ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ለመላዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የቀረበ የትግል አንድነት ጥሪ

December 18, 2015 | የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር


በአገራችን መዲና የገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖቻችንን ከመሬታቸዉ አፈናቅሎ ለአስከፊ ድህነት ብሎም ለጎዳና ተዳዳሪነት የዳረገዉንና የሚዳርገዉን፣ ጥቂት ባለጊዜዎችን፣ የሥርዓቱ ተጠቃሚዎችንና የዉጭ አገራት ባለሀብቶችን ግን የሚያበለፅገዉንና «የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ የጋራ የተቀናጀ ማስተር ፕላን» በሚል ስም የወጣዉን የድሆችን መሬት የመንጠቅ ጭካኔ የተመላበት መንግሥታዊ ዕቅድ በመቃወም በመላዉ ኦሮሚያ እየተካሄደ ያለዉ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሳምንታትን ከማስቆጠሩም በላይ ለብዙ ንፁሃን ዜጎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል። ሕዝባዊ ተቃዉሞዉ ተጠናክሮ እየተካሄደ ያለዉ በብዙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ቢሆንም የተቃዉሞዉ ምክንያት የሆነዉ ችግር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚነካዉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መብት የተነፈገዉን መላዉን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነዉ። ለዚህም ነዉ ይህ አሁን እየተካሄደ ያለዉ የኦሮሞ ሕዝብ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለእኩልነት፤ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለእዉነተኛ ዲሞክራሲ በአገሪቱ መስፈን ካደረጉትና አሁንም በተለያየ መንገድ እያደረጉ ካሉት ትግል ተነጥሎ የሚታይ መሆን የለበትም ብለን የምናምነዉ። በተለይም በፊንፊኔ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ዜጎችን የብሔር-ብሔረሰብ ስብጥር ግምት ዉስጥ ስናስገባ የማስተር ፕላን ተብዬዉ ዕቅድ መተግበር የሚጎዳዉ ኦሮሞዎችን ብቻ አለመሆኑን እንረዳለን። ይህ ደግሞ የተቀጣጠለዉ ትግል የኦሮሞ ሕዝብ የተናጠል ትግል ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዉያን የጋራ ትግል መሆን እንዳለበት ያመለክታል።

ነገር ግን ትግሉ የጋራ ሳይሆን ቀርቶ ትናንት በጋምቤላ፣ በኦጋዴን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በአማራ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልሎች ተቀጣጥለዉ የነበሩ የመብት ጥያቄዎች በጠመንጃ ኃይል ሲታፈኑና ንፁሃን ዜጎች በግፍ ሲገደሉ ጥያቄዎቻቸዉ የእኛም ጥያቄዎች እንደሆኑ አምነን ከጎናቸዉ ሆነን አብረን መታገል ሲገባን የሌላዉ ሕዝብ ጥያቄ አይመለከተንም የማለትን ያህል ከሩቅ ሆነን መመልከትን የምንመርጥ ከሆነ ለዚህ የጭቆና፣ የአፈናና የግፍ አገዛዝ የተመቻቸን እንሆናለን። በስልጣን ላይ ያለዉ ቡድንም የሕዝብን ጥያቄዎች በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ በመሣሪያ ኃይል ማፈንን አጠናክሮ ይቀጥላል። አሁን እየተካሄደ ላለዉ የኦሮሞ ሕዝብ ፍፁም ሰላማዊ የሆነ ጥያቄ እየተሰጠ ያለዉም መልስ እስከ ዛሬ ካየናቸዉ የሥርዓቱ ጭፍን አቀራረቦች የተለየ ሆኖ አላገኘነዉም።
እንግዲህ የዚያች አገር ጉዳይ ያገባኛል የሚል ማንኛዉም ግለሰብ፣ ድርጅትና ተቋም፤ በአጠቃላይ የሚያስብ አዕምሮ ያለዉ እያንዳንዱ ዜጋ «እስከመቼ ድረስ እየታሠርን፣ እየተደበደብን፣ ከገዛ አገራችን እየተሰደድን፣ ከምንም በላይ ደግሞ በግፍ እየተገደልን በዚህ የጥቂቶች አገዛዝ ሥር እንቀጥላለን?» ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት። ያለምንም ማጋነን የአገራችንና የሕዝቦቻችን መከራና ስቃይ ከልክ ያለፈ ሆኗል። ስለዚህ አንዱ ሕዝብ ሲጠቃ ሌላዉ ከሩቅ ሆኖ የማየት በሽታ ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልገዋል ብለን እናምናለን። ዘላቂ ሊሆን የሚችለዉ መፍትሔ ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዘንና ተደጋግፈን ለጋራ ድል በጋራ ሆነን መታገል ብቻ ነዉ። ምክንያቱም በጋራ ትግል ከሚገኙት ድሎች ሕዝቦቻችን የጋራ ተጠቃሚ ከመሆናቸዉም በላይ ድሉን ተከትሎ የሚመጣዉ የፖለቲካ ሥርዓትም እንደ ዛሬዉ ሕወሐት-መራሽ የኢህአዴግ ሥርዓት ትዕቢተኛና አንባገነን ሥርዓት ሳይሆን ለሁሉም ሕዝቦች እኩል የሚቆምና ሁሉንም በእኩልነት የሚያገለግል ሚዛናዊ የፖለቲካ ሥርዓት እንደሚሆን ስለምናምን ነዉ።
ስለሆነም እዉነተኛ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነት፣ ዕድገትና ብልፅግና የሰፈነባት፣ ለጥቂት ባለጊዜዎች ገነት ለብዙሃን ዜጎቿ ግን ሲዖል ያልሆነችና ሁላችንም በመከባበርና በመፈቃቀር በጋራ የምንኖርባት፤ ብሎም ለተተኪዉ ትዉልድ በኩራት የምናስረክባት የጋራ አገር እንዲኖረን የምንፈልግ ወገኖች ሁሉ በዘር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በትዉልድ አካባቢም ሆነ በፖለቲካ አመለካከት ሳንለያይ አንድ ላይ ሆነን በኦሮሞ ሕዝብ የተጀመረዉንና ተጠናክሮ የቀጠለዉን ሕዝባዊ ትግል ከግብ እንድናደርስ የትግል አንድነት ጥሪያችንን ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች እናቀርባለን።
በዚህ አጋጣሚም ገዢዉ ቡድን የከፋፍሎ መግዛት ፖሊሲዉን መሠረት በማድረግ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት፣ በተለይም የኦሮሞና የአማራ ብሔሮችን እጅግ በረቀቀ መንገድ አጋጭቶ የገዢነት ዕድሜዉን ለማራዘም፣ የጀመረዉን የተንኮል አካሄድ ተረድቶ ሕዝባችን በጥቂት ገዢዎች ሴራ ሳይነጣጠል አብሮ በመሆን የጋራ አገሩን፣ ነፃነቱን፣ የዜግነት መብቱንና ከምንም በላይ ደግሞ ያልተሸራረፈ ሰብዓዊ መብቱን ለማስከበር በአንድነት ጠንክሮ እንዲታገል አበክረን እናሳስባለን።
ፍትህ፣ ነፃነትና እኩልነት ለሁሉም ሕዝቦች!!
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር

No comments:

Post a Comment