ፊንፊኔ – የኦሮምያ ክልልና የፌዴራል ዋና ከተማ፤ ያስከተለው ችግርና መፍትሄው (ለውይይት መነሻ)

July 10, 2017 | በባይሳ  ዋቅ-ወያ *
Finfinnee City, Google Map, July 9, 2017

ለዚህ አጭር ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን ኢህአዴግ “የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ ላይ ያላት ልዩ ጥቅም” ብሎ ያወጣውን ረቂቅ ዓዋጅ አስከትሎ ከያቅጣጫው የተነሱትን የድጋፍና ባብዛኛው ግን የተቃውሞ ድምፅ በጥሞና ካዳመጥኩ በኋላ ነው። ዕውነቱን ለመናገር ምናልባት የኦህዴድን ጎራ አላውቅም እንጂ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኦሮሞ ፖሊቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ ዓዋጁን ተቃውሞታል ብል የተጋነነ አይመስለኝም። ኦሮሞ ያልሆኑቱ “ከተማዋ የፌዴራሉ መቀመጫ ስለሆነችና ያገሪቷን ብሄርና ብሄረሰቦች በሙሉ በእኩልነት በማስተናገድ ከመቶ ዓመት በላይ የኖረች ስለሆነች፤ ለኦሮሞዎች ብቻ ተለይቶ ለምን ልዩ ጥቅም አስፈለገ” ብለው ምሬታቸውን ሲገልጹ፤ ኦሮሞዎችም በበኩላቸው፤ ፊንፊኔ የኦሮሞ ምድር ዕምብርት በመሆኗ ጥያቄው የባለቤትነት ጉዳይ ነው እንጂ ከሌሎች የከተማዋ ኗሪዎች የተለየ ለኦሮሞዎች ብቻ የተመደበ ልዩ ጥቅም አልጠየቅንም፤ አያስፈልጋትምም” ይላሉ። ታዲያ “ልዩ ጥቅም” የሚለው ቅርጸ-ቢስ አንቀጽ ባገሪቷ ሕገ መንግሥት ከተካተተ ከሃያ ዓመት በኋላ ዛሬ ምን ልዩ ነገረ ተፈጠረና ነው ኢህአዴግ ይህንን ረቂቅ ዓዋጅ ለመደንገገ የተነሳው? እያንዳንዳችን የየራሳችንን መልስ በልባችን እንደያዝን እንቆይና በግሌ ግልጽ ሆኖ መቀመጥ ስላለበት ስለ ፊንፊኔ ከተማ የዛሬና የወደፊት ዕጣ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ጋር ሊኖራት ይገባል ብዬ የማስበውንና ከዚያም ባሻገር አገሪቷ ትክክለኛ የሆነ ፌዴራላዊ አስተዳደር ያስፈልጋታል የሚለውን አቋሜን ጉዳዩ ከሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን ጋር ለመወያየት ያህል ይህንን “ለውይይት መነሻ” የሚሆን ጽሁፍ ለማቅረብ ፈለግሁ።
ፊንፊኔ እንደማንኛውም በዓለማችን ላይ እንደሚገኙት ከተሞች የራሷ የሆነ የአፈጣጠር ታሪክ አላት። ታሪክ ደግሞ ማንም ሊቀይስለት የማይችልና ተከትሎት የሚሄደው የራሱ የሆነ ቦይ ስላለውና ለወደፊትም ደግሞ እንዲሁ በራሱ ፈቃድ የራሱን ቦይ ተከትሎ የሚሄድ እንጂ በኛ የማይታዘዝ በመሆኑ፤ ስለ ፊንፊኔ የወደፊት ዕጣ ስናወሳ ይህንን የታሪክ ሂደት ከወድሁ ማጤን ያለብን ይመስለኛል። ይህንን ጭፍን ሃሳብ እስቲ ባጭሩ ላብራራ።
በታሪኩ መሰረት የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ዓፄ ምኒልክ ግዛታቸውን ወደ ደቡብ ያስፋፉ በነበረበት ዘመን እቴጌ ጣይቱ አንድ ቀን እንጦጦ ላይ ቆመው የመሬቱ ባለቤቶች ማለትም ኦሮሞዎች ከብቶቻቸውን ሆራ ያጠጡበት የነበረውን የፊንፊኔን ረባዳ የጠበል መሬት ከታች አይተው ቦታው ልባቸውን ስለማረከ ዋና ከተማዬ አንኮበር መሆኑ ቀርቶ እዚህ ይሆናል ብለው ወሰኑ ተብሎ ይነገራል። አዲስ አበባ የሚለውን ስም ያወጡላትም እቴጌይቱ ናቸው ይባላል። ታድያ ቦታውን ለመውሰድ ምኒልክ ከባለቤቶቹ ጋር መደራደር አስፈላጊ መስሎ አልታየውም። እንደተለመደው በጉልበት ለመያዝ ጦሩን አሰልፎ ወጋቸው። የተቃወሙትን ባለመሬቶች በሙሉ ፈጃቸው፤ ቤታቸውን አቃጠለ፤ ከብቶቻቸውን ዘረፈ። ከግድያ የተረፉት ደግሞ ከፊንፊኔ ለቅቀው በዙርያዋ ወደሚገኙ መንደሮች ተሰደዱ። ዛሬ በኢንቬስትሜንት ሳቢያ ከቄያቸው በመፈናቀል ላይ ያሉት ኦሮሞዎች አያት ወይም ቅድመ-አያት መሆናቸው ነው። አንድ በቦታው የነበረና ሁኔታውን በቅርብ ሲከታተል የነበረ ክራፕፍ የተባለ የፕሮቴስታንት ወንጌላዊ “journals of  Krapf and Isenberg” በሚል ርዕስ በፈረንጆች አቆጣጠር ጥር 25 ቀን 1840 ዓ/ም ይህንን የምኒልክ ድርጊት እንዲህ ብሎ ነበር የጻፈው፤
…… we commenced our march this morning about nine o’clock proceeding south, south-west through the territory of the tribe Jumbitcho….about two o’clock we encamped in a plain called Sululta…..The Gallas in the neighboring mountains are called Sululta Gallas. Their neighbors in the south east are called Finfinnee Gallas, from the high mountains of the same denomination. As the Gallas did not pay their tribute in horses and cows, the King gave orders for all their villages to be destroyed by fire. I did not care much to know the names of the Galla villages as they are destroyed almost on every expedition. The soldiers take all they can get in the houses and then burn them.
ተጨማሪ ማብራርያ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። ስለዛሬዋ የፊንፊኔ ሕጋዊ ባለቤትነት ስናወራ የጠራና ቅንነት የተሞላበት አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል ብዬ እገምታለሁ።
ሁላችንም እንደምናውቀው ፊንፊኔ ዛሬ ከሞላ ጎደል ባገሪቷ የሚገኙትን ከሰማንያ የማያንሱ ብሄረሰብ አባላትን በኩልነት የምታስተናግድ፤ የመሬቱ ባለቤቶች ማለትም ኦሮሞዎች ግን ከሃያ በመቶ በታች የሆኑባት፤ የኦሮሚያና የፌደራሉ ዋና ከተማ ከመሆኗም በላይ ለአፍሪቃ አንድነትና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መቀመጫ ሆና የምታገለግል ያገሪቷ የኤኮኖሚ እምብርት ናት። ይህ እንግዲህ በጎም ሆነ ክፉ የፊንፊኔ አመሰራረት ታሪክና ዛሬ ያለችበት ሁኔታ ነው። ከቁጥር አንጻር ሲታይ ከሃያ በመቶ በታች ቢሆኑም የባለቤትነት ጥያቄ ተብሎ በኦሮሞዎች ሁሌ የሚነሳው አግባብ ያለው ጥያቄም ከዚህ የፊንፊኔ አፈጣጠር ጋር የተያያዘ ነው ማለት ነው።
ፊንፊኔን የመሳሰሉ፤ ሙሉ በሙሉም ባይሆን ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ታሪካዊ አመጣጥ ያላቸው በጣም ብዙ የሆኑ ዋና ከተሞች ባለማችን ይገኛሉ። ከነዚህ መሃል ግን ለብዙ ኢትዮጵያውያን በጣም ቅርብ የሆነችዋንና ከኢትዮጵያ ውጪ ለብዙ ዜጎቻችን መኖርያ ሆና የምታገለግለዋን ዋሺንግተን ዲሲን ለማነጻጸር ያህል ባቀርብ የውይይታችንን ይዘት ብሩህ የሚያደርገው ይመስለኛል።  (እንዲታወቅልኝ የምፈልገው ግን የሚመሳሰሉበትን አንድ የድንበር ጉዳይ አንስቼ ለማወዳደር ብዬ ነው እንጂ ካፈጣጠራቸው ጀምሮ በሁለቱ መሃል ትልቅ ልዩነት አለ። ዲሲ የተቋቋመችው በፈቃደኝነት በሥጦታ በተሰጠ መሬት ላይ ሲሆን ፊንፊኔ ግን ከህጋዊ ባለቤቶችዋ በጉልበት ተነጥቃ ነው።)
የተባበሩት የአሜሪካ መንግሥታት (States) በሕገ-መንግሥታቸው ውስጥ በስምምነት እንዳስቀመጡት ያገሪቷ ፌዴራላዊ መንግሥት መቀመጫ የሚሆን ከመንግሥታት በነጻ በሚሰጠው ስፋቱ አሥር ስኩዌር ማይል (ማለትም አሥራ ስድስት ስኩዌር ኪሎ ሜትር) በማይበልጥ ቦታ ላይ ይመሰረታል ይላል። በሰሜንና በደቡብ መንግሥታት (ስቴቶች) መካከል ይከሰት በነበረው አለመስማማትና ብሎም አለመተማመን የተባበሩትን የአሜሪካ መንግሥታት ዋና ከተማ የት ቦታ ላይ እንደሚቋቋም ለብዙ ጊዜ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በ 1800 ዓመተ ምህረት የቪርጂንያና ሜሪላንድ ስቴቶች (ድንግላዊት እና ሃገረ ማርያም ይሏቸዋል ሐበሾች) በፈቃዳቸው ከግዛታቸው ቆርሰው ላገሪቷ ዋና ከተማና የመንግሥት መቀመጫ እንዲሆን በሰጡት በጠቅላላው አሥር ስኩዌር ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ፓቶምኪን ወንዝ አካባቢ ባለው መሬት ላይ ተመሰረተች። ዋና ከተማውም ከፊላዴልፊያ ወደ ዲሲ (ዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ) ተዛወረ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዋሺንግቶን ዲሲ ነዋሪዎችን የዜግነት መብት በተመለከተ ብዙ አዎንታዊና አሉታዊ ለውጦች በየጊዜው ቢደረጉም፤ የዲሲ ድንበር ያኔ ከሶስት መቶ ዓመት በፊት ከተከለለላት ድንበር ውጪ አንዲትም ስኩዌር ሜትር አልጨመረም አልቀነሰም። ከተማዋ ግን “ዲሲ ሜትሮ” በመባል የሚታወቀው በሁሉም አቅጣጫ ወደ ቪርጂንያና ሜሪላንድ ስቴቶች ሰፍታ ተስፋፍታ በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎችና መጤዎች መኖርያ ሆና እያገለገለች ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ከአሥር ስኩዌር ኪሎሜትር ውጭ ባሻገር የሰፋውን የዲሲን ከተማ አካል የሚያስተዳድሩት የቪርጂንያና የሜሪላንድ ስቴት መንግሥታት እንጂ የዲሲ አስተዳደር ወይም የፈደራሉ መንግሥት አይደለም። በሰፋውና የዲሲ ተቀጽላ በሆነው “ዲሲ ሜትሮ” የሚኖሩ ዜጎችም ግብር የሚከፍሉትም ሆነ በኮንግረስና በሴኔት ተወካዮቻቸውን የሚመመርጡት እንደ ቪርጂንያና ሜሪላንድ ስቴት ኗሪዎች እንጂ እንደ ዲሲ ነዋሪ አይደለም።
ወደ ዋናው አርዕስታችን ወደ ፊንፊኔ ጉዳይ ስንመለስ፤  ከላይ ባጭሩ ያስቀመጥኩት የዲሲ ታሪካዊ አመሰራረትና የዛሬዋ ሁኔታ ፊንፊኔን አስመልክቶ ኦሮሞዎች ያለመታከት ለሚያቀርቡት የባለቤትነት ጥያቄና መንግሥትም “የኦሮምያ ክልል በፊንፊኔ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም” በማለት በቅርቡ በየአደባባዩ መለፍለፍ ለጀመረበት ጉዳይ፤ ጥሩ መንደርደርያ ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ለሁሉም የፊንፊኔ ኗሪ ዜጎችም ሆነ ለኦሮሚያ ክልል አስተዳደር የሚያመችና አጥጋቢ የሆነ በድርድር ላይ የተመሰረተ ድምዳሜ ላይ እንደሚያደርስ ዕሙን ነኝ።
በኔ ግምት ከፊንፊኔ የባለቤትነት ጥያቄ ባሻገር ያለው ትልቁ ችግር ባገሪቷ የፌዴራላዊ አስተዳደር ቅርጽና ይዘት ላይ ነው።እንደ ኢትዮጵያ ባሉት በጣም ብዙ የሆኑ ብሄረሰቦችን ያቀፈችና በተለይም ብሄረሰቦቹ በያሉበት የተፈጥሮያዊ ክልል ውስጥ ባንድ ላይ የሚኖሩና ባህላቸውና ቋንቋቸው ልዩ የሆነ ግን ደግሞ በፈቃደኝነትም ባይሆን ላለፉት መቶ ዓመታት ባንድ ማዕከላዊ አስተዳደር ሥር የነበሩትን ብሄረሰቦች መብት ጠብቆ ለመኖር ከፌዴራላዊ አስተዳደ ሌላ ሥርዓት ሊኖር አይችልም። ሁላችንም እንደምናውቀው አሃዳዊው ስርዓት ከመቶ ዓመታት ተሞክሮ በኋላ የየብሄሮችን ጥያቄ መመለስ ስላልቻለ ዛሬ ላለንበት ብሄራዊ ችግር ዳርጎናል። ለዚህም ነው ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ከፌዴራላዊ አስተዳደር ሌላ የማያዋጣ መሆኑን አምኖበት አገሪቷን በክልል መዋቅር ሥር ያደረገው። በኔ ግምት ዓላማው ትክክል ቢሆንም ኢህአዴግ ፌዴራላዊ አስተዳደርን የመረጠው ለርሱ አገዛዝና ቁጥጥር እንዲያመቸው እንጂ እውነትም ብሄሮች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ተብሎ አለመሆኑን ሁሉም የተገነዘበው ጉዳይ ነው። በርግጥም መሆን እንደነበረበት ብሄሮች (ክልሎች) በሕግ ተከልሎ በሚያስተዳድሩት ግዛት ውስጥ ያለኢህአዴግ ጣልቃ መግባት ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ ኖሮና ኦህዴድም በክልሉ አስተዳደርና ኤኮኖሚያዊ ሕይወት ላይ ሙሉ ባለሥልጣን ቢሆን ኖሮ፤ የፊንፊኔ መስፋት የሕዝቦችን ያላግባብ ከቦታቸው መፈናቀልንም ሆነ ተያይዞ የመጣውን ሕዝባዊ ዓመጽ ባላስከተለ ነበር።
ከዚሁ መልኩን በሳተው የፈዴራላዊ አስተዳደር ጋር የተያያዘ ሁለተኛው ትልቁ ችግር አሁንም በኔ ግምት፤ የፊንፊኔ ከተማ ድንበር በግልጽ አለመታወቅ ነው። እንደተነገረኝ ከሆነ ፊንፊኔ የተወሰነ ድንበር አላት፤ በመሆኑም በአራቱም አቅጣጫ ከፊንፊኔ ወጣ ብሎ ወደ ኦሮሚያ ክልል መዝለቅን የሚያረጋግጥ ኬላ አለ። ይህ እንግዲህ በወረቀት ላይ ብቻ ይመስለኛል። በተግባር የምናየው ግን ከተማዋ ወደ ኦሮሚያ በሰፋች ቁጥር የሚስፋፋው እንዱስትሪም ሆነ የኤኮኖሚ ጥቅሙ ለፌዴራሉ መንግሥት እንጂ ለክልሉ አስተዳደር እንዳልሆነ ነው። የኦሮምያ ክልል አስተዳደርም በክልሉ ላይ ሙሉ ባለሥልጣን ቢሆን ኖሮ ፊንፊኔ ከድንበሯ ውጪ ስትሰፋ ሌላው እንኳ ቢቀር ያካባቢውን ኗሪዎች ከቄዬአቸው ከመፈናቀል ያድን ነበር።
በኔ ግምት የእነዚህ ሁለት የተያያዙ ችግሮች መንሥዔያቸውና መፍትሄያቸው የአንድ እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት አለመኖር ነው። ያማ ቢሆን ኖሮ ኦሮሞዎች ፊንፊኔ የተፈጥሮ ሂደትን ተከትላ ወደ ኦሮሚያ ክልል በሰፋች ቁጥር በሚከተለው የኤኮኖሚ ዕድገት ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ መስፋፋቷን ደግሞ ያካባቢውን ኗሪዎች መብትና ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ዕቅድ ሊያበጁለት ስለሚችሉ ዜጎችንም ከመበደል ብሎም አስከፊ ወደሆነው ዓመጽ ባልተሄደ ነበር። እውነተኛ የፈዴራል ሥርዓት ቢኖር ኖሮ የፊንፊኔም ሆነ የፌዴራል አስተዳደሩ ልክ እንደ ዋሺንግተን ዲሲ ከተከለለው ድንበር ዘልሎ በኦሮምያ ግዛት አያዝም ነበር፤ አስከፊ የሆነውም የህዝቦች ከቄያቸው መፈናቀል አይከሰትም ነበር፤ አልፎም ሕዝባዊ ዓመጽና አለመረጋጋት ብሎም የሰው ነፍስ መጥፋትና የንብረት መውደም አይከሰትም ነበር።
መሆን ያለበት፤
በመጀመሪያ ደረጃ መግባባት ያለብን አንድ መሰረታዊ ሃሳብ አለ። በሱ ላይ ከሞላ ጎደል መግባባት ላይ ካልደረስን ከዚህ በታች መፍትሄ ነው ብዬ የማቀርበው ሃሳብ ብዙም ላያራምደን ይችላል። እኔ ግን በሙሉ ልቤ እንደ ኢትዮጵያ ባለች የብዙ ብሄሮች መኖርያ በሆነች አገር ውስጥ የብሄር ጥያቄን በትክክል ለመፍታት ብሎም በህዝቦች መካከል ሰላም እንዲሰፍንና አገሪቷም እንድታድግ ከተፈለገ መፍትሄው አገሪቱን ፌደራላዊ ማድረግ ብቻ ነው። ፌዴራላዊ አስተዳደር ስል ግን ኢህአዴግ የራሱን ሥልጣን ለማመቻቸትና የወያኔን የበላይነት ለማስረገጥ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ላይ እንዳስቀመጠው ቅርጸ-ቢስ የሆነ መብት ሳይሆን ፌዴራል መንግሥቱን የሚያቋቋሙ ክልላዊ መንግሥታት በየክልላቸው የራሳቸውን አስተዳደርና ኤኮኖሚያዊ ህይወት ያለአንዳች የፌዴራል መንግሥት ተጽዕኖ ወይም ጣልቃ ገብነት የሚመሩበት እውነተኛ የራስን በራስ የማስተዳደር መብት ማለቴ ነው። በትክክል ምን ዓይነት ቅርጽና ይዘት ይኖረዋል ለሚለው ጥያቄ ሰፋ ያለ መልስ ለመስጠት ቦታው ባይሆንም፤ በዓለማችን ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው በጣም ብዙ የፌዴራል ሥርዓት ተጠቃሚ የሆኑ ስላሉ የነሱን ተሞክሮ በጥልቅ ማጥናት አዕምሮአችንን ያሰፋል ባይ ነኝ።
አንዳዶቻችን፤ ኢህአዴግ ያመጣው የፌዴራል ሥርዓት ለብዙ ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ሰፍኖ የነበረውንና ወደ ዓሃዳዊነት እየገሰገሰ የነበረውን ጥሩ ሥርዓት ደምስሶ በቦታው መከፋፈልን ያመጣ ስለሆነ የድህረ ወያኔ ኢትዮጵያ በምንም ተዓምር ፌዴራላዊ አስተዳደርን ማስተናገድ የለባትም ባዮች ነን። ይህ እንግዲህ የአመለካከት ጉዳይ ነው። በኔ ግምት፤ አንዳንድ የታወቁ የዓፄ ኃይለ ሥላሴ ሹማምንትም እንደጻፉት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮና ተከባብሮ ይኖር ነበር ተብሎ እንደተወራለት ሳይሆን እንደሁ ላይ ላዩን በጊዜው ለነበረው አስተዳደር እንዲያመች ተብሎ በሥርዓቱ ተጠቃሚዎች ይለፈፍ ነበር እላለሁ። ከታህሳሱ 1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ “መወሰድ ስላለባቸው የፖሊሲ እርምጃዎች” በሚል ርዕስ ዕውቁ የንጉሡ ባለሟል አቶ ሃዲስ ዓለማየሁ ጥር 23 ቀን 1953 ዓም ለንጉሠ ነገሥቱ ባቀረቡት ሰፋ ያለ ማስታወሻ ላይ እንደጠቀሱት፤
“በፖሊቲካ የኢትዮጵያ ህዝብ የምንለው ከአማራ ከትግሬ ከጋላና ከሌሎችም ልዩ ልዩ ቋንቋ ልማድ ዘር ወይም ሃይማኖት ካላቸው አንድ ላይ ሆኖ  በኢትዮጵያ ዘውድ ሥር የሚተዳደር ነው። ነገር ግን እነዚህ ልዩ ልዩ ቋንቋ ልማድ ዘር ወይም ሃይማኖት ያላቸው ክፍሎች ምንም እንኳ ባንድ ላይ “የኢትዮጵያ ህዝብ” የሚል ስም ቢሰጣቸውና ባንድ ዘውድ ሥር ቢተዳደሩ በደስታም ሆነ በመከራ በመልካም ይሁን በክፉ ጊዜ አንድ ላይ የሚያስተሳስረውና ህዝብን አንድ የሚያሰኘው የህብረት ማሰርያ  ያላቸው ነው ለማለት አያስደፍርም”።
“በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክፍሎች የሚኖሩ ህዝቦች በቋንቋ በልማድ በዘርና በሃይማኖት እንደመለያየታቸው መጠን የህይወት ዓላማቸውም የተለያየ ነው። ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ከሁሉም የበላይነት ስሜት የሚሰማቸውና ይህ የበላይነት እንድሁ እንዳለ እንዲኖር የሚመኙ ናቸው። ሌሎች ደግሞ የበላይ ነን ከሚሉት ባንበልጥም አናንስም የማለት ስሜት የሚሰማቸውና ይህኑ ለማረጋገጥ አጋጣሚ ጊዜ ለማግኘት የሚመኙ ናቸው፤ ሶስተኛ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸውና የበላይ ነን የሚሉትን ክፍሎች ኃይል ሰብሮ ነጻ የሚያወጣቸው ክፉ ቀን እንዲመጣ የሚጠብቁና የሚመኙ ናቸው”።
“በዚህ አኳኋን የህይወት ዓላማቸው የተለያየ ክፍሎች “የኢትዮጵያ ህዝብ” ከሚባለው ስምና ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የጦር ኃይል በቀር ሌላ የሚያስተባብራቸውና አንድ ላይ የሚያስተሳስራቸው የፖሊቲካ  ድርጅቶች ስለሚጎድሏቸው በእውነተኛው የፖሊቲካ ትርጉም “የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ነው” ለማለትና የበሰለ ነው ለማለት ያስቸግራል” (ስርዞቹ የኔ ናቸው)
ተጨማሪ ማብራርያ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። እያንዳንዳችን፤ የማንነት ቀውስ (identity crisis) ውስጥ ካልሆንን  ወይም ቀናነት ካልጎደለን በስተቀር ማንነታችንን በጥልቁ ብንመረምር ከሶስቱ ዓይነት ሕዝቦች ራሳችንን ባንዱ ቅርጫት ውስጥ  እንደምናገኝ እርግጠኛ ነኝ። ለዚህ ነው አፌን ሞልቼ መቶ በመቶ የችግሮቻችን መፍትሄ ነው ብዬ እንኳ ለመናገር ባልችልም እስካሁን ካጤንኳቸው የአስተዳደር ሥርዓቶች ሁሉ የተሻለ መስሎ የታየኝና ለኢትዮጵያ የሚበጃት ፌዴራላዊ አስተዳደር ብቻ ነው ብዬ የምለው።
እውነተኛው ፌዴራላዊ ሥርዓት በተግባር ሲተረጎም፤
የድህረ-ወያኔ ኢትዮጵያ አስተዳደር ምን መምሰል እንዳለበት ወሳኙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢሆንም ከወዲሁ ግን እስካሁን ካየሁትና ከተገነዘብኩት ተነስቼ፤ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ፤ የሰማንያ ስምንት ብሄሮችዋን መብትና ጥቅም ጠብቆ ህዝቦችን በሰላምና በፍቅር አስተሳስሮ ለማኖር የሚችል ከፌዴራላዊ አስተዳደር ሥርዓት ሌላ የለም ባይ ነኝ። ክልሎች የየራሳቸውን ፖሊቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ሕይወት ለክልላቸው ህዝቦች (ሌሎች የክልሉን ኗሪዎችንም ጨምሮ) እንደሚመችና የሌሎች ክልሎችን መብት እስከማይነካ ድረስ ያለምንም ፌደራላዊ መንግሥት ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖ መምራት እስከቻሉ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝቦች በሰላምና በመፈቃቀርና በእኩልነት ባንድ ፈዴራላዊ ማዕከል ሊተዳደሩ ይችላሉ። የፖሊቲካ ሳይንሱም እንደሚለው አገሪቱ በኤኮኖሚ እያደገች በሄደች ቁጥር የዜጎች የተሻለ ህይወት ፍለጋ ከቦታ ቦታ መዘዋወርን ስለሚያስከትል ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ክልላዊ መዋቅሩ እየተዳከመ ፌዴራላዊው መዋቅር ራሱ እየተጠናከረ ይመጣል።
የኦሮሚያን ክልልና በፊንፊኔ ያለውን “ልዩ ጥቅም” አስመልክቶ አሁን በመካሄድ ላይ ያለው አወዛጋቢ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ የድህረ-ወያኔው እውነተኛው ፌዴራላዊ አስተዳደር በኔ ግምት ችግሮቹን እንደሚከተለው ይፈታል ባይ ነኝ። ዋናው ነገር ውሳኔው ላይ ለመድረስ የሚመለከታቸው አካላት መከባበርና ቅንነትን መሰረት ባደረገ የእኩዮች ውይይት አማካይነት መሆኑን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል። በዚህ በእኩዮች መካከል በሚደረገው ውይይት ላይ የኦሮምያን ክልልንና ፊንፊኔን በተመለከተ የሚከተሉት ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹ ይሆናሉ ብዬ እገምታለሁ።
አንደኛ፤  ያገሪቷ ሕገ-መንግሥት ለሁሉም ብሄሮች አመቺ በሆነ መንገድና የየብሄሮቹ ሕጋዊ ተወካዮች በእኩልነት ተሳትፈው የሚያጸድቁት በብሄሮች መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ይሆናል። በስምምነት በፀደቀው ሕገ-መንግሥት መሰረት የኦሮምያ  ክልል እንደማንኛውም ያገሪቱ  ክልሎች ራሱን በራሱ ያስተዳድራል፤ ይህም ማለት ከማንም ተጽዕኖ ነጻ የሆነ የራሱ የክልል ፓርላማና መንግሥት ይኖረዋል ማለት ነው። ያለምንም የፈዴራል መንግሥት ጣልቃ-ገብነትና ተፅዕኖ ፖሊቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ሕይወቱን ለክልሉ ሕዝቦች ጥቅም እንዲውል የሚያደርግ ሲሆን ለፈዴራል መንግሥትም በሕጉ መሰረት ማካፈል ያለበትን ገቢ ያስገባል ማለት ነው። ክልሉ ለማንኛውም በክልሉ ሰርቶ ለመኖር ለፈለገ ማንኛውም ብሄር ዜጋ ክፍት ይሆናል።
ሁለተኛ፤ እንደ ቪርጂንያና ሜሪላንድ ሕዝቦች ኦሮሞዎች በፈቃደኝነት ከግዛታቸው ቆርጠው የሰጡት ባይሆንም ካንድ መቶ ዓመት በኋላ ወደ ኋላ ተመልሶ ታሪክን እንደገና መጻፍ ስለማይቻልና አስፈላጊም ስላልሆነ፤ ፊንፊኔ፤ ያገሪቷ ሕዝቦች ተስማምተው ወደ ሌላ ቦታ እንድትዛወር ካልወሰኑ በስተቀር፤ በታሪክ አጋጣሚ ምክንያት አሁን ያለችበትን የፈደራሉ መንግሥት መቀመጫ ዕጣ እንደ ያዘች ትቀራለች።  የኦሮምያ ክልል ሕዝብም በራሱ ፈቃድ የክልሉን ዋና ከተማ ወደ ሌላ ቦታ ለማዘዋወር ካልፈለገ በስተቀር ፊንፊኔ የኦሮምያ ክልል ዋና ከተማ እንደሆነች ትቀራለች። ይህ የፊንፊኔ የሁለት የተለያዩ አስተዳደሮች ዋና ከተማ መሆን በፌደራሉ መንግሥትና በክልሉ መንግሥት መካከል አወዛጋቢ የሆነ ጭቅጭቅ ሊያመጣ ስለሚችል ካሁኑ ቢታሰብበት ይሻላል ባይ ነኝ። የአለመግባባቶቹን ዝርዝር በሙሉ ማቅረብ ባይቻልም አስማሚ ናቸው ብዬ የማስባቸውን ጉዳዮች ግን ለመገመት የሚቻል ይመስለኛል። እነሆ፤
ከላይ እንደገለጽኩት ፊንፊኔ የተቆረቆረችው ከኦሮሞዎች በጉልበት በተወሰደው መሬት ላይ ነው። የሕጋዊ ባለመሬቶቹ ልጅ ልጆች ዛሬም በፊንፊኔ ዙሪያ ባሉት አነስተኛ ከተሞች የሚኖሩ ሲሆን የግፉ ግፍ ደግሞ በኢንቬስትሜንት ሰበብ ለሁለተኛ ጊዜ እየተፈናቀሉ ነው። ይህ ከግፍም በላይ ግፍ ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም። ይህንን ታሪካዊ ግፍ (historical injustice) ሳናርምና በደል የደረሰባቸውን ይቅርታ ሳንጠይቅ ደግሞ ወደፊት መራመድ አይቻልም። ይህ በሌላ አገርም ለምሳሌ በአሜሪካ በካናዳና በአውስትራሊያ መጤ ብሄሮች በነባሩ ህዝብ ላይ የፈጸሙትን ግፍ ከብዙ ምዕተ ዓመታት በኋላ ወደ ኋላ ተመልሰው በማስታወስ የተበዳዮችን ሕዝብ ተተኪ ትውልዶች ይቅርታ ጠይቀዋል። ይህ ቅንነትን እንጂ ሌላ ምንም ከባድ የሆነ ሃላፊነት ስለማያስከትል የፌዴራሉ መንግሥት በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስም የኦሮሞን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ለተበዳይ ህዝብ ደግሞ ለዓመታት ብሶታቸውን በተለያየ መልክ ሲያሰሙና በሂደቱም በርካታ ልጆቻቸውን ስላጡበት መበደላቸውን መንግሥት ካወቀላቸው በላይ ሌላ ምንም ካሳ አይጠብቁም። የበደሉ ብዛትም ከግምት በላይ ስለሆነ እንክፈል ቢባል እንኳ ዕዳውን በአሃዝ ማስቀመጥ ስለማይቻል ይቅርታን ከመጠየቅ የበለጠ ውድ ካሳ የለምና እዳው በዚያ ይጣፋል ባይ ነኝ።
የካሳውን ይዘት በተግባር እንተርጉም ከተባለ ደግሞ የሚከተሉት መንግሥታዊ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ባይ ነኝ። በአንደኛ ደረጃ የፊንፊኔ ከተማ ባለቤት የኦሮምያ ክልል መሆኑ በማያወላዳ መልኩ በሕገ-መንግሥቱ መቀመጥ አለበት። ይህም ማለት ኢህአዴግ ለማወናበጃ የሚጠቀምበትን “ልዩ ጥቅም” ለማግኘት ሳይሆን ታሪካዊ ስህተትን ለማስተካከል ብቻ ነው። በፊንፊኔ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ከሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች የተለየ ልዩ ጥቅም አያስፈልጋቸውም። የኦሮምያ ክልል አስተዳደርም በገዛ ራሱ ዋና ከተማ “ልዩ ጥቅም” የሚጠይቅበት ምክንያት የለም።
መደምደሚያ፤
ከላይ እንዳልኩት ታሪክ የራሱን ቦይ ተከትሎ እንጂ ሰዎች ባዘጋጁለት ስለማይሄድ ለወደፊት በትክክል የኢትዮጵያ አስተዳደራዊ መዋቅር ይህንን ይመስላል ብሎ መተንበይ የሚቻል አይመስለኝም። በዚያው ልክ ደግሞ ያለፈውን ታሪካዊ ስህተትና ግፍ ወደ ኋላ ተመልሶ ማስተካከል ስለማይቻል በሂደት ውስጥ በተወሰኑ ብሄር አባላት ላይ በደል መፈጸሙን ብቻ ህዝባዊው መንግሥት አምኖ ይቅርታ በመጠየቅና ካለፈው ስህተት በመማር ተመሳሳይ በደል ለወደፊት እንዳይፈፀም የበደሎችን መንስዔ ከስሩ ቆርጦ መጣል ነው። ከዚህ አኳያ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር፤ ያኔ ምኒልክ በፊንፊኔ ኗሪዎች ላይ ለፈፀመው በደል የዛሬው ትውልድ ተጠያቂ የሚሆንበት ምክንያት የለም። ለዚህም ነው ደሞከራሲያዊው የህዝብ መንግሥት በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስም ተበዳዩን ይቅርታ መጠየቅ ይጠበቅበታል የምለው። የፖለቲካ በደል ካሳው በቅንነት የተሞላ ይቅርታ ጥየቃ ብቻ ነው።
በተረፈ ግን የድህረ-ወያኔዋ ኢትዮጵያ ሁሌም የምንመኛት ዲሞክራሲያዊት ሆና ህዝቦቿ በእኩልነት የሚኖሩባት በዳይና ተበዳይ የማይገኝባት የእኩዮች አገር እንድትሆን ካሁኑ መሰረቱን መጣል አለብን እላለሁ። ያ በጉጉት የምንጠብቀው ቀን ደግሞ መቼ እንደሚመጣ ስለማይታወቅና ድንገት መጥቶ ግራ እንዳያጋባን የመሰረቱን ሲሚንቶ ማቡካት ሥራ ካሁኑ መጀመር አለብን እላለሁ። ፈጣሪይችን ይርዳን።
*******
ባይሳ ዋቅ ወያ                                                                                                                                             
ጄኔቫ፣ ሃምሌ 5 ቀን 2017 ዓም

* ፀሃፊው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባልሥልጣን የነበሩ የዓለም-አቀፍ ሕግ ባለሙያ ናቸው።

No comments:

Post a Comment