ማስተር ፕላኑ ወደፊት እንደሚተገበር ሚሚ ስብሃቱ ገለጹ

January 21, 2016 | ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ

ሚሚ ስብሃቱ
በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረው ግርግር እና ሁከት እኛ ባለን መረጃ መሰረት እ እ እ … ዛሬ ጠዋትም በቅርቡ የተለያዩ አካባቢዎች ደዉለን ስናጣራ ነበረ፤ እ እ እ … የመማር ማስተማር ሂደቱ ቀጥሏል እ እ እ … ከአለፈው ሳምንት ወዲህ ሰላም መስፈኑንና የተረጋጋ … ይበልጥ እየተረጋጋ መሄዱን በተለያዩ የማጣራት ሂደቶች አጣርተናል፡፡”
ነገር ግን አሉ ሚሚ ቆምጨጭ ባለ ድምጸት፤
“ነገር ግን ይሄ ጉዳይ ደግሞ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ወገኖች አሁንም ዉሸትና አሉባልታ ከማራገብ አልታቀቡም፡፡ በተለያዩ በሚጠቀሙባቸው መገናኛ ብዙሃን በማኅበራዊ ድህረገጾች የሌላ አገር፣ በአገራችን ሳይሆን በሌላ አገር የተፈጠሩ ሁኔታዎችን ፎቶግራፍ የተነሱ ነገሮችን ፖስት እያደረጉ አሁንም ህብረተሰቡን ለማደናገር እና እንትን ለማለት እ እ እ… መሯሯጡ ተጧጡፏል፡፡ እ እ እ … አንዳንዶቹ ከፍተኛ ብስጭት ዉስጥ ወድቀዋል ሁኔታዎች በመረጋጋታቸው፡፡”

እዚህ ላይ እርሳቸው እራሳቸው በስጨት ወደ ማለት ሄደዋል፡፡ ቀጠሉ እትየ ሚሚ

“እ እ እ … ከዛ ደግሞ፤ ተከትሎ ደግሞ፤ የክልሉ መንግስትና የክልሉ ገዢ ፓርቲ ይሄ ችግር ነው ተብሎ የተነሳው ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ላልተወሰነ ግዜ መቋረጡን፤ ይሄ ጉዳይ ህዝቡ ሙሉ በሙሉ እንዲነጋገርበት እና እንዲወስንበት ብሎ ደግሞ እ እ እ … መግለጫ መስጠቱና ዉሳኔዎችን ማሳለፉ ምንጣፉን ከስራቸው ዉስጥ እንደጎተተው ያህል ነው፡፡ ጥሏቸዋል፡፡”
uወዳጄ እንዴት ነው ነገሩ? እኛ እኮ ሙሉ ለሙሉ ቆመ ሲባል ነገርየው ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜም እንዳይነሳ ሆኖ ሊቆም ይችላል ብለው አባዱላ እዚቸው ክብ ጠረጴዛ ላይ ባስታወቁት መሰረት መስሎን ነበር፡፡
እትየ ሚሚ ግን ለጊዜው ቆም ብሎ ወደፊት ሊቀጥል ነው በማለት ሲፈሩ የነበሩ ሰዎችን ስጋት ልክ እንደሆነ በክቡ ጠረጴዛቸው ላይ እያረጋገጡልን ነው፡፡ በርግጥ አባዱላም በዕለቱ ያን መልዕክት አስተላልፈው ሲሄዱ፤ እንዴት ነው እሱ ፕላኑን ለማስጠናት ይሄን ያክል ወጪ ወጦ፤ ከፈረንሳዩዋ ማንትስየ ከተማ ተኮርጆ፤ ይቅር የሚባለው? እያሉ አባዱላን ሳይቀር ሲወርፉዋቸው ነበር፡፡
እትየ ሚሚ ንግግሯቸው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
“በዚያች ላይ ነበር የተንጠለጠሉት፡፡ ተገቢ በሆነችው የህዝብ ጥያቄ ላይ ተንጠላጥለው ነበር፡፡ ግን አሁንም እየተገፋ ያለው ይሄ ሂደት ህዝቡ እንዲተላለቅ ሁከቱ እንዲቀጥል እሳት የማቀጣጠል ስራ ነው እያየን ያለነው በአንዳንድ አካባቢዎች”
ከዛ “ፀጋ!” ስሙ ይጠራል፡፡
ፀጋም አቤት እትየ እንደማለት እየቃጣው የትየ ሚሚን ሃሳብ ለማጠናከር ጉሮሮውን ስሎ ይነሳል፡-
በነገራችን ላይ በትምህርተ ጥቅስ ዉስጥ ያስቀመጥኩላችሁ የክቧን ጋዜጠኞች ንግግር ቃል በቃል በመውሰድ ነው፡፡
“እንግዴ ያው በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው … ” የሚለውን የተለመደ የመግቢያ ሃረግ አስረዝሞ ካነበነበ በኋላ፤
“ህዝቡ የራሱ ልማት እና እድገት ነውና እየተጎዳና እየተደናቀፈ ያለው ይህንን ጸረ ልማት የሆነ ተግባር የሚፈጽሙትን አካላት አሁንም ሊታገላቸው ሊያጋልጣቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ” የሚለውን ሌላ ሰሞነኛ ሃረግ አስከትሎ (ይታያችሁ እንግዴህ፤ ጥያቄው ተገቢ የህዝብ ጥያቄ ነው ብለው እንደጨረሱ እኮ ነው ይሄ ሁሉ ፍረጃ እና ዉንጀላ ህዝብ ላይ ተመልሶ የሚዥጎደጎደው)
“ብዙም ሚዲያ አልተከታተልኩም ሰሞኑን ስራ ላይ ስለነበርኩ” የሚል አከለበት፡፡ ነገር ግን ብሎ የተነሳበትን የአለቃውን ሃሳብ ያለቅድመ ሁኔታ የማራገብ ስራን መተወኑን ተያያዘው፤
“ከዚህ በኋላ የጋራ ልማት ይኖራል፡፡ ወደፊት መልማታችን አይቀርም፡፡ ሁላችንም ከድህነት ለመውጣት እየተሯሯጥን ነው፡፡ ይሄ ገና ውይይት የሚደረግበት የረጅም ግዜ ጉዳይ ነው፡፡”
በማለት ይሄ የተቀናጀ የጋራ ፕላን ተብየው ወደፊት ወደድንም ጠላንም መተግበሩ እንደማይቀር ነግሮን ንግግሩን ቋጨ፡፡ ወዳጄ? እነዚህ ሰዎች የመንግስት ደጋፊዎች ናቸው እየተባሉ የሚታሙት ዉሸት ነበር እንዴ? ይህን ነገር ሌሎች የግል ሚዲያዎች ቢናገሩት እኮ “ለህብረተሰቡ የተሳሳተ አሉባልታን በማናፈስ፤ ውዥንብር ዉስጥ የከተቱ” የሚባለው ክስ ይከታተልባቸውም አልነበር እንዴ? ተመስገን ደሳለኝ ከተከሰሰባቸው ጉዳዮች አንዱ “የህብረተሰቡን አስተሳሰብ በማናወጥ” የሚል መሆኑ ትዝ አሎት አይደል?
እትየ ሚሚ ፀጋን ተቀብለው እራሳቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በማውራት ላይ ናቸው፤
“በሌላ በኩል ግን፤ በአጭሩ ግን፤ እንዲህ አይነት ነገር ሁለተኛ እንዳይደገም! (እዚህች ላይ ቁጣና ግልምጫ ድምጸቷ ዉስጥ ይታይበታል) ጥያቄ እንኳን ቢኖር በእንደዚህ አይነት መንገድ አይደለም መቅረብ ያለበት፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታ እንዲኖር ያደረጉ ወገኖች አሉ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች መፈለግ አለባቸው፡፡ ዝምብሎ ብቻ የዉጪ ሃይል፤ ዝምብሎ ብቻ እንትን ነው እየተባል አይደለም፡፡ በትክክል እነማን ናቸው የሚለውም ነገር አንደኛው የመፍትሄው አካልና ሁለተኛ ዳግም እንደዚህ አይነት ነገር (አሁንም ሌላ የማመናጨቅ ድምጸት) እንዳይከሰት የሚደረግበት ነገር ሊሆን ይገባዋል፡፡” የሚል ግልምጫና ምንጭቂያ የታከለበት ማስፈራሪያን አስከተሉ፡፡
“መሰረት ሰአታችን እየተጠናቀቀ ነው አንድ ሁለት ደቂቃ አለህ” በሚል ለመሰረት አየሩን ለቀቁለት (ለቀቁበት አላልኩም)
እ እ እ … ብሎ ጉሮሮውን ከጠረገ በኋላ
“የኦሮሚያ ክልል ችግር ቅድም እንዳልሽው በክልሉ ገዚ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዉሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡ የመአከላዊ ኮሚቴው ዞሮ ዞሮ ባብዛኛው የመንግስት አስፈጻሚዎች ያሉበት ስለሆነ ባብዛኞቹ ዉሳኔውን መንግስትም ተቀብሎ እንደሚፈጽመው ምንም ጥያቄ የለዉም ብለን እንገምታለን፤ የክልሉ መንግስት፡፡ ስለዚህ መልካም ነገር ነው፡፡”
በሚል ንግግሩን ከፈተ፡፡ ቀጥሎም “ባለፈውም እኛ ተናግረናል ይሄ የህዝብ ጥያቄ ይህ ህዝብ ካልፈለገው እስከሚፈልገው ድረስ ባነበረበት እንዲቆም ማድረጉ የግድ ተገቢ መሆኑን ስንነጋገር ነብር፡፡ ይሄ ማለት ግን ያ ልማት ልማታዊ እንጂ — አይደለም ብሎ መገምገም እንዳልሆነ ህዝብም ማወቅ አለበት፡፡
“ማለት አንዳንድ ወገኖች አሁን፤ በተለይ ተቃዋሚ የሚባሉ ወገኖች በቃ በአጠቃላይ መጀመሪያ መቆሙን ነው የሚፈልጉት ያለው፤ መቆሙን ግን ዉጤት እንዲያመጣላቸው ይፈልጋሉ፤ የራሱ ዉጤት፡፡ ማለት ሲቆም ሌላ ምስቅልቅል ነገር እንዲፈጠርና በቃ የሆነ ዉዝግብ እንዲነሳ ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ አሁንም ህዝብን እየቀሰቀሱ ነው ያሉት፡፡ ዉሳኔውን የሚያጣጥሉ ወገኖች አሉ አሁንም፡፡ ስለዚህ ያ እንተን ምንድን ነው መነሻው ስትይ፤ ቅንነትም የጎደለው መነሻ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ የህዝብ በተለይም ደግሞ የአስ… ወጣቶች፤ ብዙ የማያገናዝቡ ልጆች እዛ በተለያየ ምክንያት ገብተው ህይወታቸውን እንዳያጡ ጥሩ መከላከያ ጥሩ መገደብያ ነው፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ግን ምንም ነገር ሊቀጥል አይገባም በዚያ መንገድ፡፡ በቃ ጥይቄው ይህ ከሆነ፤ ይህ ጥያቄ ተፈትዋል፡፡”
ይሄ ሰውየ ዞሮ ዞሮ ካላለ ያወራ አይመስለውም፡፡ እሱ ዞሮ ዞሮ ሲል እኔ ዞር ዞር ብሎ መምጣት ያምረኛል፡፡ ሃ ሃ! ዞሮ ዞሮ ታድያ የትየ ሚሚን ለጊዜው ቆመ እንጂ ለወደፊቱ መምጣቱ አይቀርምን ሃሳብ በሚከተለው መልኩ አጠናክሮታል፡፡
“በሌላ ጊዚያት ደግሞ ህዝቡ እራሱ ጥያቄ ያነሳል፡፡ ልልማ ይላል፡፡ አብረን እንልማ ይላል፡፡ ያኔ … (የሆነ የማይሰማ ቃል) ይደረጋል፡፡ አለዛ አሁንም ሌላ ነገር እናደርጋለን የሚሉ ከሆነ፤ አሁንም እንደዚህ አይነት ነገር የሚሉ ከሆነ ሌላ ነው ምክንያቱ ማለት ነው፡፡”
ታዲያ እንዴት ነው ነገሩ? የዛሬ የክቧ ጠረጴዛ ውሎ የኦህዴድን የስራ አስፈጻሚዎች መግለጫ ማስተባበል ነው እንዴ?
መሰረት ንግግሩን ቀጥሏል፤
“ፍላጎታቸውም ሌላ ነው፡፡ ህዝቡም ባለፈው እንደተነጋገርነው የኦሮሚያ ህዝብ ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ፣ መላው ኢትዮጵያ ጥያቄ ነው የሚሆነው፡፡ ጥያቄውን ህዝቡን በጋራ ይመለከተዋል፡፡ መንግስትም በዚህ ጉዳይ ላይ ሲሪየስ የሆነ አቋም ሊወስድ የሚገባበት ሁኔት ይኖራል ብየ አስባለሁ፡፡”
እዚህ ላይ ደግሞ አቶ መሰረት ጥያቄውን ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ይዘው ይነሱ የሚል ይመስላል፡፡ ወይንስ የኦሮሞ ጥያቄ የሌሎችም ኢትዮጵያውያንን ጥያቄን የሚጠይቅ ከሆነ “አይ ይህማ ያንተ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ችግር ነው፤ ዝምበል!” ሊባል ነው፡፡
መሰረት ከላይ ምን ለማለት እንደፈለገ ግልጽ ባይሆንም እሱ መናገር ቀጥሏል፤
“አሁን ይሄኛው እየፈለጉ ያሉት አንዳንድ ተቃዋሚዎች አልበረደም ምናምን ሲሉ ተስሚያለሽ፡፡ ነገር ግን በኔ ባለሁበትም አካባቢ አሁን ምንም ጸጥ እረጭ ያለ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ምንድን ነው የሚወራው? እኛ ያለንበት ሳንናገር ከሌላ ቦታ ወሬ መጦ ትሰሚያለሽ፡፡ አሁንም አለ! አሁንም ተማሪዎች አልገቡም፡፡ አሁንም ግርግር አለ። አሁንም ብለው የሚያስወሩ ወገኖች አሉ፡፡ ያ የሚፈልጉት ምንድነው? እንዲቀጥል ስለሚፈልጉ ነው፡፡ አላማ ካላቸው አላማዉን በዚህ መንገድ ለማስቀጠል ስለሚፈልጉ ነው፡፡ …… ተጠያቂ መሆን አለባቸው በይሉኝታ እየታለፈ ዝም መባል የለበትም …”
ወዳጄ አልደከሞትም፡፡ እኔ እራሱ እጅ እጅ አለኝ፡፡
“የተከበራችሁ አድማጮቻችን የዛሬ የክብ ጠረጴዛ ሰአታችን (ውሸታችን) ተጠናቋል፤ ስላዳመጣችሁን እናመሰግናለን” አሉ ሴትየዋ በመጨረሻ፡፡
እነዚህ ይክብ ጠረጴዛ ጉዶች ግን አሁን እንደዚህ በየመንገዱና በየከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ህይወቱን ነፍጥ ባነገቱ ጉልበተኞች ከሚነጠቀው ዉስጥ አንዱ የእነርሱ ልጅ ቢሆን፤ አይ ሁሉም ሰላም ነው! የሚሰማው ወሬ ሁሉ ዉሸት ነው! የመማር ማስተማሩ ሂደት በተረጋጋ ሁኔታ ቀጥሏል ይሉን ይሆን?
ቸር እንሰንብት!
እውነት ከምድርቤት
ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment