Pages

በስመ ፍኖተ ካርታም ሆነ በሌላ ዘዴ የኣንድን ብሄር ቋንቋና ታሪክ በሌሎች ላይ ለመጫን የሚጠነሰስ ሴራ መገታትና መወገዝም አለበት !

ነሃሴ  23, 2011 እ.ኢ.ኣ (Hagayya 29, 2019) | የኦሮሞ ነፃነት ግንባር መግለጫ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብልክ መንግስት የትምህርት ሚንስቴር ነሐሴ 15 ቀን 2011 በሰጠው መግለጫ የሁሉም ብሄር ብሄረ-ሰቦች ህጻናትና ተማሪዎች ከአንደኛ ክፍል ጀምረው የአማርኛ ቋንቋን ይማራሉ የሚል አስገዳጅ ህግ ማወጁ እያወዛገበ ይገኛል። እንደ አዲስ ተቀረጸ የተባለዉ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ከኣንድ ወገን በተሰባሰቡ ግለሰቦች ምክረ ሀሳብ የተነደፈ ከመሆኑም ባሻገር አገሪቱን ሃምሳ ዓመትና ከዚያ በላይ ወደ ሁዋላ በመመለስ ሌሎች ብሄር ብሄረ-ሰቦች ለዘመናት ባደረጉት መራራ ትግልና በከፈሉት መስዋዕትነት ቢያንስ የተጎናጸፉዋቸው የተወሰኑ መብቶችን እንኳ ለመግፈፍ ሆነ ተብሎ የተጠነሰሰ ሴራ ነው ብለን እናምናለን።


የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 39 ነጥብ 2 ማንኛዉም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰብ እና ህዝብ በቋንቋዉ የመናገር፣ የመጻፍ ቋንቋዉን የማሳደግ፣ ባህሉን የማዳበርና የማስፋፋት፣ እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት እንዳለው ይደነግጋል። አሁን ስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲም ሁሉም ብሄር ብሄረ-ሰቦች በራሳቸው ቋንቋ እንዲማሩ እውቅና የሚሰጥ ሲሆን የሚሰጠው ትምህርትም ለነጻነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲያዊ ኣንድነት የሚቆሙ ዜጎችን ለማፍራት፣ እንደዚሁም ህዝቦች እሴቶቻቸውን እንድጠብቁ ለማድረግ ነው የሚል ግልጽ ዓላማ ኣስቀምጧል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የሚከተለው የትምህርት ፖሊሲ፣ የትዉልድ ቋንቋቸዉንና ችሎታቸውን ተጠቅመው ዴሞክራሲያዊ ባህልን መገንባት የሚችሉ ትዉልዶችን፣ የራሳቸው ህዝቦች ታሪክና እሴቶችን ማስቀጠል የሚችሉ ዜጎችን፣ የአገርንና ማንነታቸዉን መገንባት የሚችሉ አገር ወዳዶችን ብሄረተኞችን ማፍራትና ማሳደግ የሚያስችል ፖሊሲ ነው። የሁሉንም ብሄር ብሄረ-ሰቦች ቋንቋን እኩል የሚያከብር የቋንቋ አጠቃቀም ፖሊሲንም ይከተላል። በማንኛዉም ህዝብ ቋንቋ ላይም ጥላቻ የለውም። የብሄር ብሄረ-ሰቦች ህጻናት ከአንደኛ ክፍል ጀምረው እስከ ከፍተኛው የትምህርት መዋቅር በራሳቸው የኣፍ መፍቻ ቋንቋ ለመማር የተፈጥሮ መብት ኣላቸው ብሎም ያምናል። ለተግባራዊነቱም ይታገላል። ማንኛውም የትምህርት ፖሊሲ በህዝቦች ተሳትፎ መነደፍ ኣለበት የሚል መርህ ይከተላል።
የራስን ማንነትና ታሪክን በሃይልም ሆነ በህግ ከለላ በሌላ ህዝብ ላይ ለመጫን የሚሞከረው ማንኛውም እንቅስቃሴ በየትኛውም መስፈርት (standard) ተቀባይነት የለውም። ስለዚህ ህጻናትን ከምርጫቸው፣ ከፍላጎታቸውና ፈቃዳቸው ዉጪ የራሳቸው ያልሆነውን ቋንቋ እንዲማሩ ማስገደድ የብሄሮችን ነፃነት መግፈፍ በመሆኑ በጽኑ እንቃወማለን።
የተለያዩ ብሄሮች ብሄረ-ሰቦችና ህዝቦችን በኣንድ ቋንቋ ኣንድ ወጥ ህዝብ እናደርጋለን፣ የቀድሞውን ኢትዮጵያ መልሰን እናድሳለን… ወዘተ ብለው የሚንቀሳቀሱ የቀድሞ ስርኣት ናፋቂዎች ኣንድነትን ሳይሆን መለያየትን፣ ሰላምን ሳይሆን የህዝቦችን ግጭትና ጦርነትን ኣየሰበቁ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ያለውን ህብረ ብሄራዊ የፌዴራል ስርዓት አወቃቀርን ለማፍረስ የሚደረገው ጥረት የትንኮሳና ጸብ-ኣጫሪ ድርጊት በመሆኑ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰብ እንወዳለን። የኦሮሞና ሌሎች ህዝቦች ሀቀኛ ብሄረተኝነትን በቀጥታ በመኮነንና የተለላዩ ስያሜዎችን በመስጠት ለማጥፋት የሚደረገው እንቅስቃሴ የታሪክን ሂደት ወደ ሁዋላ ሊመልስ እንደማይችል መረዳትም ይኖርባቸዋል።
በመጨረሻም ህዝባችን እስከዛሬ በትግሉ የተጎናጸፋቸዉን መብቶቹን በተለያዩ ሴራዎች መልሶ ለመንጠቅ የሚሞክሩትን ኃይሎች ሁሉ በንቃት እንድታገላቸዉ እናሳስባለን። በዚህ አጋጣሚ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ለነፃነትና ለሰላም፣ ለህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ለእኩልነትና ማህበራዊ ፍትህ፣ እንዲሁም ለጋራ ብልጽግና ከቆሙ ሃይሎች ሁሉ ጋር ለህዝቦች የጋራ ጥቅም ስባል አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።
ድል ለሰፊዉ ሕዝብ !
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር
ነሐሴ 23, 2011 ዓ.ም.

No comments:

Post a Comment