የኢሬቻን በዓል በማስመልከት አንድ ጽሑፍ እናበረክታለን ባልነው መሰረት ይህንን ኢትኖግራፊ ቀመስ ወግ ጀባ ልንላችሁ ነው፡፡ ታዲያ እኛ ባደግንበት አካባቢ በሚነገረው ትውፊት በዓሉ “ኢሬሳ” እየተባለ ስለሚጠራ በዚህ ጽሑፍ ውስጥም “ኢሬሳ” የሚለውን ስም መጠቀሙን መርጠናል፡፡ ወደ ነገራችን ከመግባታችን በፊት በዚህ ጽሑፍ የሚወሱት ጉዳዮች Carcar and the Ittu Oromo በተሰኘው የኢትኖግራፊ ጥናት ውስጥ በሰፊው የሚዳሰሱ በመሆናቸው ጥያቄ ያላችሁ ሰዎች የጥናቱን የመጨረሻ ውጤት እንድትጠባበቁ እጠይቃለሁ፡፡ ምክንያቱም በጽሑፉ ውስጥ ከቀረበው ትረካ በላይ ሄጄ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች እንዳልገባ ጥናቱን የማከናውንበት ደንብ ስለሚያግደኝ ነው፡፡
----
ጽሑፋችንን የተሳሳቱ ምልከታዎችን በማስተካከል እንጀምራለን፡፡
የዋቄፈንና እምነት ተከታይ የሆኑት ኦሮሞዎች በሙሉ የኢሬሳን በዓል ያከብሩታል፡፡ ይሁንና በዚህ ዘመን በዓሉ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረው የቱለማ ኦሮሞ ይዞታ በሆነው የቢሾፍቱ ወረዳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዲያ የበዓሉ ማክበሪያ በሆነው ስፍራ ቆሪጥን የመሳሰሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስምና ዝና ያላቸው ጠንቋዮች የከተሙ በመሆናቸው ብዙ ሰዎች ኢሬቻን ጠንቋዮቹ የዛር መንፈሳቸውን በህዝቡ ላይ የሚያሰፍኑበት ዓመታዊ የንግሥ በዓል አድርገው ይመለከቱታል፡፡ አልተገናኝቶም!!
ጠንቋዮቹ በቅርብ ዘመን የበቀሉ ሀገር አጥፊ አራሙቻዎች ናቸው፡፡ ከበዓሉ ጋር አንድም ግንኙነት የላቸውም፡፡ ኖሮአቸውም አያውቅም፡፡ የኢሬቻ በዓል ግን ከጥንቱ የኦሮሞ ህዝብ የዋቄፈና እምነት የፈለቀ እና ለብዙ ክፍለ ዘመናት ሲተገበር የኖረ ነው፡፡ ጠንቋዮቹ በዚያ አካባቢ የሰፈሩት ከጣሊያን ወረራ ወዲህ ባለው ጊዜ ነው፡፡ እነዚህ ጠንቋዮች እዚያ የሰፈሩበት ምክንያት አለ፡፡ የገላን፤ የቢሾፍቱ እና የዱከም ወረዳዎች በጥንታዊው የቱለማ ኦሮሞ ደንብ መሰረት የነገዱ ፖለቲካዊና መንፈሳዊ ማዕከላት ናቸው፡፡ እነዚህ መሬቶች በቱለማ ኦሮሞ ዘንድ “ቅዱስ” ተብለው ነው የሚታወቁት፡፡ “ቃሉ” የሚባለው የህዝቡ መንፈሳዊ መሪም የሚኖረው በዚህ አካባቢ ነው፡፡ የቱለማ ኦሮሞ ኢሬቻን የመሳሰሉ ታላላቅ በዓላት የሚያከብረውም በዚሁ ስፍራ ነው፡፡
በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የኦሮሞ ህዝብ በነዚህ መሬቶች የሚያካሄደውን በዓላትን የማክበርና “ዋቃ”ን የማምለክ ተግባራት እንዳያከናውን ታገደ (ዝርዝሩን ለማወቅ የጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሤን “ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ”፣ ወይንም የኤንሪኮ ቼሩሊን The Folk Literature of The Oromo ያንብቡ)፡፡ ይሁንና ልዩ ልዩ የኦሮሞ ጎሳዎች እየተደበቁም ቢሆን ወደ ስፍራው መሄዳቸውን አላቋረጡም፡፡ በጣሊያን ዘመን ደግሞ እንደ ጥንቱ ዘመን ሰብሰብ ብለው በዓሉን ማክበር ጀመሩ፡፡ ጣሊያን ሲወጣ እንደገና በጅምላ ወደስፍራው እየሄዱ በዓሉን ማክበሩ ቀረ፡፡ ነገር ግን ኦሮሞዎች ከጣሊያን በኋላም በተናጠልና በትንንሽ ቡድኖች እየሆኑ መንፈሳዊ በዓላቸውን በስፍራው ማክበራቸውን አላቋረጡም (እዚህ ላይ ጣሊያንን ማድነቃችን አይደለም፤ ታሪኩን መጻፋችን ነው እንጂ)፡፡
እንግዲህ በዚያ ዘመን ነው ጠንቋዮቹ በአካባቢው መስፈር የጀመሩት፡፡ እነዚህ ጠንቋዮች ይህንን ስፍራ ምርጫቸው ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት አለ፡፡ ጠንቋዮቹ ህዝቡ መሬቱን እንደ ቅዱስ ምድር የሚመለከት መሆኑን ያውቃሉ፡፡ “ቃሉ” የሚባለው የጥንቱ የኦሮሞ ሀገር በቀል እምነት መሪ በስፍራው እየኖረ የህዝቡን መንፈሳዊ ተግባራት ይመራ እንደነበረም ያውቃሉ፡፡ የኦሮሞ ቃሉ በህዝቡ ከፍተኛ ክብር እንደሚሰጠው እና ንግግሩ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዳለውም ይገነዘባሉ፡፡ “ቃሉ” አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ከ“ዋቃ” የተሰጠውን ገደብ ሳይጥስ “ራጋ” የማከናወን ስልጣን እንዳለውም ይረዳሉ፡፡
እንግዲህ ጠንቋዮቹ የዘረፋ ስትራቴጂያቸውን ሲወጥኑ በጥንታዊው የኦሮሞ የዋቄፈና እምነት ተከታዮች ዘንድ እንደ ቅዱስ የሚወሰደው ያ ማዕከላዊ ስፍራ ብዙ ገቢ ሊዛቅበት እንደሚችል ታያቸው፡፡ በመሆኑም በዚያ ቅዱስ ስፍራ ከትመው ከጥንቱ የኦሮሞ ቃሉ ስልጣንና ትምህርት የተሰጣቸው እየመሰሉ ህዝቡን ማጭበርበርና ማወናበድ ጀመሩ፡፡ ለረጅም ዘመን ማንም ሃይ ባይ ስላልነበራቸው የውንብድና ስራቸውን በሰፊው ሄደውበታል፡፡ አሁን ግን ሁሉም እየነቃባቸው ነው፡፡
ታዲያ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚኖሩት ጠንቋዮች ተመሳሳይ ስትራቴጂ የሚጠቀሙ መሆናቸውን ልብ በሉ፡፡ ለምሳሌ በወሎ፣ በሀረርጌ፣ በባሌና በጂማ የሚኖሩት ጠንቋዮች እነ ሼኽ ሑሴን ባሌ፣ እነ ሼኽ አባዲር፣ እነ አው ሰዒድ፣ እነ ሼኽ አኒይ ወዘተ… የመሳሰሉት ቀደምት ሙስሊም ዑለማ በመንፈስ እየመሯቸው መጪውን ነገር እንደሚተነብዩና ድብቁን ሁሉ እንደሚፈትሹ ይናገራሉ፡፡ በሰሜን ሸዋ፣ ጎንደር፣ ጎጃም ወዘተ… አካባቢዎች ያሉ ጠንቋዮች ደግሞ ቅዱስ ገብርኤልና ሚካኤል ራዕይ እያስተላለፉላቸው መጻኢውን ነገር ለመተንበይ እንዳበቋቸው ያወራሉ፡፡ ነገር ግን ሁላቸውም አጭበርባሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ጠንቋዮች ከክርስትናም ሆነ ከእስልምና ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ ሁሉ ከዋቄፈንና እምነትም ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡ ሶስቱም እምነቶች ጥንቆላን ያወግዛሉ፡፡ እናም የቢሾፍቱ ቆሪጦች እና ኢሬቻ በምንም መልኩ አይገናኙም፡፡ ስለዚህ ኢሬቻን ከጥንቆላም ሆነ ከባዕድ አምልኮ ጋር ማያያዝ ስህተት ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ መወሳት ያለበት ጉዳይ ለጠንቋዮች መጠሪያ ሆኖ የሚያገለግለውን “ቃልቻ” የተሰኘውን ስም ይመለከታል፡፡ ይህ ስም በአንድ ጎኑ “ቃሉ” የሚለውን የኦሮሞ መንፈሳዊ አባት ያመለክታል፡፡ በሌላኛው ጎኑ ይህ መንፈሳዊ አባት የተወለደበትን ጎሳም ያመለክታል፡፡
የቃሉ ሹመት እንደ አባገዳ በምርጫ የሚከናወን ሳይሆን ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ነው፡፡ ይህ መንፈሳዊ አባት አባል የሆነበት ጎሳም በዚሁ ስም “ቃሉ” እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ የጎሳው አባላት የሆኑ ሰዎች ሃላፊነት ህዝቡን በመንፈሳዊ ተግባራት ማገልገል ነው፡፡ የዚህ ጎሳ ተወላጆች በከፍተኛ ደረጃ ይከበራሉ፡፡ ቃላቸው በሁሉም ዘንድ ተሰሚ ነው፡፡ ይሁንና የፖለቲካ መሪ እና የጦር መሪ ለመሆን አይችሉም፡፡ የአባገዳ ምርጫ ሲከናወንም ለእጩነት አይቀርቡም፡፡ እንግዲህ “ቃሊቻ” የሚባሉት ከዚህ የተከበረ ጎሳ የተወለዱ ወንዶች ናቸው፡፡ ሴቶቹ ደግሞ “ቃሊቲ” በሚለው የማዕረግ ስም ይጠራሉ፡፡ የሁለቱም ትርጉም “የቃሉ ሰው” እንደማለት ነው፡፡ ጠንቋዮቹ “ቃሊቻ” ነን ማለት የጀመሩት ቃሉዎች በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ያላቸውን ክብር ስለሚያውቁ ነው፡፡ ነገር ግን “ቃሊቻ” እና ጠንቋይ የሰማይና የመሬትን ያህል የተራራቁ ናቸው፡፡
*******
እነሆ አሁን ወደ ኢሬሳ ገብተናል!!
በጥንቱ የኦሮሞ የዋቄፈንና እምነት መሰረት ብዙዎቹ በዓላት ወርሃዊ ናቸው፡፡ እነዚህ ወርሃዊ በዓላት የሚከበሩት በየአጥቢያው ባሉት መልካዎች፣ በኦዳ (ዋርካ) ዛፍ ስር እና “ገልመ ቃሉ” በሚባለው ቤተ እምነት ነው፡፡ ኢሬሳን የመሳሰሉት ታላላቅ በዓላት የሚከበሩት ግን በነገድ (ቆሞ) ደረጃ ሲሆን በዓላቱን የማክበሩ ስርዓቶች የሚፈጸሙትም በዞን ደረጃ ባሉ የበዓል ማክበሪያ ስፍራዎች ነው፡፡ እነዚህ የክብረ በዓል ስፍራዎች የሚገኙትም የእያንዳንዱ የኦሮሞ ነገድ የፖለቲካና የመንፈሳዊ ማዕከላት ባሉበት አቅራቢያ ነው፡፡ ምሳሌ ልስጣችሁ፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ሀረር ስትመጡ “አዴሌ” እና “ሀረማያ” የተሰኙትን ሐይቆች ታገኛላችሁ አይደል?… አዎን! የአዴሌን ሐይቅ አልፋችሁ ወደ ሀረማያ ከመድረሳችሁ በፊት ወደ ጋራሙለታ አውራጃ የሚገነጠለው የኮረኮንች መንገድ ይገጥማችኋል፡፡ መንገዳቸው ወደ ጋራ ሙለታ የሆነ ተጓዦች እዚያ ከመድረሳቸው በፊት የአውቶቡሱ ረዳት በዚያ ስፍራ እንዲያወርዳቸው ይነግሩታል፡፡ ታዲያ ስፍራውን ምን ብለው እንደሚጠሩት ታውቃላችሁ?….. Mudhii Irreessaa ነው የሚሉት፡፡ ቃል በቃል ሲተረጎም “የኢሬሳ ወገብ” እንደማለት ነው፡፡ አውዳዊ ፍቺው ግን “የኢሬሳ በዓል ማክበሪያ ስፍራ” እንደማለት ነው፡፡
በዚህ ስፍራ በአሁኑ ወቅት የኢሬሳ በዓል አይከበርም፡፡ በጥንት ዘመናት ግን የምስራቅ ሀረርጌው የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ የኢሬሳን በዓል የሚያከብረው በዚህ አካባቢ ነው፡፡ በዓሉ ይከበርበት የነበረውን ትክክለኛ ስፍራ ለማወቅ ካሻችሁ በዋናው የአስፋልት መንገድ ላይ ለጥቂት ሜትሮች እንደተጓዛችሁ ከመንገዱ በስተቀኝ በኩል ፈልጉት፡፡ በዚያ ስፍራ ላይ ከትንሽዬ ኮረብታ ስር የተጠጋ ሰፊ መስክ ራቅ ብሎ ብሎ ይታያል፡፡ ይህ ረግረጋማ ስፍራ በጥንቱ ዘመን አነስተኛ ሐይቅ እንደነበረበት ልብ በሉ፡፡ ሐይቁ ከጊዜ ብዛት ስለደረቀ ነው በረግረግ የተዋጠው መስክ እንዲህ አግጥጦ የሚታየው፡፡ እናም የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ የዋቄፈንና እምነት ተከታይ በነበረበት የጥንት ዘመናት የኢሬሳን በዓል የሚያከብርበት ቅዱስ ስፍራ በዚህ የደረቀ ሐይቅ ዳርቻ የነበረው መሬት ነው፡፡
Mudhii Irreessa የሚባለው ስፍራ ከደረቀው ሐይቅ አቅራቢያ መሆኑና ይኸው ስፍራ አሁን ካሉት የሐረማያ እና የአዴሌ ሐይቆች አቅራቢያ መገኘቱ የአጋጣሚ ነገር እንዳይመስላችሁ፡፡ በነገድ ደረጃ የኢሬሳ በዓል የሚከበርባቸው ማዕከላት በሙሉ በሐይቅ ዳርቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህም ምክንያት አለው፡፡ አንደኛው ምክንያት የጥንቱ የኦሮሞ የዋቄፈንና እምነት “ፍጥረት የተገኘው ከውሃ ነው” የሚል አስተምህሮ ያለው በመሆኑ “ዋቃ” ፍጥረተ ዓለሙን በጀመረበት የውሃ ዳርቻ በዓሉንና የአምልኮ ተግባሩን መፈጸም ተገቢ ነው ከሚል ርዕዮት የመነጨ ነው፡፡ ይሁንና ሁሉም የውሃ አካል ለዚህ ክብር አይመጥንም፡፡ ኦሮሞ ከሰው ልጅ ነፍስ ቀጥሎ ለከብቶቹ ነፍስ በእጅጉ ይጨነቃል፡፡ በመሆኑም ኢሬሳን የመሳሰሉ ታላላቅ በዓላት በዳርቻው የሚከበርበት የውሃ አካል ከሰዎች በተጨማሪ ለከብቶች ህይወት አስፈላጊ መሆኑም ይጠናል፡፡ ይህም ማለት ውሃው በኦሮሞ ስነ-ቃል “ሃያ” (ቦጂ) እየተባለ የሚጠራው ጨዋማ ንጥረ ነገር ያለው ሊሆን ይገባል ለማለት ነው፡፡ በዚህ ማዕድን በአንደኛ ደረጃ የሚታወቁት ደግሞ “ሆራ” የሚባሉት በከፍተኛ ስፍራዎች ላይ ያሉ ሐይቆች ናቸው፡፡
ታዲያ የእነዚህ “ሆራ” ሐይቆች ልዩ ባህሪ ነጠላ ሆነው አለመገኘታቸው ነው፡፡ በተለያዩ ክልሎች ያሉት ሆራዎች በቡድን ተሰባጥረው ነው የሚገኙት፡፡ በአንዳንድ ስፍራዎች እስከ ሶስት ያህል ሆራዎች አሉ፡፡ በአንዳንድ ስፍራዎች ደግሞ እስከ ስምንት የሚደርሱ ሆራዎች ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ የኦሮሞ ነገዶች እነዚህን በማዕድናት ክምችት የበለጸጉ ሐይቆች ወጥ በሆነ ሁኔታ “ሆረ” (Hora) እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡ የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ ግን “ሀረ” ነው የሚለው፡፡ “ሀረ ማያ” የሚለው የሐይቁ ስያሜም የሚያመለክተው ይህንኑ ነው፡፡ እንግዲህ ኢሬቻ የሚከበረው በእንዲህ ዓይነት ሐይቆች አቅራቢያ ነው፡፡
*******
ከላይ ስጀምር “የኢሬሳ በዓል ማክበሪያ ስፍራ ለነገዱ የፖለቲካና የሃይማኖት ማዕከል የቀረበ ነው” ብዬ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የ“ሀረ ማያ”ን ሐይቅ ያየ ሰው በአባባሌ መደናገሩ አይቀርም፡፡ ነገሩ ግን እውነት ነው፡፡ በዛሬው ዘመን “ሃረ ማያ” በትውፊት ውስጥ ያለው አስፈላጊነት እየተረሳ የመጣው የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ የኢኮኖሚ ስርዓቱን ከከብት እርባታ ወደ ግብርና ማዞር በጀመረበት ዘመን እስልምናንም እየተቀበለ በመምጣቱና የፖለቲካ ማዕከሉም በዚሁ ሂደት ውስጥ በመረሳቱ ነው፡፡ ነገሩን ጠለቅ ብሎ ያየ ሰው ግን የጥንቱን የአፍረን ቀሎ የፖለቲካ ማዕከል ከሀረማያ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ያገኘዋል፡፡ ይህም “ቡሉሎ” የሚባለው ስፍራ ነው (ስፍራው ለወተር ከተማ ይቀርባል)፡፡ በዚህ መሰረት የዛሬዎቹ የሀረማያ እና የቀርሳ ወረዳዎች የጥንቱ የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ የፖለቲካና የመንፈሳዊ ማዕከላት ነበሩ ማለት ነው፡፡
ከአፍረን ቀሎ ኦሮሞ ምድር ወደ ምዕራብ ተጉዘን “ጨርጨር” በሚባለው የኢቱ ኦሮሞ መሬት ውስጥ ስንገባ ደግሞ ነገሩ በግልጽ ይታየናል፡፡ የኢቱ ኦሮሞ የኢሬሳን በዓል የሚያከብርበት ስፍራ በአሁኑ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን የቁኒ ወረዳ፣ በደነባ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል፡፡ ስፍራው እስከ አሁን ድረስ Mudhii Irressa እየተባለ ይጠራል፡፡ ይህ ስፍራ ከዝነኛው “ኦዳ ቡልቱም” በሁለት ኪሎሜትር ያህል ብቻ ነው የሚርቀው፡፡ “ኦዳ ቡልቱም” የኢቱ ኦሮሞ ጥንታዊ የፖለቲካና የእምነት ማዕከል ሲሆን በኢቱ ኦሮሞ ትውፊት መሰረት ስድስት “ሆራዎች” አሉት፡፡ እነርሱም “ሆረ ባዱ”፣ “ሆረ ቃሉ”፣ “ሆራ ቁኒ”፣ “ሆረ ባቴ”፣ “ሆረ ጎሄ” እና “ሆረ ዲማ” ይባላሉ፡፡
እነዚህ ሃይቆች በበጋ ወቅት አነስ ብለው ቢታዩም ሙሉ በሙሉ የጠፉበት ሁኔታ አልተከሰተም፡፡ ከነርሱ መካከል ትልቁ “ሆራ ዲማ” ሲሆን በተለምዶ “ሀሮ ጨርጨር” እየተባለም ይጠራል፡፡ “ሆረ ዲማ” የምስራቅ ኢትዮጵያ ትልቁ ሐይቅ ነው (የአስፋልቱ መንገድ ወደዚያ ስለማይደርስ የመሃል ሀገር ሰዎች በአብዛኛው ሃረማያን ነው የሚያውቁት፤ ይሁንና “ሆረ ዲማ” በስፋቱ የሀረማያን ሶስት እጥፍ ይሆናል)፡፡ “ሆራ ባዱ” ደግሞ ለኦዳ ቡልቱም በጣም የቀረበው ሐይቅ ነው፡፡ የኢቱ ኦሮሞ የኢሬሳን በዓል የሚያከብረው ግን “ሆረ ቃሉ” ከተሰኘው ሐይቅ አጠገብ ነው፡፡ ይህም ሃይቅ ከሆረ ባዱ በስተምስራቅ ይገኛል፡፡
ስድስቱ ሐይቆች ካሉበት ስፍራ ጀምሮ እስከ ገለምሶ ከተማ ድረስ ያለው መሬት በኢቱ ኦሮሞ አጠራር “ፎዱ” ይባላል፡፡ “ማዕከል” ማለት ነው፡፡ ይህ ማዕከላዊ ወረዳ ለሶስት ጉዳዮች ብቻ የተከለለ ነው፡፡ አንደኛ “አባ ቦኩ” የሚባለው ርእሰ መስተዳድርና “ቃሉ” የተባለው መንፈሳዊ መሪ መኖሪያ ነው፡፡ ሁለተኛ የኦዳ ቡልቱም የገዳ ስርዓት ማዕከላዊ ተቋማት፣ የህዝቡ መንፈሳዊ ተቋማት እና የዞን አቀፍ በዓላት ማክበሪያ ስፍራዎች የሚገኙበት ክልል ነው፡፡ ሶስተኛ ለህዝብ ጠቀሜታ ብቻ የሚውሉት ስድስቱ ሆራዎች የሚገኙበት ክልል ነው፡፡ በመሆኑም የኢቱ ኦሮሞ ተወላጆች በሙሉ በዓመት ወይንም በሁለት ዓመት አንዴ ከብቶቻቸውን ወደነዚህ ሐይቆች እያመጡ ውሃ ያጠጧቸዋል፡፡ የኢቱ ሽማግሌዎች እንደሚናገሩት ከብቶች የሆራን ውሃ ካልጠጡ እንዳሻቸው ሳር አይመገቡም፡፡ ስለዚህ ከብቶቹን ወደ ሆራ መውሰዱ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይህ ስርዓት Nadha Baasuu ይባላል፡፡
የቱለማ ኦሮሞ የኢሬቻን በዓል የሚያከብርበትንም ስፍራ ካያችሁ ተመሳሳይ ነገር ታገኛላችሁ፡፡ በኦዳ ቡልቱም ዙሪያ ያሉት ስድስት ሐይቆች በቱለማ ምድርም አሉ፡፡ እነርሱም “ሆረ አርሰዲ”፣ “ሆረ ኪሎሌ”፣ “ሆረ ሀዶ”፤ “ሆረ ገንደብ”፣ “ሆራ ዋርጦ” እና “ሆረ ኤረር” ይባላሉ፡፡ የቱለማ ኦሮሞ ኢሬቻን የሚያከብረው “ሆረ አርሰዲ” በተሰኘው ሐይቅ ዳርቻ ነው፡፡
እነዚህ ስድስት ሐይቆች የቱለማ ኦሮሞ የፖለቲካ ማዕከል ከሆነው “ኦዳ ነቤ” በቅርብ ርቀት ላይ ነው የሚገኙት፡፡ ይህ ኦዳ ነቤ በዱከም ወረዳ ውስጥ ከሸገር በ37 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ የፖለቲካ ማዕከል ዙሪያም ህዝቡ ሃይማኖታዊ ጉዞ የሚያደርግባቸው Sadeettan Tulluu Waaqaa (ስምንቱ የአምላክ ተራራዎች) የሚባሉት የሸዋ ከፍተኛ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም “ቱሉ ጩቃላ”፣ “ቱሉ ኤረር”፣ “ቱሉ ፉሪ”፣ “ቱሉ ገላን”፣ “ቱሉ ዋቶ ዳለቻ”፣ “ቱሉ ፎየታ”፣ “ቱሉ ወጨጫ” እና “ቱሉ ኤግዱ” የሚባሉት ናቸው፡፡ የህዝቡ አባ ገዳዎች መቀመጫ የሆኑት የአዋሽ መልካ በሎ እና የገላን ደንጎራ መስኮች የሚገኙትም በዚሁ ወረዳ ነው፡፡ እንግዲህ የቱለማ ኦሮሞ የኢሬቻን በዓል የሚያከብርበት “ሆራ አርሰዲ” ያለው እነዚህ የፖለቲካና የሃይማኖት ማዕከላት ባሉበት መሬት ላይ ነው፡፡
እላይ ከጠቀስናቸው ሶስት ነገዶች በተጨማሪ ሌሎች የኦሮሞ ነገዶችም በዓሉን ያከብሩታል፡፡ ይሁን እንጂ ከኦሮሞ ነገዶች መካከል ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸው የአርሲ እና የመጫ ነገዶች በዓሉን በአንድ ስፍራ የሚያከብሩት አይመስለኝም (መረጃው ያላችሁ አካፍሉን)፡፡ታዲያ ከቱለማ በስተቀር ሁሉም ኦሮሞዎች በዓሉን “ኢሬሳ” እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡ ቱለማ ግን “ኢሬቻ” ነው የሚለው፡፡ ይህ ልዩነት ግን ሌላ ሚስጢር የለውም፡፡ በሌሎች ዘዬዎች በምንናገርበት ጊዜ በ“ሳ” ድምጽ የምናሳርገውን ቃል በቱለማ ዘዬ “ቻ” እያሉ መናገር የተለመደ በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ “ለሜሳ”፣ “ከሌሳ”፣ “በሬሳ”፣ “ሙርቴሳ” የመሳሰሉት ቃላት በቱለማ ዘዬ “ለሜቻ”፣ “በሬቻ”፣ “ሙርቴቻ”፣ “ከሌቻ” በሚል ድምጸት ነው የሚነገሩት፡፡
*******
ለመሆኑ የኢሬሳ በዓል የሚከበረው ለምንድነው?……
የኦሮሞ ሽማግሌዎች ይህንን ጥያቄ ሲመልሱን “የኢሬሳ በዓል የሚከበረው ለዋቃ ምስጋና ለማቅረብ ነው” ይላሉ፡፡ መነሻውንም ሲያስረዱ “ዋቃ ክረምቱን በሰላም ስላሳለፈልንና ከሰማይ ባዘነበው ውሃ መልካም ፍሬ ስለሰጠን ያለ ክፍያ በቸርነቱ ለሚንከባከበን አምላክ ምስጋና ማቅረብ የተገባ በመሆኑ ነው” ይሉናል፡፡ “ዋቃ” ፍጥረተ ዓለምን ያስገኘውና ሂደቱንም የሚያስተናብረው አንድ አምላክ ማለት ነው፡፡ ኦሮሞ ችግር ሲገጥመው አቤቱታውን የሚያቀርበው “ለዋቃ” ነው፡፡ በደስታ ጊዜም ተሰብስቦ “ዋቃ”ን ያመሰግናል፡፡ ኢሬሳ የዚህ ዓይነቱ የምስጋና ማቅረቢያ በዓል ነው፡፡
ኢሬሳ በክረምቱ የወንዞች ሙላት ምክንያት ተቆራርጠው የነበሩ ቤተ ዘመዶችና ልዩ ልዩ ጎሳዎች የሚገናኙበት በዓል ነው፡፡ በመሆኑም በበዓሉ የተገኙት ሁሉ ይቅር ይባባሉ፡፡ ገንዘባቸውን ለሌሎች ያበደሩ ሰዎችም በሌሎች ላይ ያላቸውን እዳ ይሰርዙላቸዋል፡፡ በዓሉ የሚከበርበት ቀን የዓመቱ መጀመሪያ ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ ዓመቱ የደስታና የብልጽግና ይሆን ዘንድ የመልካም ምኞት መግለጫዎች ይጎርፋሉ፡፡ የህዝቡ መንፈሳዊ መሪ የሆነው “ቃሉ” ለህዝቡና ለሀገሩ “ኤባ” (ምርቃት) ያደርጋል፡፡ ታዲያ ማንኛውም ሰው ወደ በዓሉ ስፍራ ሲሄድ አለባበሱን ማሳመር ይጠበቅበታል፡፡ በእጁም የወይራ ቀንበጥ፣ እርጥብ ሳር አሊያም የአደይ አበባን ይይዛል፡፡
በነገራችን ላይ በጥንቱ ዘመን ከዚሁ የኢሬሳ በዓል ትይዩ ሌላ በዓል ይከበር እንደነበርም ልብ በሉ፡፡ ይህኛው በዓል የሚከበረው የክረምቱ ዝናብ ሊጀምር በሚያስገመግምበት የሰኔ ወር መግቢያ ላይ ነው፡፡ የበዓሉ ማክበሪያ ስፍራዎች ደግሞ ተራሮችና ኮረብታዎች ናቸው፡፡ ይህ በዓል “መጪው ክረምት መልካም የዝናብና የአዝመራ ወቅት እንዲሆንልን ለዋቃ ጸሎት ማድረስ” በሚል መንፈስ ነው የሚከበረው፡፡ በዓሉ በምዕራብ ሀረርጌው የኢቱ ኦሮሞ ዘንድ “ደራራ” እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ የቱለማ ኦሮሞ ደግሞ “ኢሬቻ ቱሉ” (የተራራ ላይ ኢሬሳ) ይለዋል፡፡ በዓሉ በሌሎች ኦሮሞዎች የሚጠራበትን ስም ግን አላውቅም፡፡ በደራራ ጊዜ የሚፈለገው ትልቁ ነገር “ጸሎት” (Kadhaa) ማብዛት ነው፡፡ መዝፈንና መጨፈር አይፈቀድም፡፡ በኢሬሳ ጊዜ የሚፈለገው ግን “ምስጋና” (Galata) ማብዛት እና ደስታን ማብሰር ነው፡፡ በዚህኛው በዓል ዘፈንና ጭፈራ ይፈቀዳል፡፡
በሁለቱም በዓላት የዋቃ ስም ይለመናል፡፡ ለዋቃ መስዋእት ይቀርባል፡፡ ለመስዋእት የሚታረደው ጥቁር በሬ አሊያም ጥቁር ፍየል ነው፡፡ ይህም በጣም መሰረታዊ ነገር መሆኑን ልብ በሉ፡፡ በበሬው ቆዳ ላይ ቀይ ወይንም ነጭ ነጥብ በጭራሽ መኖር የለበትም፡፡ የበሬው ገላ ከጭረትና ከእከክ የነጻ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም በሬው በደንብ የበላና የደለበ ሊሆን ይገባል፡፡
አንዳንድ ሰዎች “የበሬው ቆዳ ጥቁር መሆን አለበት” የሚለውን አስተርዮ እንደ ባዕድ አምልኮ እንደሚያዩት ይታወቃል፡፡ ነገሩ ግን እንዲያ አይደለም፡፡ የበሬው ቆዳ ጥቁር መሆኑ የሚፈለገው በዋቄፈንና እምነት መሰረት “ሰዎችን የፈጠረውና በሰዎች የሚመለከው አምላክ ጥቁር ነው” ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ይህም “አምላክ በመልኩ ጥቁር ነው” ማለት ሳይሆን “ዋቃ በስራው እንጂ በአካሉም ሆነ በሚስጢሩ ለሰው ልጅ በጭራሽ አይታወቅም” ለማለት ነው፡፡ በመሆኑም የጥንቱ ኦሮሞዎች ዋቃን ሲለማመኑት እንዲህ ነበር የሚሉት፡፡
Yaa Waaqa (አንተ አምላክ ሆይ)Jabaa hundaa olii (ከሁሉም በላይ ጥንካሬ ያለህ)Tolchaa bobbaa fi galii (ወጥቶ መግባቱንም የሚያሳምረው)Guraacha garaa garbaa (ጥቁሩ እና ሆደ ሰፊው)Tokicha maqaa dhibbaa (በመቶ ስም የሚጠራው አንድዬ)ይህ የጥቁር ነገር ከተነሳ ዘንዳ በኦሮሞ ባህል መሰረት ጥቁር በሬ ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሆኑን ልብ በሉ፡፡ የቢሾፍቱና የገላን አካባቢ የኦሮሞ አርሶ አደር ሁለት ነጭ በሬዎች የሚገዙበትን ዋጋ ለአንዱ ጥቁር በሬ ብቻ ሊያወጣ ይችላል፡፡
*******
የኢሬሳ እና የደራራ በዓላት በጥንቱ ዘመን ከኦሮሞ ህዝብ በተጨማሪ የምስራቅ ኩሻዊያን (Eastern Cushitic People) በሚባሉት የቤጃ፣ የሳሆ እና የሶማሊ ህዝቦችም ይከበሩ እንደነበረ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ ህዝቦች ቀደም ብለው የእስልምናን እምነት በመቀበላቸው በዓላቱን ማክበሩን ትተውታል፡፡ ይሁንና እንደነርሱ የኩሻዊ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነው የአፋር ህዝብ እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ የኢሬሳን በዓል ያከብር እንደነበረ ልዩ ልዩ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡
ሁለቱ በዓላት የሚከበሩባቸውን ወቅቶች፣ የየበዓላቱን ዓላማ እና በዓላቱ የሚከሩባቸውን አውዶች ያጠኑ ምሁራን በዓላቱ በጥንት ግብጻዊያንም ይከበሩ እንደነበረ አረጋግጠዋል፡፡ ይሁንና ተመራማሪዎቹ “የበዓላቱ ምንጭ ጥንታዊት ግብጽ ነች ወይንስ ከግብጽ በታች የሚኖሩት የኩሽ (ኑቢያ) ህዝቦች?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተቸግረዋል፡፡ ጥያቄውን አስቸጋሪ ያደረገው የግብጻዊያኑ እምነት ብዝሃ አማልክት (Polytheism) የተቀላቀለበት መሆኑ ነው፡፡ ኩሻዊያኑ ግን “ዋቃ”፣ “ዋቅ፣ “ዋቆ” እያሉ በተቀራራቢ ቃላት ከሚጠሩት አንድ አምላክ በስተቀር ሌሎች አማልክት የሏቸውም፡፡ በዚህ ረገድ የሚደረገው ጥናት ሲጠናቀቅ ውጤቱ የሚታወቅ ይሆናል፡፡
ይህንን ጽሑፍ ከማጠናቀቄ በፊት አንድ ነገር ልናገር፡፡ ይህም “ኢሬቻ ባህል ነው” እየተባለ የሚነገረውን ይመለከታል፡፡ ሁሉም የምርምር ውጤቶች እንደሚያሳዩት ኢሬሳ በመሰረቱም ሆነ በይዘቱ ሃይማኖታዊ በዓል ነው፡፡ አከባበሩም የዋቄፈንና እምነትን ደንብ የተከተለ ነው፡፡ ስለዚህ ሚዲያዎች በዓሉን ሲያስተዋውቁ “ኢሬቻ ሁሉን አቀፍ ባህል ነው” ማለታቸውን መተው አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ከራሱ እምነት አንጻር በዓሉን ማክበሩ የማይሆንለት በርካታ ኦሮሞ ስላለ ነው፡፡ ወደ ክብረ በዓሉ ስፍራ መሄድ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው መሄድ ይችላል፡፡ የማይፈልገውም እንደዚያው!
አንዳንዶች እንደሚያደርጉት “ኢሬቻ የኦሮሞነት መለያ ነው” ማለቱ ግን አግባብ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እኔ ስለበዓሉ እዚህ የጻፍኩት ሙስሊም ነኝ፡፡ ጽሑፉን የጻፍኩትም በምርምር ሂደት ያገኘሁትን መረጃ በማቀናበር ነው እንጂ በዓሉን ስለማከብር አይደለም፡፡ ለሁሉም ግን ኢሬሳን ለሚያከብሩት የዋቄፈንና እምነት ተከታይ የኦሮሞ ወገኖቻችንን መልካም በዓል እንዲሆንላቸው እመኛለሁ!!
-----
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 22/2008
ሀረር -ምስራቅ ኢትዮጵያ
------
ምንጮች
1. Afendi Muteki: The Ittu Oromo of Carcar, Origin, Institutions and Dispersions (A Project on Progress)
2. Gada Melba: Oromia, An Introduction to History of the Oromo People: Khartum፡ 1988
3. Enrico Cerulli: A Falk Literature of the Oromo People: Harvard: 1922
4. Johann L. Krapf, :Travels, Researches and Missionary Labors during an Eighteen Year's Residence in Eastern Africa, London, 1860
5. Mohammed Hasasan: The City of Harar and the Islamization of the Oromo in Hararge, Atlanta, 1999
6. የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ “በገዳ ስርዓት የቱለማ ኦሮሞ ፖለቲካ”፤ ፊንፊኔ፣ 2000
7. ልዩ ልዩ ቃለ ምልልሶች
Written by Afendi and on Irressa or Irrecha.
No comments:
Post a Comment