የኦሮሞ ፖለቲካ ጉዳይ (ከትናንት እስከ ዛሬ)

ቡልቻ ደመቅሣ
ቡልቻ ደመቅሣ /October 28/2012/: የኦሮሞ የፖለቲካ ጉዳይ በየዘመኑ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ ሲመሏ ለዘመናት ቆይቷል፡፡ ይህ የሆነው ከአፄ ሚኒሊክ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያ በፊት፣ የኢትዮጵያ ነገስታት ኦሮሞን ለማሸነፍ ስላልቻሉ በየጊዜው እየተጋጩ እንደምንም አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ፋዘር አልሜዳ የሚባለው የፖርቱጋል ቄስ በዚህ ጉዳይ በሰፊው ጽፏል፡፡ ነገር ግን አብሮነታቸው እንደ ገዥና ተገዥ አልነበረም፡፡ ከአጼ ልብነድንግል ጀምረው እስከ ንጉስ ሳህለ ስላሤ የነበሩት አፄዎች ሁሉ ኦሮሞን ለማሸነፍ እና ለመግዛት ያላደሩጉት ጥረት አልነበረም፡፡

ኦሮሞንና ሀገሩን አሸንፈው ለማስገበር የቻሉት አፄ ሚኒሊክ ብቻ ነበሩ፡፡ እሳቸውም ኦሮሞን ለማሸነፍ የቻሉት ከኦሮሞዎች ቀደም ብለው ከፈረንጆች የጦር መሳሪያ ስላገኙ ነበር፡፡ መሣሪያ ያገኙበትም ምክንያት ከእሳቸው ቀድሞ የነበሩት አንዳንድ አፄዎች ለአውሮፓ መንግስታት “ኢትዮጵያ ብቻዋን ክርስቲያን ሆና በአፍሪካ ውስጥ የምትኖር ሀገር ነች” ብለው የአውሮፓውያን መንግሥታትን ስለለመኑና ስላስረዱ የጦር መሣሪያ ማግኘት ቻሉ፡፡ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አፄ ሚኒሊክ ሸዋን በሙሉ ለመቆጣጠር ሲነቃነቁ ደብረብርሃን አጠገብ በምትገኘው አብደላ በምትባል መንደር ውስጥ ከጎበና ዳጬ ጋር ተገናኙ፡፡ጎበና ዳጬም በዚያን ጊዜ በኦሮሞ ገዳ ሥርዓት የሉባና የነበዙ አባ ደክር ወዳጅ የነበሩ፡፡ ከአፄ ሚኒሊክ ለጎበና ዳጬ አንድ ነገር ተናገሩ፡፡ “ወደታች ወደደቡብ እንሂድ፡፡ ወደአቢቹ፣ ገላን፣ ጉለሌ፣ አርሲ አብረን እንዝመት፡፡ አንተ የጋላ ንጉስ ትሆናለህ፣ እኔ የኢትዮጵያ ንጉስ እሆናለሁ ተከተለኝ” አሏቸው፡፡ እንደተባባሉትም ወደታች ወደደቡብ መጥተው የኦሮሞን ጎሣዎች መውጋት ጀምሩ፡፡ ጎበናም ራስ ተባሉ፡፡ ነገር ግን አፄ ሚኒሊክ ለጎበና የገቡትን ቃል ሳይጠብቁ ቀሩ፡፡ ጎበናም ብዙ ጊዜ ከተዋጉ በኋላ እየተዳከሙ ሄዱ፡፡ ነገር ግን የሸዋን፣የወለጋን (በሰላም የገቡ) እና የከፋን (ከፋም በሰላም ገባ) ኦሮሞዎች ካሸነፉ በኋላ አፄ ሚኒሊክ እራሳቸው ጦርነቱን መምራት ጀመሩ፡፡ ራስ ጎበና በቀየሱት መንገድ ሄደው ሌሎች ያልተያዙትን ሀገሮች ያዙ፡፡ ለምሳሌ ሀረርን፣ ውጋዴንን፣ ሱማሌን፣ ቦረናን ያቀኑት ከዚያ በኋላ ነው፡፡ (እኔ አቀኑ እላለሁ አንዳንድ ሰዎች ግን “ኮሎናይዝ” አደረጉ ነው የሚሉት፡፡ እውነቱን ለታሪክ ተንታኞች እንተዋለን፡፡) ይህ ታሪክ አፈታሪክ ነው፡፡ የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት አፈታሪክ የተፃፈ ታሪክ ያህል ዋጋ አለው፡፡ አሁን ልክ አይደለም ብሎ መከራከር ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞዎች ሁሉ ይህን ያምናሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ የታሪኩን እርግጠኛነት የሚያረጋግጠው የራስ ጎበና ሕመም ነው፡፡ (በብስጭት እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚናገሩ የእሳቸው ተወላጆች አሉ፡፡) እኔ እንደብዙ ወገኖቼ ጎበናን አላብጠለጥልም ሰው ስራ መስራት አለበት፡፡ ቤተሰቡን የሚደግፈው የሰራ እንደሆነ ነው፡፡አለስራ መኖር አይቻልም፡፡ ስለዚህ ራስ ጎበና ስራ አግኝተው ቢሰሩም የፈለጉት ሳይሆን ቀርቶ ታመው ሞቱ፡፡ ይሄ ማንኛቸውም መሪ የሚያረገው ነገር ነው፡፡ አንዳንዱ አላደርግም ብሎ ይሞታል፡፡ ግን ብዙ ሰው ሞትን አይመርጥም፡፡ አፄ ሚኒሊክ ጎበናንም ባያገኙ ማሸነፋቸው አይቀሬ ነበር፡፡ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ ከአውሮፓውያን ብዙ የጦር መሣሪያ አግኝተዋል፡፡ ራስ ጎበና ከሚኒሊክ ጋር ያደረጉት ስምምነት ለጊዜው ለኦሮሞ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚሄድ መስሎ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ አፄ ሚኒሊክ ኦሮሞን የገዙበት የባሪያ አገዛዝ ሁለት እርምጃ ወደኋላ እንዲሄዱ አደረጋቸው፡፡ኦሮሞ ደርግ ላይ ምንም ተስፋ ስላልነበረው የጀነራል ተፈሪ ባንቴ ፕሬዝዳንት መሆን ምንም አልመሰለውም፡፡ ዶክተር ነጋሶ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ለኦሮሞ የተሻለ መስሎ አልታየውም፡፡ ዶክተር ነጋሶም እራሳቸው በስርዓቱ ባለማመን ረግጠው ወጡ፡፡

ከዚያ በኋላ የአፄ ሚኒሊክን የጦር ኃይል መመከት ያልቻለው ኦሮሞ፣ ገባርነትን ለመቀበል ተገደደ፡፡ ሆኖም ግን አፄ ሚኒሊክ ከዚያ በፊት ኦሮሞ ይዞት የነበረውን መሬት ማስለቀቅ ስላልቻሉ ኦሮሞ በአፄ ልብነድንግል ጊዜ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይዞት የነበረውን መሬት እንደያዘ ቀረ፡፡ እዚህ ላይ እናስታውስ፡፡ የወሎ አሮሞና ትግራይ ውስጥ ያሉት ራያና አዘቦ ኦሮምኛ ቋንቋቸውን እየረሱ አማርኛ ወይም ትግሪኛ መናገር ጀምረዋል፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ ያለው ኦሮሞ ዞን ከተፈጠረለት ለምን የራያና አዘቦ ዞን በትግራይ ውስጥ አልተፈጠረም፡፡ ይኼ የሚያሳየው ሕገ መንግስቱ በተፃፈበት ጊዜ (በ1986 ዓ.ም) ህወሓት የነበረውን ፍጹም የበላይነት ነው፡፡

ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቢያንስ 35 በመቶ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ሕዝቡም ወደ ሰላሳ ስድስት ሚሊዮን ይገመታል፡፡ የኦሮሞ መሬት ስፋቱ 387,000 ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ ማለትም ጀርመንን ያክላል ማለት ነው፡፡

ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም. አዲስ አበባ በገባ ጊዜ ኦነግ አብሮት ስለነበረ ኦሮሞ አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሄደ ሊገመት ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኦነግ አስራ ስድስት አመት ከታገለ በኋላ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር አብሮ ሲመለስ አንድ የፀና ስምምነት ተፈራርሞ የመጣ መስሎ ለኦሮሞዎች ታየ፡፡ ስለዚህ ኦሮሞዎች ለጊዜውም ቢሆን ተረጋጉ፡፡ ነገር ግን ሳይቆይ ኦነግ ወደ ትግል ተመለሰ፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ ኦሮሞዎች ኦነግ ፌደራሊዝምን የተቀበለ - መስሎአቸው ስለነበር ካገር በመውጣቱ አዘኑ፡፡ ከዚህ ይልቅ በሀገር ውስጥ ሆኖ ስለሰብዓዊ መብት፣ ስለእኩልነትና፣ ስለዲሞክራሲ መታገል ነበረበት ብዬ አስባለሁ፡፡

ኦነግ ተመልሶ ከአገር ሲወጣ “ኢህአዴግ ውስጥ ገብቼ አባል አልሆንም” የሚለውን ኦሮሞ ሁሉ ‹‹የኦነግ አባል ነህ›› እያሉ በጅምላ ማሰር፣ አንዳንዱን መግደል፣ የእለት ተዕለት ትእይንት ሆነ፡፡ በዚች አጭር ጽሑፍ ውስጥ የሞቱትን፣ የታሰሩትን መቁጠር አይቻልም፡፡ ነገር ግን እኔ የኦፌዴን መሪ በነበርኩበት ጊዜ ከትልልቆቹ ስራዎቼ መካከል ዋናው ስለኦሮሞ መሞት፣ መታሰር እና መሰቃየት ለኦሮሚያና ለፌዴራል መንግስታቱ እድፍ ነበር፡፡ እንዲያውም አንድ ጊዜ ለማስመሰል የፌዴራል መንግስቱ፣ ኦፌዴንና ኦህዴድ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው ስለነኚህ ችግሮች ያጥኑና የጥናታቸውን ውጤት ያቅርቡ ተብሎ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር፡፡ መጀመሪያውኑ ከልብ ስላልሆነ ኮሚቴው ቶሎ ፈረሰ፡፡

ኦሮሞ የገዳን ሥርዓት ለመተው የተገደደው በመንግስት እና በዘመኑ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለውጦች ምክንያት ነው፡፡ የገዳ ሥርዓት እንዳለ ሥራ ላይ መዋል በአሁኑ ዘመን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ዘመን ወጣቶች ሁሉ በተወለዱበት ሥፍራ አይቆዩም፡፡ ለስራና ለትምህርት ከተወለዱበት ወጥተው ወደሌላ ስፍራ ይሄዳሉ፡፡ አንዱ ትውልድ ሌላውን ትውልድ በሙሉ ካልተካ የገዳ ሥርዓት አይሰራም፡፡

ብዙ የኦሮሞ ምሁራን የገዳን ሥርዓት የሚወዱበት ምክንያት ሥልጣን ላይ ያለው ትውልድ አዲሱ ትውልድ ለስራ ሲዘጋጅ ቦታውን ለቆ መሄዱ ለዲሞክራሲ ጥሩ አስተዋጽኦ ያደርጋል በማለት ነው፡፡ ለሁሉም በአሁኑ ጊዜ ማንም በተወለደበት ቦታ ለብዙ ጊዜ ቀጥሎ ስለማይኖር የገዳ ሥርዓት ሃሳቡ ሲፀነስ በሰራበት መልኩ አሁን ሊሰራ አይችልም፡፡

የኦሮሞ ጥንታዊ ሀይማኖት ዋቄፈታ ሲሆን፤ ይኼም ብዙ ሰዎች እንደሚሉት ወይም እንደሚመስላቸው ለፍጥረት መስገድ አይደለም፡፡ ወንዝ አጠገብ፣ ታላቅ ተራራ አጠገብ፣ ታላቅ ዛፍ ስር ዋቄፈታ ማድረግ እንደዚህ አይነት ታላቅ ፍጥረትን ለፈጠረው አምላክ መስገድ ነው፡፡ አማኞቹ እንደሚሉትም እግዚአብሔር ራሱን የሚገልፀው በታላላቅ ፍጥረቶች በኩል ነው፡፡ እዚህ ላይ ስለዋቄፈታ ያነሳሁት ባለፈው አስር ቀን ውስጥ ኦሮሞዎች ቢሾፍቱ ሀይቅ አጠገብ የተለመደውን ኢሬቻ ለማድረግ የተሰበሰበውን ህዝብ (ሶስት ሚሊየን ህዝብ ነበር ተብሏል) ፖሊስ በሀይል በህዝቡ መሃከል ለብሶ የለበሳችሁት ልብስ የኦነግ ባንዲራ ነው በማለት በመደብደብ፣ በመርገጥ እና ልብሳቸውን በማስወለቅ ጭምር ከባድ ጉዳት አደረሰባቸው፡፡ ይሄ አድራጎት በኦሮሞዎች ዘንድ እንደ ታላቅ ሀጢያት እና እግዚአብሔርን እንደ መዳፈር መስሎ ታየ፡፡ ይህ ሥርዓት በጠባዩ ለእነርሱ ሀይማኖታዊ ነው፡፡ የህዝብን ድምፅ የሚሻ፣ ሰላምን የሚፈልግ እና ትብብርን ከህዝብ የሚጠብቅ መንግስት እንዲህ አይነት ፀረ-ባህልና ፀረ-ህዝብ ወንጀል አይፈፅምም፡፡ ለጊዜው ለዚህ አድራጎት የምናየው ምላሽ ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ኦሮሞ ይሄንን አድራጎት ይረሳል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ማንም ህዝብ ይህ ቢደርስበት ዝም የሚል አይመስለኝም፡፡ የፌደራሊዝም ፅንሰ-ሀሳብ የተዋወቀው ይህን መሰሉን በደል ለማስቀረት ነበር፡፡

ይህ ሁኔታ በፌዴራሊዝም ስርዓት የሚያምኑትን የኦሮሞ ምሁራን አቋም የሚፈታተን ነው፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞ ከሌላው ህዝብ ሁሉ ተለይቶ እንደባእድና ጠላት እየታየ መኖር ቢመረውም ከቀሪዎቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ተስማምቶ በፍቅር መኖር ይፈልጋል፡፡
የኦሮሞ ጥንታዊ ሃይማኖት ዋቄፈታ ነበር፡፡ አሁንም በዋቄፈታ የሚያምኑ ኦሮሞዎች ቁጥራቸው በጣም ብዙ ነው፡፡ ዋቄፈታ ከክርስትናም ሆነ ከእስልምና የተለየ የኦሮሞ የጥንት እምነት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ልዩነቶች ቢኖሩም ብዙዎቻችን የኢትዮጵያ አካል ሆነን በፌዴራሊዝም ሥርዓት እንኖራለን ብለን በቆራጥነት ተነስተናል፡፡ እንዲህ የሚለው ወገን ግን ዛሬ ድምፁ እየተዳከመ ሄዷል፡፡ ህዝብ መናቅ እንደ ቀላል ነገር ሆኖ እየታየ ነው፡፡ ቢሾፍቱ ላይ ለኢሬቻ የመጡትን አማኞች የኦነግን ባንዲራ ለብሳችኋል በማለት ደብድበው ልብሳቸውን የነጠቋቸው ሰዎች ራቁታቸውን ከስፍራው ሲወጡ ታይተዋል፡፡ የኢሬቻን በዓል መንግስት ለምን እንደፈራው አይታወቅም፡፡ ከዚህ በፊት ለዘመናት በየዓመቱ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ አሁን የመንግስት የፀጥታ ሰራተኞች አንድ ቡድን ያደመው ወይም ያዘጋጀው ተንኮል ኖሮ የደረሱበት ነገር ኖሮ ይሆን? አናውቅም፡፡ ጨርሶ ኢሬቻን ለማጉላት አይመስለኝም፡፡ ሌላ የኦሮሞ ቅሬታ አለ፡፡ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የመንግስት ብወዛ ተደርጎ ነበር፡፡ ለጊዜውም ቢሆን የመንግስትን አቅጣጫና ፕላን የሚያመላክቱ ብወዛዎች ተፈፅመዋል፡፡ እዚህ ውስጥ ኦሮሞዎች ምንም ሚና አለመጫወታቸው ብዙ ሰዎችን አስገርሟል፡፡ ከሃገሪቷ አጠቃላይ ህዝብ 35 በመቶ ከመሆናቸው ባለፈ ምድራቸው እጅግ በጣም ሰፊና ሀብታም ሆኖ ሳለ፤ ዛሬ ለኦሮሞ ህዝብ ዝቅ ያለ ግምት እየተሰጠው ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ለምንድን ነው? የጥያቄው መልስ ያለው ኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ነው፡፡ ኦሮሞ ሙሉ የዴሞክራሲ መብቱን የሚጠይቅበት ጊዜ ቅርብ ነው፡፡ ኦሮሞንና የደቡብ ህዝቦችን ማጥቃትና መናቅ በምንም ዓይነት መንገድ ፍትሀዊ አይሆንም፡፡ የሚመጣው የኦሮሞ ትውልድ እንደዛሬው ትውልድ ዓይናፋርና ዝምተኛ አይሆንም፡፡

ፓርላማ ውስጥ እኔና ጓደኞቼ ለምንድን ነው ኦሮሞ የሚጠመደው? ለምንድን ነው ኦሮሞ እንደ ጠላትት የሚታየው? ብለን ስንጠይቅ መልስ አላገኘንም፡፡ ነገር ግን በሽብርተኝነት ህጉ መሠረት ኦነግን ትደግፋላችሁ በማለት በፍፁም ከኦነግ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ሰዎች በብዛት ታስረው ዛሬ እስር ቤት ውስጥ ይማቅቃሉ፡፡ ፍርድ ቤት የእነኚህን ሰዎች ጥፋት በጥልቀት ቢመረምር አንድም የሚያስከስስ ስራ አልሰሩም፡፡ አንዳንዶቹ የፖለቲካ ነፃነት ያለ መስሏቸው ህዝብን ለማደራጀት እንዲሁም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትምህርት ለመስጠት ሲሞክሩ ያለአንዳች ጥያቄ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ብዙ ቀናት ከማቀቁ በኋላ ፍርድ ቤት ይቀርቡና ለረጅም ጊዜ እስር ቤት እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ በቀለ ገርባ የሚባል የኦፌዴን ም/ፕሬዝዳንት እነሆ ያለአንዳች ጥፋት ዛሬ ቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ ይማቅቃል፡፡ የተያዘው ስለ ሰብዓዊ መብት ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የነበሩ ፈረንጆች ስለአነጋገሩት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተፃፈው ታምኖበት ነው ወይንስ አንዳንድ ገር ሰዎችን ለማታለል ነው፡፡ ዜጋ የሚያዝበት ሁኔታ፣ ተይዞ ፖሊስ ጣቢያ የሚቆይበት ጊዜ፣ ፍርድ ቤት የሚቀርብበት ጊዜ፣ፍርድ ቤትም ጉዳዩን በቀጠሮ የሚያቆይበት ጊዜ ሁሉ በሕገ መንግሥትና በሲቪልና ክሪሚናል ፕሮሲጀር ኮድ ተጽፏል፡፡ እነኚህ ሕጎች ሁሉ በየቀኑ እየተጣሉ ነው፤ በትንሹ ሳይሆን በብዛት ነው፡፡ ይህን ሁሉ አቶ መለስ ከዕረፍታቸው በፊት ያውቁ ነበር፡፡ እኔ ራሴ ከእኔ ቢሮ ስለሚሞቱት ሰዎች፣ ስለሚያዙ ሰዎች፣ ስለሚታሰሩ ሰዎች፣ ብዙ ጊዜ ለክልሉ ፕሬዚዳንት እና ለጠቅላይ ሚ/ር ቢሮ ጽፌአለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬም በእሳቸው ቦታ የተተኩ ሰዎች በኦሮሞ ላይ የሚደርሰውን ግፍ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን የሕዝብ መብት እንዳይደፈር አንድ ወገን ለይቶ ማጥቃት ተገቢ አለመሆኑን የወጣ አዲስ ትዕዛዝ አላየንም፡፡ ለወደፊትም ላናይ ነው?

ማስታወሻ

ከዚህ አጭር ጽሁፍ ጋር አያይዤ ለአንባቢያን የማሳስበው ነገር አለ፡፡ አንዳንድ ወዳጆቼ አንድ ጥያቄ ሁልጊዜ ይጠይቁኛል፡፡ “ለምን ሁልጊዜ ስለ ኦሮሞ ብቻ ትጽፋለህ?” መልሶቼ ባያጠግቡም ሁልጊዜ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ “እኔ ደህና አድርጌ የማውቀው ስለ ኦሮሞዎች ስለሆነ ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግስትም ኦሮሞን ለይቶ ስለሚያጠቃ ነው፡፡ ሌላውንም ህዝብ አጥቅቷል፡፡ለምሳሌ ሲዳማና ጋምቤላ በጣም ተመቷል፡፡ ስለነሱ በዝርዝር የሚያውቁት መጻፍ ይገባቸዋል፡፡ እኔ ስለ ኦሮሞ ስጽፍ ኦሮሞ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም በማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ህግና ሥርዓት ባለበት ሀገር ማንም ቡድን፣ ብሔር ወይም ሌላ ስብስብ መጠቃት የለበትም፡፡ ፌደራሊዝም ስራ ላይ እንዲውል እንደዚህ አይነቱን የተዛባ አመለካከት እና አያያዝ ለመከላከል ነበር፡፡ እኔ ለኦሮሞ የምፅፍበት ሌላ ምክንያት የለኝም፡፡ ግን ሌላም የኢትዮጵያ ጉዳይ ደጋግሜ እጽፋለሁ፡፡
Feteh

No comments:

Post a Comment