“ሚኒሊክን ብትወቅሱ ማንነታችሁን ትረሱ” በሚል አርዕስት ፅፈህ የለጠፍከዉን ሀተታ አይቸዋለው። የግዕዝ ፊደሎችን መፃፍ ባልችልም ፤ ጫፍ የወጣ ወገንተኝነትህና ጥላቻህ ፊደል እየለቀምኩም ቢሆን መልስ እንድሰጥ አስገድዶኛል። ለነገሩ ቃለ ምልልህን ከሰማሁ ጊዜ ጀምሮ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ልዩ ጥላቻ እንዳለህ የተረዳሁ ቢሆንም ምክንያቱ ምን እንደሆነ ላውቅ የቻልኩት ከዚህ ፅሁፍህ ላይ ነው፡፡ በዚህ ፁሑፊ ራስህን ያልቻልክ የስርአቱ ሰለባ መሆንን ስላስመሰከርክ ፥ ይህ መልስ ለስርአቱ አቀነንቃኞች የተሰጠ ነው። ለማንኛውም እስኪ የፅሁፍህን ይዘት ወደ መገምገም ልመለስ፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ
የኢትዮጵያ ታሪክ የዉሸት ታሪክ ነዉ። ባለሟሎቹ ነገስታቱን ለማስደሰት ንጉሱን በማሞገስ ታረክ በማስመሰል ይጽፉለታል። እንድያው ም የኢትዮጽያ ታረክ ክብረ መንግስት ይባል የለም:: ጠላቱን ደግሞ በማዉገዝ ያስደስቱታል። እንግዲህ እነ ደብተራ ዘነብ እና አባ ባህሪ ከዚሁ ቡድን የሚመደቡ ናቸው፡፡ በተለይም አባ ባህሪ ብእራቸውን ከወረቀት ጋር ሲያገናኙ የነገዱን ቁጥር ብዛት ፣ ሰውን ለመግደል ያለዉን ትጋት ወዘተ እያሉ በጥላቻ እና በጠላትነት መንፈስ ልክ እንዳንተ የፃፉ በመሆናቸው እነዚህን ታሪኮች እንደ እውነተኛ ታሪክ አድርገህ ልትከራከርባቸው መሞከርህ የታሪክ ምሁርነትህ ን አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ ይህ ማለት ልክ ዛሬ የመለስ ደጋፊዎች “የተለየ ራዕይ ያለው፣ መልካም መሪ”፣ በሚሊዮን ዓመት አንዴ የተፈጠረ፣” ወዘተ… እያሉ እየፃፉለት ያሉት ነገ ታሪክ መሆኑ አይቀርምና ያኔ እነዚህ አጨብጫቢዎች የፃፉለትን እንደማጣቀስ ይቆጠራል፡፡ ከኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልናምናቸው የምንችላቸው እውነታዎች ጥቂቶች በመሆናቸው ስለተፃ ፉ ብቻ አንቀበላቸሁም፡፡ በተቻለ መጠን ወገንተኛ ባልሆኑ አካላት የተፃፉትን መርጠን እንጠቀማለን፡፡
የግል ጥላቻ
ከከንባታ ጎሳ የተወለድክ መሆንህን ጠቅሰህ የአርሲ ኦሮሞዎች እናትህን፣ የእናትህን እናት(አያት) እና በአጎትህ ላይ ጭፍጨፋ መፈፀማቸውን ጠቅሰሀል:: ድርጊቱም የተፈፀመው በጎሳ ግጭት ሳቢያ መሆኑን ገልፀሀል፡፡ ለመሆኑ የከንባታ ጎሳ በጦርነት የበላይነትን ቢያገኝ አርሲዎችን አይገልም ነበርን? የአበባ ጉንጉን ነበር ወይ የሚያጠልቁላቸው? እንዲህ አይነት ጦርነቶች በጎሳዎች መካከል የተለመዱ ስለሆኑ የኦሮሞን ጨካኝነት ለማሳየት ይህንን በምሳሌነት መጥቀሽ ያንተን ወገንተኝነት እና የበቀል ስሜት ከማሳየት ውጪ ምንም እርባና የለውም፡፡
አኖሌ
የአኖሌ ታሪክ እንደሚያስረዳው በአኖሌ የተፈፀመው የቀኝ እጅ እና ጡት ቆረጣ በጦርነት ወቅት የተፈፀመ አልነበረም:: ይህ ድርጊት የተፈጸመው በራስ ዳርጌ በተመራው ስድስት ዙር ዘመቻ አራቱን አርሲዎች ያሸነፉ ቢሆንም በመጨረሻ “አዙሌ” በተባለው ቦታ በተደረገው ጦርነት በቁጥር 120,000 (አንድ መቶ ሃያ ሺህ) የአርሲ ጦረኞች ከተገደሉ በኋላ የነፍጠኛው ጦር አሸንፎ አርሲን ሊቆጣጠረው ችሏል፡፡ ከዚህም በኋላ ቢሆን የአርሲ ኦሮሞዎች በተፈለገው መጠን አልገብር ስላሉ እና በተበታተነ ሁኔታ ማጥቃት ባለማቆማቸው አኖሌ በተባለው ቦታ “ሰላም እናወርዳለን እና የእርቅ ጉባኤ ተሳተፉ”በማለት ነፍጠኞቹ ነጭ ባንዲራ እያውለበለቡ ህዝቡ እንዲሰበሰብ ካደረጉ በኋላ በሦስት ሺህ አርሲዎች ላይ አሰቃቂውን የቀኝ እጅ እና የጡት ቆረጣ ፈፀሙ፡፡ (ይህን በተመለከተ የዶክተር አባስ ሀጂን መፀሀፍ አንብብ) ይህ የቀኝ እጅ ቆረጣ በአድዋ ጦርነት በተማረኩት የኤርትራ አስካሪዎች ላይም ተፈፅሟል። ስምንት መቶ ወታደሮች ቀኝ እጅ እና እግራቸውን በአፄ ሚኒሊክ ትዕዛዝ ተቆርጧል፡፡ ይህን ሲያደርጉ ግን ከነዚህ ጋር የተማረኩትን የጣሊያን ወታደሮች ምንም ሳያደርጉ ነበር የሸኟቸው፡፡ ይህም አፄዉ የፈረንጅ አጎብዳጅ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ይህ በኤርትራ አስካሪዎች ላይ የተፈፀመው ድርጊት እንደዚህ አይነት የጭካኔ እርምጃ የተለመደ መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ በተጨማሪም “አፄ ሚኒሊክ እጅግ ተዋረዱ የሸዋን ነገስታት እጅ ነስተው ሄዱ” የሚለው ቅኔ እጅ የመቁረጥ ባህል ስር የሰደደ መሆኑን ማሳያ ነው። ጳዎሎስ ኞኞ አፄ ቴዎድሮስ አንድ ጊዜ አራት መቶ ሰው ሌላ ጊዜ ስድስት መቶ ሰው እጅ ቆርጠው አንገታቸው ላይ አንጠልጥለው እንዲሄዱ ያደረጉ መሆኑን እና ይህም በተለያየ ጊዜ ይፈፀም እንደነበር ፅፏል፡፡
ጨካኝነት
ኦሮሞ በጦርነት ሲያሸነፍ “ጨካኝ” ይሉታል። ሲያሸነፋቸዉ “ፈጀው፣ ጨፈጨፈው፣ ጨረሰው” በማለት እና አቢሲኒያውያን የኦሮሞን ህዝብ ሲያሸንፉ ደሞ “ዛሬ አምላክ አሳልፎ በእጃችን ሰጠ” አንገታቸውን ቆራርጠን ጭንቅላታቸውን ከመርን። በእግዚአብኤር ኃይል ይህን ያህል ገደልን እያለ ኦሮሞን መግደል ፅድቅ እንደሆነ አድርጎ ይጽፍ የነበረው አባ ባህሪ ነበር። በውጊያ እነሱ ሲያሸንፉ ጀግንነት እና የአምላክ እርዳታ፤ ኦሮሞ ሲያሸንፋቸው ደሞ እንደ ጨካኝነት መቁጠራቸው ወገንተኝነትን እና ጥላቻን ከማንፀባረቅ ውጪ ሌላ ምንም ፍቺ የለውም። ጦርነት ከሆነ ጦርነት ነው:: ኦሮሞ እየተወጋ ዝም አይልም። ምናልባትም ወግተውት አፀፋውን ሲመልስ መንጫጫቱ “አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው” መሆኑ ነው፡፡ በሌላ የሕግ መርህ ባለቤት በራሱ ጉዳይ ፈራጅ አይሆንም ስለሚባል በራሳችሁ ጉዳይ ለራሳችሁ የሰጣችሁት ምስክርነት ተአማንነት አይኖረውም፡፡ እንዲሁም ጠላት ነው ብላችሁ በጥላቻ እና በፍራቻ ስለምታዩት የኦሮሞ ህዝብ የምትሰጡት ምስክርነትም ቢሆን ከወገንተኝነት የፀዳ ሊሆን አይችልም። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ኦሮሞን ከሚጠሉት ጎራ ካሉት ፀሀፊዎች እንደ እነ አለቃ ታዬ አይነቶቹ በመፀሀፋቸው ኦሮሞ ሰላም ወዳድ፣ እግዚአብሄርን የሚፈራ፣ በሸንጎው በውሸት የማይፈርድ፣ ምንም እንኩዋን ክርስትናን ያልተቀበለ ቢሆንም አስርቱን ትዕዛዛት “ክርስቲያን ነን” ከሚሉት በላይ ያከብራል በማለት መስክሯል። ምንም እንኩዋን ክርስቲያኖች ብንሆንም ክፉዎች እና በመፀሀፉ የማንመራው እኛ ነን እንጅ “ኦሮሞ እንኩዋን በሰው በእንስሳ እንኩዋን አይጨክንም” በማለት በሰፊው ያተተውን እንድታነብ እጋብዝሀለው፡፡ ይህንን የዋህ እና ሰላም ፈላጊ ህዝብ ጫና እና ጥቃት ካበዛችሁበት በኋላ እሱ አምርሮ አፀፋውን ሲመልስ “ጨካኝ” እያላችሁ ብትንጫጩ ማንም አይሰማችሁም። ኦሮሞ ጀግና እንጂ ጨካኝ አይደለም፡፡ ስለ ኦሮሞ ጀግንነት በደንብ አድርጋችሁ ታዉቃላችሁ። በአድዋ ጦርነት የአምባላጌን ምሽግ የሰበረዉ በማን የተመራ ጦር ነዉ? ገበየሁ ገቦ አይደለም እንደ? ሚኒሊክ ፈርቶ ስደራደር ፣ ገበየሁ ሳይታዘዝ ድል አድርጎ በዉጊያዉ ተገደለ:: ፈረንጆቹን ፈርቶ መቐለ ላይ የሸኛቸዉ ሚኒሊክ፣ ጣይቱ ባትኖር ከጣሊያን ጋ ይዋጋ ነበር? ኢትዮጵያዊነትን እንድንቀበል ለማባበልም ብሆንም ጣይቱ ኦሮሞ መሆኗን አምናችኋል::
ወራሪ
የኦሮሞ ህዝብ የኩሽ ዝርያ ነው፡፡ ይህ የኩሽ ነገድ ህዝብ ከደቡባዊ ግብፅ ጀምሮ በዛሬይቷ ሱዳን እና በአፍሪካ ቀንድ ለብዙ ሺህ ዓመታት በመኖሩ ይህ አካባቢ ለኩሾች ጥንት መኖሪያቸው ነው፡፡ ከደቡብ የመን ከ700 ዓመተ አለም እስከ 100 ዓ.ም ፈልሰው ወደ አፍሪካ ቀንድ የመጡት ሀበሻ እና ሀማሴን የተባሉት የሴም ዘሮች ናቸው፡፡ የኩሽ ነገድ የሆኑት እነ ሲዳማ፣ ሀዲያ፣ አፋር፣ ሱማሌ፣ አገው፣ ሁሉ አገራቸው የአፍሪካ ቀንድ መሆኑ እየታወቀ የኩሽ ነገድ የሆነው ኦሮሞን ብቻ የህንድ ውቂያኖስን አሻግራችሁ ስታሰፍሩት እፍረት ነገር አልፈጠረባችሁም፡፡ “የአብዬን እከክ ወደ እምዬ ልከክ” እንደሚባለው መጤ የሆነው የሴሜቲክ ነገድ ነባሩን ህዝብ ወራሪ የማለት የሞራል ብቃት የለውም፡፡ አባ ባህሪ ኦሮሞዎች ገላና የተባለውን ወንዝ ወደ ምስራቅ አቋርጠው መጡ ይበል እንጂ ይህ ገሞ የተባለው ቦታ ጋሞ ጎፋ ስለመሆኑ ምንም ደጋፊ ማስረጃ የለም፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮች አሉ፡፡ በመጀመሪያ፣ ገላና የትኛው ወንዝ ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ገላና ማለት ወንዝ ወይም ትልቅ ውሃ ከማለት ውጪ ገላና የሚባል ወንዝ የለም፡፡ የሰገን ወንዝ ወይም ገላና አባያን አቋርጠው ወደ ጋሞ ጎፋ መጡ እንዳይባል ወደ ምስራቅ እንጂ ወደ ምእራብ ተሻገሩ አላሉም፡፡ አባያ ከጋሞ ጎፋ በምእራብ በኩል ስለምትገኝ አባያን ከተሻገሩ ወደ ምእራብ ተሻገሩ ማለት ነበረበት፡፡ ሌላኛው አወዛጋቢ ጉዳይ አባ ባህሪ ገሞ ከማለት ውጪ ከገሞ እስከ ሸዋ መካከል ባለው ሰፊ አካባቢ ምንም ገጠመኞች ሳይፅፉ በግንደበረት፣ በጎጃም እና በሌሎች ሸዋ አካባቢዎች የተደረጉ ጦርነቶች እና ግጭቶችን ብቻ ማተታቸው እንዲሁም በሰሜን ሸዋ አካባቢ እና በሌሎች ሸዋ አካባቢዎች ገሞ ተብለው የሚጠሩ ቦታዎች መኖራቸው አባ ባህሪ የነበሩት በሰሜን ሸዋ አካባቢ እንጂ ጋሞ ጎፋ አልነበረም የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡ በተጨማሪም አባ ባህሪ ከነበሩበት ገሞ ከሚባለው ቦታ ሸሽተው ወደ ደብረ ዳሞ ነው የገቡት፡፡ በደብረዳሞ እና በገሞ መካከል ያለው ርቀት አጭር መሆኑን ከፅሁፋቸው ማወቅ ስለሚቻል የነበሩበት ቦታ ሸዋ ውስጥ መሆኑን የበለጠ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የዘር ግንድ
በዚህ ፅሁፍህ የኦሮሞ ህዝብ ነገድ እንጂ የዘር ግንዱ አይተሳሰርም፡፡ ከአንድ የዘር ግንድ የወጣ አደለም፤ በቋንቋም በባህልም አይገናኝም ብለሃል፡፡ ይህ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ለፅሁፍህ ዋቢ ያደረከው በዋናነት የአባ ባህሪን መፀሀፍ ሲሆን፤ አባ ባህሪ ደግሞ ኦሮሞ ከአንድ የዘር ግንድ የተገኘ አንድ ህዝብ መሆኑን አልካደም፡፡ እንደውም ኦሮሞ ቦረና እና ባሬንቱማ በሚባሉ ሁለት ትላልቅ ጎሳዎች ስር የተደራጀ መሆኑን ጠቅሶ የቦረና እና የባሬንቱማ ልጆች እነማን እንደሆኑ በመዘርዘር ህዝባቸው በመብዛቱና አገራቸው በመራራቁ በተለያዩ ገዳዎች ስር መተዳደር መጀመራቸውን አትቷል፡፡ በዚህም መሰረት የቦረና ኦሮሞዎች ኦዳ ነቤን ማእከላቸው ሲያደርጉ ባሬንቱማዎች ደግሞ ማእከላቸውን ኦዳ በቡልቱም አድርገዋል፡፡ ያለምንም እፍረት የኦሮሞ ህዝብ በቋንቋም በባህልም አይገናኝም በማለትህ እኛ አፍረንልሀል፡፡ ይህ ህዝብ የአንድ ቋንቋ ባለቤት፤ በገዳ ስርአት ሲተዳደር የነበረ እና አንድ ሃይማኖት “ዋቄፈና” የነበረው ህዝብ ነው፡፡ አንተም ሆንክ አባ ባህሪ፣ የኦሮሞ ህዝብ ዘሩን ቆጥሮ ከአስራ አምስት እስከ ሃያ አባት ድረስ የትኛው ጎሳ ከየትኛው ቅርንጫፍ እንደሆነ እንደሚያውቅ ታውቃላችሁ፡፡ “ጋላ” የሚለው ቃል ኦሮሞን አይወክልም ብለህ ያቀረብከው ኦሮሞን ለመከፋፈል ካለህ ፍላጎት እንጂ ከኦሮሞ በስተቀር በዚህ ስም ሲሰደብ ወይም ሲጠራ የነበረ ሌላ ብሄርም ሆነ ብሄረሰብ የለም፡፡ አለመኖሩን በደንብ እያወክ ይሄን ህዝብ ለመከፋፈል ባለህ እኩይ አስተሳሰብ ህዝቡ በቋንቋም በባህልም ሆነ በዝርያ በጭራሽ አይገናኝም ማለትህ በእጅጉ የሚያሳፍር ነው፡፡
የገዳ ስርአት
የገዳ ስርዓት ስልጣን ከአንድ ቡድን ወደ ሌላ ቡድን በሰላማዊ መንገድ የሚተላለፍበት ስርዓት ነው፡፡ ይህ ስርዓት በየስምንት ዓመት እድሜ እርከን የስራ ድርሻ በመከፋፈል ህብረተሰቡን በአምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ስር በማደራጀት አምስቱ ቡድኖች ተራ በተራ ለስምንት ዓመት የሚያስተዳድሩበት ስርዓት ነው፡፡ “በዚህ ሹመት ላይ ባለ ግዜ ውስጥ ሰው ካልገደለ ጠጉሩን አይላጭም ጉቱን አያሳድግም” ብለሃል፡፡ ይህ ከእውነት የራቀ እና ከጥላቻ የመነጨ አገላለፅ ነው፡፡ አንድ ጉዳይ ግን አለ፡፡ ሁሉም ሉባ የራሱ የሆነ የሚያከናውነው ተልዕኮ አለው፡፡ ለምሳሌ በጠላት የተያዘ መሬት ካለ የማስለቀቅ ግዴታ ስለሚኖርበት ያንን ጉዳይ እስካላከናወነ ድረስ እረፍት አይኖረውም፡፡
ገዳ የኦሮሞ መንግስ ስለሆነ ልክ ቡሽ የጀመረውን ጦርነት ኦባማ እንደሚጨርሰው ሁሉ የሙደና ገዳ የጀመረውን የሮበሌ ገዳ ይጨርሰዋል፡፡ ይህን ከአደራ ጋር የተሰጠውን ተልህኮ ሳያሳካ እረፍት አይኖረውም፡፡ ይህ ዳር ድንበሩን መከላከል እና የብሄሩን ክብር ማስጠበቅ እነ አባ ባህሪ በስርዐቱ ጥንካሬ ምክንያት በደረሰባቸው ሽንፈትየተነሳ የቻሉት ያህል ስርዐቱን አሉታዊ አስመስለው ስለፃፉ የስርዐቱ ዲሞክራሲያዊነት አያሳጣውም፡፡ የገዳ ስርዐት የኦሮሞን ህዝብ በእኩልነት እና በዲሞክራሲ እንዲኖር ያስቻለና በተሻለ አደረጃጀት የኦሮሞ ህዝብ በጎረቤቶቹ ላይ በጦርነት የበላይነትን ያጎናፀፈው በመሆኑ የኦሮሞን ህዝብ የሚጠሉ “አባ ባህሪዎች” እና ተሸናፊዎች ይህንን ስርዐት ሊወዱት አይችሉም፡፡
ሰለባ
መስለብ የሰሜቲኮችና የአማራ ባህል ነዉ። ማስርጃ ፩። በመጽሀፍ ቅዱስ መጽሀፈ ነገስት ዉስጥ ዳዊት የሳኦልን ልጅ ለማግባት የፊልስጤማዉያን ብልት ቆርጦ ማምጣቱ፥፥ ዳዊት የሰለሞን ኣባት ነዉ። የሰለሞን ልጆች ነን የሚሉት እነማን እንደሆኑ ማስረዳት አይጠበቅብንም። ማስርጃ ፪። በመጽሀፍ ቅዱስ የሀዋርያት ሥራ መጽሀፍ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዞ ነበር። ይህ ግዜ በግምት ፩ኛ ክፍለ ዘመን ነዉ። ሰዉየዉ ከሰሜን ኢትዮጵያ ስለመሆኑም ግልጽ ነዉ። ማስርጃ ፫ ። ኮሎኔል አልኸንድሮ ዴል ባየ የተባለው የኢትዮጵያ ወዳጅ በጻፈዉ “ቀይ አንበሣ” በተሰኘዉ መጽሀፍ ውስጥ አማሮች ከ፲ እስከ ዕድሜ የሆኑ ህጻናትን ብልት እየሰለቡ የንጉሶች፣ የራሶች እና የፊታዉራሪዎች አገልጋይ ጃንደረባ ያደርጏቸዉ እንደነበር ጽፏል። ድምጻቸዉ ወደ ቀጭንነትም ስለምቀየር ቤቴ ክርስቲያን ዉስጥም ይቀድሱ እንደነበር ይታወቃል።
ስልጣኔ
ሌላው በፅሁፍ ውስጥ ልትገልፀው የሞከርከው የኦሮሞ ህዝብ ኃላቀር እንደሆነ ልታሳይ የሞከርከው ሙከራ ነው፡፡ በዚህ ሙከራ ዘላንነትን (አርብቶ አደርነት) የአኗኗር ዘይቤ መሆኑን ረስተህ እንደ ኃላቀርነት ለማየት መሞከርህ ምን ያህል ኃላቀር እንደሆንክ የሚያሳብቅ ነው፡፡ ክርስቲያን አለመሆን ወይም በአፍሪካዊ እምነት (ዋቄፈና) ተከታይ መሆንም ቢሆን ሊደነቅ እና ሊኮራበት የሚገባ እንጂ እንደ ኃላቀርነት ሊታይ አይችልም፡፡ የራስ የሆነ የእምነት ፍልስፍና የዛን ህዝብ ታላቅነት የሚያሳይ ነው፡፡
አፄ ሚኒሊክ
1. ቡላቶቪች የተባለው ራሺያዊ በ1900 ከሚኒሊክ ጦር ጋር ዘምቶ የነበረ ሲሆን “Ethiopia though Russian Eyes” በተሰኘው መጸሀፉ የሚኒሊክ ወረራ የኦሮሞን ህዝብ ቁጥር በግማሽ ያሳነሰ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
2. ማርቲን ዴሳልቫክ የተባለ ፈረንሳዊ የካቶሊክ ሚሺነሪ (1900) “The Oromo: An Ancient Africa Nation” በተባለው መጸሀፋቸው በዚህ ወረራ የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር በግምት ከአስር ሚሊየን ወደ አምስት ሚሊየን መውረዱን ገምቷል፡፡
3. August 18, 1895 እ.አ.አ የታተመው የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አፄ ሚኒሊክ በኦሮሞ ላይ ዘመቻ በመክፈት ወንዶቹን በመፍጀት ሕፃናት እና ሴቶችን በባሪያነት መውሰድ በሰፊው ይተገበሩ እንደነበር ፅፏል፡፡
4. February 26, 1895 እ.አ.አ የታተመው የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አሰቃቂው የሚኒሊክ ዘመቻ በሚል ርዕስ ስር ሰሞኑን ንጉስ ሚኒሊክ በኦሮሞ ህዝብ ላይ በደቡብ አቢሲኒያ የከፈቱት ዘመቻ 70,000 ሰዎችን በመግደል 15,000 መማረካቸውን ገልፀዋል፡፡
5. August 2,1874 እ.አ.አ የታተመው የኒውወርክ ታይምስ ጋዜጣ የአቢሲንያ ባሪያዎች በሚል አርስት ስር በየዓመቱ ከ80,000 እስከ 90,000 የሚሆኑ ባሪያዎች በምፅዋ ወደብ በኩል ወደ ውጪ የሚሽጡ መሆኑን ጠቅሶ የባሪያ ነጋዴዎቹ ባሪያዎችን የሚገዙት ከነፍጠኞቹ ሲሆን ንጉሰ ነገስቱም የቀረጡ ተቋዳሽ መሆኑን ያትታል፡፡6. አኖሌ ላይ የሦስት ሺህ ኦሮሞዎች እጅ እና ጡት ከማስቆረጣቸው በተጨማሪ በአደዋ ጦርነት የተማረኩ 800 የኤርትራ አስካሪዎችን ቀኝ እጅ እና ቀኝ እግር አስቆርጠዋል፡፡
7. November 7, 1909 እ.አ.አ የታተመው የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በአርስቱ የአቢሲኒያው ንጉስ ሚኒሊክ በአሜሪካው የባቡር ሃዲድ ስራ ተቋራጭ ከፍተኛ የአክሲዮን ባለቤት ናቸው በማለት ወደ ዝርዝሩ ውስጥ ስንገባ ይህ የባቡር ሃዲድ አክሲዮን ከሃያ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑ እና ከዚህ በተጨማሪ በቤልጅየም እና እስካንዲኒቭያ ከተሞች የወርቅ አምራች ኩባንያ ውስጥ አክሲዮን እንዳላቸው ዘርዝረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ንብረት ከዬት መጣ ብለን ብንጠይቅ ከተወረሩ ብሄር ብሄረሰቦች የተዘረፈ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት የሚኒሊክ ወታደሮች ከአርሲ 66,000 የቀንድ ከብት (ፕሮፌሰር መኩሪያ ቡልቻ)፤ ከወላይታ 18,000 (ተሻለ) ከደቡብ ኦሞ 40,000 ከጂጂጋ 50,000 (ጆን ማርካኪስ) ወዘተ… የተዘረፈ ነው፡፡ ከ፩ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጽያዊያኖችን በባርነት ሸጠዋል(መኩሪያ ቡልቻ)::
8. አፄ ሚኒሊክ ከምእራብ ኢንዲያ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የጥቁር ህዝብ መሪ ሁንልን ብሎ የጠየቀውን ቤኒቶ ሲልቪያን የተባለውን ሰውዬ እኔ ጥቁር አይደለሁም፡፡ ሴማዊ ነኝ በማለት አባረውታል፡፡ ሀይለስላሴም HO Davis የተባለው ታዋቂው የጥቁር መብት ታጋይ እና Marques Garvey የተባለው ጃማይካዊ የጥቁር መብት ታጋይ ባናገሩት ጊዜ እኔ የሰለሞን ዘር ነኝ በማለት አፍሪካዊነታቸውን ክደዋል፡፡ እነዚህ በአፍሪካዊነታቸው የማያምኑ፣ በአፍሪካዊነታቸው የሚያፍሩ የበታቸው ስነ ልቦታ የተጠናወታቸው እና በራሳቸው የማይተማመኑ ናቸው፡፡
9. ተወራሪው የደቡብ ህዝብ መሬቱን ተነጠቀ፤ ነፍጠኞቹ መሬቱን ተከፋፍለሁ ለሚፈልጉት ሰጡ፡፡ በሃብት ንብረቱ ላይ አዘዙበት ህዝቡ ወደ ባርነት ወረደ :: መሬት አልባ፣ ታሪክ አልባ፣ ባህል አልባ፣ ሀይማኖት አልባ፣ አረመኔ ህዝብ ብለው ሰደቡት፡፡
ያልተሳካዉ ፕሮጀክት
እናንተማ እጃቸውንና ጡታቸውን ቆርጠን አዋርደናቸዋል፤በማንነታቸዉ እንዲያፍሩ አድርገናቸዋል፤ ስነልቦናቸውን ሰልበናል፤ ቋንቋውን እና ባህሉን ቀብረናል ብላችሁ ተዝናንታችሁ ነበር:: “የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ” የተባለው ቃል ይፈፀም ዘንዳ ግድ ነውና ከአንድ መቶ ሰላሳ ዓመታት በኋላም ስነ፡ልቦናው፣ ቋንቋው፣ ማንነቱ፣ ባህሉም ተጎዳ እንጂ አልጠፋም:: ምንም እንኩዋን የወሎ ኦሮሞ ጎሳዎች የነበሩት እነ የጁ፣ ወረ ቃሉ፣ ወረ ሂመኖ፣ ወረ ባቦ፣ ወሎ፣ ወረ ሼህ፣ ለገ አምቦ፣ ራያ፣ እና አዜቦ የመሳሰሉትን ማንነታቸውን እና ቋንቋቸውን በማስቀየር ቢሳካላችሁም ከዘጠና በመቶ በላይ የኦሮሞ ህዝብ ማንነቱ ያልተፋቀ በመሆኑ ፕሮጀክታችሁ ባለመሳካቱ ኢትዮጵያዊ ማንነት እንጂ ሌላ ማንነት የለም እያለችሁ ብታለቃቅሱ አይፈረድባችሁም::
ማጠቃለያ
አሁን የሚታለቅሱት የተወራሪ ብሄርና ብሄርሰቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ ሀይማኖትና ማንነት ለማጥፋት አያቶቻችሁ የነደፉት ፕሮጀክት ባለመሳካቱና የከተሞቹን ስም ለውጣችሁ፣ የሰዎችን ስም አስቀይራችሁ፤ ቀብረነዋል ብላችሁ ያሰባችሁት ህዝብ የወጠናችሁት ሁሉ ሳይሳካ ቀርተዋል። የጭቁን ህዝብ ትግል እያሸነፈ ሲመጣ የሚትጮሁ የፊውዳል ቡችሎች ሆይ እናንተ ትቀበራላችሁ እንጂ የሰፊው ህዝብ ቋንቋ፣ ሀይማኖት፣ ባሀል ይለመልማል እንጂ ወደ ኋላ ስለማይመለስ እርማችሁን አውጡ፡፡ አረመኔ፣ ኋላ ቀር፣ ያልተገረዘ፣ ወራሪ፣ ታሪክ አልባ፣ አገር አልባ፣ ዘላን ብላችሁ ብትሳደቡ የህዝቡን ቁጣ ከመቀስቀስ እና የህዝቦችን ተቻችሎ አብሮ መኖር እና ሠላምን ከማደፍረስ ውጪ የማንነት ስነ-ልቦና ልትጎዱ ስለማትችሉ በ130 ዓመት ውስጥ ያልተሳካው አሁን ሊሳካላቹ አይችልምና ለሞት የተቃረበ ሰው ከሚናዘዘው ኑዛዜ ለይተን አናየውም፡፡
No comments:
Post a Comment