Pages

ኦህዲድ (OPDO) የመጨረሻ ውሳኔ ለማድረግ የምገደድበት ደረጃ ላይ ደርሷል

December 13, 2017 | ብርሃኑ ሁንዴ

“የኦሮሞ ሕዝብ አንገብጋቢ ችግሮችና የኦህዲድ (OPDO) ትልቅ ፈተና” በሚል ርዕስ ከዚህ በፊት ባቀረብኩት አጭር ፅሁፍ ውስጥ የኦህዲድ አዲሱ አመራር በምናገረው፣  የኦሮሞን ብሔርተኝነት በሚያንፀባርቁ አነጋገሮች በስተ ጀርባ ምን እንዳለና የድርጅቱ እውነተኛ መልዕክትም ሆነ ዓላማ ምን ሊሆን እንደሚችል የተለያዩ ግምቶችን ለመግለፅ ሞክሬ ነበር። ይህ እንደ ግምት የተወሰዱት ዓላማቸውና መልዕክታቸው ምን እንደሆኑ አሁንም ባይታወቅም፣ ነገር ግን እንደኔ አመለካከት ከቃላቶች መጣፈጥ ውጭ በስራ የታየና እውነትም ለሕዝባቸው መጨነቃቸውና የኦሮሞን ሕዝብ ስቃይ ለማብቃት ቆርጠው የተነሱ መሆናቸው አይታይም።

በሱማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ድንበሮች ላይ ሕዝባችን ከቀን ወደ ቀን እንደ ቅጠል እየረገፉ እያሉ፤ የድርጅቱ አመራር አባላት በየሄዱበት ጥሩ ቃለት ብቻ መናገር ትርጉሙ ምኑ ላይ ነው? ጌቶቻችን ሕዝባችን ነው እያሉ ሕዝቡን ከጥቃት መከላከል ካልቻሉ የቃላት መብዛት በቻውን ምን ያደርጋል? በነገራችን ላይ የሁለቱንም ወገን ፍላጎት እኮ ማሟላት አልቻሉም። ወይ ከመስራቹ ጌቶቻቸው ተልዕኮ ወስደው፣ የሕዝቡን አመፅ ማብረድ ኣልቻሉም። ወይንም ደግሞ ወደ ሕዝባቸው የነፃነት ትግል ተቀላቅለው የጠላትን ጥቃት መመከት ኣልቻሉም። ታዲያ በሁለት ኃይሎች መካከል ገብተው መጨነቃቸው ትርጉሙ ምንድነው? እስከመቼስ እንደዚህ ይቀጥላል?
እኔ የሚመስለኝ ወይም የሚታየኝ ድርጅታዊ ተሃድሶ ለማድረግ ብውስኑም እንኳን፣  ይህ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ በድርጅቱ ውስጥ የሚታይ አይመስለኝም። ምናልባትም ወደ ሕዝባቸው ለመመለስና የሕዝቡን የነፃነት ትግል ለመቀላቀል የሚፈልጉት ጥቂት የአመራር አባላትና የድርጅቱ አባላት ሊሆኑ ይችላሉ። ቀሪው አሁንም የተቋቋሙለትን ዓላማ ለማሳካትና ሕዝቡን ሳይሆን የጌቶቻቸውን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ የሚሰሩ ይመስሉኛል። ይህ አሁንም ግምቴ ነው። ለምን ከተባለ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ በየቦታው ሲገደል፣ ሲፈናቀል፣ ንብረቱ ሲዘረፍ፣ ሲዋከብ ዝም ብለው ማየትን ባልመረጡ ነበር። ወይንም ደግሞ እኛ እንደምናስበው ሳይሆን፣ ምንም ዓይነት የስልጣንም ሆነ ሌላ ኃይል እንደ ሌላቸው ያሳያል።
ባንድ በኩል ያላቸው ዓቅም ደካማ ቢሆንም፣ የህወሃት/ኢሕአዲግ አባል ድርጅት እንደ መሆናቸው መጠን የውስጥ ህግና ደንብ ቢያግዳቸውም፤ በሌላ በኩል ግን እዉነት ለሕዝባቸው ለመስራትና ለመታገል ብወስኑ ኖሮ በሕገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው የስልጣንም ሆነ ማንኛውንም መብት በመጠቀም የክልላቸውን ሰላም ማስጠበቅና ሕዝባችን እንዳይገደሉ ማድረግ ይችሉ ነበር። ይህ እስካልሆነ ድረስ ደግሞ የክልሉ መንግስት መሪ ድርጅት መሆናቸው ምኑ ላይ ነው? መንግስታዊ ድርጅት ሆኖ በክልሉ መዋቅር የዘረጋ፤ በክልሉ ላይ ውሳኔ የማስተላለፍ መብትና ስልጣን ያለው ድርጅት ይቅርና አንድ የተራ ቤተሰብ ኃላፊ (Abbaa Warraa) እንኳን ቤተሰቦቹን ከውጫዊ ጥቃት ይከላከላል። ታዲያ ሕዝባችን በየቀኑ በየቦታው እየተገደሉ ዝም ማለት ወይ ጉልበት ማጣት ነው ወይንም ደግሞ ጥሩ ቃላት ከመናገር ውጪ አውነትም ለሕዝቡ ለመስራት ፍላጎትም ሆነ ዓላማ የላቸውም ማለት ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ በገፍ በሚገደልበት ባሁኑ ወቅት በሚቻለው መንገድ ሁሉ ሕዝቡ ጎን ቆመው በሕዝባችን ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ካላቆሙ፣ እኔ መሆን አለበት በዬ የማስበው ጣፋጭ ንግግር ብቻ በማድረግ የሕዝቡን ልብ ከሚስቡ፤ እንደ ድሮውና እንደተለመደው አንድ ጎን በመያዝ ጌቶቻቸውን ማገልገልና፤  ሕዝባችን  የዕጣ ፋንታውን ለራሱ እንዲወስን መተው ይሻላል። ከዚያ በኋላ ሕዝባችንም ከማንም ምንም መጠበቅ እንደማይችል ግልፅ ይሆናል። በእውነት ወደ ሕዝባችን ተመልሰው የነፃነት ትግሉን ለመቀላቀልና ለመምራትም ቆርጠው ከሆን ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሕዝባችን ላይ የተከፈተው ጦርነት እንዲቆም ማድረግ አለባቸው። ይህ ከሁሉ ችግሮች ቅድሚያ ማግኘት ያለበት በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ኦህዲድ የመጨረሻ ውሳኔ ለማድረግ የምገደድበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ወይ የጠላት መሳሪያ ሆኖ መቀጠል ወይንም የሕዝብ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ መውጣት።

No comments:

Post a Comment