የማንነት ፖለቲካ፣ የኣንድነት ኣቀንቃኞች ስላልፈለጉ ወይም ስለጠሉ ሊጠፋ ኣይችልም።

March 04, 2014 በቀለ ጅራታ ከስዊድን*
“ኢትዮዽያ፣ የቀበሌዎቿና የህዝቦቿ ጠቅላላ ድምር ናት። ግዛቷ ካልተከፋፈለ፣ ህዝቦቿ ካልተገነጣጠሉ በቀር ይህ ትርጉም ሊዛባ ኣይችልም። ዛሬ፣ ኢትዮዽያ የሚለው ቃል ገዥውን ብቻ የሚመለከት ሆኗል። ኢትዮዽያዊ ባህል ሲባል፣ የሚነገረው የዚሁ ወገን ባህል ነው። ሃይማኖት ሲነሳ፣ የሚነገረው ኢትዮዽያ የኣንድ ሃይማኖት ተከታዮች ኣገር ሆና ነው። ስለቋንቋ ሲወሳ፣ ኢትዮዽያ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ኣገር መሆኗ ፈጽሞ ተክዶ ነው። የዛሬዪቱ ኢትዮዽያ ህልውና የህዝቦቻችን ባህሎችና ቋንቋዎች ተደምስሰዉ፣ የገዥዉን ወገን ባህል፣ ሃይማኖትና ቋንቋ እንድንወርስ ይፈለግብናልን? ያንድ ህዝብ ውበትና ጌጡ፣ በነዚህ ነገሮች ኣንድነት ማግኘቱ ኣይደለም። ጌጡና ውበቱ እንደምንነቱ ተከባብሮና ተቻችሎ፣ በማይፈርስ ጽኑ ኣንድነት በነጻነት ተሳስሮ መኖሩ ነው።”
ከላይ የኣንድነት መሰረቱ ምን እንደሆነ በማያሻማ ቋንቋ ሰፍሮ የሚገኘዉ “ግዝትና ግዞት” በተባለዉ የአቶ ኦላና ዞጋ መጽሐፍ ዉስጥ ሲሆን፣ ያሰፈሩትም ከሃምሳ ዐመት በፊት እነ መቶ ኣለቃ በቀለ ሰጉና ኮሎኔል እምሩ ወንዴ የተባሉ የሃይለ ስላሴን መንግስት ከገለበጡ በኋላ በረዲዮ ለህዝብ ለመግለጽ ኣዘጋጅተውት በነበረው የፖለቲካ ማኒፌስቶዋቸው ውስጥ ነው።

ይህንን ሃሳብ ለመውስድ የፈለኩበት ምክንያት ዛሬ ያለማቋረጥ ስለኢትዮዽያ ኣንድነት የሚያዜሙ ወገኖች ኣሁን የሚታየዉ የፖለቲካ ቀውስ የተፈጠረው ለህዝቦቻቸው መብትና ነጻነት ለመታገል የተደራጁ የብሄር ድርጅቶች ያመጡት እንደሆነ በማስመሰል የህዝቦችን ማንነት ለማራከስ የሚፍጨረጨሩት የችግሮቹ ዋናው ምንጭ እነሱ፣ ለመመለስ የሚታገሉለት የተዛቡ የቀድሞ ኣገዛዞች መሆናቸውን ከዚህ በፊት ኣልተረዱ እንደሆነ፣ እንዲረዱ ለማስገንዘብና ከላይ እንደተጠቀሰው ለኣንድነት ጽኑ መሰረት ለሆነው የህዝቦችን ማንነት እንደምንነቱ ማክበርና ለእውነተኛ የህዝቦች ኣንድነት ከሚታገሉት ጋር ተባብረው ቢሰሩ ከማንም የበለጠ እነሱን እራሳቸውን የሚጠቅም መሆኑን ለመምከር ነው።
በኢትዮዽያ ኣንድነት ስም ብዙ ተነግዶበታል። በዚህም ከገዥዎች ወገን ያልሆኑ የኢትዮዽያ ህዝቦች ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል። ከእንግዲህ በዚያው መንገድ ለመቀጠል መሞከር የቆጡን ኣወርድ ብላ የብብቷን ኣጣች ኣይነት ኣባባል ሊሆን ይችላል። የኢትዮዽያ ህዝቦች በተለይም የኦሮሞ ህዝብ እንደብዛቱና በሚያበረክተው የኤኮኖሚ ኣስተዋጽኦ መሰረት ይህቺን ሃገር በደማቸውና በኣጥንታቸው ጠብቀው ለዚህ ያደረሷት መሆኑ ተረስቶ እነሱ እራሳቸው ለኣንድነቷ ኣስጊ ናቸው መባሉ እራሱ እጅግ የሚያስገርም ከመሆኑም በላይ እንደዚህ ዓይነት ኣስተሳስብ ህዝቦችን ከመናቅ የሚመነጭ ኣጉል ትምክህተኝነት ነው።
እነዚህ ህዝቦች ባለፉት ዘመናት የተፈጸሙባቸውን በድሎችና ግፎች ምን ጊዜም የማይረሱት ቢሆንም እነዚያን ለታሪክ በመተው ለወደፊቱ ኣብሮነት በተለያየ ጊዜና መንገድ መፍትሔ ለመፈለግ ብዙ የደከሙና አሁንም እየደከሙ ቢሆንም ዛሬም እኩልነትና መከባበር ክብራቸውን የሚነካ እንደሆነ ኣድርገው የሚገምቱ የባዶ ኣንድነት ኣቀንቃኞች ካለፉት ስተቶች ለመማር ባለመቻላቸዉ ለመተባበር ፈቃደኞች ሆነ ኣልተገኙም። ካለፈው ኣንድ ኣመት ጀምሮ ኣንጋፋ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የኢትዮዽያን የዘመናት የፖለቲካ፣ እኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ማንኛውም ቅን ኣሳቢ የሆነ ግለሰብም ሆነ ቡድን ልቀበለው የሚገባ ኣዲስ ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
እነዚህ የእድሜኣቸውን ኣብዛኛውን በትግል ያሳለፉ ፖለቲከኞች ዛሬም ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ለዘመናት በፈላጭ ቆራጮችና በኣምባገነኖች የግፍ ኣገዛዝ ስር ለማቀቁትና እየማቀቁ ላሉት የኢትዮዽያ ህዝቦች ሰላም፣ ብልጽግና፣ እኩልነት፣ የመከባበርና የመደጋገፍ ስርኣት እንዲዘረጋ በመጣር ላይ ናቸው። የኦሮሞ ፖለቲከኞች ለሃገሪቷ የፖለቲካ ችግሮች የበኩላቸውን መፍትሔ መፈለግ የጀመሩት ዛሬ ኣይደለም። ኦነግ በ1991 ከሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ጋር በመሆን የሽገገር መንግስት በማቋቋም ህደት ውስጥ ስፊ ተሳትፎ ኣድርጓል። የኦሮሞ ህዝብ ኮንግሬስና (ኦህኮ) የኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ቀድም ሲል ለየብቻ በኣሁኑ ጊዜ ደግሞ ተዋህደው በኦሮሞ ፈደራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ስም ለሁላችንም የሚትሆን ኢትዮዽያን እንፍጠር በማለት ትግል ከጀመሩ ኣመታት እየተቆጠሩ ነው።
በኣንጻሩ ለኢትዮዽያ የግዛት ኣንድነት እንጂ ለህዝቦች አንድነት ነጻነትና እኩልነት ደንታ የሌላቸው የቀድሞ ኣገዛዞች ናፋቂዎች የብሄረሰቦችን ማንነት በመናቅ በኢትዮዽያ ስም ካልተደራጃችሁ የኢትዮዽያ ኣንድነት ኣይጠበቅም እያሉ እራሳቸውን ብቸኛ የሃገር ኣንድነት ጠበቃና ፖሊስ ኣድርገው በመቁጠር የመተባበር ፍላጎት ለማሳየት ኣለመፈለጋቸውን በተለያየ መንገድ ሲገልጹ ድፍን ሃያ ሁለት ኣመታት ኣልፈዋል። “የኢትዮዽያ ኣንድነት ጠበቆች” ነን የሚሉ የፖሊቲካ ፓርቲዎች ከብሄር ፓርቲዎች ጋር ግንባር ፈጥረው ለዘመናት መላ ላጣው የሃገሪቷ የፖለቲካ ችግር መፍትሄ ለመፈለግ ከልብ ከመስራት ይልቅ ጸረ የህዝቦች ማንነት ኣቋም በማራመድ ላይ ይገኛሉ። የህዝቦችን ፍላጎት በመናቅና በማራከስ የብሄር ብሄረ ሰቦችን የፖለቲካ ኣደረጃጀት “የጎሳ፣ የዘርና የመንደር ፖሊቲካ” እያሉ ባገኙት ኣጋጣሚና መድረክ በማጥላላት ላይ ተሰማርተዋ ል።ኢትዮዽያ የህዝቦችዋና የቀበሌዎችዋ መሆኑን በመካድ ወይም ባለመቀበል በውስጥዋ የምገኙት ህዝቦች እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሃገር የማፍረስ ኣላማ እንዳላቸው እየቆጠሩ የህዝቦችን ማንነት በኣደባባይ ስቃወሙ ይታያሉ።
ከሃገርና ከህዝቦች ሃላፊነት ኣንጻር በማሰብ እራሳቸውን መለወጥ ያልቻሉ፣ ከተጨባጩ የሀገሪቷ የፖለቲካ ኣሰላለፍና የህዝቦችን ፍላጎት ለማክበር ዝግጁ ሳይሆኑ በኣየር ላይ ኣንድነት ለመገንባት የሚጥሩ ኣዋቂዎች ሳይሆኑ የዋሆች ብቻ ናቸው። እነዚህ ወገኖች በኣሁኑ ወቅት በሃገሪቷ ስለደረሰው የፖለቲካ ቀውስ የኣሁኑ ገዢ መንግስት ያመጣው ጣጣ ነው ብለዉ ሌሎችን ሳይሆን እራሳቸውን ብቻ በማታለል ላይ ይገኛሉ። እዉነቱ ግን ሀገሪቷ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ ሲንከባለል የመጣ ስለመሆኑ ከላይ በእነ በቀለ ሰጉ የተገለጸዉ በቂ ምስክር ነዉ።
“የኣንድነት ጠበቆች” ባለፉት ሃያ ሁለት ኣመታት ከተጨባጩ የሃገሪቷ የፖለቲካ ሁኔታና ኣደረጃጀት ጋር የማይሄድ ብቻ ሳይሆን ከእራሳቸዉ በስተቀር ኣድማጭ የሌለውን ባዶ ጩሄት ስያሰሙ ከርመዋል። ይህ የሃገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታ ሆን ብሎ ወደ ጎን በመተው ከእንግዲህ በምንም ሁኔታ ወደኋላ መመለስ የማይቻለውን የፖሊቲካ ህደት መቃወምና መናቅ ከትምክህት የሚመነጭ ካልሆነ ሌላ ትርጉም ልሰጠው ኣይችልም። ሌሎች በእኩልነትና በመከባበር ኣብረን የምንኖርባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮዽያ ለመመስረት በጋራ ለመታገልና ለመስራት ጥሪ ስያሰሙ “እኛ የጎሳ ፖለቲካ ኣናካሄድም” በማለት ለብሄር ብሄረ ሰቦች ያላቸውን ንቀት ያለሃፍረት ስያቀነቅኑ መቀጠላቸው ያለ ምንም ጥርጥር ኢትዮዽያን የሚያፈርስ መሆኑን ልያውቁት ይገባል። በዚህ እራስ ወዳድነትና ኣጉል ትምክህታቸው ከቀጠሉ ወደፊት ሊከሰት ለሚችለው የመበታተን ኣደጋ ተጠያቂዎቹ እራሳቸው መሆናቸውን ከኣሁኑ ሊያውቁት ይገባል።
በሃገር ውስጥ በፖለቲካ ፓርቲ ስም የተደራጁት እንደ ኣንድነት ለፍትሕና ዲሞክራሲ (ኣንድነት) ያሉ “የኢትዮዽያ ኣንድነት ብቸኛ ተቆርቋሪ እኛ ነን” የምሉ ለስሙ ከብሄር ፓርቲዎች ጋር ለመስራት የሚፈልጉ መስለው የማታለልና የህጻን ጫወታ ለመጫወት ሲሞክሩ እንደከረሙ የኣደባባይ ምስጢር ነው። “ኣንድነት ሃገር ኣቀፍ ፓርቲ” ነው እያሉ በባዶ ሜዳ መመጻደቅ በምንም መልኩ ሃገር ኣቀፍ ፓርቲ ሊያደርግ ኣይችልም። ምናልባት ይህ የሚጠቅመው የፓርቲዎቹን ኣመራሮች ዝናና ከዚያም ኣልፎ ከኣርባና ሰላሳ ኣመታት በፊት ሃገሪቷን ጥለው በወጡና የሃገሪቷ የፖለቲካ ሁኔታ እነሱ ትተውት በሄዱበት ዘመን ያለ እየመሰላቸው ገንዘባቸውን የሚያፈሱ ዲያስፖራዎችን በማታለል የግል ጥቅማቸውን ለማርካት ነው። በርግጥ ኣንድነት ኣመራር የሚያገኘውም ከዲያስፖራው በመሆኑ ሊፈረድበት ኣይገባም። ሆኖም ከመድረክ ጋር የቆሙ ለማስመሰል የራሳቸዉንም ሆነ የሌሎችን ጊዜ በከንቱ ሲያባክኑ ከቆዩ በኋላ ቀናቸው ደርሶ ከመድረክ ኣባልነታቸው ተባረዋል። በባዶ ሜዳ ሃገር ኣቀፍ ፓርቲ ነን ማለት ብቻውን ሃገር ኣቀፍ ፓርቲ ሊያደርግም ሆነ የ ሕዝብ ድምጽ ሊያስገኝ እንደማይችል የኣንድነት መሪዎችም ሆኑ መመሪያ ሰጭ ዲያስፖራ መገንዘብ ኣለመቻላቸው በጣም ያሳዝናል።
ከብሄር ብሄረሰቦች ጋር መደራጀት ክብራቸውን የሚነካ በመሆኑ በሰማይ ላይ ለመደራጀት የሚጥሩም ተፈጥረዋል (ሰማያዊ ፓርቲ)። “የብሄር ፖለቲካን” በመሬት ላይ ሆነው ለማጥፋት ስላልቻሉ ከወደ ሰማይ ለመምጣት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። እንኳን በሰማይ በጨረቃ ላይ ቢደራጁ የህዝቦችን የማንነት መብት ሊያስቀሩ ኣይችሉምና ብዙ ባይለፉ መልካም ነው።
ስለዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት እየጻፉና እየለፈፉ ዞር ብለው እነዚህኑን መብቶች ሲቃወሙና በተቃራኒው ሆነው ሲታገሉ ማየት በእጅጉ ከማሳዘኑም በላይ የእነዚህን ወገኖች ኣስተሳሰብ ለመረዳት ያስቸግራል። የኢትዮዽያ ብሄር, ብሄረ ሰቦች ዲሞክራሲያዊ ስራት እንዲመሰረት የምያደርጉትን የመብት ትግል መቃወም ማለት ህዝቦች ከሰቆቃ፣ ከኑሮ መጎሳቆልና ኋላ ቀርነት እ ንዳይላቀቁ ከመፍረድ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው ኣይችልም። እነዚህ ወገኖች በኢትዮዽያ የተለያየ ባህልና ቋንቋ ያላቸው ህዝቦች መኖራቸውን ኣይክዱም። ሆኖም እነዚያን የማንነታችውን መገለጫ ጥለው “ኢትዮዽያዊ የሚለውን ካባ” ብቻ እንዲደርቡ ለማስገደድ ይሞክራሉ። በእነሱ አስተሳሰብ ኣንድ ሰው ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ሶማሌ ወዘተ ሆኖ ኢትዮዽያዊ መባል ኣይችልም።
የኢትዮዽያ ህዝቦች በጋራ ኣብረው መኖር የምችሉት ሙሉ መብታቸው ስክበርና የእኔ ኣውቅልሃለው ኣስተሳሰብ ሲወገድ ብቻ መሆኑን ተረድቶ በዚህ መንፈስ እራስን ማዘጋጀትና መደገፍ ኣማራጭ የሌለው ነው። “የኣንድነት ጠበቆች” ለሃያ ሁለት ኣመታት ያለ ማቋረጥ የሚያወግዙት “የጎሳ፣ የዘር ወዘተ ፖሊቲካ” እነሱ ስላልፈለጉ ሊጠፉ ወይም ሊቀየሩ እንደማይችሉ መታወቅ ኣለበት። “ፌደራሊዝምን እንቀበላለን ግን በቋንቋ ላይ የተመሰረተን ፌደራሊዝም ኣንቀበልም” ሚባለውም የቁራ ጩሄት ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ሊኖረው ኣይችልም። ኣንድ ቁዋንቁዋ፣ ኣንድ ባህል፣ ኣንድ ስነልቦናና በኣንድ ክልል የሚኖርን ህዝብ በኣምስት ቀጠና ከፋፍሎ ለመግዛት መሞከርና ማሰብ የማይቻል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ቅንጅት የተባለው ኢትዮዽያን በኣምስት ቀጠና ከፋፍሎ ገዢዎችን መሾሙ ይታወሳል። ወራሾቹም ያንኑ የሚያስቡ ከሆነ ለቅንጅትም ኣልበጀምና ሳይዘገይ እራሳቸውን ኣስተካክለው የብሄር ፖለቲካ ድርጅቶችን ይቅርታ ጠይቀው ኣብረው ለመስራት ቢወስኑ ይሻላቸዋል ብቻም ሳይሆን ግዴታቸው ነው። ኣለበለዚያ እንደኣባታቸው ቅንጅት በነፋስ ተጠርገው ይጠፋሉ። ያኔ የኢትዮዽያ ህዝቦች ተባብረው መብታቸው የተከበረባት ኣዲሲቷን ኢትዮዽያ ይመሰርታሉ።
በየፓልቶኩና ድህረገጾች በማንነት ላይ የተመሰረተን ፌደራሊዝም (ethnic federalism) ማውገዝ ህዝቦች የበለጠ ለማንነታቸው በርትተው እንዲሰሩና የበለጠ እንዲያጠናከሩ ከማድረግ በስተቀር ኣንድነት ሊያመጣ እንደማይቻል መገንዘብ ብልህነት ነው።
ወጣቱ የፖለቲካ ኣናሊስት ጀዋር መሃመድ “እኔ በመጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ” በማለቱ የኣንድን ግለስብ መብትና ነጻነት እንኳን ለመቀበል ዝግጁ ያልሆኑ ወገኖች ያደረሱበት ውግዘት ሚሊዮኖች የኦሮሞ ተወላጆች “እኛም በመጀመሪያ ኦሮሞ ነን” በማለት በመላው ኣለም ስፊ እንቅስቃሴ እንዲካሄድ ምክንያት ሆኖኣል። ይህ ደግሞ የሚፈለገውን የህዝቦች ኣንድነት ለማምጣት የሚያግዝ ኣይደለም።
በመሰረቱ ጀዋር የተፈጠረው ኦሮሞ ሆኖ በመሆኑ “መጀመሪያ እኔ ኦሮሞ ነኝ” ማለቱ በምንም መልኩ ማንንም ሊያስቆጣ የሚችል ጉዳይ መሆን የለበትም። የፈለገ ዜግነቱን መቀየር ቢችልም ማንነቱን መቀየር ኣይችልም። ኦሮሞነትም ሆነ ኣማራነት ወይም ጉራጌነት ዘር እንጂ ዜግነት ኣይደሉም። ሰው ዜግነቱን ቀይሮ የትም መኖር ይችላል። ዘሩን ወይም ደሙን መቀየር ግን ኣይችልም። እነዚህ የትም ቢሆን ኣብረውት ይገኛሉ። ኢትዮጵያዊነት ዜግነትን እንጂ ዘርን ወይም ማንነትን አይገልጽም።
የሚገርመው ደግሞ በጀዋር ላይ የውግዘት ዘመቻ የከፈቱት “ለግለሰብ መብት” እንጂ የወል መብትን ኣንቀበልም በማለት ላለፉት ሃያ ሁለት ኣመታት የብሄር የፖለቲካ ድርጅቶችን ሲያውግዙ የኖሩት ወገኖች መሆናቸው ነው። እነዚህ ወገኖች የምታገሉለት ከዚህ የበለጠ የግለስብ መብት ምን እንደሆነ ብያስረዱ ጥሩ ይሆናል። ምክንያቱም እኔ እከሌ ነኝ ቢሎ ኣንድ ሰው እራሱን መግለጹና መወሰኑ የግለሰብ ሙሉ መብት መሆኑን የማይቀበል የፖለቲካ ኣቋም ምን ኣይነት የግለሰብ መብት ለማስክበርና ለማክበር እንደሚታገል ለማወቅ ኣይቻልም። ኣንድ ሰው እራሱን በፈለገው ስም የመጥራት መብት የዲሞክራሲ ግንባር ቀደም መርህ ነው። ይህንን የማይቀበል ወገን ፈጽሞ ስለዲሞክራሲ መጻፍም ሆነ መናገር የሚችል ኣይመስለኝም። ስለ ዲሞክራሲ እየሰበኩ ዲሞክራሲን መቃወም ማለት መሆኑን እንኳን ኣልተረዱትም። ኣንድ ሰው ኣንተ ማን ነህ ተብሎ ቢጠየቅ ኣማራ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ፣ ከምባታ፣ ሃዲያ ወላይታ ወዘተ ቢሎ መልስ ቢስጥ ወንጀሉ የቱ ላይ ነው? በኢትዮዽያ ውስጥ ሰማኒያ የምደርሱ የተለያዩ ህዝቦች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን “ኢትዮዽያ” የሚል መጠሪያ ያለው ብሄር ብሄረሰብ ወይም ህዝብ የለም። ኣንድ ሰው ማነህ ሲባል እከሌ ነኝ ቢሎ ማንነቱን መግለጽ በምንም መልኩ ሊያበሳጭ ኣይገባም።ኣንድነትንም ከማራቅ ይልቅ ኣያቀርብም።
በዚህ ኣይነት ገታራ ኣቋም በህዝቦች የነጻነት ፣ የዲሞክራሲ፣ የእኩልነትና የእድገት ፍላጎት ላይ እንቅፋት በመሆን የስቆቃ ኑሮው እንዲራዘም ማድረግ ግን ግብዝነት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም የለውም። በኣጠቃላይ ያለፉትም ሆኑ የዛሬዎቹ ለኢትዮዽያ ኣንድነት እራሳቸውን ብቸኛ ተቆርቋሪ ኣድርገው የሚገምቱት የፈጸሙትና እየፈጸሙ ያሉት እውነተኛ የኢትዮዽያ ህዝቦች ኣንድነት እንዳይመጣ ከፍተኛ እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል።
ህዝቦች ለምን በክልላቸው ስም ይጠራሉ ወይም ለምን የኦሮምያ ፣ የኣማራ፣ የትግራይ ወዘተ ክልል ተባሉ በማለት ስያወግዙና ስተቹ ዛሬ ድረስ ቀጥለዋል። በኔ ግምት በኢትዮዽያ ማምጣት የሚፈለገው ኣንድነት የህዝቦች ኣንድነት እንጂ የግዛት ኣንድነት ኣይደለም። ምክንያቱም ከላይ በመግቢያዬ ላይ እንደተጠቀሰው የዛሬ ሃምሳ ኣመት ገደማ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮዽያውያን እንደጠቀሱት የጠፋው ለኣንድነት መሰረት የሆነ የህዝቦች በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ኣንድነት ነው እንጂ የኢትዮዽያ የግዛት ኣንድነት ኣይደለም። ያለፉት የኢትዮዽያ ገዢዎች ስለግዛት ኣንድነት እንጂ ስለ ህዝቦች ኣንድነት ደንታ ኣልነበራቸውም። በመሆኑም የህዝቦችን መብት በማፈን በጭካኔ ስገዙ እንደኖሩ ይታወቃል። ኣፈናና ጭቆና ዉሎ እያደረ ተቃውሞ በመቀስቀስ ኣገዛዞቹን ተራ በተራ ኣስወገዳቸው። ያኔ ልቦና ሰጥቶኣቸው የህዝቦችን መብት በማክበር በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የኣስተዳደር ስርአት ቢመሰርቱ ኖሮ የሃገሪትዋ የፖለቲካ ሁኔታ ከኣሁኑ የተለ በሆነ ነበር።
ይህ ዛሬ በኣንጻራዊ መልኩ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች እራሳቸውን በኣራሳቸው የማስተዳደር መብቶች የተገኙት በቀላሉ ኣይደለም። ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት እንደሆነ የሚስተው ያለ ኣይመስለኝም። ታዲያ ይህንን ብዙ ዋጋ የተከፈለበትን በቀላሉ ለመቀልበስ የሚቻል የሚመስላቸውና ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውንና ጊዜኣቸውን የሚያጠፉ መኖራቸው ያስገርማል።
የኣሁኑን ኣገዛዝም የሚቃወሙትና የሚታገሉት በጨቋኝነቱና በኢ-ዲሞክራሲያዊነቱ ሳይሆን ለብሄር ብሄረ ሰቦች እውቅና በመስጠቱ ብቻ እንደሆነ በግልጽ ለመናገር ይቻላል። ይህ ባይሆን ኖሮ ህዝቦች በፈለጉት ኣይነት ተደራጅተው ይመቸናል ያሉትን የኣስተዳደር ስርአት የመዘርጋት ሙሉ መብት ያላቸው መሆናቸውን በተቀበሉትና በደገፉት ነበር። የኢትዮዽያ ህዝቦች በተፈጥሮ በሰፈሩበት ክልል እየኖሩ መሆናቸው እየታወቀ ለምን በክልላቸው ስም ይጠራሉ ብሎ መከራከርና ጊዜን ማጥፋት ለምን እንዳስፈለገ ለእነሱ እንጂ ለማንም ሊገባ ኣይችልም። እነሱ እንደምፈልጉት ኢትዮዽያ በኣምስት የፌደራል ቀጠና ቢትከፋፈል የማንን ቋንቋ በመጠቀም ለማስተዳደር እንደሆነ ለመረዳት ብዙም ኣያስቸግርም። በቀላሉ ኦሮምኛ፣ ሱማልኛና ወላይተኛ ወዘተን በማጥፋት በኣማርኛ ለመተካት መሆኑ የኣዳባባይ ሚስጢር ነው። የክልሎች ስም የተጠላበት ዋናው ምክንያት ይሄ ነውና፣ የምቻል ከመሰላቸው በጣሙን ተሳስተዋልና ሳይመሽ መንቃት ኣለባቸው።የኢትዮዽያ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተደምስሰዉ ኣንድ ቋንቋ ኣማርኛ ብቻ የሚነገርባት ሃገር ለማድረግ የሚደረገው ሙከራ ጊዜው ያለፈበት መሆኑን ዛሬም ያልተረዳ ካለ ጤነኛ መሆኑ ያጠረጥራል።
የኢትዮዽያ ኣንድነት ኣቀንቃኞች በማንነትና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም የዜጎችን በፈለጉት አካባቢ ተዘዋውረው የመስራትና የመኖር መብትን ይገድባል ብለው ለመከራከር ይሞክራሉ። በመሰረቱ ኣውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት ኣይሰማም እንደተባለው ካልሆነ በስተቀር ኣብዛኞቹ በፈደራል ስርአት የምተዳደሩ ሃገሮች በዋናነት በቋንቋ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸው ግልጽ ነው። ለዚህ ምሳሌ ካናዳና ስዊዜርላንድን መጥቀስ ይቻላል። በካናዳ የክቤክ ግዛት በፌደራል ኣስተዳደር እንዲተዳደር የተደረገው ኣብዛኛው ህዝብ ፈረንሳይ ኛ ተናጋሪ በመሆኑ ነው። ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ፈረንሳይ ኛ ተናጋሪ ሆኖ ሳይሆን ኣብዛኛው በመሆኑ ያ መብት ተከብሮለታል። ዲሞክራሲ የብዙሃን ኣስተዳደር የኣናሳዎች መብት ማስከበር የተባለውም ለዚህ ነው።
በስዊዘርላንድ ኣራት በቋንቋ ላይ የተመሠረቱ ክልሎች ኣሉ። እያንዳንዱ የስዊዘላንድ ዜጋ ከኣራቱ ኣንዱን የመማር ግዴታ ኣለበት። በመሆኑም የስዊዘርላንድ ህዝብ ባለ ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ (bilingual)እንዲሆን ኣስችሎታል። እነዚህ ሃገሮች በኣለም ላይ በዲሞክራሲ፣ በሰላምና፣ በእድገት በግንባር ቀደምት ነት የምጠቀሱ ወይም የምታወቁ ናቸው። ባለብዙ የስራ ቋንቋ ባለቤት መሆናቸው ከማንኞቹም የኣለም ሃገሮች ኣንድነታቸው የጠበቀና በእድገት ቀዳሚ እንዲሆኑ ኣደረጋቸው እንጂ በኣንድም ወቅት ለኣንድነታቸው ስጋት ሆኖ ተሰምቶ ኣይታወቅም።ታዲያ ኦሮሞው፣ ሱማለው፣ ኣፋሩ፣ ኣማራው ፣ ትግሬው፣ ወዘተ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዚም ኣስተዳደር ብኖራቸው ለኢትዮዽያ ኣንድነት እንዴት ስጋት ሊሆን ይችላል? መብታቸውስ ኣይደለምን?
የዜጎችን የመዘዋወር መብት ይገድባል የሚባለውም ከእውነታ የራቀ ምክንያት እንጂ ተጨባጩ ሁኔታ ያንን ኣያመለክትም። የፌደራል ኣወቃቀሩ ያስቀረው ነገር ቢኖር በመቶ ሺዎች የምቆጠሩት ሰዎች ከሰሜኑ ከልል ወደ ኦሮምያና ሌሎች ክልሎች ኣምጥቶ ማስፈርን ነው እንጂ ዜጎች በግላቸው የትም ክልል ሄደው ሰርተው የመኖር መብታቸው ኣልተገደበም። በመንግስት ስራ ላይ ተሰማርቶ ለመስራትም እንደ ስዊዜርላንድና ሌሎች ሃገሮች ባለ ሁለት ቋንቋ (bilingual) መሆን ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከክልሎች ቋንቋ የፈለጉትን መርጦ መማር ብቻ በቂ ነው። በመሰረቱ ኣንድ ሰው የክልሉን የስራ ቋንቋ የማይችል ከሆነ ህዝብ ለማገልገል ኣይችልም። ምክንያቱም የመንግስት ስራ ህዝብን ለማገልገል ስለሆነ ነው። ኣንድ ሰው ለመኖር መስራት ኣለበት ሰርቶ ለመኖር ደግሞ የሚሰራበትን ክልል የስራ ቋንቋ መቻል ሃላፊነቱ የራሱ ነው እንጂ የክልል ሊሆን ኣይችልም። ፈረንጅ ሃገር ስራ ፍለጋ የምሄድ ሁሉ የተሰደደበትን ሃገር ቋንቋ ለመማር ያልተቸገረ የራሱን ሃገር ወገን ቋንቋ ተምሮ ለመስራት ኣለመፈለግ እራሱ የሚያስተዛዝብ እንጂ የሚያሳዝን ፈጽሞ ልሆን ኣይችልም።
በመጨረሻም የአንድነት አቀንቃኞች ተጨባጩን የወቅቱን የህዝቦች የፖለቲካ ኣሰላለፍ ሳይወዱ በግድ እየመረረም ቢሆን በመዋጥ የህዝቦችን ማንነትና ፍላጎት በማክበር እውነተኛ የሆነ ኣንድነት ለመመስረት እንዲቻልና ሃገሪቷ ከገጠማት የፖለቲካ ኣጣብቂኝ ተላቃ ወደ እድገት ጎዳና እንዲታመራ ለዚህ ኣላማ ሌት ተቀን ከሚለፉት ጋር የበኩላችሁን ቢታበረክቱ ከታሪክ ተጠያቂነት ትድናላችሁ። ይህ ካልሆነ ምናልባት በእናንተ ገታራና እራስ ወዳድነት ምክንያት የመበታተን ኣደጋ ከመጣ ግንባር ቀደም ተጠያቂዎቹ እናንተ ትሆናላችሁ። በኔ እምነት በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ ወረዳዎች የየእራሳቸው ባንዲራ ቢያውለበልቡ ለኢትዮዽያ ኣንድነት ጽኑ መሰረት ይሆናሉ እንጂ በምንም መልኩ ስጋት ኣይሆኑም።
የሰውን ልጅ በፍቅር እንጂ በ ጉልበት የመግዛት ዘመኑ ካለፈ በርካታ ኣመታት የተቆጠሩ ስለሆነ ከዚህ በኋላ ያለፈውን መናፈቅ ህልም እንጂ እውነት ልሆን ኣይችልም። የማንነት ፖለቲካም የኣንድነት ኣቀንቃኞች ስላልፈለጉ ወይም ስለጠሉ ሊጠፋ ኣይችልም።
በቀለ ከስዊድን: bji2050@yahoo.com 

No comments:

Post a Comment