ጄኔራል ታደሰ ብሩና ኮሎኔል ሀይሉ ረጋሳ

December 11, 2014 | አፈንዲ ሙተቂ


ይህንን ፎቶግራፍ ሰሞኑን በኢንተርኔት ላይ ሲንሸራሸር ነው ያገኘሁት፡፡ ፎቶውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጣው በ1967 በመጋቢት ወር አጋማሽ የታተመ አንድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅጂ ነው፡፡ ያ ጋዜጣ በደርግ ዘመን በድብቅ በከተማችን ይዘዋወር እንደነበረ ትዝ ይለኛል፡፡ በደርግ ውድቀት ማግስት ደግሞ የገለምሶ ከተማ ቀደምት ፎቶ ቤት የሆነው “ፎቶ አብደላ” የጋዜጣውን ኮፒና ይህንን ፎቶግራፍ ለየብቻቸው በማባዛት በሰፊው ሲያሰራጭ ቆይቷል (ፎቶ ቤቱ አንዱን ምስል በሶስት ብር ነው የሚሸጠው)፡፡

*****
በፎቶግራፉ ላይ የሚታዩት የሜጫና ቱለማ ማህበር አንጋፋ አባላት የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ እና ኮሎኔል ሀይሉ ረጋሳ ናቸው፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሁለቱን ሰዎች ፎቶግራፍ ያተመው “ታደሰ ብሩና ግብረ አበሮቹ ተያዙ” የሚል ርዕስ ከሰጠው የዜና ዘገባ ጋር ይመስለኛል (ሙሉ ርዕሱን ዘንግቼዋለሁ)፡፡ ይሁን እንጂ በዘገባው የቀረበው “የመሬት ላራሹን አዋጅ በመቃወም ሸፍተው ሀገር ሲያተራምሱ የነበሩት እነ ጄኔራል ታደሰ ብሩ በህዝብ ትብብር ተያዙ” የሚል ከእውነታ የራቀ ሐተታ ነው፡፡ እነ ጄኔራል ታደሰ ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር ሲሉ ነው በጫካ የመሸጉት እንጂ የመሬት አዋጁን በመቃወም አይደለም፡፡ ይህ የነ ጄኔራል ታደሰ ብሩ የትጥቅ አመጽ ጥንቱ የሜጫና ቱለማ እንቅስቃሴ ቀጣይ ሆኖ ነው የተለኮሰው፡፡

ጀኔራል ታደሰ ብሩ በዚያን ጊዜ በምስራቅ ኦሮሚያ የተጀመረውን የትጥቅ ትግል ሁለተኛ ግንባር በማዕከላዊው ኦሮሚያ ለመክፈት ከአስራ አምስት ያልበለጡ ሰዎችን አስከትለው በጥር ወር 1967 ወደ ምዕራብ ሸዋ ጫካዎች ገቡ፡፡ ይሁንና ብዙም ሳይራመዱ በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ በጸጥታ ሀይሎች ተያዙ፡፡ ደርጎችም ጀኔራል ታደሰንና ኮሎኔል ሀይሉን በይስሙላ ፍርድ ቤት ካቆሟቸው በኋላ በመጋቢት ወር 1969 ረሸኗቸው (በነገራችን ላይ “መለስ ተክሌ” የሚባለው የትግራይ ቀደምት ፋኖ “በማዘጋጃ ቤት ላይ ፈንጂ አጥምዷል” የሚል ክስ ቀርቦበት ከጄኔራል ታደሰ ብሩ ጋር በአንድ ላይ ተረሽኗል፡፡ በቅርቡ የሞቱት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ "መለስ" በሚለው የትግል ስም ራሳቸውን የጠሩት መለስ ተክሌን ለማስታወስ በሚል ነው፤ የአቶ መለስ ዜናዊ የልደት ስም “ለገሠ ዜናዊ” ነው)፡፡
*****
የሜጫና ቱለማ እንቅስቃሴንና የጄኔራል ታደሰ ብሩን አመጽ ደራሲ ኦላና ዞጋ “ግዝትና ግዞት” የሚል ርዕስ በሰጠው መጽሐፍ በሰፊው ጽፎልናል፡፡ ስለዚህ ሰፊውን ታሪክ ከዚያ ማንበብ ይቻላል፡፡ እኔም ለወደፊቱ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የመጻፍ እቅድ አለኝ፡፡ ለአሁኑ ግን የሜጫና ቱለማ ማህበርን በተመለከተ አንድ አስፈላጊ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

“ሜጫና ቱለማ” ከየትኛውም የፖለቲካና የሀይማኖት ቡድን ጋር ያልወገነ አንጋፋ ማህበር ነው፡፡ መላውን የኦሮሞ ህዝብ የሚያስማማና የሚያግባባ ማህበር ቢኖር እርሱ ብቻ ናቸው፡፡ ባለቤትነቱም የመላው ህዝብ ነው፡፡ አባላቱም በፖለቲካና በሀይማኖት የተገደቡ አልነበሩም፡፡ ታዋቂው የኢትዮጵያ የውትድርና ሊቅ ሌፍትናንት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ፣ በቅርቡ ስልጣናቸውን ያስረከቡት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ነጋሦ ጊዲዳ፤ የኦፌዴን አባላት የነበሩት እነ ዶ/ር ሞጋ ፍረዲሳና ኃይሥላሤ ወልዲያ፣ የኦነግ መስራች አባላት የሆኑት አባቢያ አባጆብር፣ ገላሳ ዲልቦ፣ ሌንጮ ለታ ወዘተ… የማህበሩ አባላት ነበሩ፡፡ ሟቾቹ ባሮ ቱምሳ፣ ቄስ ጉዲና ቱምሳ፣ የድሬ ዳዋው ቀኛዝማች አብዱልዓዚዝ መሐመድ፣ የአርሲው ሃጂ ሮበሌ፤ ወዘተ ከማህበሩ አንጋፋ መካከል ነበሩ፡፡

ሜጫና ቱለማ በኦሮሞዎች መካከል አንድነትንና ፍቅርን ለማጎልበት በሰፊው ሰርቷል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋን ለማሳወቅም ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ዛሬ ሁሉም የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ሲቪክ ማህበራትና የባህል ቡድኖች እንደ መለያ አርማ የሚገለገሉበትን የ“ኦዳ” (የሾላ ዛፍ) ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው የሜጫና ቱለማ ማክበር ነው፡፡ ይህ ማህበር በኦሮሞ ህዝብና በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል በጠላትነት የመተያየት ክፉ አባዜ እንዳይኖርም በሰፊው አስተምሯል፡፡ በመሆኑም ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች የተወለዱ በርካታ አባላት ነበሩት፡፡

የሜጫና ቱለማ ማህበር ታሪክ በአዎንታዊነቱ የምንጊዜም ተጠቃሽ ነው፡፡ ከኦሮሞ ህዝብ ውጪ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖችና ግለሰቦችም በታሪኩ ይኮሩበታል፡፡ ህወሐት፣ ኢህአፓ፣ ኦነግ፣ “ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ” እና ሌሎችም የፖለቲካ ድርጅቶችና አባላቶቻቸው የጻፏቸውን ድርሳናት ብታዩ ይህንን በቀላሉ መረዳት ትችላላችሁ፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ (ሕወሐት)፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ (ግንቦት ሰባት)፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና (ኦፌኮ-መድረክ)፣ አቶ አባዱላ ገመዳ (ኦህዴድ)፣ አቶ አረጋዊ በርሀ (ትዴን)፣ አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ (መኢሶን)፣ አቶ ክፍሉ ታደሰ (ኢህአፓ)፣ ዶ/ር ታደሰ ኤባ (ኦነግ) የጻፏቸውን መጻሕፍትና ያደረጓቸውን ንግግሮች ብትመለከቱ ስለሜጫና ቱለማ ማህበር ቀናውን ሲናገሩ እንጂ አንድም የነቀፋ አስተያየት ሲሰነዝሩ አታገኙም፡፡

ታዲያ በብዙዎች አንደበት እንዲህ የተደነቀው ታሪካዊ ማህበር ባለፉት 10 ዓመታት ከኦነግ ጋር ንክኪ አለው በሚል ምክንያት አላግባብ ታግዶ ነው ያለው፡፡ ማህበሩ የታገደው የዛሬ አስር ዓመት ገደማ “የኦሮሚያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ እንጂ አዳማ አይደለችም” የሚል የተቃውሞ ሰልፍ በመዘጋጀቱ ነው፡፡ መሪዎቹና በርካታ አባላቱም “ከሽብርተኞች ጋር ንክኪ አላችሁ” ተብለው ታስረው ነበር፡፡ መሪዎቹ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ባደረጉት ሽምግልና ተፈተዋል፡፡ ከአባላቱ መካከል ከፊሎቹ አሁንም እስር ቤት ነው ያሉት፡፡

ታዲያ የሚገርመው ነገር “የኦሮሚያ ዋና ከተማ አዳማ ናት” የሚል ውሳኔ ያሳለፉትና ውሳኔውን የተቃወመውን ሁሉ በጸረ-ሰላም ሲፈርጁ የነበሩት የኦህዴድ መሪዎች ከምርጫ-97 በኋላ ውሳኔያቸውን አጥፈው “የኦሮሚያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ ናት” በማለት ወደ ፊንፊኔ (አዲስ አበባ) መመለሳቸው ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ በቀዳሚነት ያነሳው የሜጫና ቱለማ ማህበር ግን ከኦነግ ጋር ንክኪ አለው ተብሎ ታገደ፡፡ ያ ውሳኔ ዛሬም ድረስ እንደጸና ነው፡፡ ይህ ምን ዓይነት ፍትሕ ነው?
*****
እኛ ኦነግ አይደለንም፤ ኦህዴድም አይደለንም፤ ኦፌኮም አይደለንም፡፡ ፖለቲካው ውስጥ በጭራሽ የለንበትም፡፡ ሜጫና ቱለማ ግን የሁላችንም ነው፡፡ ኦሮሞ ነኝ የሚል ሰው በሙሉ ታሪኩን ይጋራዋል፡፡ ስለዚህ ይህ አንጋፋ ማህበር አላግባብ የተላለፈበት የእግድ ውሳኔ ተነስቶለት ታሪካዊ ሚናውን ይቀጥል ዘንድ እንዲፈቀድለት በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
-------
ግልባጭ
----ለሚመለከተው ሁሉ

No comments:

Post a Comment