ሰኔ 7, 2014ዓ.ም | የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
በወያኔ መንግስት የኦሮሞ ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጭካኔ የተመላበት የግድያ ወንጀል፡ በሃበሻ ገዢ መንግስታት የኦሮሞ ምሁራንን ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት ለረዥም ዓመታት ኣቅደው በመስራት ላይ ያሉት የዘር ማጥፋት ተግባር ኣካል ነው። በተለይም የህዝቡ ዓይንና ኣለኝታ፡ የነገ ሃገሪቷ ተስፋ የሆኑ ወጣቶችን በእስር ቤት ውስጥ ለኣካላዊና ለሰነ-ልቦናዊ ሰቆቃ በመዳረግ በኣሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እንድታልፍ ማድረግ የተለመደ ሁኔታ ሆኗል። የወያኔ ኣምናገነን መንግስት የፖለቲካ ስልጣኑን በሃይል ከተቀጣጠረ ኣንስቶ ባሉ 23 ዓመታት ውስጥ ይህን በመሰለ ዘግናኝ ሁኔታ የተገደሉ የኦሮሞ ዜጎች ቁጥር የትየለሌ ነው። የወጣት ኒሞና ጥላሁን ሞትም በዚሁ ስልት ጠላት ካደረሳቸው ግድያዎች ውስጥ ኣንዱ ነው። ኒሞና በሩጫ ላይ ሳለ ካሰበበት ሳይደርስ ያለኣንዳች ጥፋት የኦሮሞ ዜጋ በመሆኑ ብቻ ተወንጅሎ በወያኔ ስርዓት በኣጭሩ የተቀጨ የ28 ዓመት ወጣት ነው።
ኒሞና ከኣባቱ ኣቶ ጥላሁን ኢማናና ከእናቱ ወ/ሮ ላቀች እንዳለማ ሙልአታ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኣርጆ ከተማ ተወለደ። የ1ኛ እና
2ኛ ደረጃ ትምህርቱንም እዚያው ኣርጆ ከተማ በማጠናቀቅ የከፍተኛ ትምህርቱን ለመቀጠል በ2004ዓም ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ ገባ።
በዚሁ ዓመት የኦሮሞ ተማሪዎች ከፊንፊኔ ጉዳይ ጋር ኣያይዘው ባስነሱት ተቃውሞ የወያኔ ስርዓት ከ400 በላይ ተማሪዎች ላይ
ባሳለፈው ኢ-ፍትሃዊ ብይን ኒሞና ጥላሁንም ለኣንድ ዓመት ከትምህርት ገበታው ተባረረ። ከኣንድ ዓመት በኋላም ወደ ትምህርት
ገበታው በመመለስ በ2007 ዓም የመጀመሪያ ዲግሪውን በ'Banking and Insurance' በማጠናቀቅ ተመረቀ። በወያኔ መንግስት
ሃይሎች ህይወቱ እስካለፈችበት ዕለት ድረስም በመምህርነት ስራ ላይ ተሰማርቶ በሸኖ ከተማ ህዝቡን ሲያገለግል ነበር። በስራ
ላይ እያለ ኦሮሞ ሆኖ በመፈጠሩና በብሄርተኝነቱ ብቻ ከወንጀለኛ ተቆጥሮ በ2008ዓም በወይኔ መንግስት የደህንነት ሃይሎች
ታፈነ። የወይኔ ስርዓት የኦሮሞ ምሁራንና የህዝብ ኣለኝታ የሆኑ የኦሮሞ ዜጎችን በኦነግ ኣባልነት ወንጅሎ የመሰወር ያረጀ-ያፈጀ
ስልት ሰለባ የሆነው ወጣት ኒሞና ጥላሁን እጅግ ዘግናኝና ኢ-ሰብዓዊ ሰቆቃ ሲፈጸምበት ነበር።
ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥም በማዕከላዊ፣ በቃሊቲ፣ በቂሊንጦና በዝዋይ እስር ቤቶች ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት
እስከተለየበት ቀን ድረስ የድብደባና ቶርቸር ተግባር ሲፈራረቅበት ነበር። በደረሰበት ድብደባና ሰቆቃም ለከፋ የጤና መታወክ
ተዳርጎ ተገቢውን የህክምና ኣገልግሎት በመነፈግ ህይወቱ እንድታልፍ ተደርጓል። ከረዥም ግዜ ድብደባ የተነሳ ቁስሉ ኣመርቅዞ
ለከፋ የእጢ በሽታ ዳረገው። ለይስሙላ ወደ ሃኪም ቤት ተወስዶ የቀዶ ጥገና ህክምና ከተደረገለት በኋላ ቁስሉ ሳያሽር ወደ
እስርቤት እንዲመለስ በማድረግ በቁሙ እንዲሞት ፈረዱበት።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የወጣት ኒሞና ጥላሁን ሞት ከህመም የተነሳ የሚያጋጥም ተፈጥሮኣዊ ሞት እንዳልሆነ ያምናል። የወያኔ
መንግስት የኦሮሞ ልጆችን ኣፍኖ ካሰረና የከፋ ሰቆቃ ከፈጸመባቸው በኋላ ህይወታቸው ልታልፍ ስትል ኣንገታቸው ላይ ገመድ
በማንጠልጠል እራሳቸውን እንደገደሉ በማስመሰል እንዲሁም ታመዋል በሚል ለይስሙላ ሃኪም ቤት መውሰድና የመሳሰሉትን
በመጠቀም በኦሮሞ ልጆች ደም የጨቀየውም እጁን ንጹህ ለማመሰል እያደረገ ያለው ጥረት የኦሮሞ ህዝብን ሊያሞኝ እንደማይገባ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ያስገነዝባል። የወያኔ መንግስት በተደጋጋሚ የኦሮሞ ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን ይህንን ድርጊትም በጽኑ
ያወግዛል። እንዲህ ባለው እስነዋሪ ተግባርና ኢ-ሰብዓዊ እርምጃ ህዝቡን ለማንበርከክ ወያኔ እየተጠቀመበት ላለው ስልት
ሳይንበረከክ የኦሮሞ ህዝብ ትግሉን ኣፋፍሞ መቀጠል እንዳለበት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መልዕክቱን ያስተላልፋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወጣት ኒሞና ጥላሁን በከፈለው መስዋዕትነት ቤተሰቦቹ ላይ የደረሰውን ሃዘንና ቁጣ በሚገባ ይገነዘባል።
ይሁንና የሁሉም የኦሮሞ ልጆች የከፈሉት መስዋዕትነትና የፈሰሰው ደማቸው በከንቱ እንደማይቀርና ተገቢውን ካሳና ውሳኔ
የሚያገኝበት ዕለት እንዳለ፡ የወጣት ኒሞናም ከዚህ የተለየ ኣለመሆኑን ማስገንዘብ ይወዳል።
እስካሁን ድረስ የተከፈለውና እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነትም ነጻነታችንን እውን ለማድረግ የምናደርገውን ጉዞ ለማሳካት
የሚከፈል ክቡር የህይወት ዋጋ ኣካል ስለሆነ ጠላት በየቀኑ የሚወስደው ኣረመኔያዊ እርምጃ የኦሮሞ ህዝብን ከትግል ወደ ኋላ
ኣይመልሰውም።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከዚሁ ጋር ኣያይዞም በኣሁኑ ወቅት በመላው ኦሮሚያ ካለው ሁኔታ የተነሳ የወያኔ መንግስት ባዶ እጆቻቸውን የመብት ጥያቄ ባነሱ የኦሮሞ ዜጎች ላይ እያካሄደ ያለውን የግድያ ዘመቻ እንዲገታ ኣጥብቆ ይጠይቃል። ህዝቡ ያቀረበው የመብት
ጥያቄና ኣሁንም እያነሳ ያለው ጥያቄ ፍትሓዊና ህጋዊ ኣግባብ ያለው በመሆኑ ይህ ጥያቄ መልስ እስከሚያገኝ መስዋዕትነት መክፈሉን ይቀጥላል። ስለሆነም የመብት ጥያቄና ኣመጹን ኣፋፍመን በመቀጠል የኦሮሞ ልጆች ደም የፈሰሰበትንና የህይወት ዋጋ የተከፈለበትን ዓላማ ከግቡ ለማድረስ እጅ ለእጅ ተያይዘን ትግላችንን እስከመጨረሻ እንድንቀጥል ኦነግ ጥሪውን ያስተላልፋል። እንዲሁም
ለወጣት ኒሞና ጥላሁን ቤተሰቦች፣ ጓደኞችና ለመላው የኦሮሞ ህዝብ ጽናቱን እንዲሰጣቸው ይመኛል።
ድል ለኦሮሞ ህዝብ!
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ሰኔ 7, 2014ዓም
No comments:
Post a Comment