መንግሥትና ኢሕአዴግ ለአንደኛ ሴሚስተር ፈተና ይዘጋጁ

Wednesday, 07 November 2012 (ሪፖርተር ጋዜጣ)

ከሐዘን በኋላ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሾም ጉዞው ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የታቀደው በሙሉ ተፈጸመ ወይ ብለን አንገመግምም፡፡

ገና ጅምር ላይ ነንና፡፡ ይህ ጥያቄ የሚነሳው በአጠቃላዩ የመልቀቂያ ፈተና ጊዜ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ እየተደረገ ያለው ጉዞ ግን የመጀመሪያ ሴሚስተር በመሆኑ፣ ኢሕአዴግም እንደ ድርጅት መንግሥትም እንደ መንግሥት ሊዘጋጁ ይገባል፡፡ ከተዘጋጁበት ፈተናው በጣም ቀላል ነው፡፡ ካልተዘጋጁበት ደግሞ ፈተናው ቀላል ቢመስልም፣ መልስ ለመስጠት ግን አዳጋች ሊሆን ይችላል፡፡

የአሁኑ የመጀመሪያው ሴሚስተር ፈተና ዋነኛው ጥያቄ ኢሕአዴግም መንግሥትም በውስጣቸው አንድ ሆነው፣ በአንድ ልብ እየተወያዩ፣ እየተመካከሩና እየተናበቡ እየተንቀሳቀሱ ናቸው ወይ የሚል ነው፡፡


ሕዝብ እንደ ፈታኝ ይህንን ጥያቄ ያቀርባል እንጂ መልሱን እንደ ፈተና ኢሕአዴግና መንግሥት የሚመልሱት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ስንልም ሁለት ገጽታ አለው፡፡ አንደኛው ኢሕአዴግ እንደ ኢሕአዴግ በአጠቃላይ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አራቱ አባል ድርጅቶች በተናጠል ናቸው፡፡ አራቱም ድርጅቶች በየግላቸው በውስጣቸው አንድ ሆነው እየተጓዙ ናቸውን?

ልዩነት የሚባል ነገር አይኖርም እያልን አይደለም፡፡ ልዩነት ኖረም አልኖረም በዴሞክራሲያዊ መንገድ በድምፅ ብልጫ እየወሰኑና እያፀደቁ እየተጓዙ ነው ያሉት? ወይስ የግልና የቡድን ስሜትና ዕምነት ይዘው ሳይቀናጁ እየተንገዳገዱ ናቸው?

የየግላቸውን ሁኔታ አይተውና መርምረው አንድ በመሆን ጠንካራ አንድነት ያለውን የጋራ ድርጅት ኢሕአዴግን እያንቀሳቀሱ ናቸው ወይ?

መልሱን ለራሱ ለኢሕአዴግና ለመንግሥት እንተወዋለን፡፡ በመልሱ ዙሪያ ግን አጽንኦት ሰጥተን የምንለው ነገር አለ፡፡ አንደኛ ‹‹ለተማሪ ዜሮ አይሰጥም›› የሚባለው ነገር በዚህ ፈተና አይኖርም፡፡ ሁለተኛ ፈተናውን ማለፍ ግዴታ ነው፡፡ በዚህ ፈተና ከወደቁ በኋላ በሌላ ፈተና እናልፋለን ችግር የለም ብሎ መፅናናት አያዋጣም፡፡

የድርጅት አባላትና የመንግሥት ባለሥልጣናት የተሸከሙት ኃላፊነት እጅግ ከባድ መሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡ እንኳን ተደክሞ ጠንክሮም ቢሆን ጉዞው አስቸጋሪ ነው፡፡ አካባቢያችን አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ የኢኮኖሚው ሁኔታ ዓለምን እያናጋ ነው፡፡ የኑሮ ሁኔታ ከጭነት ልክ በላይ ሸክም ሆኗል፡፡ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማዳከም ሁሉንም ዓይነት እንቅስቃሴ ከማድረግ ወደኋላ አይሉም፡፡ የተያዘው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እጅግ ጠቃሚ ቢሆንም አፈጻጸሙ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ተቋማት ጠንካራ አይደሉም፡፡ ሙስና አገሪቱን እያጨማለቀ ነው፡፡ ወዳጅ መስሎ ጠላትም እየበዛ ነው፡፡

በእንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ለግል ሥልጣንና ክብር ብቻ እያሰቡ መንቀሳቀስ ለአገርና ለሕዝብ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ተያይዞ መወደቅን የሚያስከትል ነው፡፡ ሕዝብ ይመሩኛል፣ ከችግር ያወጡኛል፣ ወደላቀ ደረጃ ያሸጋግሩኛል ብሎ እየጠበቀ ነው፡፡ይህ ሕዝብ ምን ያህል ቅንና ወርቅ እንደሆነ በዓለም ፊት አስመስክሮአል፡፡ መሪዎቹን እባካችሁ እናንተም ቅንና ወርቅ ሁኑ እያለ እየጠየቀና እየፀለየ የድርሻውን እየተጫወተ ነው፡፡

ከኢሕአዴግ ከመንግሥት የሚጠበቀው መልስ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ኃላፊነታችንን እንወጣለን፡፡ ሕዝባችንን እናገለግላለን፡፡ ራዕያችንና ዕቅዳችንን ተግባር ላይ እናውላለን የሚል፡፡ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የሚል ሳይሆን አሁኑኑ፡፡

ኢሕአዴግ ተሰበሰበ፣ መንግሥት ተሰበሰበ፣ አስተዳደር ተሰበሰበ ማለት መብት ተገኘ ማለት አይደለም፡፡ ስብሰባ ችግር ፈቺ ሊሆን ይችላል፡፡ ስብሰባ ከቢሮ ለመሸሽና ለመደበቅ የሚውል መሣርያም ሊሆን ይችላል፡፡ ስብሰባ ውጤት ካላመጣና ችግር ካልፈታ በስተቀር ተጨማሪ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ቁምነገሩ ስብሰባው ምን ፈየደ የሚል እንጂ፣ ተሰበሰቡ ወይ? የሚል አይደለም፡፡

በተለይም ኢሕአዴግም መንግሥትም ልዩ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ መረጃ ለሕዝብ ያቅርቡ፡፡ ኢሕአዴግ ምን እየሠራ እንደሆነ ሕዝብ አያውቅም፡፡ ኦሕዴድ ምን እየሠራ እንደሆነ የኦሮሞ ሕዝብ በግልጽ አያውቅም፡፡ ብአዴን ምን እየሠራ እንደሆነ የአማራ ሕዝብ አያውቅም፡፡ ደኢሕዴን ምን እየሠራ እንደሆነ የደቡብ ሕዝብ አያውቅም፡፡ ሕወሓት ምን እያከናወነ እንደሆነ የትግራይ ሕዝብ አያውቅም፡፡ በአጠቃላይ መንግሥትና ኢሕአዴግ ምን እየሠሩ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ አያውቅም፡፡

በየዕለቱ የሚነግረው የለምና፡፡ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የሚመለከተው ተቋም ቢኖርም፣ መረጃ የለም፡፡ ተቋሙ እየተናገረ አይደለም ማለታችን ሳይሆን ሕዝብ የሚጠብቀውና የሚነገረው ተመጣጣኝ አይደለም ማለታችን ነው፡፡በዚህ ሴሚስተር ሕዝብ ለኢሕአዴግና ለመንግሥት እያቀረበው ያለው ትልቁ ጥያቄ ምን እየሠራችሁ ነው የሚለው ነው፡፡ አንድ ሆናችሁ እየተነጋገራችሁ፣ እየተገማገማችሁና እየተጠናከራችሁ እየመራችሁን ነው? ወይስ እየተራራቃችሁና እየተለያያችሁ? ሀቁን መናገር ያለባችሁ እናንተ ናችሁና ንገሩን እያለ ነው፡፡ ግዴታችሁ ነው እያለም ነው፡፡

አሁን ያለንበት ወቅት ወደፊት ስንጓዝ ግራ ቀኙን እያየን፣ ዞር እያልንም የኋላችንን እያስተዋልን የምንጓዝበት ነው፡፡ መንግሥት ሕዝብን አምኖና ከጎኑ አሠልፎ ብቻ ሊጓዝና ሊዘልቅ የሚችልበት ጉዞ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ጠንካራ አንድነትና በጋራ የተቀናጀ ጉዞ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ወሳኝ ነውና፡፡

በዚህ የሴሚስተር ፈተና የሕዝብ  ጥያቄ ለኢሕአዴግና ለመንግሥት ቀርቧል፡፡ መልሱን እየጠበቅን ነው፡፡ ማለፍ ግዴታ ነው!
Ethiopian Reporter News Paper   

No comments:

Post a Comment