Pages

የወያኔ ትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ የኦሮሞን ህዝብ የእምቢታ ኣቅም ዳግም ያስመሰከረ ድል ነው

May 31, 2016 | ቦሩ በራቃ


እነሆ የወያኔ ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ለሌላ ጊዜ እንዲዛወር ወስኗል። ውሳኔውን ያደረገው ደግሞ ወዶና ፈቅዶ ሳይሆን በኦሮሞ ህዝብ የተቀናጀ ትግል ተገዶ ነው። እንደሚታወቀው የኦሮሞ ተማሪዎችና ኣክቲቪስቶች ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት በሰከነ መልኩ ያሰቡበትን ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበረ። በኦሮምያ ለወራት እየተካሄደ ካለው ህዝባዊ ኣመፅ ጋር በተያያዘ የክልሉ ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ ለፈተናው ባለመዘጋጀታቸው የፈተናው ወቅት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን የክልሉን ትምህርት ቢሮ ጠይቀው ነበር። የኦሮምያ ትምህርት ቤሮ ግን ይህንን ሞራላዊና ፍትሃዊ ጥያቄ ውድቅ የሚያደርግ መግለጫ ሰጠ። ፈተናው ከጥቂት የኦሮምያ ትምህርት ቤቶች በስተቀር በተቀረው ኣብዛኛው ኣካባቢ በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት እንደሚስጥ ነበር ያስታወቀው።

ከዚህ የወያኔ ባለስጣናት ትእቢት የተሞላበት ምላሽ በሁዋላ ነበር የፈተናው መልሶች ሾልከው ወጥተው እንዲበተኑ በኦሮሞ ታጋዮች እርምጃ የተወሰደው። የእርምጃው ኣላማም የኦሮሞን ተማሪዎች ያገለለ ብሄራዊ ፈተና ከቶ ተቀባይነት እንደሌለው ለማሳየት ነው። ወያኔዎቹ ተሸንፈው የፈተናውን መስጫ ፕሮግራም ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ ከተገደዱ በሁዋላ የእናቴ ቀሚስ ኣደናቀፈኝ እያሉ ናቸው። የፈተናውን መልስ ኦንላይን ላይ መልቀቅ ሞራላዊ ኣይደለም ኣያሉም ማጉረምረማቸው ኣስቂኝ ነው። ሞራላዊ ያልሆነውማ የገዛ የራሳቸው ትእቢት ነው። ለኦሮሞ ህዝብ ካላቸው ንቀት የተነሳ የብዙሃኖቹን ኦሮሞ ተማሪዎች ድምፅ መስማት ተሳናቸው። ኦሮሞን በገዛ ኣገሩ ላይ ሰላም ኣሳጥተው ተማሪዎቹ ትምህርት ኣቁዋርጠው እንዲታገሉ ማስገደዳቸው ሳያንስ ኣምስት ስድስት ወር ሙሉ ክፍል ገብቶ የማያውቀውን የኦሮምያ ተማሪ ሙሉ ጊዜውን በክፍል ውስጥ ካሳለፈው የሌላ ክልል ተማሪ እኩል መፈተን ኣማራቸው። ከዚህ በላይ ኢሞራላዊ ውሳኔ የለም።

የኦሮሞ ተማሪዎች ፋና ወጊ የሆኑበት የኦሮሞ ህዝብ ትግል እንዲህ ባሉት ጠላታዊ ውሳኔዎች ሳይበገር ተጠናክሮ ይቀጥላል። እነሆ በድል ላይ ድል እየደረበ የጠላቶቹን ኣንገት ኣስደፍቶ እየገሰገሰም ይገኛል። ‘Qabbanaahu harka, gubu fal’aana (ካላቃጠለ በእጅ ካቃጠለ በማንኪያ)’ እንደሚለው የኦሮሞ ብሂል ትግሉ በህጋዊ መንገድ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ህጋዊና ፍትሃዊ ምላሽ ከተነፈጉ እጸፋውን እንዲህ ባሉት ኣይምሬ እርምጃዎች መመለስ ሞራላዊ ኣንጂ የሚያሰወቅስ ኣያደለም።
የዚህ ፈተና መልስ ሾልኮ መውጣት ወያኔ ብቻም ሳይሆን ለሌሎችም ኣካላት ኣንድ ከባድ መልእክት ኣስተላልፏል ተብሎ ይገመታል። ‘እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው’ እንዲሉ የኦሮሞ ተማሪዎች ኣፋቸውን ተለጉመው በሚቀርቡበት ብሄራዊ ገበታ ላይ ሌሎቹም ነጻ የገበታው እድምተኞች ኣንደልባቸው መመገብ ኣይችሉም። በኣጭር ኣማርኛ ኦሮሞን ያገለለ ብሄራዊ ፈተና ለሌሎቹም የሚሳካ ፈተና ሊሆንላቸው ኣይችልም። ስለሆነም ኦሮምያ ውስጥ የሚካሄደው ትግል ድሉም ሆነ ውድቀቱ ለሌሎቹም ክልሎች እንደሚተርፍ ከዚህ ምሳሌ መረዳት ጠቃሚ ይመስለኛል። ከስድስት ወር በፊት ኦሮምያ ውስጥ የተፋፋመው የእምቢታ ኣመፅ ከኦሮምያ ኣልፎ በሌሎች ክልሎች የትምህርት ሂደት ላይ ተፅእኖ ያሳድር ይሆናል ብሎ ያሰበ ኣልነበረም። እድሜ ለወያኔ ትእቢት እነሆ ሌሎቹም ተርፎ ‘ጉዳዩ የማይመለከታቸው’ ክልሎችም ሰለባ ለመሆን በቁ። ስለሆነም የኦሮሞ ህዝብን የትግል እንቅስቃሴ ከኣገሪቱ ብሄራዊ ጉዳዮች ነጥለው መመልከት ኣልያም ኣናንቀው መዝለፍ የሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ መሬት ላይ ማየት የተሳናቸውን ሃቅ የሚመለከቱበትን መነፅር በጊዜ ቢጠቀሙ ይጠቅማቸዋል።

No comments:

Post a Comment