Pages

ወሎና ፖለቲካ-ወለድ ረሃብ ከድሮ እስከ ዘንድሮ

November 13, 2015 | በቦሩ በራቃ
ethiopia_drought_cows_2012_8_21ረሃብ ኢትዮጵያ ውስጥ በተሰማ ቁጥር የወሎው ወገናችን ስም ሁሌም ቀድሞ ይነሳል። ከ40 ኣመት በፊት የጀመረው ይህ በገዢዎች ሆን ተብሎ ትኩረት የተነፈገው ፖለቲካ-ወለድ የረሃብ ኣዙሪት ዛሬም ድረስ ቀጥሏል። ያኔ ንጉሱ የ80 ኣመት ልደታቸውን ያከብሩ ነበር። በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከድሃ ኣገር ካዝና አየወጣ እንደ ውሃ ይረጫል። ድግስ ከበርቻቻው በቤተ መንግስቱ ድምቁዋል። ንጉሱና ባለሙዋሎቻቸው በፌሽታ ግለው ነፍሳቸውን ኣያውቁም። የየኣገር ግዛቱ ትልልቅ ፊውዳሎች ሁሉ የንጉሱ ድግስ ታዳሚዎች ናቸው። ትንንሽ ፊውዳሎችም ቢሆኑ እስከ ቤተ መንግስት ድረስ የመጋበዝ እድል ቢያጥራቸውም ባሉበት ትንንሽ ቤተመንግስቶቻቸው ነግሰው ቢያንስ በሬ ጥለው የንጉሱን 80 ኣመት የልደት በኣል ሻማ ለኩሰዋል፣ ግብር ኣብልተዋል። ንጉሱ በልደታቸው በኣል በውሻቸው ስም ሳይቀር ሙክትና በሬ ኣስጥለዋል፣ የልደት ኬክም ኣስርተዋል። በገዢዎች መንደር ይህን የመሰለ ድግስ ፈንጠዝያው ሲቀልጥ ታዲያ በሚሊዮን የሚቆጠረው የወሎ ህዝብ ግን ኣስታዋሽ ኣጥቶ በረህብ እንደ ቅጠል እየረገፈ ነበር። በገዢዎቹ መንደር ውሾችና ድመቶች ቡርንዶ ስጋ ጠግበው ሲጠየፉ ወሎ ውስጥ ግን የሰው ልጅ እፍኝ ቆሎ ኣጥቶ እስከወዲይኛው ኣሸለበ። የወቅቱን ረሃብ ፖለቲካ-ወለድ የሚያስብለውም ይሄው ነው።

ደርግ በበኩሉ ስልጣን በሃይል የያዘበትን 10ኛ ኣመት በሚሊዮን የሚቆጠር የድሃ ኣገር ገንዘብ እንዳሻው በትኖ ሲያከብር ወሎ ውስጥ ብቻ በየቀኑ ሺዎች በረሃብ ኣደጋው ደራሽ ኣስታዋሽ ኣጥተው ህይወታቸው እየተቀጠፈ ነበር። ደርግ በረሃብ ኣደጋው ላለቁትና ለተጎሳቆሉት ወገኖች የሚያዝን ኣንጀት ኣልነበረውም። የህዝብ መራብ ዜና ተነግሮበት የበኣሉን ድባብ እንዲያጨግግበት ኣልፈለገም።  የረሃብ ኣደጋውን ግዝፈት በወቅቱ የቢቢሲው ጋዜጠኛ ማይክል በርክ በሰራው በዚያ ታሪካው ሪፖርቱ ለኣለም ህዝብ ባያጋልጥና እንደ ባንድ ኤይድ ያሉት ታሪካዊ ኣለም ኣቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴዎች ባይደረጉ ኖሮ ደርግ ኣደጋውን ሸፋፍኖ ሊያስቀረው ኣስቦ ነበረ። ይሄኛውም ኣይን ያወጣ ፖለቲካ-ወለድ ረሃብ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር ኣይደለም። የረሃቡ መንሲኤ ድርቅ መሆኑ ባያጠያይቅም መንግስት ነኝ ባዩ ኣካል ኣፋጣኝ እርምጃዎችን ወስዶ ረሃቡ ወደ ገዳይ ኣደጋነት ከመሸጋገሩ በፊት የዜጎችን ህይወት ማዳን ይችል ነበር።
ዛሬም በወያኔ ዘመን ረሃብ ደጋግሞ እየጎበኘ የሺዎችን ህይወት ከሚቀጥፋቸው የኣገሪቷ ኣካባቢዎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ያው ወሎ ሆኖ ቀጥሏል። ትግራይ ስር የተጠቃለለው የወሎ ጎሳችን ኣካል ሲራብ ኣማራ ክልል ስር ነህ የተባለውም የወሎ ኣካል ከረሃቡ ኣደጋ ኣላመለጠም። ኣማራ ክልል ውስጥ የኦሮምያ ዞን ነህ የተባለውም እንዲሁ። የወሎ ህዝብ 40 ኣመት ሙሉ ሲራብ ኖሮ ዛሬም ከኣደጋው ኣላመለጠም። በደርግ ዘመን ኣብሮት የተራበው የትግራይ ህዝብ ዛሬ ኣልፎለት የምድራዊ ገነት ህይወቱን ሲያጣጥም ወሎ ግን የቆመለት መንግስት የለውምና ዛሬም ይራባል። የወሎው ህዝባችን ክንዱን ኣስተባብሮ የደረሰበትን የፖለቲካ ክህደት እንዳይቃወም ሆን ተብሎ እየተሰራበት ያለ ይመስላል። ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ ገዢዎች ስልታዊ የማስራብ ፖሊሲ ዋነኛው ሰለባ ሆኖ ቀጥሏል። በረሃብ ጠኔ ተመትቶ፣ በድንቁርና ተሸብቦ፣ ተዳክሞና ኮስምኖ ስለ ጉሮሮው ከማሰብ ያለፈ ለፖለቲካ መብት እንቅስቃሴ እንዳይነቃቃ ተደርጎ ለበርካታ ኣስርት ኣመታት በሞትና ህይወት መካከል ሲዳክር ነው የኖረው።
ሰሞኑን የቢቢሲ ዘጋቢ ከወሎ ኮረም ባጠናቀረው ሪፖርት መሰረት ከኣካባቢው ቢያንስ በቀን 2 ህጻናት በረሃብ ተጎድተው ደራሽ በማጣት እየሞቱ ናቸው። በኣስር ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለዳቦ ያለህ ጩሄታቸው ሰሚ ኣጥቶ ረሃብ መንጋጋ ስር ገብተው እለተ ሞታቸውን እየተጠባበቁ ናቸው። መንግስት ነኝ ባዩ ወያኔ የኣደጋውን ስፋት ለኣላም ኣቀፍ በጎ ኣድራጊ ኣካላት ኣመልክቶ የዜጎቹን ህይወት ከሞት መታደግ ሲጠበቅበት ይባስ ብሎ በቢቢሲው ዘገባ ላይ የቁጣ ናዳ ሲያወርድ ተሰማ።
እንዳለፉት ስርኣቶች ሁሉ የወያኔ መንግስትም 15 ሚሊዮን ያገሪቷ ዜጎች ተርበው እያለ የቅንጦት ድግስ መደገስ ምርጫው ኣድርጉኣል። የረሃብ ኣደጋ ስር የወደቀውን ወሎን ኣንደ ክልሉ ኣካል የሚቆጥረው የኣማራ ክልል ኣስተዳዳሪው ብኣዴን ለ35ኛ ኣመት የልደት በኣሉ ድግስ ለማመን የሚያዳግት ከፍተኛ ገንዘብ መድቧል። እንደ ኢሳት ዘገባ ከሆነ ብኣዴን ከ200 ሚሊዮን በላይ የሚቆጠር ገንዘብ ረጭቶ ኣባላቱን ሊያንበሸብሽ ዝግጅት ላይ ባለበት በዚህ ወቅት ነው እንግዲህ የክልሉ ኣካል ነው በተባለው ወሎ ውስጥ ሰዎች በረሃብ እየሞቱ ያሉት። ሌላው ወሎን እንደ ክልሉ ኣንዱ ኣካል የሚቆጥረው ወያኔም ህወሃትም ለኣደጋው የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሏል። ህወሃት ሙሰኛ ባለስልጣኖቹ በስልጣን ዘመናቸው የዘረፉት ሃብት ኣይበቃቸውም ብሎ በጦረታ ዘመናቸውም የሚኖሩባቸውን ኣፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያው የተባለለትን የቅንጦት መኖሪያ ስፈር ግንባት ፕሮጀክት ተግባራዊ በማድረግ ስራ ተጠምዷል።
ትግራይ ክልል ውስጥ በእርሻ ምርት ተስማሚነቱ የሚታወቀው የራያና ኣዘቦ ወይም በወያኔው ኣስተዳደር ደቡባዊ ዞባ ተብሎ የሚጠራው ዞን ነው። ኣካባቢው በኣፈር ለምነቱና በኣየር እርጥበቱ ተመራጭ ከመሆኑ የተነሳ በምርታማነቱ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ትግራይ ካላት የቀንድ ከብቶችና ግመሎች ሃብት የራያና ኣዘቦ ኣካባቢ የኣንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ለትግራይ ገበያዎች የሚቀርቡት የወተት ተዋፅኦ ምርቶች ምንጭም እዚሁ የራያ ኣካባቢ መሆኑ ኣሌ የሚባል ኣይደለም። ታድያ ይህ የትግራይ የዳቦ ቅርጫት የሆነው ኣካባቢ ህዝብ ኣንዲህ ሲራብ የተቀረውና ለግብርና ምርት ኣመቺ ያልሆነው የትግራይ ክፍል በረሃቡ ኣደጋ ስሙ ሲጠራ ኣልተሰማም። ትግራይም ሆነ ኣማራ ክልል ስር ተከፋፍሎ በሃይል የተጠቃለለው የወሎው ወገናችን የዘመናት ረሃብ ፖለቲካ-ወለድ ረሃብ መሆኑን የሚያረጋግጠው ይሄው ኣስደማሚ እውነት ነው።
ደጉ የወሎ ህዝብ የደግነቱ ብዛት ጠላት ኣበርክቶበት እነሆ መንግስት ወድቆ መንግስት በተተካ ቁጥር በሰው ስራሽ የረሃብ ኣለንጋ ይገረፋል። የወሎው ወገናችን የፖለቲካ ማንነቱን የመነጠቁ እንገብጋቢ እውነት ሳያንሰው ተፈጥሮ የለገሰችውን የኣካባቢና ኣካላዊ ውበቱን እየተነጠቀ ነው። ቀደም ሲል በለምለምነታቸው የሚታወቁት የወሎ ሸንተረሮች ዛሬ ወደ ምድረበዳነት እየተለወጡ ናቸው። ኣገሪቷ ውስጥ በኣዝማሪዎችና ድምፃውያን ሁሉ የደም ገንቦነታቸው የሚመሰከርላቸው የወሎ ጠምበለሎች በረሃብ ኣደጋ ተጎሳቁለው የተፈጥሮ ማራኪ ወዛቸውን በፖለቲካ ገዢዎች እየተነጠቁ ከትውልድ ወደ ትውልድ መሻገር የኣርባ ቀን እድላቸው ሆኗል።
የወሎ ህዝብ ትግራይ ክልል ስር ተጠቃለለና ኣንደ ትግራይ ዜጋ ተቆጥሮ የክልሉ ዜግነት መብቱ ኣልተከበረለትም። በዘሩ ትግሬ ኣይደለምና ትግራያዊ እንክብካቤ ሲደረግለት ኣላየንም። ራያዎችም ቢሆኑ ይህን ኣላጡትም። ስለሆነም ማንነታቸውን በትግራያዊነት ኣልቀየሩም። ለዛም ነው በኣፋን ኦሮሞ ‘Raayya Raayyuma (ራያ ራዩማ)’ እያሉ ራሳቸውን የሚጠሩት። ትርጉሙም ‘ራያ ያው ራያ ነው’ ማለት ነው። ራያ ትግራይ ስር ገባና ትግራያዊ ሊሆን እንደማይችልና ራያ ያው ራያ መሆኑን በጥንት በጠዋቱ ቁዋንቁዋቸው በኣፋን ኦሮሞ ለጠላትም ለወዳጅም እየነገሩ መሆኑ ነው።
ራያ በሰራው ጀብዱ ታሪካዊውን ቀዳማዊ ወያኔን ወልዶ ዛሬ ስልጣን ለጨበጠው ዳግማዊ ወያኔ የጀግንነት ተምሳሌት ከመሆኑ የዘለለ ለራሱ የተረፈለት ነገር የለውም። እንዲያውም ወያኔ ወደ ስልጣን ከመጣ በሁዋላ የራያ ኣካባቢ ኣድገት እንደ ካሮት ቁልቁል ከማደግ በቀር ያሳየው መሻሻል ኣልታየም። ባለፉት 24 ኣመታት ከራያ ኣዘቦ ኣካባቢ በስተቀር ሌላው የትግራይ ኣካባቢ በኣስደማሚ ፍጥነት ሲበለፅግ የራያው ኣካባቢ ግን ቀደም ሲል ማደግ የጀመሩት ከተሞቹ ሳይቀሩ ወደ ምድረበዳነት ተለውጠዋል።
ኣማራ ክልል ስር የተጠቃለለው ወሎም ኣማራ ኣለመሆኑ ግልፅ ነውና ኣማራዊ ኣያያዝ ኣልተደረገለትም። ኣማራ ክልል ውስጥ የኦሮምያ ዞን የሚል መደለያ ስም የተለጠፈለት የወሎ ኣካልም ቢሆን የኦሮሞነት መብቱን በሚገባ ኣስከብሮ ከኦሮምያ ክልል ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲመሰርት ኣልተመቻቸለትም። ራሱ ኦሮምያ የሚባለው ክልልም ቢሆን የኦሮሞ ህዝብ ባልወከላቸው ሆዳደር ተላላኪዎች የሚመራ ልፍስፍስ ኣስተዳደር ነውና ግንኙነቱ ቢፈጠርም ትርጉም ኣይኖረውም። የኦፒዲኦ ኣመራር ኣይደለም ለወሎ ህዝብ መብት ሊሟገት ኦሮምያ እምብርት ውስጥ በምትገኘው ፍንፊኔ ላይ ያለውን ህገመንግስታዊ መብት እንኩዋን ማስከበር ኣላቸለም። ኦሮምያ ውስጥ ለተራበው ህዝብም ኣልተቆረቆረም።
የወሎ ህዝብ ረሃብ እልባት የሚያገኘው መላቅጡ የጠፋው የኢትዮጶያ ፖለቲካ መፍትሄ ሲያገኝ ብቻ ነው። ፖለቲካ-ወለዱ የረሃብ ኣለንጋ ተበጣጥሶ የሚወገደው ፈላጭ ቆራጮች ከህዝብ ጫንቃ ላይ ወርደው ሁሉም የራሱን እድል በራሱ ወስኖ ብሄራዊ ማንነቱን ሲያስመልስና ራሱን በራሱ ማስተዳደር ሲችል ብቻ ነው። ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት ከሌለ ህዝቦች በረሃብም ሆነ በሌላ ኣደጋ ሲመቱ ኣቤት የሚሉበት ኣካል ያጡና የሺዎች ምናልባትም የሚሊዮኖች ህይወት ይቀጠፋል። ባለፉት በርካታ ኣስርት ኣመታት ያየነውና ከሁሉም በላይ የወሎውን ወገናችን ሰለባ ያደረገው የረሃብ ኣደጋም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። ፖለቲካ-ወለድ ረሃብን ድል ለማድረግ የፖለቲካ መብት ማስከበርን ይጠይቃል። የፖለቲካ መብት ለመጎናፀፍ ደግሞ መታገል ብቸኛው ኣማራጭ ይሆናል።

No comments:

Post a Comment