Pages

ኦሮሞ እና ኢትዮጵያ

November 26, 2017 |  በብርሃኑ ሁንዴ

ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ውስጥ በሚያልፉትና በሚመጡት የሀበሾች መንግስታት ስር ኦሮሞ ባንድ በኩል አየተጨቆነ በሌላ በኩል ግን ለዚህች ሀገር ስታገልና መስዋዕት ስከፍል ቆይቷል። ለዚች ሀገር በተደረጉት ጦርነቶች ውስጥ እንደ ኦሮሞ ጉዳት የደረሰበትና በጣም ከባድ መስዋዕት የከፈለ የለም ቢባል ከእውነት መራቅ አይሆንም፤ ነገር ማጋነንም አይደለም። የኦሮሞ ሕዝብ ለራሱ ነፃነት ይህን ያህል ትልቅ መስዋዕት ብከፍል ኖሮ ምናልባት ዛሬ የሀገሩን ባለቤትነት ማረጋገጥ ይችል ነበር።
በሌላ መንገድ ሲታይ ግን፣ ኦሮሞ ኢትዮጵያን ማሞገስና ይህችን ሀገር ለማኖር ስንከራተት እንጂ፤ ኦሮሞን የምትወድና ለኦሮሞ የምትቆረቆር ኢትዮጵያ አይተነም ሰምተንም አናውቅም። ይህ ያለውን እውነታ ለመናገርና በመሬት ላይ የሚታየውን እውነታ ለመግለፅ እንጂ፣ ይህችን ሀገር ለመጥላትና በሷ ላይ ፕሮፓጋንዳ ማድረግ አይደለም።  ሰዎች ይህንን እውነታ በጥልቅት ሳያዩና ሳይገነዘቡ፣ ቶሎ ብለው ነገሩን ወደ ሌላ መንገድ መተርጎም የለባቸውም። ያለውን እውነታ መናገርና ማስታወስ አስፈላጊ ስለሆነ ነው ይህን ጉዳይ ያነሳሁት። ይህንን ጉዳይ እንደ ጠባብነት የሚያዩትና ነገሩን ከፖለቲካ ጋር ለማዛመድ የሚሞክሩት ይህን ለማድረግ መብታቸው ነው። ይሁን እንጂ እውነታን መደበቅ እይቻልም።

ለምንድነው ይህንን ስለ ኦሮሞና ኢትዮጵያ ጉዳይ ያነሳሁት?
እስቲ የድሮውን ትተን በቅርብ ጊዜያት የተደረጉና እየተደረጉም ወይም እየሆኑ ያሉትን ጎን ለጎን ይዘን ለማየት እንሞክር፥ በኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ መካከል በተደረጉት ጦርነቶች ለምሳሌ እንደ ሶማሊያ እና ኤርትራ ጦርነቶች ውስጥ እንደ ዛፍ ቅጠል የረገፉት የኦሮሞ ልጆች ነበሩ። ይህ ሁሉ የሆነው ይህችን ሀገር ለማዳንና ለማኖር ተብሎ ነው። ለዚህች ሀገር ተብሎ ይህ ነው የማይባል መስዋዕት ተከፍሏል። የኦሮሞ ውለታ ሌላ ሆኖ እነዚህ ጦርነቶች ካለፉ በኋለ፣ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ውስጣዊ ጦርነት ታውጆ፤ ይኸው ስንት የኦሮሞ ልጆች ሕይወት አልፏል፣ እያለፈም ነው። በዚህ ምክንያት ስንት የኦርሞ ልጆች ከሀገር ተሰደዱ? ስንት የኦሮሞ ልጆች ናቸው የት እንደ ገቡ የማይታወቀውት? ስንት የኦሮሞ ልጆች ናቸው በየእስር ቤቶች እየተሰቃዩ ያሉት? የሰንቶቹ  ሕይወት ፈርሶ በየመንገዱ ላይ ለማኝ ሆነው የቀሩት? ወዘተ
ይህ ሁሉ ሆነው እያሉ፣ ልክ ይህ እንዳነሰን ተደርጎ፣ ነገሮች ሁሉ እየተበላሹ መጥተው ይኸው በኦሮምያና ሶማሌ ድንበር ላይ ጦርነት ተክፍቶብን ሕዝባችን ከቀን ወደ ቀን እያለቀ ነው። እስቲ እዚህ ላይ ራሳችንን እንጠይቅ፤ እርሰ በርሳችንም እንጥያየቅ። ይህ ጦርነት በኛ ላይ ስታወጅ፣ ኦሮሞ ስሞትላት የቆየው ኢትዮጵያና በዉስጧ የሚገኙት ብሔርና ብሔረሰቦች ለኦሮሞ ሕዝብ ተቆርቁረው የተናገሩት ነገር አለ? በፌደራሊዚም ስም የተቀመጡትን ሕጎች እንኳን ተጠቅመው ይህ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየተደረገ ያለው ነገር ትክክል አይደለም ብለው ጥያቄ አቅርበዋል? ፍርሃት እንዳለ ይገባኛል። ይሁን እንጂ ፍላጎትና ቆራጥነት ካለ የመብት ጥያቄን መጠየቅ ይቻላል። ለኦሮሞ ቢቆረቆሩ፣ የኦሮሞ ቁስል ብሰማቸው፣ ይህንን መግለፅ የምችሉበት መንገድ አይጠፋም። ነገር ገን ዝምታን መረጡት።
ኦሮሞዎች በተለይም የኦሮሞ አዋቂዎችና ተንታኞች፣ አንዳንድ የኦሮሞ ምሁራንና የፖለቲካ ድርጅቶች ያለውን እውነታ መረዳትና መገንዘብ ተተው፣ በሕዝባችን ላይ ጦርነት ተከፍቶ በጅምላ አየተገደሉ እያሉ፣ ለዚህ እስቸኳይ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ኢትዮጲያ የምትባለዋን ሀገር በቻሉት መንገድ ለማኖር ሌት ተቀን ስንከራተቱ ይታያሉ፥ ) ስለ አዲሷ ኢትዮጵያ መገንባት፤ ) ስለ ፖሊሲ ለውጥ፤ ) ስለ ኢትዮጵያ  ሀገራዊ ንቅናቄ፤ ) ስል ኢኮኖሚ አብዮት ወዘተ ላይ እውቀታቸውን፣ ችሎታቸውንና ጊዜያቸውን ያጠፋሉ።
በየትኛውም ምክንያት ይሁን፣ ለኢትዮጵያ መታገል መፈለግ አንዳለ ሆኖ፣ የሚገርመው ግን ሕዝባችን እየተሰቃየ፤ ለረሃብና እርዛት እየተጋለጠ እያለ፤ ጦርነት ተከፍቶበት እያለቀ እያለ፤ ዜጎቻችን በየእስር ቤቶች እየተሰቃዩ እያሉ፤ ባጠቃላይ የነፃነት ትግል ቀርቶ ሕዝባችን ለመኖር ትግል እያደረግ ባለበት ወቅት፤ እነዚህ አስካፊ ችግሮች ቅድሚያ ማግኘት ሲገባቸው፤ ይህን አሳሳቢ ጉዳይ ትተው ስለ ሌሏ ነገር ማዉራት ትርጉሙ ምንድን ነው? በቂ የማስተዋል እጥረት ነው ወይንስ የሕዝባችን ቁስል ነው የማይሰማን?

አንድም ጊዜ ለኦሮሞዎች ቦታ ያልሰጠች ኢትዮጵያ፤  በችግር ጊዜ ለኦሮሞዎች የማትደርስ ኢትዮጵያ፤ በተቃራኒው በኦሮሞ ደምና አጥንት ላይ ለተገነባች ኢትዮጵያ ይህን ያህል መጨነቅ ለምንድነው? እዚህ ላይ ማስገንዘብ የምፈልገው ነገር፥ ለሁሉም ሕዝቦቿ እናት መሆን የሚትችል ኢትዮጵያ መገንባት ከተቻለ እኔ ችግር የለብኝም። ይሁን እንጂ የኔ ትልቁ ጥያቄ “የዚህን አይነት ኢትዮጵያ መገንባት ይቻላል??” የሚል ነው። የዚህ አይነት ኢትዮጵያ ለማገንባት የምንታገል ከሆነ ደገሞ በቅድሚያ የራሳችንን ቤት ማፅዳት የግድ ይሆናል። እዚህ ላይ የራሳችንን ቤት ማፅዳት ስል ቅድሚያ ማግኘት ያለበት በመጀመሪያ ለተቃጣብን ጥፋት የመጨረሻ መፍትሄ መፈለግ ነው። በመጀመሪያ ሕዝባችን በሰላም እንዲኖር ማድረግ ነው። ሰላም በሌለበት ለውጥም የኢኮኖሚ ዕድገትም ሊኖር አይችልም። ሙከራዉም ሊሳካ አይችልም። ይህን ግዳይ ማስተዋልና በጥልቀት ማየት በጣም አስፈላጊ ነው። የሕዝባችን ችግርና ስቃይ ይሰማን።

No comments:

Post a Comment