Pages

ኢህአዴግ – “ይሉሽን በሰማሽ፣ ገበያ ባልወጣሽ”

February 03, 2016 | By Seyoum Teshome* | Source Horn Affairs - Amharic

ልክ ከሥራ እንደገባሁ የፌስቡክ ገፄን ስከፍት አንድ ርዕሰ ዜና አነበብኩ፡፡ በጣም ደክሞኝ ስለነበር ዝርዝሩን ለማንበብ አቅሙ አልነበረኝም፡፡ ታዲያ እንደተለመደው ‘በኋላ አነበዋለሁ’ በሚል ዜናውን በገፄ ላይ አካፍዬ (Share) ተውኩት። ትንሽ ቆይቼ የፌስቡክ ገፄን ስከፍት ዜናው በነበረበት አለ። እንዲህ ይላል፣ “የኢትዮጲያ መንግስት በቅርቡ ከአውሮፓ ህብረት ፓርላማ እየደረሰበት ያለውን ጫና ለመከላከል “ደጅ-ጠኚ” ተቋም (lobbying firm) ሊቀጥር ነው”

ወደ ዝርዝር ዜናው የሚወስደውን ሊንክ ተጭኜ ማንበብ ቀጠልኩ። የኢትዮጲያ መንግስት የ1997 ዓ.ም ምርጫ ተከትሎ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር ተያይዞ በአሜሪካ የሕግ-መወሰኛ ምክር ቤት ሊጣልበት የነበረውን ማዕቀብ ለመከላከል “DLA Piper” የተባለ ታዋቂ የአሜሪካ “ደጅ-ጠኚ” ተቋም በወር 50,000 ዶላር እየከፈለ ቀጥሮ እንደነበር ይጠቅሳል፡፡ በተመሳሳይ፣ ሰሞኑን በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በኩል የተፈጠረበትን ጫና  ለመከላከል “ደጅ-ጠኚ” ተቋም ለመቅጠር እያሰበ መሆኑንና ለዚህ ተግባር የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ እና ከገንዘብና ኢኮኖሚ አቶ አብዱላዚዝ ሞሃመድ ያሉበት ኮሚቴ መዋቀሩን ዘግቧል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ከቀረቡት ሰባት የአሜሪካና አውሮፓ ድርጅቶች ውስጥ “Chalgate” የተባለው የእንግሊዙ “የሕዝብ ግንኙነት ተቋም” ከፍተኛ የማሸነፍ እድል እንዳለው በጋዜጣው የተጠቀሰ ሲሆን ድርጅቱ በአመት 2ሚሊዮን ዶላር (42,722,600 ብር) ሊከፈለው እንደሚችል ጭምር ዘግቧል፡፡
በመጀመሪያ፣ በእንግሊዘኛ “lobbying firm” ለሚለው ሐረግ “ደጅ-ጠኚ ተቋም” የሚለውን የአማርኛ ፍቺ የተጠቀምኩበት ምክንያት፣ “የሕዝብ ግንኙነት ተቋም” ከሚለው መደበኛ ስያሜ ይልቅ፣ የተቋማቱን ተግባርና አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ገላጭ ሆኖ ስላገኘኹት ነው። በመሰረቱ፣ እነዚህ ተቋማት በዋናነት በከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችና ተቋማት፣ እንዲሁም በሕግ አውጪና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ዘንድ ደጅ-በመጥናት፣ የተለያዩ ውሳኔዎች እና የሕግ አዋጆችን ከቀጣሪዋቻቸው ፍላጎት አንፃር የተቃኙ እንዲሆኑ ከፍተኛ የማሳመንና ግፊት የመፍጠር ስራ እንደሚሰሩ ይታወቃል።
Photo - European Parliament [Credit chelgate.com]
በእርግጥ አሜሪካ ብቻዋን በአማካይ 1 ቢሊዮን ዶላር፣ የአውሮፓ ኮሚሽን በጥቅሉ 2.5 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ በየአመቱ ለኢትዮጲያ የሚሰጡ እንደመሆኑ፣ መንግስት በሁለቱ ዘንድ ያለው ተቀባይነትና ድጋፍ እንዲቀንስ አይፈልግም። እዚህ ጋር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉትን ንግግር አስታወሰኝ። የቀድሞው ጠ/ሚ “የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት በእርዳታ ላይ የተንጠለጠለ ነው” በሚል ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በኩል ለተሰነዘረ አስተያየት ምላሽ ሲሰጡ፤ “የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት አድራሻው የት ነው?… አድራሻው ዋሽንግተን ዲሲ እና ለንደን አይደለም። የኢኮኖሚ እድገቱ መሰረት የኢትዮጲያ ገበሬ ነው። አድራሻውም እዚህ ሀገር ውስጥ ነው…” ብለው ነበር። ነገር ግን፣ የኦሮሞ አርሶ አደር ገበሬ “ተሳስታችኋል፣ …አይሆንም…እኔን ያላማከለ ልማት ይቅርብኝ” ብሎ ሲቃወም፣ መንግስት በአመት 42.7 ሚሊዮን ዶላር እየከፈለ በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ “ደጅ-ጠኚ” የሚቀጥር ከሆነ፣ ነገሩ ከቀድሞው ጠ/ሚ አባባል የተገላቢጦሽ እንደሆነ መገንዘብ ቀላል ነው።
የኢትዮጲያ መንግስትም ከላይ የተጠቀሰውን ተቋማት በከፍተኛ ክፍያ የቀጠረበት ምክንያትም የአውሮፓ ፓርላማ አባላትን ደጅ-እንዲጠናና በዚህም ከሰሞኑ ያጋጠመውን ጫና ለማቃለል፣ ብሎም ለወደፊቱም ከተመሣሣይ ጫና ራሱን ለመከላከል እንደሆነ እሙን ነው። ነገር ግን፣ የአውሮፓ ፓርላማ ሆነ ደጅ-ጠኚው ተቋም ከሀገራችን ነባራዊ እውነታ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው ውጫዊ አካላት ናቸው። የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በኢትዮጲያ መንግስት ጫና ማሳደር የጀመረው ህዝቡ ላነሳው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ በአግባቡ መስጠት ስለተሳነው ነው። ለወደፊትም ቢሆን፣ ከህዝብ ለሚነሳ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት እስከተሳነው ድረስ ተመሣሣይ ጫና እንደሚያጋጥመው እርግጥ ነው። ስለዚህ፣ ለችግሩ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው የኢትዮጲያ መንግስት ምልከታውን ከውጪ ወደ ውስጥ ሲያዞር ነው። ይህም፣ “የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ምን እያሰቡ ይሆን?” ብሎ ከመጠየቅ በፊት “የኢትዮጲያ ህዝብ ጥያቄ ምንድነው?” ብሎ በመጠየቅ ሲጀምር ነው።
በመሰረቱ፣ የአውሮፓ ፓርላማ ለወሰደው እርምጃ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው የኢትዮጲያ መንግስት ነው። ይሄው ላለፉት ሁለት አስርት አመት ህዝብ የመንግስትን ሥራና አሰራር ሰልፍ በወጣ ቁጥር በፖሊስ ዱላ ተጀምሮ፣ ቀጥሎ በጥይት፣ በመጨረሻም በጅምላ እስር ነው የሚጠናቀቀው። ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ሰብዓዊ መብት መሆኑ ቀርቶ በባለስልጣናት ፍቃድና ችሮታ የሚቸረቸር የቅንጦት ዕቃ ሆኗል። እንዲህ ያለውን አስተዳደራዊ ሥርዓት የዳበረ የፖለቲካ ሥርዓት ባላቸው የአውሮፓ ሀገራትና ህዝቦች ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ ሊኖረው አይችልም። የዴሞክራሲ እሴቶች የዳበሩበት እና ከፈተኛ ተጠያቂነት ያለበት ሀገር መንግስትና ተቋማት የዜጎቹንን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለማቋረጥ ለሚጥስ አምባገነናዊ መንግስት በየአመቱ በቢሊዮኖች እርዳታ እየሰጡ የሚቀጥሉበት የፖለቲካ’ም ሆነ የሞራል መሰረት የላቸውም።  
የኦሮሞ ህዝብ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን መነሻ በማድረግ ላሳየው ሰፊ ተቃውሞ መሰረታዊ የሆኑት ምክንያቶች፤ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49.5 ላይ ከአገልግሎት አቅርቦት፣ ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ረገድ የተደነገገው የክልሉ ልዩ ጥቅም እስካሁን አልተከበረም፣ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እና የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች የአከባቢውን አርሶ-አደር ዘላቂ ጥቅም በሚያስከብር መልኩ እየተተገበሩ አይደለም፣ የከተማ መሬት አስተዳደርና የሊዝ ህግ አተገባበር መሰረታዊ ችግር አለበት፣ እንዲሁም ኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች እና የመንግስት ሥራ አስፈፃሚዎች የመንግስትን መዋቅር ሙሉ-በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቆጣጥረውት በመልካም አስተዳደር እጦት እና በሙስና ተሰቃየን እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ናቸው። (ስለችግሩ መነሻ ዝርዝር ትንታኔ ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ)
የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ያለው ቤልጂዪም፥ ብራሰልስ ሳይሆን ኢትዮጲያ፥ አዲስ አበባ ነው። መልሱ የሚገኘው ከአውሮፓ ፓርላማ ዘንድ ሄዶ ደጅ-በመጥናት ሳይሆን እዚሁ ከሕዝብ ጋር በመነጋገርና በመወያየት ነው። በመሰረቱ፣ የኢትዮጲያ መንግስት የጋራ ደህንነታችንን እንዲያስጠብቅልን አምነንና ፈቅደን የቋቋምነው አስተዳደራዊ መዋቅር ነው። የእኛው መንግስት ከእኛ ጋር ሲጣላ እርቅና ይቅርታ እንዲወርድ መጠየቅ ያለበት እኛን ነው ወይስ የሩቅ ሀገር  ባለፀጋዎችን?
መንግስት ከእኛ ጋር ለመታረቅ የሚሻ ከሆነ ከህዝቡ ተወካዮችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በግልፅ ተነጋግሮ፣ ለፀቡ መነሻ የሆኑ ስህተቶች መለየትና ስለወደፊቱ መመካከር ያስፈልገዋል። ሆኖም ግን፣ ከ10 ቀን በፊት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በወጣው ዜና መሰረት ፣ ከኦሮሚያ ክልል የተወጣጡ የማህብረሰብ መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ከቀድሞው የክልሉ ፕረዘዳንት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ ጋር ለመወያየት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት እንዳጣ ተዘግቧል።
ይህ “የኢትዮጲያ መንግስት ህዝቡን ጥያቄ ለመስማት ፍላጎትና ተነሳሽነት አለው ወይ?” የሚል ጥያቄ ይጭራል።  በተቃራኒው ደግሞ የአውሮፓ ፓርላማ የኢትዮጲያ መንግስት በሕዝቡ ላይ እየወሰደ ያለው የሃይል እርምጃ አግባብ እንዳልሆነ የሚገልፅ መግለጫ ስላወጣ በአመት 42,722,600 ብር ከፍሎ ደጅ-ጠኚ ተቋም ይቀጥራል። ይህ “Chalgate” ለሚባለው ደጅ-ጠኚ ተቋም ለአንድ አመት የሚከፈለው የብር መጠን በሞጆ-ሃዋሳ የፈጣን መንገድ ፕሮጀክት ምክንያት ከአከባቢው አርሶ-አደሮች ላይ እስከ መጨረሻው (Permanently) ለተወረሰ 216.5 ሄክታር የእርሻ-መሬት የተከፈለ ካሳ መጠን፣ ወይም በፕሮጀክቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ 5,152 የአርሶ-አደር ቤተሰቦች የተከፈለ የካሳ ክፍያ ጋር እኩል ነው።
እንዴ…ቆይ ለዚህ የውጪ ሀገር ተቋም እንደሚከፍለው ሁሉ በተለያዩ ግንባታዎች ምክንያት ለሚፈናቀሉ የሀገሪቱ ዜጎች ተገቢውን የመልሶ-ማቋቋሚያ ካሳ  ቢከፍል ኖሮ እኮ ህዝቡ ለተቃውሞና አመፅ አይነሳሳም ነበር። ይህም ሳይሆን ቢቀር፣ ህዝቡ ተቃውሞውን በሚያሰማበት ወቅት መንግስት ተገቢውን ምላሽ ቢሰጥ ኖሮ፣ በዚህ አመት የታየው ዓይነት ስር-ነቀል ተቃውሞ አይከሰትም ነበር። የተቃውሞው እንቅስቃሴ አቅጣጫውን ስቶ የሚጠበቅበትን በህዝብ ንብረትና ሕይወት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በመጠበቅ ሕዝቡ ድምፁን እንዲያሰማ ቢፈቅድ ኖሮ የዜጎች ሕይወት ባልጠፋ ነበር። የዜጎች ሕይወት ያላግባብ ባይጠፋ ኖሮ የአውሮፓ ፓርላማ የአና ጎሜዝን የተለመደ ተቃውሞ ከማዳመጥ አልፎ ጠንካራ የአቋም መግለጫ ባላወጣ ነበር። ያ ባይሆን ኖሮ የኢትዮጲያ መንግስት ደጅ-ጠኚ ተቋም ለመቅጠር ገበያ ባልወጣ ነበር። በአጠቃላይ… ነገሩ ሁሉ “ይሉሽን በሰማሽ፣ ገበያ ባልወጣሽ” የሚሉት ነው!!!
==================================================================
Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, 35 years ago and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

No comments:

Post a Comment