Pages

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ በተመለከተ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣቋም

April 05, 2018 | Oromo Liberation Front (OLF)

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር, ሚያዚያ 5 ቀን 2018 ዓም
Resolutions of the Oromoo Liberation Front National Councilየኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን የፖለቲካ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ኣሁንም ዝግጁ መሆኑን እያሳወቀ፡ በኦነግና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የሚደረግ ንግግር ሶስተኛ ወገን ባለበትና ያለኣንዳች ቅድመ-ሁኔታ እንዲከናወን ጥረት ሲደረግ ቆይቶ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ፍላጎት ከማጣት የከሸፈው ጥረት እንዲቀጥል በኢህኣዴግ ለሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ጥሪውን ያድሳል። የወያኔ/ኢሕኣዴግ መንግስት በበኩሉ የሚጠበቅበትን እንዲያሟላ ኣጥብቆ ያሳስባል።
ኦነግ ከኣንድ ምዕተ-ዓመት ተኩል በላይ እያስቆጠረ ላለው የኦሮሞ ህዝብ የመብት ጥያቄና በህዝቡ ላይ ተዘርግቶ ከባድና ዘግናኝ ሰቆቃ እያደረሰበት ያለውን የጭቆና ስርዓት ለመፋለምና የራስን እድል በራስ ለመወሰን መብት መረጋገጥ በትግል ላይ የነበረና ያለ ድርጅት መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው።

የኢትዮጵያ ኢምፓዬር የፖለቲካ ችግር በውይይት መፍትሄ እንዲያገኝ ኦነግ ያደረገው ጥረት ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። ይህ ተመራጭ መንገድ ግን በሃይል በሚያምኑ የኢትዮጵያ መንግስታት ዘንድ ስላልተለመደ ተቀባይነት ኣላገኘም። በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለችግሮች መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ ከጠላት በመፈራረጅ ለመጠፋፋት ዘመቻ ማካሄድን ነው የኢትዮጵያ ገዢዎች የመረጡት። ይህ ጸረ-ዲሞክራሲ ኣቋም ያሉ የፖለቲካ ችግሮች እንዳይፈቱ በማድረግ ከትውልድ ትውልድ ኣሸጋገረ። ለመብታቸው የሚፋለሙትን ውድ መስዋዕትነት ኣስከፈለ።
ይህ ኋላቀር፣ በእኩልነትና በዲሞክራሲ ያለማመንና ላሉ ችግሮች ሃይል መፍትሄ ነው ብሎ የማመን ኣስተሳሰብ ቀርቶ፡ ያለው ችግር በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ ይችላል የሚል ተስፋ በ1991ዓም ተፈጥሮ ነበር። በወቅቱ የደርግ መንግስትን ያሸነፉ የፖለቲካ ድርጅቶች፡ ጭቆናና ዝርፊያ በህዝቦች ላይ ምን ጉዳት እንዳደረሰ ያዩና የተገነዘቡ፣ ታግለውት የህዝቡን መብት ለማስከበር በወጣትነት እድሜያቸው ጫካ የገቡ መሆናቸው ህዝቡ ተስፋ እንዲሰንቅ ምክንያት ሆነ። የኦሮሞ ነጻነት ግንባርም በበኩሉ ለህዝቦቻቸው መብት የሚታገሉት የሌሎቹንም ህዝቦች መብት ያከብራሉ በሚል እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ለማስገኘት የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት በሽግግር መንግስት ውስጥ መሳተፉ ይታወሳል።
ኦነግ በሽግግር መንግስት ለመሳተፍ የወሰነው የኦሮሞ ህዝብ መብት እንዲከበር እንጂ ከኣዳዲስ ገዢዎች ጋር ስልጣን በመጋራት የኦሮሞን ህዝብ ለመዝረፍና ለማስዘረፍ፣ ለመጨቆንና ለማስጨቆን ኣልነበረም። ይህ የኦነግ ኣቋምም የዝርፊያ ዓላማ ያላቸውን ገዢዎች ኣስኮረፈ። ከነዚህ ኣብረው ሊጓዙ ከማይችሉ ተቃራኒ የሆኑ የኦነግና የገዢዎች ዓላማም ኦነግ ተገፍቶ፣ በኦነግና በኦሮሞ ህዝብ ላይ ጦርነት ታውጆ በ1992ዓም ከሽግግር መንግስቱ እንዲወጣ ተደረገ። ለኦነግ ከቻርተሩ የመውጣት ምክንያት ጠላቶችና ኣጫፋሪዎቻቸው ባልጠበቁት ሁኔታ የኦነግ ዓላማ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ ስላስበረገጋቸው እንዲሁም ኦነግ እስካለ ድረስ የኦሮሞን ህዝብ እንዳሻቸው መግዛትና መዝረፍ ከባድ መሆኑን በመገንዘባቸው ነበር።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጦርነት ተከፍቶበት ከቻርተሩ ከመውጣቱ በፊትም ይሁን ከወጣ በኋላ ከወያኔ/ሕወሃት ጋር መዋጋቱን ኣላቋረጠም። በተለይ ደግሞ በቻርተሩ ወቅት በየቦታው ሲካሄድ የነበረው ውጊያ በኦነግ ከቻርተሩ መውጣት ወደ ሙሉ ጦርነት እንዲሸጋገር ተረደገ። ይህ ጦርነትም በኦነግ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው የኦሮሞ ህዝብ ላይ ታወጀ። ይህም ሆኖ ኦነግ ሰላማዊ መፍትሄ በማስገኘቱ ላይ ከመስራት ወደኋላ ኣልተመለሰም። ለዚህም ማስረጃው ያለውን ችግር በምክክር ለመፍታት፡
  1. በኣስመራ መስከረም 14 ቀን 1992ዓም የኤርትራ መንግስት፣ የዩናይትድ ኪንግደም(UK)፣ የጀርመን፣ የስዊድንና የኣሜሪካ ኣምባሳደሮች ባሉበት የእርቅ ንግግር ሊደረግ በዝግጅት ላይ ሳለ፡ ይህንን ኣስቀድመው ነሃሴ 3 ቀን 1992ዓም በናይሮቢ ልዩ ሃይል በመላክ በሽግግር መንግስቱ የኦነግ ተወካይ የሆኑትን ኣቶ ጃተኒ ኣሊ ተንዱን ሲገድሉ የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑትን ኣቶ ለሜሳ ቦሩን በመስከረም ወር 1992ዓም ውስጥ ኣፍነው እስከ ዛሬ ድረስ የት እንዳሉ የሚታወቅ ነገር የለም

  2. ሁሉን-ኣቀም መፍትሄ ለማፈላልግ በኣያሌ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ተቃዋሚዎች ኣቀናጅነት በ1993ዓም በፓሪስ ከተካሄደው ኮንፈረስን ቢካፈልም፡ ከኦነግ መስራቾች ኣንዱ የሆኑትና በቻርተሩ ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር የነበሩት ኣቶ ኢብሳ ጉተማ በመታሰራቸው ጥረቱ ከሸፈ

  3. የካርተር ሴንተር(Carter center) ውይይት ከየካቲት 7 – 8 ቀን 1994ዓም በመካሄድ ላይ ሳለ እነሱ ደግሞ በዚሁ ወቅት ኣባገዳ ቦሩ ጉዮን የእርቅ ንግግር በሚል ጋብዘው ፍላጎታቸውን ስላላሟሉላቸው ገደሏቸው። እንዲሁም ወርሃ መስከረም 1994ዓም ታዋቂውና ተወዳጁን ኣቶ ደራራ ከፈኒን በምዕራብ ሸዋ ኣምቦ ውስጥ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ገደሏቸው።

  4. በ1994-95ዓም በኮንግረስማን ሃሪ ጆንስተን የሚመራው ኮንግረሽናል ታስክ ፎርስ (Congressional Task Force (CTF) ያደረገው ጥረት፥ ከየካቲት 6 – 9 ቀን 1995ዓም በዋሺንግተን ዲሲ ሊካሄድ ከነበረው ውይይት ኣንድ ቀን ኣስቀድሞ በምስራቅ ሀረርጌ ደደር ወረዳ ሱሬና ክዮ ቀበሌ ውስጥ የካቲት 5 ቀን 1995ዓም ወደ 30 ገደማ ሰዎችን በጅምላ ገድለው በርካቶችም ቆሰሉ።

  5. ከ1996 – 1997ዓም በቦን የጀርመን መንግስት ኣምባሳደር የነበሩትና በ1992ዓም ኣስመራ በተካሄደው ስብሰባ ላይም የነበሩት ኣምባሳደር ዊንክልማን፡ ኦነግና ሶስት መንግስታት የተገኙበትና ኋላም የኢትዮጵያ መንግስት ያቋረጠው

  6. ከ1999 – 2000ዓም በኖርዌይ መንግስት በኩል ውይይት የሚሻ መስሎ በመቅረብ ኦነግ ፍላጎቱን ሲገልጽ የኦሮሚያን ደን በማጋየትና ከፊንፊኔ ጉዳይ ጋር ኣያይዞ የኦሮሞን ህዝብ ማሰቃየት ጀመረ

  7. በሉተራን ወርልድ ፌዴሬሽን(Lutheran World Federation) በኩል ዶር. ኢስማኤል ኖኮን ተወክለው የወያኔ መንግስትና ኦነግን እንዲያወያዩ፡ ይህንንም ለማሳካት ኣምባሳደር ብርሃኑ ድንቃ ከሁለቱም ወገን ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ ኣስተባባሪ ኮሚቴ በማሰባሰቡ ላይ እንዲሰሩ የተወሰነውና ሌላውም ጥረት እንደምሳሌ ይጠቀሳል።

  8. ከ2006ዓም ኣንስቶ በኦሮሞ የሃገር ሽማግሌዎች በኩል እወያያለሁ እያለ በሌላ በኩል በምስራቅ ኦሮሚያ ሱፊ ተራራ ላይ የካቲት 2007ዓም የኦሮሞ ዜጎችን በኣሰቃቂ ሁኔታ ፈጀ።
በነዚህ ጥረቶች ሁሉ ላይ ኦነግ ድርሻውን ቢያበረክትም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ፍላጎት በመታጠቱ ሁሉም ጥረቶች ከሽፈው ሳይሳኩ መቅረታቸው የወያኔ መንግስት ለውይይት ዝግጁ ኣለመሆኑን ያሳያሉ።
የወያኔ መንግስት ከሰላማዊ ንግግር በመራቅ የህዝቦችን ጥያቄ በተለይ ደግሞ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ በሃይል ለመፍታት ያደረገው ጥረት ኣልተሳካም። የኦሮሞን ህዝብ ኣንድነት ይበልጥ በማጠናከር እንዲፋለም ኣደርገ። ኦነግን ለማጥፋት ጦርነት ቢታወጅበትም ይበልጥ እንዲጠናከርና በህዝብ እንዲታቀፍ ኣደረገው እንጂ ኣላጠፋውም። ኦነግ ከከፈለው መስዋዕትነት
በተጨማሪ የኦሮሞ ህዝብ የኦነግን ዓላማ የራሱ ዓላማ ኣድርጎ በመውሰድ ከጠላት ጋር ባካሄደው ፍልሚያ ውስጥ የከፈለው መስዋዕትነት ከባድ ነው። በሺዎች የህይወት መስዋዕትነት ከፍሏል። ለኣካላዊ ጉዳት ተዳርጓል። ሃብት-ንብረቱን ኣጥቶበታል። በዚህ ለረዥም ዓመታት በተካሄደ ጦርነት ውስጥ፡ የተለያዩ ኣዋጆችና እጅግ ዘግናኝ የሆኑ ጠላታዊ እርምጃዎች በኦነግና በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሲወሰዱ በነበሩበትና እየተወሰዱ ባለበት ወቅት ውስጥ የዛሬዋን ዕለት ጨምሮ የኦፒዲኦ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የኦሮሞ ህዝብ ዛሬም በሃዘንና ከቁጭት ያያል።
የኦሮሞን ህዝብ የነጻነት ትግል ከፍተኛ ላይ ደረጃ በማድረሱ ውስጥ የቄሮ ቢሊሱማ ሚና ኣክሪና ታሪካዊ ነው። ይህ ትግል ይኔ ነው ብሎ ወደራሱ በመውሰድ ባካሄደው ፍልሚያ የጠላትን ጎራ ኣርበድብዷል። በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተተበተበውን የቅኝ ኣገዛዝ(ኮሎኒ) ስር በመበጣጠስ ጠላትን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከቷል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደቄሮ ቢሊሱማ
ተደራጅተው ከኣብራኩ ለወጡት ህዝብ መታገል በተጨቋኝ ህዝቦች እንደተምሳሌት ተወስዶ እንደቄሮ በመደራጀት ትግላቸውን ማፋፋማቸው የኦሮሞን ህዝብ የነጻነት ትግል ጥንካሬ የሚያሳይ ከመሆኑም በተጨማሪ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ መብት ትግልን ወደ ኣዲስ ምዕራፍ ኣሸጋገረ። ጨቋኞች እንደለመዱት ህዝቦችን በኣፋኝ ኣገዛዛቸው ክንድ ደቁሰው ማስተዳደር እንደማይችሉ ኣረጋገጠ።
ዛሬ በኢሕኣዴግ በሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ጎራ ውስጥ “ለውጥ፣ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ ተሃድሶ፣ እርስ በርስ መነጋገር” የሚሉና በርካታ ቃላት እየተነገሩ መሆናቸውን ሁሉም ይውቃል። ለዚህም ኢህኣዴግ ኣዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መምረጡ እየታወጀ ነው። ይህ ጠቅላይ ሚኒስትርም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ እድሎች እንዳመለጡና ኣሁንም እድል መገኘቱን ከንግግሩ ውስጥ ተሰምቷል።
ይሁን እንጂ ኣሁንም ቢሆንም በ27 ዓመታት የኢህኣዴግ ስርዓት የኣገዛዝ ዘመን ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ ችግር ኣልተፈታም፣ ወደ ባሰ ደረጃ ተሸጋገረ እንጂ። ዝርፊያና ጭቆና ከኦሮሞ ህዝብ ላይ ኣልተገታም። የወያኔ ስርዓት ኣስተማማኝ መፍትሄ ለማስገኘት ከመስራት ይቅል በማባበያና እውን በማይሆን ተስፋ ዓላማውን ማሳካቱን መረጠ። ይህ በኦሮሞ ህዝብም ይሁን በኦነግ ዘንድ ተቀባይነት የለውም።
የኢትዮጵያ ኢምፓዬር ኣንቆ ለያዘው የፖለቲካ ችግር መፍትሄው፡ ያለውን ችግር ያለኣንዳች ፍራቻ ግልጽ ኣውጥቶ መወያየትና የታወጀውን ጦርነት ገትቶ ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ በቋጫ ማበጀት ከኢትዮጵያ መንግስት የሚጠበቅ መሆኑን ኦነግ ኣጥብቆ ያሳስባል።
ይህንን በመገንዘብ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ያለውን የፖለቲካ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ኣሁንም ዝግጁ መሆኑን እያሳወቀ፡ በኦነግና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የሚደረግ ንግግር ሶስተኛ ወገን ባለበትና ያለኣንዳች ቅድመ-ሁኔታ እንዲከናወን ጥረት ሲደረግ ቆይቶ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ፍላጎት ከማጣት የከሸፈው ጥረት እንዲቀጥል በኢህኣዴግ ለሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ጥሪውን ያድሳል። የወያኔ/ኢሕኣዴግ መንግስት በበኩሉ የሚጠበቅበትን እንዲያሟላ ኣጥብቆ ያሳስባል።
የዚህ መንግስት ደጋፊዎች ባጠቃላይ የዓለም መንግስታትና የዓለም ማህበረሰብ ይህ ችግር እንዲፈታ እስከኣሁን ሳያሟሉት የቀረውን ድርሻቸውን እንዲወጡ ኦነግ ኣጥብቆ ጥሪውን ያቀርብላቸዋል።
ዘመኑ የጭቆና ፍጻሜ ዘመን ነው!
ድል ለኦሮሞ ህዝብ!
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ሚያዚያ 4 ቀን 2018ዓም

No comments:

Post a Comment