የተጀመረው መብትን የማስከበር ህዝባዊ ትግልና የታየው የመተባበር መንፈስ ተጠናክሮ መቀጠል ኣለበት

December 31, 2015 | በበቀለ ጅራታ*

ገዢው የወያኔ ቡድን ገና በኣሜሪካ መንግስት ደጋፊነት የሀገሪቷን ስልጣን ከተቆጣጠረበት 1983 ጀምሮ በኢትዮዽያውያን ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘ ቡድን መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም ይሄዉ ለሃያ ኣምስት ኣመታት በስልጣን ላይ ሊቆይ ችሏል። ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ተቃዋሚዎቹን እየገደለ፣ እያሰረ ከሀገር እያሳደደ ዛሬ ላይ ደርሷል። በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን የሚያቀርቡትንና የሚጽፉትን ያለ ምህረት በማፈን በገዛ ሃገራቸው የህሊና እስረኞች ሆነው እንዲኖሩ ኣድርጓል። “ህገ-መንግስታዊ ስራትና ህገ-መንግስቱን ለመጠበቅ” በሚል መፈክር ዜጎችን መኖሪያ ኣሳጥቷል። ቁጥራቸው ያልታወቁትን ጸረ-ሰላም፣ ጸረ-ልማትና ኣሸባሪ በማለት ገድሏል። በተለይም በኦሮሞ ወጣቶች፣ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች ላይ በማነጣጠር ኣድኖ ጨርሷቸዋል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትን በታወቁና ባልታወቁ የማሰቃያ ቦታዎች በማጎር ሰቆቃ ፈጽሞባቸዋል። ዛሬም ከምን ጊዜውም በላይ የኦሮሞ ተወላጆች በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢዎች በዚሁ መንግስታዊ ህገወጥ ቡድን እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ይህ ቡድን በ1997 ምርጫ የህዝቡን ድምጽ በኣደባባይ በመስረቁ ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ድምጻቸውን ለማስከበር ሰላማዊ ሰልፍ የውጡትን ከሁለት መቶ ያላነሱ የኣዲስ ኣበባ ወጣቶችን ያለ ምህረት በጥይት ደብድቦ ገድሏቸዋል። በወቅቱ በኦሮሚያ የተቋቋመው ኣጣሪ ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት መሰረት ወደ ኣርባ የሚጠጉ ስዎች በኦሮሚያ ተገድለዋል።

ያ ኣልበቃ ብሎት የጸረ-ሽብር ኣዋጅ በማውጣት ጭቆናን፣ የመልካም ኣስተዳደር እጦትን፣ የህግ የበላይነት መጣስን በኣጠቃላይ የመንግስታዊ ህገ-ወጥነትን የተቹትን ሁሉ ኣሸባሪዎች በማለት በእስር ቤቶች ኣጉሮ ይገኛል። ሙስሊም ኢትዮዽያውያን ህይማኖታቸውን በነጻነት ለማካሄድ እንዲችሉ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም በሰላማዊ መንገድ በመጠየቃቸው በርካቶች ተገድለዋል። ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከመንግስት ጋር ተነጋግረው ያለውን ችግር እንዲፈቱላቸው መርጦ የላካቸውን ሰዎችኣሸባሪዎች ናቸው ብሎ ድራማ በመስራት በሃሰት በመወንጀል ወህኒ ውስጥ ኣጉሯቸው በማሰቃየት ላይ ይገኛል።
ለዚህ ሁሉ ህገወጥነት የጠቀመው የኢትዮዽያን ህዝቦች ለመከፋፈል በመቻሉ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። በመከፋፈላችን ነጣጥሎ ኣጠቃን። ለጥቃት ያጋለጠንን ምክንያት በሚገባ እያወቅን መፍትሔ ለመፈለግ ዝግጁ ሳንሆን በመቅረታችን እነሆ የመንግስታዊው ቡድን ንቀት፣ ጭካኔና በደል እያንዳንዱን ቤት በማንኳኳት በሃገራችን ኑሮ ከሲኦል የከፋ ሆኖ ይገኛል። የዚህ መንግስት ንቀት ከመጠን እያለፈ ሂዶ ህዝብን ለዘመናት ከኖረበት በማፈናቀል መሬቱን በመቀማት ለውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች እየቸበቸበ ሚሊዮኖችን በማደህየት በልመና እንዲኖሩ ኣድርጓል።
ኣሁን ደግሞ “በኣዲስ ኣበባና በዙሪያው የሚገኙ ከተሞች የተቀናጀ ማስተር ፕላን” በሚል የቀሩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኣርሶ ኣደሮችን የሚያፈናቅል እቅድ ኣዘጋጅቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ህዝቡን ያላቀፈ፣ ከኑሮው የሚያፈናቅልና ለከፋ ድህነት የሚዳርግ ልማት ህገ-መንግስታዊ መብቱን የሚጻረር በመሆኑ መተግበር የለበትም በማለት ተቃውሞ ያነሱትን ሁሉ በመናቅ “ወደዳቹም ጠላችሁ ይተገበራል” የሚል መልስ በመስጠት እብሪተኛነቱን በዲጋሚ ኣረጋግጧል።
ባለፈው ኣመት በተለያዩ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ ተቃውሞ ያደረጉትን ያለርህራሄ ከ80 የማያንሱትን ተማሪዎችና ነዋሪዎችን በጥይት ቆላቸው።
በዚህም ኣመት ማስተር ፕላኑን ኣስመ ልክቶ ለተነሳው ጥያቄ ደንታ በማጣትና በንቀት የኦሮሚያ ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) በሚባለው ስብስብ ኣማካይነት ኣዋጅ በማውጣት የማስተር ፕላኑን እቅድ ተግባራዊ የማድረግ እንቅስቃሴውን ቀጠለበት። ከዚህም ሌላ በምእራብ ሸዋ ኣምቦ ኣካባቢ የሚገኘውንና ለዘመናት ሳይነካ ህዝቡ ጠብቆ ያኖረውን የጭልሞን የተፈጥሮ ደን ለባለ-ሃብት ሰጥቶ ለማውደም በመንቀሳቀሱ የኣካባቢው የኦሮሞ ተማሪዎች በኋላም ህዝቡን ጨምሮ ኣካሄዱን በሰላማዊ መንገድ በመቃወም ጥያቄ ለማቅረብ ኣደባባይ ወጡ። ለዚህም ኣምባገነኑና ህገወጡ መንግስታዊ ቡድን የሰጠው መልስ በጅምላ መግደልን ነው። በዚህም መሰረት በሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ምንም የማያውቁ የትምህርት ቤት ህጻናት ወሬ ለማየት የሚሯሯጡ ሳይቀሩ በጥይት ተቆልተዋል። እናትና ልጅ እቤታቸው ደጅ ላይ በጠላት ጥይት ተደብድበው ወድቀዋል። እርጉዝ እናት በሆዷ ከያዘችው ሽል ጋር በፋሽስቶች ጥይት ተግድላለች።
እስካሁን በተጠናቀረው መረጃ መሰረት ከ100 በላይ ተማሪዎችና ሌሎች የኦሮሞ ተወላጆችን በጥይት ግድሏል።
ተደጋግሞ እንደተነገረው ይህ መንግስት እንደልቡ እንዲፈነጭና ለህዝብ ያለው ንቀት ገደብ ያጣው እኛ ተገዢዎች በመከፋፈላችን ነው። ለሃያ ኣምስት ኣመታት በተናጠል ሲንገረፍ፣ ሲንገደልና እንደ በግ መንጋ ወደ እስር ቤት ሲንጋዝ የኖርነው በኣንድነት ቆመን በቃህ ለማለት ኣለመቻላችን ነው።
ከእንግዲህ እስካሁን የነበረው ሁኔታ መቀየር ኣለበት። ኣሁን ሁላችንም ኣንድ ላይ ሆነን ለነጻነት፣ ለእኩልነት ለሰላምና ለዲሞክራሲ በኦሮሚያና ኣማራ ክልል የተጀመረውን ትግል ኣጠናክረን መቀጠል ኣለብን። ሌላ ምርጫ የለም። ኣሁን የማያዳግም ትግል ተጀምሯል። የቀረው ነገር ቢኖር መላው የኢትዮዽያ ህዝቦችን ከዳር እስከዳር ማንቀሳቀስና በትግሉ እንዲሳተፍ ማድረግ ነው። የነብር ጭራ ኣይይዙም፣ ከያዙ ኣይለቁም ይላል የኣበው ምሳሌያው ኣነጋገር። የነብር ጭራ ይዘው ከለቀቁ የሚደርሰውን ኣደጋ ስለሚያውቁ ነው እንዲ ያሉት። እነዚህ ኣሁን ከፋፍለው የሚገዙን ነብር ናቸው ለማለት ኣይደለም። እነሱ ህጻናትና ሴት የሚገድሉ ፈሪዎች ናቸው። ተረቱን ያመጣሁት ኣንዴ ቆርጠው የገቡበትን የመብትና የነጻነት ትግል ከጀመሩ ዳር ሳያደርሱ መቆም ለጠላት ጊዜ መሰጠት ስለሆነ የድል ጊዜውን ስለሚያራዝም እንጠንቀቅ ለማለት ነው።
ትግሉ በሁሉም ኣካባቢዎች መቀጣጠል ያስፈልጋል። ይህን ጸረ-ህዝብ የወያኔ ቡድን በሁሉም ማእዘናት ፋታ መንሳትና ማጣደፍ ይገባል። ግፍና መከራን ተሸክሞ በውስጥ ማጉረምረምና መቃጠል ዋጋ የለውም።
ይህ በኦሮሚያ የተጀመረው ትግል የሁሉም ኢትዮዽያዊ የመብት ትግል መሆኑን ያለ ማመንታት ማመን ያስፈልጋል። በኢትዮዽያ የሚገኙ የሁሉም ዜጎች መብት እየተረገጠ፣ ዜጎች በገዛ ሃገራቸው በፍርሃትና በመሸማቀቅ የሚኖሩበት ጊዜ እንዲያበቃ ሁሉም ለመብቱ መታገል ኣለበት። በኢትዮዽያ ከህግና ከህዝብ በላይ ለሆነ ኣገዛዝ ኣንገዛም ማለት ኣለብን።
ትግሉ ዳር እንዲደርስ ከተፈለገ ለእውነተኛ የህዝቦች ነጻነት እንታገላለን ከሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚጠበቅ ትልቅ ሃላፊነት ኣለ። ትግሉ የተቀናጀ ካልሆነ ኪሳራውና መዘዙ ክፍተኛ ይሆናል። ኣሁን እንደታየው በኦሮሚያ የተጀመረው ሰላማዊ የመብት ጥያቄ በጀብደኛውና የህዝብ ጠ ላት የወያኔ ቡድን ወደ ደም ማፍሰስ ተሸጋግሮኣል። ይህ እንዲቆም የጋራ ትግል ኣስፈላጊ ብቻም ሳይሆን ታሪካዊ ሃላፊነት ነው።
ባለፈው ወር በመላው ኦሮሚያ የተቀጣጠለው የመብት ማስከበር ትግልን ለማዳፈን ገዢው መንግስት የወሰደው የግፍ እርምጃ መላውን የኢትዮዽያ ህዝብ ማስቆጣቱ ግልጽ ነው። በውጭም ሆነ በሃገር ውስጥ ያሉትና ኣምባገነኑን መንግስት ለማንበርከክ የሚታገሉት የፖለቲካ ድርጅቶችንም የትግላቸውን ኣካሄድ እንዲመረምሩ እንዳደረጋቸው ጥርጥር የለም። ለዚህም ያደረጉትን የትግል ትብብር ጥሪ ማየቱ በቂ ነው። ለምሳሌ የኦርሞ ዲሞክራቲክ ግንባር (ኦዲግ) ቀጥሎ የተመለከተውን የትብብር ጥሪ ኣስተላልፎኣል።
“እንግዲህ የዚያች አገር ጉዳይ ያገባኛል የሚል ማንኛዉም ግለሰብ፣ ድርጅትና ተቋም፤ በአጠቃላይ የሚያስብ አዕምሮ ያለዉ እያንዳንዱ ዜጋ «እስከመቼ ድረስ እየታሠርን፣ እየተደበደብን፣ ከገዛ አገራችን እየተሰደድን፣ ከምንም በላይ ደግሞ በግፍ እየተገደልን በዚህ የጥቂቶች አገዛዝ ሥር እንቀጥላለን?» ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት። ያለምንም ማጋነን የአገራችንና የሕዝቦቻችን መከራና ስቃይ ከልክ ያለፈ ሆኗል። ስለዚህ አንዱ ሕዝብ ሲጠቃ ሌላዉ ከሩቅ ሆኖ የማየት በሽታ ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልገዋል ብለን እናምናለን። ዘላቂ ሊሆን የሚችለዉ መፍትሔ ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዘንና ተደጋግፈን ለጋራ ድል በጋራ ሆነን መታገል ብቻ ነዉ” ይላል።
የኦርሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በበኩሉ “The OLF calls upon all Ethiopian to join the Oromo people struggle for freedom, democracy, justice & human rights, and once for all to dismantle the genocidal regime of TPLF. To that effect, the OLF calls for all inclusive struggle that include all political parties and civil organizations that will enable the Ethiopian people to decide their destiny by establishing government of people, for people and by people in Ethiopia.” ይህም በኣጭሩ ተባብረን ይህን የኣናሳና ገዳይ ቡድን ኣገዛዝ ኣሰወግደን በህዝብ፣ ለህዝብና የህዝብ መንግስት በኢትዮዽያ እንዲመሰረት የጋራ ትግል እናድርግ ነው።
የግንቦት ሰባት ኣርበኞች ግንባር መሪ ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋም ሁሉም ከያለበት ጥያቄውን እያነሳ ትግሉን መቀላቀል እንዳለበትና ከኦሮሞ ተማ ሪዎች ጎን እንዲቆሙና ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ትብብር ኣስፈላጊ መሆኑን ኣጽኖት ሰጥተው ጥሪ ኣቅርበዋል፣ በሃገር ውስጥም የሰማያዊ ፓርቲ ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ጋር በጋራ ለመ ስራት መስማማታቸው ታቋል። በጋራ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ለማ ድረግ ኣቅደው በእምቢተኛው ገዢ ቡድን ተከ ልክለዋል። የሰማያዊ ፓርቲ ኣባላትም የኦሮሞን ህዝብ ትግል ደገፋችሁ ተብለው መታሰራቸውን ሰምተናል።
ይህ ኣሁን የታየው የትብብር መንፈስ ወደ ላቀ ደረጃ ማደግ ኣለበት። ይህ የኣሁኑ የትብብር ጥሪ እንዲሁ በድንገት በተፈጠረው ወቅታዊ ጉዳይ ምክንያት የተከሰተ ኣይመስለኝም። ሁሉም ኣንዳችን ለኣንዳችን ኣስፈላጊዎች መሆ ናችንን በመገንዘብ የተደረገ ከልብ የመነጨ ነው ብዬ እገምታለሁ። ስለዚህ በኔ ግምት እስካሁን ድረስ እነዚህ ጥሪ ያደረጉ ድርጅቶች በጉዳዩ ላይ መነጋገር ጀምረዋል የሚል እምነት ኣለኝ። ካላደረጉ ያሳዝናል። ምክንያቱም ከዚህ በላይ የሚናባክን ጊዜ የለምና። ተባብረን በኣንድነት ካልቆምን በኢትዮዽያ ሃብት እስከ ኣፍንጫው የታጠቀውን ኣምባገነን ለማስወገድ የማይቻል ባይሆንም ብዙ መስዋእትነትን ያስከፍላል። ለዚህም ነው የጋራ ትግል ኣስፈላጊ የሚሆነው። በተግባር የማሳያው ጊዜ ኣሁን ነው። የዚህ መንግስት ገበናው ኣሁን ለሁሉም ለውጭም ሆነ ለውስጥ ይፋ ሆኗል። ይህ መንግስት የኢትዮዽያን ህዝቦች መብትና ነጻነት ረግጦ መቀጠል እንደማይችል ለሃያ ኣምስት ኣመታት ደግፈው ያቆዩት ጭምር ተገንዝበዋል። ኣሁን እያሰቡ ያሉት ማን ይተከዋል የሚለውን ነው። ጥያቄያቸው ተገቢና ማንም መጠየቅ ያለበት ነው። ስለዚህ የኢህአድግ መንግስት ከመውደቁ በፊት በሚገባ የተደራጀና መንግስታዊ ሃላፊነት የሚሸከም ድርጅት መኖሩ መረጋገጥ ኣለበት። ለህዝብ፣ በህዝብና የህዝብ መንግሥት ለመመሥረት የሚችል ሃይል መፈጠር ኣለበት።
እስካሁን ድረስ ጭራሽ መነጋገር የማንችል መስለን ኖረናል። ያተረፍነው ነገር ቢኖር ከፋፍሎን ለሚገዛን መመቸት ብቻ ነው። ኣሁንም ይህ ሃይል እንዳንቀራረብ ሌት ተቀን እንደሚሰራ ማወቅ ኣለብን። ይህ ኣሁን የተፈጠረውን መልካም ኣጋጣሚ ተጠቅመን ህዝባችንን ከሰቆቃ፣ ግዲያ፣ እስራትና ስደት ካላዳን ተጠያቂው እኛ እንጂ ገዢዉ መንግስት ኣለመሆኑን ማወቅ ኣለብን። ይህ ኣሁን የተደረገው የትብብር ጥሪ ወደ ተግባር ካልተቀየርና ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የተደረገ ሆኖ ከቀረ በታሪክ ፊት ተጠያቂ ከመሆንም ኣልፎ ኣሁን ህጻናት ልጆቻችንን በገፍ እየገደለ ካለው ገዳይ መንግስታዊ ቡድን ጋር ከመተባበር ተለይቶ ሊታይ ኣይችልም።
ለትብብር ጥሪው ተግባራዊነት የሚዲያዎች እገዛ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል የሚል እምነት ኣለኝ። በኦሮሚያ ተማሪዎችና ህዝቡ እያደረገ ያለውን የመብት ትግል ተከታትለው ለሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጪ ላሉት ኢትዮዽያውያንና ሌሎች በማሰራጨት በኩል ያደረጉት ስራ በጣሙን የሚያስመካ ሆኖ ታይቷል። የኢትዮዽያ ሳቴላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት)፣ ኦሮሞ ሚዲያ ነትዎርክ (OMN)፣ ገዳና (Gadaa.com) ኢትዮሚዲያ ድረገጾች እንዲሁም የተለያዩ ረዲዮ ጣቢያዎች የኣሜሪካ ድምጽ ኣማርኛና ኦሮሚኛ ፕሮግራሞችን ጨምሮ የሙያና የሀገር ግዴታቸውን ተወጥተዋል ለማለት ይቻላል።
ኣሁን የተጀመረውን የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የመተባበር ጥሪም ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ ጥረት ማድረግ ኣለባቸው የሚል እምነት ኣለኝ። ሶሻል ሚድያም የተጫወተው ሚና በጣሙን የሚደነቅ ነው።
ሚዲያ ሃገር ለመገንባትም ሆነ ለማፍረስ የሚችል ትልቅ ሃይል ነው። ባለፉት ኣመታት ህዝብን ከማቀራረብ ይልቅ የማራራቁ ስራ ጎልቶ ስታይ እንደነበር የሚካድ ኣይደለም። ኣሁን ግን ሰሞኑን እንደታየዉ ህዝቦችንም ሆኑ የተለያዩ የፖለቲካ ኣመለካከት ያላቸውን በማቀራረብ መርዳታቸዉን ኣጠናክረው መቀጠል ኣለባቸው። ሰዎች የመሰላቸውን ሃሳብ የመስጠት፣ የመጻፍና የመናገር መብት እንዳላቸው ቢታወቅም ኣሁን ኢትዮዽያ ባለችበት ሁኔታ ህዝብን ከህዝብ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያጋጩትን ሃሳቦች፣ ጽሁፎችና ኣስተያየቶች ከማስተናገድ መቆጠብ ኣለባቸው። እኛን ለያይቶን የኣገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም የሃገር ሃብትና ጉልበት የሚያባክነውን ጸረ-ህዝብ የሆነውን ኣምባገነን መንግስት በማጋለጥ ላይ በማተኮር ህዝቦቻችን የዚህ መሰሪ ቡድን ድርጊት ሰለባ እንዳይሆኑ ማስተማር፣ መምከርና የማቀራረብ ስራ በሰፊው እንዲሰሩ በበኩሌ ኣደራ እላለሁ።
በኣጠቃላይ ለነጻነት፣ ለእኩልነት፣ ለሰላምና ዲሞክራሲይዊ መብታችን መከበር የተጀመረው ትግል ከግቡ እንዲደርስና በጭካኔው ወደር የማይገኝለትን ጸረ-ሰላምና ኣሸባሪውን መንግስታዊ ቡድን ለማስወገድ የሃገሪቷ ህዝቦች ተባብረው ትግሉን ማፋፋም ኣለባቸው። በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች በኩል የቀረቡት የትብብር ጥያቄዎችና የመቀራረብ መንፈስም ለዘመናት ሰቆቃ ላልተለያቸው የኢትዮዽያ ህዝቦች ሲባል ተጠናክሮ ለኣንድ ኣስተማማኝ ውጤት እንዲበቃ ሁሉም መደገፍና ግፊት ማድረግ ኣለበት። የተባበረ ህዝባዊ ሃይል ምንጊዜም ኣሸናፊ ነው።
በቀለ ጅራታ:- የቀድሞ የኦፌዴን ዋና ጸሃፊ

No comments:

Post a Comment