ለተፈጠረው የፀጥታ ችግር ዋነኛ መንስዔ ቴፒ ከተማ የምትገኝበት የኪ ወረዳ የእኛ ነው የሚል አቋም በያዙ የሸኮ ብሔረሰብ ተወላጆችና በሸካ ብሔረሰብ ተወላጅ አመራሮች መካከል፣ ከጊዜ በኋላ እየተካረረ የመጣ አለመግባባት በመኖሩ ነው ተብሏል፡፡የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የግብርና ኢኮኖሚ እምብርት ከሆኑ ከተሞች አንዷ በሆነችው ቴፒ ከተማ፣ በፀጥታ መደፍረስ ሳቢያ ውጥረት ነግሷል፡፡ ቴፒ ከተማና ዙሪያዋ በፌዴራል ፖሊስ ጭምር ጥበቃ ቢደረግላቸውም፣ የሽፍታ ኃይል በመኖሩ ከሥጋት መላቀቅ እንዳልቻሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
አለመግባባቱን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ኃይል የመረጡ የአካባቢው ተወላጆች በመሸፈታቸውና ጊዜ እየጠበቁ ጥቃት በመፈጸማቸው፣ ከፍተኛ ውጥረት መንገሡን መታዘብ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሚዛን ተፈሪ ወደ ቴፒ፣ ከሽሽንዳ ከተማ ወደ ቴፒ፣ ከማሻ ከተማ ወደ ቴፒ የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ በደቡብ ክልል ልዩ ኃይል፣ በፌደራል ፖሊስና በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር እየተደረገባቸው ይገኛሉ፡፡ ቁጥጥሩ ማንኛውም መንገደኛ ላይ ጥብቅ ፍተሻን የሚያካትት ሲሆን፣ የፀጥታ ኃይሎች አካባቢውን በንቃት በመቆጣጠር ላይ መሆናቸውም ተስተውሏል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ቴፒ ከንግድ ከተማነት ይልቅ የስጋት ቀጣና መስላለች ይላሉ፡፡ ምክንያቱም በመንግሥት የታወጀ የሰዓት ዕላፊ ገደብ ባይኖርም፣ ሁሉም ነዋሪዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በከተማ ውስጥ እንዲዘዋወሩ አይፈቀድም፡፡ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ግድያ ባይፈጸምም ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያት በየምሽቱ የሰው ሕይወት መጥፋቱ የተለመደ እንደነበር ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳ አጎራባች በሆነው የጋምቤላ ክልል በሚገኘው በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስና በክልሉ ልዩ ኃይል የታገዘ ጥበቃ ቢደረግም እጅ ያልሰጠ የሽፍታ ኃይል በመኖሩ ነዋሪዎች ሥጋት ውስጥ እንዳሉ ይናገራሉ፡፡
የሚፈጸመው ግድያ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ፣ የፌዴራል መንግሥት ሰላም ለማስጠበቅ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጓዳኝ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊሰጥበት ይገባል በማለት ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የከተማው ነዋሪ ለሪፖርተር ሲያብራሩና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉበት ምክንያት ሲናገሩም፣ “የፀጥታ ችግሩን ለመቅረፍ በተጠሩ መድረኮች አስተያየት የሰጡ ሰዎች ላይ ዕርምጃ የተወሰደ በመሆኑ፣ በአደባባይ ሐሳብን መግለጽ በራስ ላይ እንደመፍረድ ይቆጠራል፤” በማለት የችግሩን ጥልቀት አስረድተዋል፡፡
የሸኮ ተዋላጆች የሚያነሱት ጥያቄ መሠረቱ በቤንች ማጂ ዞን የሚገኘው ሸኮ ወረዳ፣ በሸካ ዞን የሚገኘው የኪ ወረዳና በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን የሚገኘው ሜጢ ወረዳ፣ አንድ ላይ ተዋህዶ ዞን እንዲሆንና ዞኑንም የማስተዳደር ሥልጣንም እንዲሰጣቸው ነው፡፡ የማጃንግ ብሔርን ማጠቃለል የፈለጉበትን ምክንያት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሸካ ዞን ተወላጅ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የማጃንግና የሸኮ ብሔረሰብ አባላት ለዘመናት አብረው የኖሩና ባህላቸውም ተመሳሳይ በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ፖለቲካዊ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ከማንሳት ይልቅ ኃይል የሚጠቀሙ መኖራቸው፣ ክልሉንም ሆነ የፌዴራል መንግሥትን እንዳስቆጣ እኝሁ የሸካ ተወላጅ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ይህ ፖለቲካዊ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ቢቀርብ እንኳ ለጋምቤላ ክልል፣ ለቤንች ማጂ ዞንና ለሸካ ዞን ባለሥልጣናት የሚዋጥ አይደለም የሚሉም አሉ፡፡ ምክንያቱም ለጋምቤላ ክልል የማጃንግ ዞን ዋነኛ የሀብት ምንጭ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ ክልሉም ከፍተኛውን ገቢ የሚያገኘው ከዚሁ አካባቢ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩልም ቴፒ ከተማ የሚገኝበት የኪ ወረዳ ለሸካ ዞን ዋነኛ እስትንፋስ መሆኑን የሚገልጹ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ ወረዳው ከፍተኛ የሆነ ሀብት ባለቤት እንደሆነና ከዚህ በተጨማሪም ሸኮ ወረዳም ለቤንች ማጂ ዞን ዋነኛ የገቢ ምንጭ በመሆኑ ጥያቄው ከዚህም ወገን እየተነሳ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
እነዚህን በሀብት የበለፀጉ ወረዳዎች ዞኖቹ በቀላሉ አስረክበው ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ይገኛል የሚል እምነት የለም የሚሉ አስተያየቶች ቢኖሩም፣ ዋናው ጉዳይ ግን ኃይል ከመጠቀም ይልቅ ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣት ይገባል በማለት ሐሳብ የሚያቀርቡ የሁለቱም ብሔረሰብ ተወላጆች ለውይይት እየጎተጎቱ ነው፡፡ የቴፒ ከተማ ከንቲባ አቶ በሱፈቃዱ መኮንን በአካባቢው በየጊዜው እየተፈጠረ ባለው አለመግባባት የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር መኖሩን አምነዋል፡፡
“በአሁኑ ወቅት የፀጥታ መዋቅሩ በኅብረተሰቡና በፀጥታ ኃይሎች ተሳትፎ እየተሻሻለ መጥቷል፤” በማለት የተናገሩት ከንቲባው፣ ነዋሪዎች ያነሷቸው የፀጥታ ችግሮች ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታዩ የተጋነኑ ናቸው ብለዋል፡፡ ያም ሆኖ በአካባቢው ለሚገኙ ሕዝቦችና ለግብይት ወደ ቴፒ ከተማ ለሚመጡ ነጋዴዎች የፀጥታ ችግሩ ሥጋት መፍጠሩን አክለዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነጋዴዎች በፀጥታው ችግር ምክንያት ምርት ወደ ገበያ እየወጣ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ ገዥዎችም ከተማውን እየጎበኙ አይደሉም ብለዋል፡፡ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ ለከተማው የንግድ እንቅስቃሴ መንግሥት አፋጣኝ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ነጋዴዎቹ ጠይቀዋል፡፡
በቴፒ ከተማ የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር ብዛት ከ35 ሺሕ በላይ ሲገመት፣ ከአምስት ሺሕ ያላነሱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም በቴፒ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
No comments:
Post a Comment