የሕዝቦችን ሕገመንግሥታዊ መብቶች በመጣስ የሚከናወኑ የኢህአዴግ ሕገወጥ እርምጃዎች ሕዝባችንን ለከፍተኛ ችግር፣ ሀገራችንንም ለአሳሳቢ ሁኔታ እየዳረጉ ስለሆነ በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል!!

December 15, 2015 | ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ መግለጫ

የኢህአዴግ አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በተግባር ሊያውላቸው ያልተዘጋጀባቸውን ድንጋጌዎች ከሀገሪቱ ሕገመንግሥት ጀምሮ ሲያውጅ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ያወጃቸውን ድንጋጌዎች በማፍረስና በተግባር እንዳይውሉ በማድረግ የዜጎችንና የሕዝቡን መብቶች የሚጥሱ ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ይህ ሁኔታ ከአንድ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት በጉልበትና በማጭበርበር ቀምቶ መንግሥት ነኝ ከሚል አምባገነን ቡድን የሚጠበቅ ቢሆንም፣ መዘዙ የሀገራችንን ደህንነትና የሕዝቦቻችንን እኩልነትና አንድነት ለማይሹ ኃይሎች አፍራሽ እንቅስቃሴ ቀዳዳ እየሰጣቸው መሆኑ መድረክን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡

ከእነዚህ ሕገመንገሥታዊ ድንጋጌዎች ጥሰት መነሻነት ከተፈጠሩት ውስብስብ ችግሮች ውስጥ አንዱ የአዲስ አበባ ከተማንና የኦሮሚያን ክልላዊ መንግሥት ግንኙነት በሚመለከት፣ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 “የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል” የሚለውን በማንአለብኝነት ከመጣስ የመነጨ ችግር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢህአዴግ ሥርዓተ-አልበኝነት መገለጫ ሆኖ የቆየው በሕገመንግሥቱ የሰፈረው ዝርዝር የአፈጻጸም ሕግ ሳይወጣ ከ21 ዓመታት በላይ መቆየቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ እንዲሁም በአዲስ አበባ አከበቢ የሚሠሩ የልማት ሥራዎችንም በሚመለከት ሕዝቡን በአግባቡ ሳያወያዩ ጥቂት እበላ ባይ ካድሬዎችን በአስፈጻሚነት በማሰማራት የእርሻ መሬታቸውን እየነጠቁ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የማካለል እንቅስቃሴ ላይ መሠማራቱ በተከታታይ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችንና ውዝግቦችን ከማስነሳቱም በላይ ለብዙ ዜጎች ሕይወት በኢህአዴግ መንግሥት አርመኔአዊ እርምጃ መቀጠፍ ምክንያት ሆኖአል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአዲስ አበባ ከተማን ከሕግ አግባብ ውጪ ማማስፋት ጋር በተያያዘ በሕዝቡ ዘንድ ካደረው ስጋት በመነሳት የተቀሰቀሰውን ሰላማዊ ሕዝባዊ ተቃውሞን በኃይል ለማስቆም የኢህአዴግ መንግሥት በወሰደው እርምጃም በርካታ ተማሪዎችና ሌሎች ዜጎች መገደላቸውን መድረክ በእጀጉ ይኮንነዋል፡፡ የተገደሉት ዜጎችም 1ኛ፡- ተማሪ ካረሳ ጫላ ምዕራብ ወለጋ ጉልሶ ወረዳ፣ 2ኛ፡- ተማሪ ጉቱ አበራ ምዕራብ ወለጋ ጉልሶ ወረዳ፣ 3ኛ፡- ተማሪ ሚፍታህ ጁንዲ በምዕራብ ሐረርጌ በደኖ ወረዳ፣ 4ኛ፡- ተማሪ ገዘሃኝ ኦልሂቃ የሀራማያ ዩንቨርሲቲ ተማሪ፣ 5ኛ፡- ተማሪ ደጀኔ ሰርቤሳ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ቶሌ ወረዳ፣ 6ኛ፡- ተማሪ በቀለ ሰቦቃ አዳበርጋ ወረዳ ሙገር፣ 7ኛ፡- ተማሪ በቀለ ሰይፉ አዳበርጋ ወረዳ ሙገር፣ 8ኛ፡- ተማሪ ሙራዲ አብዱ የሀራማያ 2ኛ ደረጃ ተማሪ፣ 9ኛ፡- አቶ ጫላ ተሾሜ ምዕራብ ሸዋ ጨለያ ወረዳ ባቢቻ ከተማ፣ 10ኛ፡- ተማሪ አብደታ ባይሳ ምዕራብ ሸዋ ጫለያ ወረዳ ባብቻ ከተማ፣ 11ኛ፡- ተማሪ ዱሌ ምዕራብ ሸዋ ጨለያ ወረዳ ጌዶ ከተማ፣ 12ኛ፡- አቶ ታመነ ጸጋዬ ምዕራብ ሸዋ ጨለያ ወረዳ ጌዶ ከተማ፣ 13ኛ፡-ተማሪ ደረጀ ጋዲሰ ምዕራብ ሸዋ ጨለያ ወረዳ ጌዶ ከተማ፣ 14ኛ፡- ተማሪ ፈቃዱ ግርማ ምዕራብ ሸዋ ጨለያ ወረዳ ጌዶ ከተማ፣ 15ኛ፡-ተማሪ ሉጫ ገማቹ ምዕራብ ወለጋ ኢናንጎ ወረዳ፣ 16ኛ ተማሪ አያና ባንቲ ምዕራብ ወለጋ ኢናንጎ ወረዳ፣ 17ኛ፡- ተማሪ አላዛር ምዕራብ ወለጋ ኢናንጎ ወረዳ ነዋሪ 18ኛ አቶ ኤብሰ ቱጆ ሆሮ ጉዱሩ ፍንጫ፣ 19ኛ፡- አቶ ደበላ ጣፋ ጫንጮ ላይ ተገድሎ ተጥሎ የተገኘ፣ 20ኛ ወ/ሮ ዲሶ ሚሊኬሳ ሕልፈታ ወረዳ 21ኛ፡- አቶ አበበ ቡሎ ወሊሶ ከተማ፣ 22ኛ፡- አቶ ታዴ ሰፈራ አመያ ከተማ፣ 23ኛ፡- አቶ ሌንጮ ሁንዴራ ወሊሶ ከተማ፣ 24ኛ፡- አቶ ሰለሞን ሞገስ አማያ ከተማ፣25ኛ፡- አቶ ታዴ አንዲሳ ወንጪ ከተማ፣ 26ኛ፡- አቶ እናውጋው ኃይሉ ግንደበረት ወረዳ፣ 27ኛ፡- ተማሪ አብደታ ለታ ግንደበረት ወረዳ 28ኛ፡-አቶ ባይኢሳ ገደፋ አቡና ግንደበረት ወረዳ 29ኛ፡- ተማሪ አስቻለው ወርቁ ግንጪ ወረዳ፣ 30ኛ፡- ተማሪ ሰይፉ ቱራ ግንጪ ወረዳ፣ 31ኛ፡- ተማሪ አሸናፊ ግንጪ ወረዳ፣ 32ኛ፡- አቶ ገላና ባቃና ጪቱ ከተማ ነዋሪ የነበሩ ስለመሆናቸው የደረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ከመቶ ባለይ ዜጎች ቆስለዋል፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለእስራት ተዳርገዋል፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ ተቃውሞን ለማፈን በመንግሥት እየተወሰደ ያለው የኃይል እርምጃ እስከ አሁንም እንደቀጠለ በመሆኑ፣ በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት መድረክን በእጅጉ እያሳሰበው ይገኛል፡፡ እንደዚሁም በቅርቡ በጎንደር ከተማ በሚገኘው ወሕኒ ቤት በእስረኞች ላይ የተፈጸመው ግዲያ መድረክን አሳስቦታል፡፡
ከዚህም ሌላ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ “የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው” የሚለውንና በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ለግጦሽም ሆነ ለእርሻ የሚጠቀሙበት መሬት በነፃ የማግኘት፣ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብት አላቸው” ተብሎ የተደነገገውን በመተላለፍ፣ በከተሞችና በእንቨስትመንት ማስፋፋት ስም የአርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን መሬት እየቀሙ በማፈናቀል ለከፍተኛ የኑሮ ችግሮች እየዳረጉዋቸው ይገኛሉ፡፡ መድረክ ይህንን የኢህአዴግ መንግሥት የመሬት ቅሚያ እርምጃ ደጋግሞ ሲያጋልጥ የቆየ ሲሆን በእርምጃው ምክንያት በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለው የጉዳት መጠን ከጊዜ ወደጊዜ በአሁኑ ወቅት እየሰፋ ስለመገኘቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፤
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገዛዙ በርካታ የሀገሪቱን ከተሞች ለማስፋፋትና መሬቱንም በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ሥር በመሬት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ለማስተዳደር፣ የማስተር ፕላንና የሪፎርም ከተሞች ብሎ በመሰየም፣ በየከተሞቹ አከባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ይዞታዎች አርሶ አደሩን ሳያማክሩና ተገቢውን ካሳ ሳይከፍሉ ወደ ከተማ ለማካለል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ነዋሪውን ሕዝብ ለከፍተኛ ስጋትና ጭንቀት እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡ ስለሆነም የኢህአዴግ አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ በማንአለብኝነት አምባገነናዊ ስሜት እየተመራ ፌዴራላዊ ሥርዓቱንና የዜጎችን ሕገመንግሥታዊ መብቶች በመጣስ እየፈጸመ ከሚገኘው ሕገወጥ ተግባር እንዲቆጠብ እንጠይቃለን፡፡ በተለይም፡-
1ኛ፡- ከአዲስ አበባ ከተማና ከኦሮሚያ ክልል ግንኙነት ጋር በተያያዘ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች ሕገመንግሥቱን ተግባራዊ ባለማድረግ ምክንያት እየተከሰቱ ስለሆኑ የሕገመንግሥቱን አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ተግባራዊ የሚያድርግ ሕግ በአስቸኳይ ወጥቶ ተግባራዊ እንዲደረግና ለችግሩ ዘላቂ እልባት እንዲሰጥ፣ ለከተማዋ ልማት የሚወጡ እቅዶችም የሕገመንገሥቱን ድንጋጌ የሚያከብሩ ሆነው የአከባቢውን አርሶ አደሮች መብትና ጥቅም በሚገባ የሚያስጠብቅ እንዲሆኑ፣
2ኛ፡- በቅርቡም መንግሥት ሕገወጥ እርምጃ ለመውሰድ በተንቀሳቀሰበት ምክንያት በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎችን ባደረጉና በሌሎችም ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው የኃይል እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም፣
3ኛ፡- እስከአሁን የዜጎችን ሕይወት በሕገወጥነት ያጠፉና ሌሎች ጉዳቶችን ያደረሱ የመንግሥት አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡና ለሟቾቹ ቤተሰቦችም ተገቢው ካሳ እነዲከፈላቸው እንዲደረግ፣
4ኛ፡- በመላ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ሕገመንግሥቱ ያረጋገጠላቸው ከመሬታቸው የያለመፈናቀል መብታቸው ተከብሮ፣ በየአከባቢያቸው በልማት ሥራዎች ሰበብ ኑሮአቸው እየተናጋ ለችግር የሚዳረጉበት ሁኔታ በአስቸኳይ ተወግዶ፣ የሚከናወኑት የልማት ሥራዎችም ቢሆኑ የአከባቢውን ሕዝብ ይሁንታ ያገኘና መብታቸውን የጠበቀ እንዲሆን እንዲደረግ፤
5ኛ፡- በተለይም በአሁኑ ወቅት ከተሞችን በማስፋፋት ስም የአርሶ አደሩን መሬቶች ወደ ከተማ ለማካለልና በከፍተኛ ዋጋ በሊዝ ለመሸጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ፣ አርሶ አደሩን በስጋት ውስጥ እየከተተው ስለሚገኝ፣ ኑሮአቸውን ለማሻሻል የሚበቃ በቂ ካሳ ሳይከፈል ይዞታቸውን ለመንጠቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲቆም እንዲደረግ፣
6ኛ፡- በቅርቡ በጎንደር ከተማ በሚገኘው ወሕኒ ቤት የተገደሉ በርካታ ዜጎች ጉዳይ በአስቸኳይ ተጣርቶ የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ያጠፉና ጉዳት ያደረሱ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡና ለሟቾቹ ቤተሰቦችም ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
በመጨረሻም መድረክ በንጽሐን ዜጎቻችን ላይ በኢህአዴግ መንግሥት የተወሰደውንና እየተወሰደ ያለውን ኢሰብአዊ ግዲያ በጥበቅ እያወገዘ ለሟቾቹ ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል፡፡ መላው ሕዝባችንም በኢህአዴግ በጉልበትና በማጭበርበር በተካሄዱት ምርጫዎች የተቀማውን ሕገመንግሥታዊ መብቶቹን ለማስከበር ሰላማዊ ትግሉን እንዲያጠናክር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ጥሪ ያቀርባል፡፡
ድል ለሕዝባዊ ትግላችን !!
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ

ታህሳስ 5 ቀን 2008 ዓ ም

አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment