የኦሮሞ የነፃነት ትግል (ኦነት) ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው? ሁለተኛ ዙር፥ ክፍል ስድስት

ሰኔ 15, 2019 | በብርሃኑ ሁንዴ

በሁለተኛ ዙር ክፍል አምስት ፅሁፍ ውስጥ የኦነግ አመራር ከቴክኒክ ኮሚቴ ጋር የሰጠውን መግለጫ በሚመለከትና ሌሎች የተለያዩ አንዳንድ ጉዳዮችን አንስቼ ነበር። ከነዚህ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ እየተቃረበ ያለው የአገሪቷ ብሔራዊ ምርጫ ሲሆን፣ ባሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ውስጥ እየታየ ባለው ሁኔታ ውስጥ ኦነግ ይህንን ምርጫ አሸንፎ የተነሳለትን ዓላማ ከግብ ማድረስ ይችል ይሆን? የሚል ጥያቄ አንስቼ አንዳንድ ነገሮችን ለማብራራት ሞክሬ ነበር። በዚህኛው ክፍል ስደስት ፅሁፍ ውስጥ ባሁኑ ወቅት በአገሪቷ እየተደረገ ያለውን በሚመለከት እያስተዋልኩ ያለሁትን አቀርባለሁ።

የኦሮሞ ሕዝብ ትዕግስት እንደ ሞኝነት መታየት የለበትም
የኦሮሞ የዋሕነትና ትዕግስት አንዳንድ ጊዜ እንደ አለማወቅ ወይም ሞኝነት የሚወሰድ ይመስላል። ይህ ደግሞ የሚታየው ከባዕድ በኩል ብቻ ሳይሆን ኦሮሞም ሆነው እንደዚህ የሚያስቡ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም። የኦሮሞ ሕዝብ ስያነሳቸው ለነበሩት ጥያቄዎች መልስ እየጠበቀ እንደሆነ የሚታወስና የማይካድ ነው። ይሁን እንጂ እስቲ ይህ ለውጥ ወደ ዲሞክራሲ ይሻገር ብሎ በትዕግስት ስጠብቅ፣ ባንድ በኩል ይህ ሕዝብ ጥያቄዎቹን እነደዘነጋ ወይም እንደተወ ተደርጎ ይታያል። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሕዝብ ለጊዜው ዝምተኝነትን ስመርጥ የተታለለ መስሎአቸው በጥያቄዎቹ ላይ በመዝለል የባዕድን ፍላጎት ለመጠበቅና ለማሟለት ይጥራሉ።
እንደዚህ የሚያስቡት ግን ደግመውና ደጋግመው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። ትዕግስት ከወሰን ካለፈ ወደ ሌላ ነገር ሊወስድ እንደሚችል መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህንን ጉዳይ ያነሳሁበት ምክንያት በኦሮሞ ሕዝብ ትግል ከመጣው ለውጥ ጋር ስለሚያያዝ ነው። እውነት እንናገር ከተባለ ይህ ለውጥ በኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ተገኘ እንጂ ለዚህ ሕዝብ የተቀየረ ነገር የለም ቢባል ሀሰት አይሆንም። ይህ ራሱን አድሷል የሚባልለት የኢሕአዴግ መንግስት ኦሕዴድ (OPDO) በመንግስት ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን አግኝቶ አገሪቷን እያስተዳደረ ስለሆነ የኦሮሞ መንግስት ነው ይባላል እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ከዚህ ያገኘው ጥቅም አለ ብዬ ለማስብ ይቸግረኛል።
የኦሮሞ ሕዝብ ከዚህ ለውጥ ያገኘው ጥቅም ምንድነው?
በወያኔዎች የበላይነት አገዛዝ ስር ኦሮሞ ሲታሰር፣ ሲሰቃይ፣ ሲገደል፣ ሲደፈር፣ ከአገሩ ሲስደድ፣ ንብረቱና መሬቱ ሲቃማ ወዘተ ነበር። የኦሮሞ ሕዝብ ከባድ መስዋዕትነትን ከፍሎበት ካስገኘው ለውጥ በኋላ ያለውንም ሁኔታ ካየን፣ ይነስ ይብዛ እንጂ እነዚህ የተዘረዘሩት እየታዩ ናቸው። ምናልባት ከአገር መሰደድ ቀንሶ ሊሆን ይችላል። በዚያ በሕዝባዊ አመፅና እንቅስቃሴ ወቅት የኦሮሞ ሕዝብ ስያነሳቸው ከነበሩት ጥያቄዎች ውስጥ አንድም አልተመለሰም። እነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘታቸው ቀርተው ይህ ሕዝብ ዛሬ በሰላም ወጥቶ መግባትም አልቻለም። ሰላሙና ደህንነቱ አልተጠበቁም። ይህ ለምን ሆነ? ብለን ጥያቄ ካነሳን፣ መልሱ ባጭሩ ይህ አሁን ያለውም መንግስት ያው ድሮ የለመደውን አሰራርና አካሄድ እየተጠቀመበት ነው ያለው እንጂ ለሕዝብ ጥያቄ ጆሮውን ሰጥቶ በጥሞና አዳምጦ ለችግሮች መፍትሄ ለማግኘት ፍላጎት ስለሌለው ነው።
ሀበሾች በኦሮሞ ላይ ለምያደርጉት የስም ማጥፋት ፕሮፖጋንዳና እየገለፁ ላሉት ፍላጎታቸው ግን ይህ መንግስት ተኝቶ የሚያደርም አይመስልም። ከኦሮሞ ሕዝብ የወጡት የኦሕዴድ ከፍተኛ የአመራር አባላት መጀመሪያ አካባቢ ወደ ስልጣን ሊመጡ ስሉ በነበረበት ወቅት የኦሮሞን ሕዝብ ስያሞግሱ፣ የኦሮሞን ብሔርተኝነት የሚያንፀባርቁትን ንግግሮች ስያሰሙ፣ ጌታችን ይህ ሕዝብ ነው እያሉ ይህንን ሕዝብ ስያባብሉና ስያታልሉ ነበር። ዛሬ ግን ሁኔታዎችን ካመቻቹ በኋላ ይህንን ሕዝብ ረስተው፤ ለባዕድ ግን በተቻላቸው መንገድ ሁሉ እየሰሩላቸው ይገኛሉ። ኦሮሞ ስያነሳቸው የቆየውን ጥያቄዎች ትተው የባዕድን ፍላጎት ግን ለማሟላት ሌት ተቀን ይሰራሉ። ይህ ጉዳይ በደንብ ሲታይ እነዚህ ሰዎች ኦሮሞ መሆናቸው ራሱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። በስጋና ደም ኦሮሞ መሆናቸውን ጥያቄ ውስጥ ማስገባቴ አይደለም። ነገር ግን ትኩረታቸውና ፍላጎታቸው የት እንደሆኑ ለመገመት አያስቸግርም ማለት ፈልጌ ነው።
ሀበሾች በተለይም ደግሞ የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች፤ የአንድን ብሔር የበላይነት በሕዝቦች ላይ ለመጫን የሚፈልጉት ኃይሎች የኦሮሞን አንድነት የምጠሉበትና የኦሮሞ ነፃነት ትግልን የሚቃወሙት ኦሮሞ ይህችን ኢትዮጵያ የሚትባለዋን አገር ያፈርሳል ብለው ስለምያስቡና ስለምያምኑም ነው። የሚደንቅና አልፎም የሚያሳዝን ግን በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተቋቋመው ድርጅትና መሪዎቹ ሀበሾች እያደርጉ ያሉትን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እውነት አድርገው ወስደው፣ ለነሱ ተባባሪ መሆናቸው ነው። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንይ። በአማራ ክልልና ሌሎች ቦታዎች ሰዎች ተደራጅተው፣ ታጥቀውና ተሰማርተው ኦሮሞን ጨምሮ በሌሎች ሕዝቦች ላይ ጉዳት እያደርሱ ይገኛሉ። መንግስት ግን ይህንን በዝምታ አንዳለፈ በመሬት ላይ የታየ ሀቅ ነው። የኦሮሞ ግን እንደ ልዩ ጉዳይ ታይቶ ለኦሮሞ ነፃነት ትግል ብለው ኑሮአቸውን ጫካ ያደርጉትን ሽፍቶች በማለት ይዘመትባቸዋል። ጦርነት ይከፈትባቸዋል። እነዚህ ባጫካ ያሉት ልጆች የሚያነሱት አግባብ ያለው ጥያቄ እንኳን ታይቶ፣  በሰላማዊ መንገድ ለችግሮች የጋራ መፍትሄ ለማግኘት ይህ መንግስት ሙከራም አላደረገም። በኃይል ተጠቅሞ እነዚህን ልጆች ለማጥፋት የወሰን ይመስላል።
እነዚህን ልጆች ለማጥፋት ሲባል በሚደረገው ጦርነት ውስጥ የሚጎዳው ሰላማዊ ሕዝብ ነው። እዚህ ላይ አንባቢዎች እንድገነዘቡ የምፈልገው እኔ ለነዚህ ልጆች መናገሬ አይደለም። እነዚህ ልጆችም ከጥፋት ነፃ ይሆናሉ ብዬም አላስብም። ይሁን እንጂ እነዚህ ልጆች ለሽፍታነት ብለው ከቤታቸው እንዳልወጡ አምናለሁ። ይህ መንግስት ለምን በነዚህ ልጆች ላይ ጦርነት እንደከፈተ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ እኔ ግን እንደ ራሴ አመለካከት ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶችን እገምታለሁ።
  • አንደኛ፣ ከዚህ በላይ እንደተገለፀው፣ ለሀበሾች ፕሮፖጋንዳ ትኩረት በመስጠት፤ የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ በሚል ስም እነዚህን ልጆች ለማጥፋት፤ የኦሮሞ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ እንዳይነሳ ለማድረግ፣ ይህ የኦሮሞ ሕዝብ የመወስን መብቱ እንዳይረጋገጥ ለማድረግ ተብሎ ይህ ጦርነት የተመረጠ ይመስላኛል።
  • ሁለተኛ፣ በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን የሚሉትን የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በጉያው ስር አስገብቶ በመቆጣጠር፣ በትጥቅ በኩል የምንቀሳቀሱትን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት፣ የኦሮሞ የአገር ባለቤትነት ጥያቄ እንዳይነሳና መልስ እንዳያገኝ ለማድረግ ዓላማ አድርጎ የምንቀሳቀስ ይመስላል።
  • ሶስተኛ፣ የሕግን የበላይነት ማስጠበቅ በሚል ሽፋን ይህንን መንግስት የሚቃወሙትን ኃይሎች ከተቻለ መሉ በሙል ለማስወገድ፣ ካልተቻለ ግን ለማዳከም፤ ለራሱ ግን የበላይነቱን አረጋግጦ እንደ ፈለገ ለመሆን የወሰነ ይመስላል።
“የምትችለውን ደብድብ ሲባል ሞኝ ባል ገብቶ ሚስቱን ደበደባት” እንደሚባለው ተረት፣ ይህ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተቋቋመው ድርጅትና ይህ ድርጅት እያመራ ያለው መንግስት ለኦሮሞ ሕዝብ የሚቆረቆር ቢሆን፤ እውነትም እንደሚባለ የኦሮሞ መንግስት ቢሆን ኖር፤ እውነተኛ የኦሮሞ ብሔርተኝነት በወኔአቸውና ልባቸው ቢኖር ኖሮ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ችግርና ስቃይ ቢታያቸው ኖሮ፤ የኦሮሞ ቁስል ብያማቸው ኖሮ፣ ዛሬ የታጠቁ የባዕድ ኃይሎች ኦሮሞን በምጎዱበት ጊዜ ለዚህ ሕዝብ ከመድረስ ይልቅ በተቃራኒው ግን የኦሮሞን ልጆች ሽፍታዎች ናቸው ብለው፣ እነዚህን ልጆች ለማጥፋት ያለውን ጉልበት ሁሉ በመጠቀም ጦርነት አይከፍትባቸውም ነበር። እንግዲህ ይህ ሁል ድርጊት ነው ይህንን በኦሮሞ ስም የተቋቋመውን ድርጅትና በዚህ ድርጅት የሚመራውን መንግስት ማንነታቸውን በግልፅ የሚያሳየው። ይሁን እንጂ ለፍትህና ነፃነት የሚደረገውን ትግል ለጊዜው ማዳከም ይቻል ይሆናል እንጂ ማጥፋትና ማቆም አይቻልም።
ተመልሰን እስከምንገናኝ በደህና ቆዩ

No comments:

Post a Comment