ጭብጥን በጭብጥ መመከት የማይፈልጉ አንድ አንድ ሰዎች፣ ብዕርን እንደ ጦር ይፈራሉ። በእርግጥ ሰውዬው እንዳለ ‹‹ብዕር የወጋዉን ቁስለኛ ዶክተር አያድነዉም!›› ከማንኛውም የጦር መሣሪያ በላይ እሳት የሚተፋ ብዕር የሚፈራ ለዝህ ይመስለኛል። በሀገራችን ኢትዮጵያ ‹‹ፍደል ቆጠርኩ›› የሚል ጥሩንባ ነፊ፣ ለተነሳው ሐሳብ/‹‹ክርክር›› ምክንያት ማቅረብ ስያቅተው፣ ተቃራኒውን/ሌላውን ወገን ለማሸማቀቅ፣ የስድብ ውርጅብኝ ማጦዝ ይጀምራል። እንድህ ዓይነቱ ሕፀፅ ‹‹አህያውን ፈርቶ ዳውላውን›› (Argumentum ad Hominem) ይባላል!! በሥነ-አመክንዮ፣ ሐሳብን በሐሳብ መመከት ማለት፣ ‹‹አንድ በቂ ምክንያት ከሃምሳ ሰበቦች የተሻለ ነዉ!›› የሚለውን አባባል በትክክል መረዳት ማለት ነው።
በሕዝብ ስም የራሳቸውን ኑሮ አደላድሎ መኖር የሚፈልጉ ሰዎች፣ ማንኛውንም ‹‹ነገር›› ከነባራዊ እውነት (Objective Truth) አንፃር ለመረዳትና ለማብራራት አይፈልጉም። ያላቸው ብቸኛ አማራጭ፣ በተለያዩ ድኅረ-ገጾች ላይ ቅዱሱን ነገር ፍጹም እርኩስ፣ እርከሱን ደግሞ ፍጹም ቅዱስ አድርጎ ማቅረብ ነው። ይህንን ስያደርጉ ትክክለኛ ስማቸውን ይቀይራሉ። በዝህ የተነሳ፣ አብዛኛው ሰው የሚደርስበትን ትችትና ስድብ በመፍራት፣ እውኔታውን ለመጻፍ አይደፍርም። በተለይ፣ አድናቆትንና ክብርን አብዝቶ የሚሹ ምሁራንና ጻሐፍዎች፣ ከሌላ ወገን የሚሰነዘርባቸውን ሂስ/ማስፈራሪያ/ስድብ መቋቋም ይሳናቸዋል።
አንድ ጸሐፍ/ተመራማር አንዱን ወገን ላመስደሰት፣ ሌላውን ደግሞ ለማስከፋት እስከጻፈ ድረስ፣ መቼም ቢሆን ቡከን መሆኑ የማይቀር ነገር ነው። የምርምር ዓለም እስከገባኝ ድረስ፣ የአንድ ጸሐፍ/ተመራማር ዋና ተልዕኮ መሆን ያለበት አንድን ወገን በጅምላ ማዋረድ (ማስከፋት)፣ ሌላውን ወገን ደግሞ ማወደስ (ማስደሰት) ሳይሆን፣ በሰከነ መንፈስ እውነቱን ጽፎ ማኅበረሰቡን/ግለሰቡን ማስተማር፣ መገጸጽና ማስረዳት ብቻ ነው። ይሁን እንጂ፣ ሌላውን ወገን ላለማስቀየም በሚል ሰበብ፣ የማያምኑበትን ነገር እንደ ወረደ ተቀብለው ጽፈው የሚያስተምሩ ሰዎች አሉ። ይህ ደግሞ ቡከንነትና በጣም አሳፋር ድርጊት ነው። ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ስብሃት ገብረ- እግዚብሄር ለተስፋዬ ገ/አብ የለገሰውን ምክር መቼም ቢሆን መርሳት የለብንም፤ “ሰዎች ሲያደንቁህ አትኩራራ! ሲያጥለሉህ ደግሞ አትደንግጥ። የምረግሙህም የሚያደንቁህም በብዛት ይፈጠራሉ። መልስ እንዳትሰጥ። ይህን እርሳዉና ሌላ መፅሐፍ ጀምር።”
‹‹የሰው ልጅ ህሊና ትንሹ እግዚአብሔር ነው!›› ከተባለ፣ አንድ ግለሰብ ትክክለኛውን ነገር ጽፎ ማስተማር እንጅ፣ የለሎችን ዛቻ/ስድብ ፈርቶ እውነቱን መደበቅ የለበትም። በዓሉ ግርማ እንድህ ይላል፤ ‹‹ድፍረት የሌላት ብዕር ወረቀት ባታበላሽ ይመረጣል፣ ከአድርባይ ብዕር ባዶ ወረቀት ብዙ ይናገራል።›› እንድህ ዓይነቱ ድፍረት ግን ንብረትና ልጆች ላፈሩት ግለሰቦችም ሆነ ‹‹ከአስር ድግሪ አንድ ግሮሰሪ›› ቢሎ ለሚፈላሰፉ አድርባዮች ላይዋጥላቸው ይችላል። ይሁን እንጅ፣ ገንዘብና ህሊና የተሰማሙበት ጊዜ አልነበረም፤ አይኖርምም። ስለዝህ፣ የሰው ልጅ ለእውነት የመኖርና የመሞት ግዴታ አለበት።
ፍልስፍና በተፈጥሮው የአዞ-ቆዳ አለው! ‹‹ዳንሰኛውን ከዳንሱ ነጥሎ ማዬት የማይችሉ ሰዎች›› የሚሰነዝሩትን ማንኛውም ዓይነት አፍራሽ ትችት (ስድብ፣ ማስፈራሪያ፣ ዛቻ…ወዘተ) የማስተናገድ አቅም አለው። በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ፣ ስፍር-ቁጥር የሌላቸው ጥያቄዎች ይከሰታሉ። ለእነኝህ ጥያቄዎች እንዳስፈላግነቱ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔዎችን ማፈላለግ፣ የፍልስፍና ተፈጥሯዊ (ሳይንሳዊ አላልኩም!) ግዴታ ነው። ይህንን ተልዕኮ በማሳካት ሂዴት ውስጥ፣ ከሌላ ወገን ለሚሰነዘርበት ማንኛውም ዓይነት አፍራሽ ትችቶች እጅ መስጠት የፍልስፍና ተፈጥሮአዊ ባህርይ አይደለም። በሰው ልጅ ታሪክ ውሰጥ፣ ፍልስፍና ፈላስፎችን እየቀበረ፣ ራሱ ግን ሕያው ሆኖ የሚኖርበት ዋና ምክንያት ይሄው ነው።ለምሳሌ፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የሰውሻዊያንን ፈተና ማለፍ የሚቻለው፣ በእውቀት ደረጃ ሳይሆን፣ በጥበብ (በፍልስፍና) ብቻ ስንመራ መሆኑን ለአንድ አፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም። ለመሆኑ ሰውሻዊያን ማን ናቸው?
ሰውሻዊያን ሰው ያላሰበውን የሚያሳስቡ ሰዎች ናቸው!! ሰውሻውያን የተባሉበት ዋና ምክንያት ደግሞ፣ ድርጊታቸውና አካሄዳቸው ሉሉ ከሚትባል የአፄ ኃይሌ ሥላሴ ውሻ ጋር በጣም ስለምመሳሰል ነው። ዶ/ር መረራ ጉዲና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅ ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች በተሰኘ መጻፉ ውስጥ ሰለዝች ጉደኛ ውሻ እንድ ሲል አስፍሮ ነበር፡-
‹‹በአፄ ኃይለ ሥላሴ ላይ ተንኮል የሚያስብባቸዉን ሰው ፊቱን አይታ የምትናገር ውሻ አንደነበራቸው፣የውሻዋ ፊት በጣም ከተቆጣ እጅ ሊነሳ የሄደው ባለስልጣን እንዲገደል ወይም እንዲታሰር፣ መጠነኛ ቁጣ ከሆነ ደግሞ፣ ስልጣኑ እንደምቀነስበት፣ አንድ ቀን በጣም ቀልደኛ ነው የሚባለዉ የአፄ ኃይለ ሥላሴ በለስልጣን፣ አቶ ይልማ ዴሬሳ የሚባለው (ይህ ሰው አነጄነራል መንግስቱ ኖዋይ የአፄ ኃይለ ሥላሴን በለሥልጣን ሰብስቦ የጨረሱ ግዜ፣ አቴጌ ታማለች ብለው ሲጠሩት እኔ ኢኮኖምስት ነኝ እንጅ ሀኪም አይደለሁም ብሎ ዲኖዋል ይባላል) አፄውን እጅ ሊነሱ ሲሄዱ፤ ውሻው ያዙኝ ልቀቁኝ ትላለች አሉ። የውሻዋን ጨወታ በትክክል የሚያውቁ አቶ ይልማም ‹ተይ አንቺ ውሻ ሰዉ ያላሰበውን፣ አተሳስቢ› አሉዋት ይባላል።››
በሀገራችን ኢትዮጵያ፣ አንድ ተመራማሪ/ጸሐፍ ትምክህተኝነትንና ጠባቢነትን አስወግዶ፣ በንፁህ ህሊና ከሱ የሚጠበቀውን ተልዕኮ በሚወጣበት ጊዜ፣ የሉሉን መንቃራ አመል የተላበሱ ሰዎች ሆን ብሎ ችግር ይፈጥራሉ። ሰውሻዊያንና ሉሉ የአንድ ሣንትም ሁለት ገጽታ ናቸው ያልኩበት ምክንያት ለዝህ ነው። ‹‹ተው ወንድም-አለም ሰው ያላሰበዉን፣ አታሳስብ!›› ማለት ግን ጠቢብነት ነው። ፈጣሪ ከሰውሻዊያን ፍልስፍናዊ ወጥመድ ይሰውረን እያለኩኝ፣ በማረፊያ በቀለ ግጥም የዛሬ መጣጥፌን ላሳርግ!
እንደ ተንጣለለ―አንደ ውብ ከተማ
ባንድ ጎንህ ብርሃን―በሌላው ጨለማ
ግማሽን ገልጠህ―ግማሽህን ግጠም
ልክ እንደ ጨረቃ―ተደበቅ ግድየለም
ይበቃኛል በርግጥ―ግማሽህን ማየት
ግማሽ በመሆኑ―ሰው የመሆን እዉነት
ባንድ ጎንህ ብርሃን―በሌላው ጨለማ
ግማሽን ገልጠህ―ግማሽህን ግጠም
ልክ እንደ ጨረቃ―ተደበቅ ግድየለም
ይበቃኛል በርግጥ―ግማሽህን ማየት
ግማሽ በመሆኑ―ሰው የመሆን እዉነት
ቸር እንሰንብት!
No comments:
Post a Comment