እኔ አዉቅልሃላሁ የብልጣብልጥ ጉዞ

በበሪሶ ገዳ* | 11/21/2012

የጥሎ ማለፍ ሩጫ
እሽቅድምድም ወደ ዙፋን መዉጫ
የትም ፍጪዉ ዱቄቱን አምጪዉ
እንደ ምንም አድርገሽ አድርሺኝ ከኮርቻዉ
ወቅቱ የሚጠይቀዉ ተጨባጭ ሁኔታ
አምኖ እንደ መቀበል ያለዉን እዉነታ

ዛሬም እንደ ድሮ በቆረጣ በጓሮ
አምታቶ ሊቀሙ ስልጣንን አባሮ
የገዥነት ስሜት የልምራህ አባዜ
የማጭበርበር ልክፍት ላሞኝህ ሁል ጊዜ
ዘወትር ፋሲካ ልረስ በድሮ በሬ
ወጉ አልፎበታል ሆኗል የከሰረ
ወንድም እያጠፉ ወደ ስልጣን መምጣት
እየተጠላለፉ አንዱን በሌላዉ መምታት
በዉስጥ ጉዳይ ገብተው ወገንን ማጋጨት
ወደ ፊት በማየት የጠፋዉን ከማቅናት
ያለፈዉን የሚመኙ ተሞልተዉ በትዕቢት
ላይ ታች የሚማስኑ በስመ አንድነት
በወከባ ሆያሆዬ ሀገር ለመገንባት
የሚፍጨረጨሩ ህልማቸዉን ለማሳካት
እኔ ልንገራችሁ ከእንግድህ አይሰራም
የማስመሰል መንገድ ፍፁም አያዋጣም
የእኔ አዉቅልሃላሁ የብልጣብልጥ ጉዞ
ጊዜዉ አልፎበታል አይሰራም መልሶ
ይጠቅም እንደሆን ለራስ ለዘመድ እንጂ
አይፈይድም ለሀገር ለወገን አይበጂ
ሲሮጡ ይፈታል ሲሮጡ የታጠቁት
አይበረክትም የሽንገላ አንድነት

የጊዜ ጉዳይ ነዉ ጨለማዉን አልፈን
ብርሃን እናያለን የነገ ሰዉ ይበለን!


*በሪሶ ገዳ:  ear_tuf12@hotmail.com
Gadaa.com 

No comments:

Post a Comment