጾች ተሳትፏቸው እጅግ ዝቅተኛ ነው። ፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ላይ አስተያየት አይሰጡም፣ አያካፍሉም ወይም ማንበባቸውን የሚጠቁም ምልክት አያሳዩም። የመንግሥት ሥርዓት የለሽ ክስ እና እስራት (በርካታ ጦማርያን እና ጋዜጠኞች እንዲሁም የማኅበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ሃሳባቸውን ብቻ በመግለጻቸው በግፍ መታሰር እና መወንጀል) ለብዙሃን ፍርሃት ምክንያት ኾኗል።
ይሁንና ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ችግሩ ውስብስብ ኾኖ ይታያል። የሃሰት ስሞችን ተጠቅሞም በአደባባይ ሃሳብን መግለጽ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ዋስትና ላይኖረው ይችላል። ለምሳሌ ያህል በአሜሪካ አገር መቀመጫውን ያደረገው የኢትዮጵያዊው የተመሳሳይ ጾታ መብት አቀንቃኝ የፌስቡክ ገጽ ከተጠቃሚዎች በተላኩ በርካታ መልዕክቶች በሚል ሰበብ እንዲዘጋ ተደርጎ ነበር። ፌስቡክ የተላኩለት መልዕክቶች ጥላቻን መሠረት አድርገው የተፈበረኩ መኾናቸውን ተረድቶ ገጹን በመጨረሻ ለባለቤቱ ቢመልስም፤ አጋጥሚው ግን የስውር ስም ወይም ምስጢራዊነትን መጠቀም ብቻውን የመንግሥትን አፋኝነት ጥሶ ለማለፍ በቂ አለመኾኑን አሳይቷል።
ራስን ከስለላ የመከላከያ ብልሃቶች መመሪያ በአማርኛ እንደ መፍትሄ?
ይህንን የስለላ መከላከያ ብልሃቶች መመሪያ ለመተርጎም ሞያዊ እና ግለሰባዊ ምክንያቶች ነበሩኝ። በመጀመሪያ ደረጃ ውስብስብ እና ሕገ-ወጥ የኾነው የስልክ መጥለፍ ስለላ ተጠቂ ነኝ። በ2005 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት መንግሥት ስልኬን ጠልፏል። ይህንንም የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ባልደረቦቼን እና ወዳጆቼን ሕጋዊ ባልኾነ መንገድ ለመወንጀል ተጠቅሞበታል። እንዴት የስልክ አገልግሎት ሰጪው ኢትዮቴሌኮም ስልኮች እንዲጠለፉ ለመንግሥት ፍቃዱን ሰጠ ብለው ለሚጠይቁ የዋህ አንባቢዎች መልሱ ግልጽ ነው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አገልግሎት ሰጪ ሲኾን ያለው ንብረትነቱም የመንግሥት ነው። በዚህም ምክንያት የማንኛውም ግለሰብ የስልክ ግንኑኘት መንግሥት በፈለገው ግዜ ሁሉ ይጠለፋል።  ይህ ወደ አማርኛ የተረጎምኩት የስለላ መከላከያ መመሪያ ችግሩን ሁሉ ይቀርፋል ብዬ ባልናገርም፤ የሚልዮኖችን ግላዊነት ለማስጠበቅ ግን አንዱ እርምጃ ነው የሚል ዕምነት አለኝ። በአንድ በስለላ በተከበበ ሥርዓት ውስጥ እንደመኖሬ መጠንም መመሪያውን በአገራችን ቋንቋ ማዘጋጀቱ የእኔም ኃላፊነት እንደኾነ አስባለሁ። ስለዚህም መመሪያውን ወደ አማርኛ መመለሱ በሕይወቱ የስለላን አስከፊነት የተገነዘበ ወይም የሥርዓቱ ሰለባ የኾነ ግለሰብ የሰጠው ምላሽ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ዘወትር በመንግሥት የስለላ መረብ ውስጥ ሌት ተቀን መከራቸው ለሚያዩ ዜጎች የሚደረግ አንዱ የድጋፍ ዘመቻ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዘመነው ዓለም ጥቂት ዓመታትን እንደማስቆጠሬ እራሴን የኢትዮጵያ የዲጂታል ከባቢ “አንትሮፖሎጂስት” አድርጌ እቆጥረዋለሁ። ኢትዮጵያ ለሰዓታት አልፎም ለቀናት የኤሊክትሪክ ኃይል የሚቆረጥባት ስትሆን በርካቶች የኢንተርኔት አገልግሎት ለማግኘት ኢንተርኔት ካፌዎችን የሚያጨናንቁባት አገር ናት። ኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጡ ሳይበግራቸው ለሰዓታት በኢንተርኔት ካፌ ውስጥ የሚገለገሉ በርካቶች ናቸው። አዲስ አበባ በነበርኩበት ወቅት በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ሳይዘጉ የተተዉ የሌሎች ሰዎችን ፌስቡክ እና ኢሜል የመዝጋት ኃላፊነት አጋጣሚዎች ነበሩኝ። ብዙዎች ስለድረገጽ የደህንነት ጉዳዮች በቂ መረጃ እንደሌላቸው ተገንዝብያለሁ። ከአስተዋልኳቸው የተጠቃሚዎች ደካማ የድረገጽ አጠቃቀም ጠባይ የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው። የድር ማሰሻውን ድርብርብ በኾነው ማመስጠሪያ አለመጠቀም፣ ለሁሉም የመስመር ላይ ግንኙነት ተመሳሳይ ወይም ደካማ የኾኑ ማለፊያ ቃላትን መጠቀም፣ ደህንነቱ ያልጠረጋገጠ ድረ ገጽ መክፈት፣ ስምምነቶችን እና የደረገጽ ደንቦችን በወጉ ሳያስተውሉ መፈረም እንዲኹም ለሰርጎ ገቦች መረጃን አሳልፎ መስጠት እና የመሳሰሉት። እንደዚህ ዓይነት ስህተቶች ይህን የአማርኛ ትርጉም የበለጠ አስፈላጊ ያደርጉታል። በተጨማሪም ዊኪ ሊኪስ በቅርቡ ኢትዮጵያ ከሃኪንክ ቲም ውድ የኾነ የስለላ ሶፍትዌር መግዛቱን እነደዘገበው ሁሉ መንግሥት ዜጎቹን ለመሰለል ብዙ ገንዘብ ያወጣል እና እንዲህ ዓይነቱ መመሪያ መዘጋጀቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ይህንን መመሪያ በአማርኛ በማተምም፣ በሚያካሂዳቸው መጠነ ሠፊ የስለላ ወንጀል የኢትዮጵያ መንግሥትን ለፍርድ ለማቅረብ ኢ.ኤፍ.ኤፍ የሚያደርገውን ጥረት ያጎላዋል።
ስለ ትርጉም ሥራው
እራስን ከስለላ የመከላከያ ብልሃቶች መመሪያ ውስብስብ ጉዳይ ነው። ይኹንና መመሪያውን በጥልቀት በማንበብ እና ተግባራዊ ሙከራዎችን በማድረግ የአማርኛው መመሪያ ይበልጥ ተነባቢ እና ቀላል እንዲኾን ጥረት አድርጊያለሁ። ማንኛውም አንባቢ እንደሚረዳው አማርኛችን በቴክኖሎጂ ቃላት የበለጸገ አይደለም። ለምሳሌ ያህል በኢንክሪፕሽን እና በክሪፕቶግራፊ ያለውን ልዩነት በአማርኛ ለማስቀመጥ ይቸግራል። እንዲህ ዓይነት ጉዳይ በሚያጋጥም ወቅትም በአውደ ንባቡ አንባቢ እንዲረዳው ተጨማሪ ማብራሪያ እንድጽፍ አስገድዶኛል። እንዲሁም እንደ ኦፕን ሶርስ፣ ዳታ፣ ሊንክ፣ ዳታ ቢዝ፣ እና ዶሜይን ኔም የመሳሰሉት የቴክኖሎጂ ቃላት ሲያጋጥሙኝ የአማርኛ-ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት እንዲሁም መደበኛውን የአማርኛ-እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት በመጠቀም ፍቻቸውን አስቀምጫለሁ። በተጨማሪም “ጌይ” የሚለውን ያለ ምንም ቅጥያ ለማስተዋወቅ ስለፈለግሁ “ሓዋረ ብእሲ” የሚለውን ፍቺ ከዎልፍ ሌስላው ግዕዝ-እንግሊዝኛ መዝገባ ቃላት ተጠቅሚያለሁ። ይህም በኢትዮጵያዊው ጦማር ላይ ተጠቅሶ ይገኛል።
ማጠቃለያ
ግለሰቦች የመስመር ግንኙነታቸውን ደህንነት እንዲጠብቁ ማስተማር አንዱ የግላዊነት መብት ተከራካሪነት ተግባር ነው። መንግሥት እና የሕግ አስፈጻሚው አካል እንደ ሕግ ስለላን ወስደው ዜጎችን በቁጥጥር ውስጥ በሚያስገቡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ደግሞ አስፈላጊነቱ የጎላ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ስለላ የሚያካሂደው ለዜጎቹ ደህንነት አስቦ እንደኾነ በመከራከል ለማሳመን ይሞክራል። እውነታው ይህ እንዳልኾነ ጸሐይ የሞቀው ጉዳይ ቢኾንም። ይህ የአማርኛ መመሪያ ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲቆዩ ግላዊነትን መመሪያቸው እንዲያደርጉ ይመክራል፤ ያስተምራልም።

No comments:

Post a Comment