ለመሆኑ የእሬቻ በዓል እንዴት ተጀመረ? በምርቃት የሚከፍቱት እነማናቸው? የእሬቻ ጊዜ እንዴት ይወሰናል? የእሬቻ በዓል ሃይማኖታዊ ነው ወይስ በህላዊ? ለኦሮሞ ህዝብ ብሄራዊ አንድነት ያለው አንድምታ ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በዚህ አጭር ጽሑፍ ለመመለስ እሞክራለሁ።
የእሬቻ በዓል ታሪካዊ አመጣጥ
የእሬቻ በዓል እንዴት እንደ ተጀመረ የሚገልፅ ጥልቅ ጥናት የለም። አከባበሩም ከቦታ ቦታ ውሱን ልዩነቶች ይኖሩታል። የኦሮሞ ህዝብ ለረጅም አመታት ታሪካዊ እና ባህላዊ ክንዋኔዎቹን በህዝባዊ ትውስታ መልክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላለፍ ስለነበረ፤ ሰፊና ጥልቅ ጥናት ቢደረግ ታሪካዊ አመጣጡን በተሻለ ሊያስረዳ የሚችል በቂ መረጃ ሊገኝ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለም። ለጊዜው በቱለማ ኦሮሞ አፈ ታሪክ ላይ ተንተርሼ የተወስነ ፊንጭ የሚሰጡ ነገሮችን ለማሳየት እሞክራለው።
በመቀጠልም ጨፌ ደንጏራ በሚባለው ቦታ ወለደች። ጨፌ ቱማ የሚባለው ቦታ ደግሞ “የእንግዴ ልጁዋ ወጣ” ይላል ቱውፊቱ። ናቤም የተወለደው ኮርማ እስኪያደግ ድረስ ጠብቆ ይዞ ወደ መጣበት መደ ወላቡ ለመመለስ አስቦ ነበረ። ይሁን እንጂ፣ ኮርማው የረር ተራራ ላይ በመውጣት እምቢ ይለዋል። ከዚያ በሁዋላ ወደ መደ ወላቡ በመመለስ የተቀሩ ወገኖቹን ይዞ ይመለሳል።” ይላል አፈታሪኩ። በዚህ የተነሳ በቱለማ ኦሮሞ ምርቃት ዉስጥ “የረር ኮርማ” የሚለው ሃረግ ምንጊዜም አይቀርም። ናቤ የቱለማን ገዳ ባዲስ መልክ እንዳዋቀርና በአከባቢው የተለያዩ ቦታዎች ሲዘዋወር እንደነበረ ይነገራል። በአካባቢው በቆየበት ጊዜ እሱ የተዘዋወረባቸው ቦታዎች፣ የተሸገራቸው መልካዎች፣ ያረፈባቸው ጥላዎች እና የወጣባቸው ተራራዎች ከሞላ ጎደል በቱለማ ምርቃት ውስጥ ይንፀባረቃሉ። ስለዚህ የቱለማ ሰዎች እነዛን እሱ የተሻገራቸውን መልካዎች ሲሻገሩ፣ ጥላዎች ሲያልፉ ወይም ተራራዎችን ሲወጡ እሬቻ ያደረጋሉ።
የቱለማ ኦሮሞ የገዳ ጉባዔ በኦዳ ናቤ ሲያካሂዱም፣ ወደ ጨፌ የሚጓዙ የቱለማ ሃዩ (አንጋፋ) እና አባ ፋጂም የሚሄዱበት መንገድ ናቤ በአካባቢው በቆየበት ጊዜ ተጉዞባቸዋል ተብለው በሚታመኑ መንገዶች እንጂ ዝም ብለው ከቤት ተነስተው ባገኙት መንገድ አይጓዙም።
እነዚህ በአብዛኛው በቱለማ ኦሮሞ ምርቃት የሚንፀባረቁ ቦታዎች ከሞላ ጎደል የሚከተሉት ናቸው። ሆራ ሃረሰዲ፣ ኦዳ ናቤ፣ ጨፌ ዶንጏራ፣ ጨፌ ቱማ፣ ሆራ ፊንፊኔ፣ ዸካ ዐራራ ፣ ብርብረሣ ፎቃ፣ የረር ኮርማ፣ ቱሉ ጩቋላ እና መልካ አዋስን መጥቀስ ይቻላል። እሬቻ ማለት ጥሬ ትርጉሙ ለተከበረ ወይም ለተቀደሰ ነገር የሚከፈል ዋጋ ማለት ነው። ለምሳሌ የባህል መድሃኒት ለሚሰጡ ሰዎች ወይም ልጆችን ለማሰመረቅ (ammachiisaa) ቃሉ ጋር ሲወሰዱ፣ ገንዝብ ወይ ሳር ይሰጣል። ያ እሬቻ ይባላል። “እሬቻ” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ “ዋጋ” ማለት ነው። ሳር ደግሞ እርጥበቱ ህይወትን የሚያሳይ በኦሮሞ ባህል ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው ነገር ነው። በዚህ የተነሣ የክረምትን ጨለማ በሰላም አሻግሮ ወደ ፀደይ ወቅት ላደረሰ አምላክ በምስጋና መልክ የሚቀርብ ስጦታ ነው። እሬቻ የምስጋና ቀን ነው የሚባለው ለዚህ ነው።
የእሬቻ ምርቃት እና ዜማዎች፡
ኦሮሞች ለእሬቻ ወደ መልካ በሚጓዙበት ጊዜ የሚያዜሙት “ማሬ-ሆ”(Maree Hoo) ይባላል። መሬ-ሆ ወደ መልካ ስኬድ ሁል ጊዜ የሚዜም ዜማ ነው። መልካ ማለት አንድን ወንዝ በቀላሉ ልሻገሩ የሚችሉበት ቦታ ማለት ነው።ወንዝን ከጥልቀቱ ወይም በውስጡ በሚገኙ አደገኛ እንስሣት የተነሣ በሁሉ ቦታ መሻገር፣ ውሃ መቅዳት፣ መጠጣት፣ ወይም ከብቶችን ማጠጣት አይቻልም። እነዚህን ሁሉ ማድረግ የሚቻልበት አደገኛ ያልሆነ የወንዝ ወይም የሐይቅ ቦታ መልካ ይባላል። መልካዎች የየራሣቸው ስሞች አላቸው።
የእሬቻ በዓል ጊዜ አወሳስን
የበዓሉ ጊዜ የሚወሰነው የአሁኑ አይነት የቀን አቆጣጠር ከመምጣቱ በፊት አያንቱ(ayyaantuu) በሚባሉ በህላዊ ኮከብ ቆጣሪዎች (አስትሮኖመሮች) ነው። በኦሮሞ ባህል ከጥንት ዘመናት ጀምሮ የጨረቃንና የከዋክብትን እንቅስቃሴ በማቀናጀት የአመታትንና የወቅቶችን ለውጥ መወሰን እጅግ በጣም የቆዬ ባህል መሆኑ በጥናትም ጭምር የተረጋገጠ ሃቅ ነው። ታዋቂው የአንትርፖሎጅ እና የገዳ ሥርዓት ተመራማሪ ፕሮፈሰር አስመሮም ለገሰ የአሜሪካን የህዋ ምርምር ሳይንቲስቶችን በመጨመር እንዳረጋገጡት የኦሮሞ ህዝብ የብዙ ሺህ አመታት የኮከብ ቆጠራ(Dhahaa) ወይም አስትሮኖሚ ባህል ነበረው። በዚሁ መሰረት አያንቱዎች የኮኮቦችን እንቅስቃሴ በመከተል የእሬቻን ትክክለኛ ቀን ይወስናሎ።
የእሬቻ በዓል ባህል ነው ወይስ ሃይማኖት?
የእሬቻ በዓል ሃይማኖት ወይስ ባህል ነው የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ የሚነሣ ጥያቄ ነው። በርግጥ በሃይማኖት እና ባህል መካከል ያለው ድንበር በጣም ቀጭን ነው። በዓለም ላይ ያሉ ብዙ በዓሎች በአንድ ወቅት ሃይማኖታዊ መስረት ነበራቸው። የፈረንጆቹን አዲስ አመት ብንወሰድ ቅደመ ክርስትያን እና ድህረ ክርስትያን ሃይማኖታዊ ይዘት ነበረው። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት፣ ክርስትያኖች፣ሙስሎሞች፣ ይሁዳውያን፣ ሂንዱዎች፣ ቡድስቶች፣ኮንፍሸውያንና የጃፓኖቹ ሽንቶዎች እንደራሳቸው በዓል ወሰደው በባህላዊው መልክ የፈረንጆቹን አዲስ አመት በድምቀት ያከብራሉ።
በተመሣሣይ መልኩ የኦሮሞ ህዝብ የደረሰበትን ረጅም የባህል ወራራ ተቋቁሞ፤ ከተረፉለት ባህሎች፣ የእሬቻ በዓል ከፍተኛ ስፍራ የሚይዝ ነው። ስለዚህ ኦሮሞዎች ምንም ዓይነት ሃይማኖት ቢከተሉ የእሬቻ በዓል ሁሉንም ኦሮሞዎች የሚያስተሳስር ባህላዊ እሴታቸው ነው። በአሁኑ ጊዜ በየአመቱ ቢያንስ ከሁለት እሰከ ሶስት ሚሊዮን ኦሮሞዎች ወደ ቢሾፍቱ በመሄድ በኦሮሞ ብሔራዊ የእሬቻ ክብረ በዓል ላይ ይሣተፉሉ። ይህ ማለት ከአጠቃላዩ የኦሮሞ ህዝብ 10% የሚሆነው ህዝብ በአካል እና በቀጥታ ይገናኛል ማለት ነው። በየአመቱ ከአጠቃላዩ ህዝብ አስር ፐርሰንቱ መገናኘት ማለት ለኦሮሞ ህዝብ ብሔራዊ ትሥሥር እና እድገት ከፍተኛ አሰተዋጾ አለው። ከዚህም በተጨማሪ ይህን መጣጥፍ ስጀምር እንደገለፅኩት የእሬቻ በዓል በብዙ ህዝብ የሚከበር ብቸኛ አህጉር በቀል የሆነ በዓል ነው። ይህ ደግሞ ወደፊት የቱሪስት መስህብ በመሆን የኦሮሞ ህዝብን ለዓለም ህዝብ የበለጠ ለማስተዋወቅ ያግዛል። በዚህ ላይ በሀገር ውስጥ እና ውጭ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ሙሁራንና አክቲቭስቶች በዓሉ በዩኔስኮ አለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረት እንዲያደርጉ ለማስታወስ እፈልጋለው።
መልካም የ2014 የእሬቻ በዓል!!!
No comments:
Post a Comment